Monday, July 22, 2024

መንግሥት ቃሉና ተግባሩ ይመጣጠን!

‹‹ሁሉንም ሰው በአንዴ ለማስደሰት ከፈለግህ አይስክሬም ነጋዴ ሁን›› የሚል የተለምዶ አባባል ይታወቃል፡፡ በፖለቲካው መስክ በተለይ ሥልጣነ መንበሩን የጨበጠ ኃይል ለሚያስተዳድረው ሕዝብ ባለበት ኃላፊነት፣ በተቻለ መጠን ሁሉንም ማስደሰት ባይችልም ሁሉንም ማስከፋት ግን አይኖርበትም፡፡ በመንግሥት ውሳኔና ዕርምጃ የሚደሰቱ ያሉትን ያህል የሚከፉ መኖራቸው የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ሁሉንም ወገኖች ያማከለ አስተዳደር እንዲኖር ግን የገባውን ቃል ጠብቆ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታም መንግሥት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ ጉዳዮችና በዲፕሎማሲው ጭምር በሚያከናውናቸው ተግባራት መንግሥት የሚወደስባቸውም ሆነ የሚነቀፍባቸው ምክንያቶች መኖራቸው ተጠባቂ ነው፡፡ የተለያዩ ፍላጎቶች፣ ዓላማዎችና ስሜቶች ከግራ ወደ ቀኝ በሚያላጓት የአሁኗ ኢትዮጵያ ደስታና መከፋት የሚፈጥሩ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህን ሁለት ጉዳዮች ከአገርና ከሕዝብ ዘለቄታዊ ሰላምና ደኅንነት አኳያ በቅን መንፈስ የሚያስተናግድ ዓውድ መፍጠር አስፈላጊ ነው፡፡

አዲስ አበባ ከተማን በኮሪደር ልማቱ አማካይነት ወደ ‹‹ስማርት ሲቲ›› ለመለወጥ በሚደረገው ጥረት፣ የልማቱ መነሻና መድረሻ ሰው መሆን አለበት፡፡ ልማቱ በደፈናው ‹‹ሰው ተኮር ነው›› ከመባል አልፎ ለበርካታ ዓመታት ከኖሩበት ቀዬ የሚነሱ ነዋሪዎችን መብት፣ ጥቅምና ክብር በተግባር ማሳየት ይኖርበታል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ የተባበሩት መንግሥታት ደርጅት ሃቢታት (UN-Habitat) ዓላማ፣ ማኅበራዊና አካባቢያዊ ጥበቃን መሠረት ያደረጉ ሥራዎች በማከናወን ዜጎች በቂ መጠለያና የሥራ ዋስትና ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ በኮሪደር ልማቱ አማካይነት ለኑሮ ከማይመቹ ያረጁና የተፋፈጉ መንደሮች  ወደ ተሻሉ መኖሪያ ሥፍራዎች እንደተዘዋወሩ ወገኖች ሁሉ፣ ቅሬታና ስሞታ እያቀረቡ ያሉ የልማት ተነሺዎችም ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው መንግሥት ቃሉን ጠብቆ ማስተናገድ ይኖርበታል፡፡ የተለያዩ ሰበቦች እየተደረደሩ ጎዳና ላይ እስኪወድቁ መጠበቅ ተገቢ ባለመሆኑ ቅሬታቸው በሰብዓዊነት ይደመጥ፡፡

ከግብይት ሥርዓቱ ጋር ያለው አሳሳቢ ሁኔታም ልዩ ትኩረት ይፈልጋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የእርሻና የኢንዱስትሪ ውጤቶች የሆኑ የተለያዩ ምርቶች የዋጋ ንረት የተቆጣጣሪ ያለህ እያሰኘ ነው፡፡ በአገር ውስጥ በፀጥታ ችግር ባለመመረታቸው ወይም ተመርተው ገበያ መድረስ ባለመቻላቸው ምክንያት እንደ ጤፍ፣ ምስር፣ አተር፣ ሽንኩርትና መሰል ምርቶች ዋጋቸው ከአቅም በላይ ነው፡፡ በአገር ውስጥ በበቂ መጠን የማይመረቱና ከውጭ ደግሞ በውጭ ምንዛሪ ምክንያት ባለመግባታቸው ዋጋቸው እያደር የሚጨምረው የኢንዱስትሪ ምርቶች ሁኔታም ሌላው ችግር ነው፡፡ ገበያ የደረሱ ምርቶችም በተበላሸው የግብይት ሥርዓት ምክንያት አቅርቦታቸው በሕገወጦች በመታነቁ፣ ዋጋቸው በየሰዓቱ እየጨመረ ሸማቾች ኑሮ ከመጠን በላይ እየከበዳቸው ነው፡፡ የግብይት ሥርዓቱን ፈር ማስያዝ የሚቻለው መንግሥት ለሕዝብ የገባውን ቃል አክብሮ ሲሠራ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የብልሹ አሠራር ተሳታፊዎችን ከውስጡ መንጥሮ ማውጣት አለበት፡፡

ዜጎች በተፈጥሮና በሕግ የተጎናፀፏቸው መብቶች ጉዳይ መንግሥትን ከምንም ነገር በላይ ሊያሳስበው ይገባል፡፡ በሰብዓዊና በዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በዓለም አቀፍ መድረኮች ስሟ ጎድፏል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ የዜጎቿ እስር ቤት›› እስከትመስል ድረስ በርካቶች ሐሳቦቻቸው ታፍነው፣ እነሱም ተሳደው፣ ታስረው፣ ተሰቃይተውና ተገድለው ያለፉባቸው የታሪክ ሰበዞች ብዙ ይናገራሉ፡፡ እነዚያን የመከራና የፅልመት ዓመታት በጋራ ተሻግሮ ብሩህ ተስፋ መፈንጠቅ ሲገባ፣ አሁንም በየቦታው በሚጫሩ ግጭቶችና ጦርነቶች ምክንያት ከዕልቂቱና ከውድመቱ በተጨማሪ ከፆታዊ ጥቃት ጀምሮ ለመስማት የሚዘገንኑ የመብት ጥሰቶች ሪፖርቶች ይወጣሉ፡፡ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች የሚወጡ ሰቅጣጭ ሪፖርቶች ልዩ ትኩረት ባለማግኘታቸው፣ ሕግ ማስከበር የሚገባቸው ሳይቀሩ በመብት ጥሰት ሲከሰሱ መስማት እየተለመደ መሆኑ ከማስደንገጥ አልፎ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ መንግሥት ችግሩን ማመን ብቻ ሳይሆን ለተግባራዊነቱ ቁርጠኛ ይሁን፡፡

ለአንድ አገር ልማትም ሆነ ዕድገት ሰብዓዊ ሀብት ከምንም ነገር በላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በበርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች የታደለች አገር ብትሆንም፣ የሰው ኃይሏን በአግባቡ ካልተጠቀመችበት ፋይዳ የላቸውም፡፡ በተለይ ከ120 ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን ከሚገመተው ሕዝቧ 70 በመቶ ያህሉ ወጣት መሆኑ ትልቅ ፀጋ ነው፡፡ ወጣቱን ኃይል ጥራት ባለው ትምህርት ከማነፅ በተጨማሪ፣ በተለያዩ የሙያና የቴክኒክ ዕውቀቶች ብቁ ማድረግ የግድ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው ሕይወታቸውን እንዲለውጡ የተጀመረው ጥረት በማጠናከር በርካታ ሚሊዮኖችን ማንቀሳቀስ፣ በአዲሱ የስታርትአፕ መርሐ ግብር መሠረት ደግሞ ልዩ ክህሎት ያላቸውን በስፋት ማሳተፍና ሁለቱንም በፍትሐዊ መንገድ ማስተናገድ ይገባል፡፡ ጥቂቶችን ለማበልፀግ ብቻ ትኩረት የሰጡ ባንኮችም ከወጣቶች አዋጭ የሥራ ፈጠራ ጋር ተባባሪ በመሆን፣ ለነገዎቹ አገር ተረካቢዎች ተደራሽ እንዲሆኑ አዋጭ ፖሊሲ መቅረፅ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡

በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት ከግራና ከቀኝ የሚጠመዝዙ ፍላጎቶች ሊያስገድዱት አይገባም፡፡ መንግሥትን የመምራት ኃላፊነት የወሰደው ብልፅግና ፓርቲ የመጀመሪያ ተግባሩ፣ የመንግሥትና የፓርቲ ሥራን መለያየት ነው፡፡ በመቀጠል ደግሞ በብሔር፣ በእምነትና በሌሎች ትስስሮች ሊመጡ የሚችሉ ተፅዕኖዎችን መመከት ነው፡፡ ይህንን ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ ከምንም ነገር በላይ ለተቋማት ግንባታ የተለየ ትኩረት መስጠት ይገባል፡፡ ተቋማቱ ያልተጠናከሩና ብቁ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ሠራተኞች ያላፈራ መንግሥት የጉቦኞችና የዘራፊዎች ዋሻ ይሆናል፡፡ የተቋማት ግንባታ ጉዳይ ሲነሳ እንደ ዋዛ መታለፉ ለበርካታ ችግሮች ማጋለጡ አይዘነጋም፡፡ ለተቋማት ልዩ ትኩረት መስጠት ግዴታ መሆን አለበት፡፡ ለዚህም መንግሥት አገር የመምራት ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት የሚችለው፣ ለሕዝብ የገባው ቃል በተግባር ሲተረጎም ብቻ ነው!   

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ትርፍ ቢያገኝም የውጭ ምንዛሪ ገቢው ቅናሽ ማሳየቱ ተጠቆመ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የውጭ ምንዛሪ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...