Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በመስኖ ይለማል ከተባለው አሥር ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ እየለማ ያለው 13 በመቶው ብቻ መሆኑ ተነገረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሦስት ሚሊዮን ሔክታር የሚጠጋ መሬት መልማቱን ተናግረዋል

በኢትዮጵያ በመስኖ የሚለማ አሥር ሚሊዮን ሔክታር መሬት ቢኖርም፣ እየለማ ያለው 13 በመቶ ወይም 1.2 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ብቻ መሆኑን፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ 

ሚኒስትሩ ይህንን የገለጸው ሐሙስ ሰኔ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት ባለሙያዎች ማኅበር ጋር በመተባበር፣ በመስኖ ልማት ያጋጠሙ ችግሮችና የቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በተመለከተ ባደረገው ውይይት ነው፡፡

የሚኒስቴሩ የመስኖ ምርምር ዴስክ ኃላፊ አቶ ያሬድ ሙላቱ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያን የመስኖ ልማት ካለበት ደረጃ ከፍ ለማድረግ የ30 ዓመታት ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ሒደት ላይ ነው፡፡  

የግል ባለሀብቶች ተሳትፎና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ውስንነት፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚታየው የግንዛቤ እጥረት፣ እንዲሁም የመንግሥት ተቋማትን ጨምሮ ይህንን ዘርፍ ከሚመሩ ባለድርሻ አካላት ጋር ያለው የአሠራር ክፍተት የመስኖ ልማትን እንዳያድግ አድርጎታል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች ለመስኖ ልማት እንዲውሉ የተዘረጉ ፕሮጀክቶች ከታሰበው በታች አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ፣ እስካሁን በአጠቃላይ በመስኖ እየለማ ያለው 1.2 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ብቻ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር የ30 ዓመታት ፍኖተ ካርታ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ የግል ባለሀብቶች፣ እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የራሳቸውን አስተያየትና ሐሳብ ከሰጡ በኋላ እንደሚዘጋጅ አስረድተዋል፡፡

በኢትየጵያ አንድ ትሪሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ዝናብ እንደሚኖር፣ ከዚህ ውስጥ ደግሞ 124 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ያህል ወደ ወንዞች እንደሚፈስ ገልጸዋል፡፡

በወንዞች ከፈሰሰው 124 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውስጥ ለመስኖ ልማት ጥቅም ላይ የዋለው አሥር ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ወይም ከአንድ በመቶ በታች መሆኑን አቶ ያሬድ ለሪፖርተር አስረድዋል፡፡

በተለይ 80 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ውኃ ወደ ተለያዩ አገሮች የሚፈስ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ ‹‹የሚፈሰውንም ውኃ በአግባቡ መጠቀም ቢቻል ኖሮ የመስኖ ልማታችንን በተሻለ ሁኔታ ማሳደግ ይቻል ነበር፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የመስኖ ልማት ተጠቅማ ራሷን በምግብ ምርቶች እንድትችል፣ የማኅበረሰቡን ገቢ ለመጨመር፣ እንዲሁም የተመረቱ ምርቶችንም ከራሷ አልፋ ለሌሎች አገሮች በመላክ የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ ለማድረግ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት አስፈላጊ እንደሆነ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር አማካሪ ውብሸት ዠቅአለ (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡

የመስኖ ልማትን ከመሠረቱ ለማሳደግ ምን ዓይነት ነገሮች ያስፈልጋሉ የሚለውን ለማጥናት፣ የ30 ዓመታት ፍኖተ ካርታውን ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖ ወደ ሥራ መገባቱን ጠቁመዋል፡፡

የመስኖ ልማትን ወደ ተሻለ ደረጀ ለማሳደግ በሦስት ምዕራፎች በየአሥር ዓመቱ የሚከናወኑ ሥራዎችን መለየት፣ ምርትና ምርታማነትን እንዴት መጨመር ይቻላል የሚለውን በማየት ሰፊ እንቅስቃሴ የሚካሄድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በምዕራብ በኩል ለመስኖ ልማት የሚሆን ከፍተኛ ውኃ ሲኖር፣ በምሥራቅ በኩል ደግሞ ጥቂት የሚባል ውኃ እንዳለ ተናግረዋል፡፡

በዚህ መሠረት ያለውን የውኃ መጠን በመጠቀም ብዙና ጥቂት ውኃ የሚፈልጉ አዝዕርቶችን በመለየት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ 930 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የውኃ ሀብት እንዳለ፣ ከዚህ ውስጥ ለመጠቀም የሚቻለው 223.4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር እንደሆነና እስካሁን ግን በጣም በአነስተኛ መጠን ጥቅም ላይ መዋሉን ገልጸዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ተሞክሮን በመጠቀም እንዴት ነው የመስኖ ልማትን ማሳደግ የሚቻለው የሚለውን በማወቅ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን፣ ለአብነትም ባንግላዴሽ 82 በመቶ የሚሆን የውኃ ሽፋኗን ለመስኖ ልማት መጠቀም መቻሏን ማየት ተችሏል ብለዋል፡፡

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ይህንን ቢልም፣ ሐሙስ ሰኔ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ሲካሄድ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ዶ/ር) በ2015 በጀት ዓመት ሦስት ሚሊዮን ሔክታር የሚጠጋ መሬት በመስኖ ልማት በመሸፈን ስንዴ ማምረት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በዘንድሮ ዓመት ከ24 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በላይ በመስኖ ልማት ለማረስ ዕቅድ መያዙን ገልጸው፣ አጠቃላይ የእርሻ መሬትን በኖራ በማከምና ውኃ ለሌላቸው ማድረስ ከተቻለ 40 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ማረስ እንደሚቻል ተናግረው ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች