Wednesday, July 24, 2024

የአማራ ክልል ፀጥታና የሰላም ካውንስል ምሥረታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በወሎ አካባቢ ያደረጉትን ጉብኝት በተመለከተ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ አብራርተው ነበር፡፡ ‹‹ይህ ጉብኝት ለእኛ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ምክንያቱም ክልላችን ትናንት ከነበረበት የፀጥታ መታወክ ችግር እየወጣ መሆኑን ያበሰረ ነው፡፡ እንደ ክልል በልማት ላይ አተኩረን መሥራት እንዳለብን የጠቆመም ነው፤›› በማለት የጉብኝቱ መሠረታዊ ዓላማ ያሉትን ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ይህን ቢሉም ከቀናት ቀደም ብሎ በባህር ዳር ተካሂዶ በነበረው የሰላም ጉባዔ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ደግሞ፣ ሌላኛውን የክልሉን ገጽታ ሲናገሩ ተደምጠው ነበር፡፡ በአማራ ክልል በአውቶብስ እንኳን መጓዝ ብርቅ ሆኗል ሲሉ የተደመጡት አቶ አገኘሁ፣ ተማሪዎች መማርም ሆነ ለፈተና መቀመጥ አለመቻላቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹መንግሥት የልማት ሥራዎችን መሥራት አልቻለም፡፡ ማዳበሪያም ለገበሬው ማድረስ አልቻለም፤›› በማለት የክልሉ የፀጥታ ችግር ያለበትን አሳሳቢ ደረጃ ገልጸውታል፡፡

ስለአማራ ክልል የፀጥታ ጉዳይ የአማራ ክልልን እንወክላለን የሚሉ ፖለቲከኞች በቀናት ልዩነት የሰጡት አስተያየት ፍፁም የሚራራቅ ነበር፡፡ በሌላ በኩልም ለችግሩ ዕልባት ለመስጠት ያስችላሉ ተብለው የሚቀርቡ የመፍትሔ ሐሳቦችም እንዲሁ ፍፁም የተለያዩ ሲሆኑ በተደጋጋሚ ተስተውሏል፡፡

በቅርቡ በአማራ ክልል ሰላም ለማስፈን ይረዳሉ የተባሉ ተከታታይ የሰላም ኮንፈረንሶች ሲካሄዱ ሰንብተዋል፡፡ በእነዚህ በሰባት ከተሞች በተካሄዱ የሰላም ኮንፈረንሶች በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን የሚጠይቁ ድምፆች ተስተጋብተዋል፡፡ በስብሰባዎቹ መቋቋሙ የተነገረው የሰላም ኮሚቴም የፋኖ ኃይሎችን ከመንግሥት ጋር ለማደራደር መንገድ እንደሚጠርግ ታምኖበት ነበር፡፡

ይህ ሆኖ በስተመጨረሻ በባህር ዳር ከተማ የሰላም ጉባዔ ማጠናቀቂያ ላይ የወጣው አቋም መግለጫ ብዙ ውጤት ያለው ነገር ይዞ እንደሚመጣም ተጠብቆ ነበር፡፡ በስብሰባው ማሳረጊያ የወጣው ባለአሥር ነጥብ የአቋም መግለጫ ግን የተብራራ የሰላም ሒደት ወይም ቅደም ተከተል እንደሌለው የሚናገሩ ነበሩ፡፡

የአቋም መግለጫው ከድርድር ወይም ከዕርቀ ሰላም ጥሪነት ይልቅ ስለሆደ ሰፊነት ነበር የሚያብራራው በሚል ሲተች ሰንብቷል፡፡ የታጠቁ ኃይሎችን ትርጉም ባለው መንገድ የፖለቲካ ጥያቄ ያላቸው ኃይሎች ናቸው ብሎ ከመቀበል አይነሳም፣ በአንዳንዶች እምነት ጉዳዩን ልክ እንደ አባትና ልጅ ፀብ በማሳነስ ዝንባሌ የሚታይበት የአቋም መግለጫ ተደርጎ ነው የተወሰደው፡፡ የታጠቁት ኃይሎች አካሄዳቸው ለክልሉ ሕዝብ የማይጠቅም በመሆኑ መሣሪያ ጥለው ከጫካ እንዲመለሱ ለምክርና ለተግሳፅ ያጋደለ ሐሳብ የሚሰጥ የአቋም መግለጫ ተደርጎም መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡

በአማራ ክልል ትጥቅ አንግበው ከመንግሥት ጋር የሚፋለሙ ኃይሎች የራሳቸው የፖለቲካ አቋምና ፍላጎት እንደያዙ ዕውቅና የሚሰጥ መደበኛ (Formal) የሰላም ንግግር ጥያቄ ማቅረብ አስፈላጊ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡና የክልሉ ቀውስ እንዲፈታ የፈለገ ሰው ደግሞ የሰላም ሒደቱ በምን አግባብ፣ በምን ቅደም ተከተል እንደሚካሄድ በግልጽ መቀመጥ እንደሚኖርበት የሚያሳስቡ በርካታ ናቸው፡፡

ይህም ቢሆን ግን የአቋም መግለጫውን ለፋኖ ኃይሎች የተደረገ የሰላም ጥሪ አድርገው የቆጠሩት በርካታ ናቸው፡፡ ለረዥም ጊዜ ድምፁን ያጠፋው ፖለቲከኛ ጃዋር መሐመድ ከማንም ቀድሞ ነበር ጉዳዩን የሚደነቅ የሰላም ጥሪ አድርጎ ሲጠራው የነበረው፡፡ ‹‹መከላከያ ሠራዊት ለአማራ ክልል ቀውስ የሰላም አማራጭ ለማፈላለግ የጀመረው ጥረት የሚደነቅ ነው፡፡ መከላከያው በአማራ ክልል ስለተፈጠረው ቀውስ በቂ ግምገማ ያደረገ ይመስለኛል፡፡ ለዚህም ነው የሰላም መፍትሔ ለማፈላለግ ጥረት የጀመረው፤›› በማለት ፖለቲከኛው መልዕክት አስተላልፎ ነበር፡፡

ፖለቲከኛ ጃዋር ከስድስት ቀናት በፊት ይህን መልዕክት በፌስቡክ ገጹ ሲያወጣ፣ መንግሥት (የፌደራልም ሆነ የአማራ ክልል) በይፋ ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ለመደራደር መፈለጋቸው አልታወቀም ነበር፡፡

ይህ በሆነ በማግሥቱ ደግሞ አቶ ጃዋር ወደ ፌስቡክ ገጹ ብቅ ብሎ የቀደመውን ሐሳቡን አሻሽሎ ለማቅረብ ሲሞክር ታየ፡፡ ‹‹በአማራ ክልል ሰላም ለመፍጠር ከተፈለገ በእኔ ግምት መንግሥት መደበኛ የድርድር ጥሪ ማቅረብ አለበት፡፡ ፋኖም ራሱን የቻለ በድርድሩ የሚወክለው ቡድን ማደራጀት አለበት፤›› በማለት የተብራራ ሐሳብን ጃዋር በዚህ ዙር አቅርቦ ነበር፡፡

ጃዋር በሁለኛው ዙር አስተያየቱ የመንግሥት ባለሥልጣናት አሳማኝ የድርድር መፍትሔ ይዘው ሳይመጡ በየመድረኩ የታጠቁ ኃይሎች ትጥቅ ፈተው ይመለሱ የሚል ተግሳፅ መሰል አስተያየት መስጠታቸው፣ ለሰላም እንደማይበጅ ነው የተናገረው፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናቱ በሚመሯቸው የሰላም ኮንፈረንሶችና በሚያወጧቸው የአቋም መግለጫዎች የሰላም ጥሪ እንዳደረጉ መጀመሪያ ቢቆጠርም፣ የኋላ ኋላ ግን መደበኛና ይፋዊ የሰላም ጥሪ መንግሥት ማድረግ ይገባዋል የሚለው ጫና ተመልሶ ወደ እነሱ መጥቷል የሚሉ አሉ፡፡

ይህ ከሆነ ከቀናት በኋላ ደግሞ ‹‹የሰላም ካውንስል›› የተባለ ግብረ ኃይል ስለመደራጀቱና የሰላም ጥሪ ስለማድረጉ ተሰማ፡፡ ግብረ ኃይሉ ለአማራ ክልል፣ ለፌደራል መንግሥትና ለፋኖ ኃይሎች ብሎ በስም ጠርቶ ባቀረበው የሰላም ጥሪ በክልሉ ያለው ቀውስ እንዲቆም ጠይቋል፡፡ ይህ የሰላም ካውንስል ለክልሉ ቀውስ የድርድር መፍትሔ ለማፈላለግ እንደሚሠራ ይገልጻል፡፡ የሰላም ካውንስሉ ወንድም ከወንድም መገዳደሉ ሊያበቃ ይገባል ይላል፡፡ የሰላም ካውንስሉ በንግግር በድርድርና በውይይት ብቻ ችግሩ መቆም እንዳለበትም ይናገራል፡፡ የሰላም ካውንስሉ ሁሉም አሸናፊ መሆን በሚችልበት የድርድር መንገድ ችግሩ እንዲፈታ እንደሚጠይቅ በመጥቀስ ይህን ለማመቻቸትም እንደሚሠራ ያስታውቃል፡፡

የሰላም ካውንስሉ ሲቋቋም ጀምሮ አሉታዊና አዎንታዊ አስተያየት ሲስተጋባበት መቆየቱን ይናገራል፡፡ የሰላም ካውንስሉ ጥረቱ የማይሳካና የማስመሰል ነው የሚል ትችት እንደገጠመውም ገልጿል፡፡

‹‹ይሁንና እየሆነ ያለውን ሁኔታ ተመልክተን፣ የሕዝባችንን ሥቃይ ተመልክተን ለምናቀርበው የሰላም ሐሳብ መንግሥት በቅንነት በመረዳት ችግሩን በድርድር ለመፍታት መታመንን እንጠብቃለን፤›› በማለት ነው የካውንስሉ መግለጫ ላይ የተገለጸው፡፡

ይህን የሰላም ካውንስሉን መግለጫ ተከትሎም በርካታ ሐሳቦች እየተስተጋቡ ነው፡፡ በዚህ መግለጫ ላይ ለሦስቱም ማለትም ለክልሉ መንግሥት፣ ለፌደራልና ለፋኖ ወደ ሰላማዊ የችግር መፍቻ መንገድ እንዲገቡ ጥሪ ቀርቧል፡፡ ይሁን እንጂ ከፋኖ ኃይሎችም ሆነ ከመንግሥት ወገን ወደ ድርድሩ ሜዳ ለመግባት ቃል ስለመግባታቸው የሰጡት ምላሽ እስካሁን አልታወቀም፡፡

የሰላም ካውንስሉ ሚና ልክ እንደ ፕሪቶሪያው ድርድር ሁሉ የአፍሪካ ኅብረት ዓይነት የአደራዳሪነት ሚና ይኑረው አይኑረው የታወቀ ነገር የለም፡፡ ካውንስሉ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን ዓይነት ያለው ስለመሆኑም የታወቀ ነገር የለም፡፡ ካውንስሉ በመግለጫው በአገሪቱ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አስቀያሚ ጦርነት የሚካሄደውና ሕዝቡም ከጦርነት ይልቅ ሰላማዊ ትግልን የማይከተለው፣ ‹‹በሰላማዊ ትግል የሚያምን የፖለቲካ ማኅበረሰብ መፍጠር ባለመቻላችን ነው፤›› በማለት ለዚህ ደግሞ የሁሉም ወገን ተጠያቂነት መኖሩን ያስረዳል፡፡

የሰላም ካውንስሉ በመግለጫው ለሰላም ጥሪ የተደረገላቸው ሁሉም ወገኖች ጥሪውን በቀናነት ተቀብለው ቀና ምላሽ እንዲሰጡም ይጠይቃል፡፡

ይሁን እንጂ የፋኖም ሆነ የመንግሥት ኃይሎች ጥሪውን ተቀብለናል ቢሉ መቼ? የት? በምን አጀንዳ? በማን ሸምጋይነት? በምን አግባብ? የሰላም ንግግርም ሆነ ድርድር እንደሚያደርጉ የተብራራ ነገር ከመግለጫው አልተገኘም፡፡

ካውንስሉ ጀመረ የተባለውን የዕርቅ ወይም የሰላም ጥሪ በሚመለከት ሪፖርተር በስልክ ያናገራቸው አንድ የፓርላማ አባል ስለጉዳዩ ማብራሪያ ለመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ የሕዝብ እንደራሴው ነገ ሐሙስ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር የምክር ቤት አባላት ውይይት እንደሚኖራቸው በማስታወስ በጉዳዩ ላይ በዕለቱ ጥያቄ እንደሚነሳ ገልጸዋል፡፡ ‹‹እንደ ፓርቲም እንደ ፓርላማ አባልም በዚሁ የሰላም ካውንስሉ ጉዳይ ጥያቄ ስለምናቀርብና በዕለቱ ማብራሪያ ስለምናሰጥበት ከዚያ በፊት የምሰጠው አስተያየት አይኖርም፤›› ሲሉ በአጭሩ ተናግረዋል፡፡

የካውንስሉ መቋቋምና የሰላም ጥሪ ማቅረብን በተመለከተ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዱ ሁሴን (ዶ/ር)፣ ‹‹ጥሪውን ተቀብለናል፤›› የሚል ሐሳብ በክልሉ መገናኛ ብዙኃን በኩል ሲሰጡ ተደምጠዋል፡፡ ‹‹በየትኛውም ቦታና በየትኛውም አካል ለመደራደር የሰላም ጥሪውን ተቀብለናል፡፡ ስለሆነም በጫካ ያሉ ኃይሎችም ይህን ጥሪ መቀበል ለእነሱም ለክልሉም ሲባል አስፈላጊ ነው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ መንግሥታቸው ይህን የሚያደርገው ለክልሉ ሕዝብ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ልጆቻችን ከትምህርት ገበታ፣ አርሶ አደሮቻችን ከእርሻ፣ ነጋዴዎቻችን ከንግድ እንዳይስተጓጎሉ ለማድረግ ስንል ነው የሰላም ጥሪውን የተቀበልነው፡፡ ሁላችንም የምንተጋው ለምንመራው ሕዝብ ነው፡፡ የምንመራው ሕዝብ ፍላጎት እንዲረጋገጥ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፤›› በማለትም አብዱ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

ይህ የሰላም ጥሪ ከፋኖ ወገን ምን ዓይነት ምላሽ እንደሚያገኝ ገና አልታወቀም፡፡ ወደ ድርድር ከተገባና የሁለቱንም ወገኖች ቅቡልነት የሰላም ጥሪው ካገኘ ፋኖ በምን መንገድ ለድርድር ይቀርባል የሚለው ራሱን የቻለ ጥያቄ ነው፡፡

ከሰላምና ስለሰላም ጥሪ ጉዳይ ከሚሰማበት ከዚሁ አማራ ክልል ከሰሞኑ እየተፈጠሩ ያሉ ሁኔታዎች ክልሉ ወደ ሰላም ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ባሰ ውስብስብ ችግርም ሊገባ እንደሚችል የሚጠቁሙ ይመስላል፡፡ ከሰሞኑ የይገባኛል ውዝግብ ወደ የሚነሳበት ጠለምት አካባቢ የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆች ተመልሰው መስፈር ጀመሩ የሚል መረጃ ሲሰማ ሰንብቷል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ የትግራይ ኃይሎች አጨቃጫቂ ቦታዎችን ተመልሰው መያዝ ጀመሩ የሚል ሥጋት ሲያስነሳ ሰንብቷል፡፡ በሌላ በኩል ሀቁን ያረጋገጠ ወገን ባይኖርም ከሰሞኑ እንደ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ያሉ የጦር መኮንኖች የፋኖ ኃይሎችን ተቀላቀሉ የሚል ወሬ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲናፈስ ከርሟል፡፡

መንግሥትና ፋኖ ወደ ድርድር ሊገቡ ነው፣ በአማራ ክልል ሰላም ሊሰፍን ነው፣ እንዲሁም የሰላም ካውንስል የተባለ የሰላም ሒደት አመቻች ግብረ ኃይል ተመሠረተ እየተባለ በአንድ ወገን ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ በተቃራኒው ደግሞ በአማራ ክልል ግጭቱ በተለያዩ ቦታዎች ስለመቀጠሉ ይሰማል፡፡

ከሰሞኑ ብቻ ሰኔ 17 እና ሰኔ 19 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰሜን ሸዋና በጎጃም አካባቢዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ27 ያላነሱ ንፁኃን ዜጎች መገደላቸው ተዘግቧል፡፡

በዚህ ሁኔታ ክልሉ ወደ ሰላም እንዴት ይመለሳል የሚለው ጥያቄ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -