Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኤክስፖርት ምርት ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች በኤሌክትሪክ የሚሠሩ አይደሉም በሚል አገር ውስጥ እንዳይገቡ ተከለከሉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን በኤሌክትሪክ በሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ለመተካት የሚያበረታታ የፖሊሲ ውሳኔ በማሳለፍ ተግባራዊ እያደገ ነው፡፡ 

ከሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተውም፣ በውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራዎች ላይ የሚሠማሩ ማሽነሪዎች፣ ከኮንስትራክሽን፣ ኢንዱስትሪና ከግብርና ጋር የተያያዙ ትልልቅ ማሽነሪዎች ካልሆኑ በስተቀር፣ የትኛውም ወደ አገር ውስጥ የሚገባ ተሽከርካሪ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠራ መሆን አለበት የሚል አቅጣጫ መቀመጡን ነው፡፡ 

ይህንን የመንግሥት ውሳኔ ለማስፈጸምም በተለያዩ ደረጃዎች አስገዳጅ የሚባሉ መመርያዎች ጭምር እየወጡ መሆኑም ታውቋል፡፡  በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን በኤሌክትሪክ ለመተካት በተወሰነው ውሳኔ መሠረት የአሥር ዓመታት ዕቅድ የተቀረፀ ሲሆን፣ በዚህ የዕቅድ ዘመን ውስጥ 148 ሺሕ በላይ የቤት አውቶሞቢሎችንና ወደ አምስት ሺሕ የሚደርሱ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ አውቶቡሶችን ወደ ሥራ ለማሰማራት እየተሠራ ነው ተብሏል፡፡ ዕቅዱን ከዚህም በላይ ከፍ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታዎች ያሉ በመሆኑ የአሥር ዓመቱ ዕቅዱ ሊከለስ እንደሚችልም መረጃው ይጠቁማል።

ዕቅዱን ወደ መከለስ የሚገባበት አንዱ ምክንያትም በአሁኑ ጊዜ ከ80 ሺሕ በላይ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር የገቡና እየተገጣጠሙ በመሆኑ፣ በአሥር ዓመታት ውስጥ ይዳረሳል ተብሎ የተያዘውን ዕቅድ ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው አመላካች ሆኗል።

መንግሥት ወደ እዚህ ዕርምጃ ለመግባቱ ካስቀመጣቸው ምክንያቶች መካከል፣ ለነዳጅ የሚወጣውን ወጪ መቀነስና ኢትዮጵያ የአረንጎዴ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር የተጣጣመ ማድረግ የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው። በተጨማሪም የአካባቢ ጥበቃን የሚያግዝ በመሆኑና በዓለም ላይ ያለው አሠራርም በኤሌክትሪክ ወደሚሠሩ ተሽከርካሪዎች እየተሸጋገረ በመሆኑ፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በአስገዳጅ ሁኔታ ማበረታታት አስፈላጊ ሆኖ እንደተገኘ መረጃው ይገልጻል።

በዚህ የመንግሥት የፖሊሲ ውሳኔ መሠረት በተለይ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ የቤት ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ በብዛት እየገቡ ሲሆን፣ የከተማ አውቶቡሶችን በኤሌክትሪክ በሚሠሩ አውቶቡስ ለመተካትም እየተሠራ መሆኑ ታውቋል፡፡ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ሚኒባስ ታክሲዎችም በተመሳሳይ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ እንዲሆኑ በአገር ውስጥ የተገጣጠሙ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ታክሲዎች የሙከራ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።

መንግሥት በፖሊሲ ደረጃ እያራመደ ያለውን ይህንን ዕቅድ ከማስፈጸም አንፃርም በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች እንዳይገቡ ገዳቢ የሆኑ አሠራሮች እየተተገበሩ ነው፡፡ ይህ የመንግሥት ውሳኔ ግን ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም፡፡ በተለይ ትልልቅ ተሽከርካሪዎች በአስገዳጅነት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ መሆን አለባቸው የሚለው ውሳኔ ሊፈተሽ እንደሚገባ እየተነገረ ነው፡፡ 

በኤሌክትሪክ ኃይል ለሚሠሩ ተሽከርካሪዎች የሚሆን በቂ መሠረተ ልማት ባልተዘረጋበት ሁኔታ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ብቻ ወደ አገር እንዲገቡ የሚያስገድድ አሠራር መከተልና ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል በመንግሥት የወጣ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር ብዥታ እንደፈጠረባቸው በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው በሆርቲካልቸራል ዘርፍ የተሰማሩ አልሚዎች ይገልጻሉ፡፡  

በተለይ በግብርና ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየገጠማቸው ያለው ችግር በኢንቨስትመንት ኮሚሽንና በገንዘብ ሚኒስቴር ጭምር ተፈቀዶላቸው ወደ አገር ለማስገባት የገዟቸው ለወጪ ንግድ ምርት ማጓጓዣ የሚሆኑ ትልልቅ ተሽከርካሪዎችና ትራክተሮች ወደብ ከደረሱ በኋላ እንዳይገቡ ክልከላ ተጥሎባቸዋል።

እንዲህ ያለው ችግር የገጠማቸው አንድ በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ በማምረት ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ ኩባንያ ተወካይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እንዲገቡ ፈቃድ ያገኙባቸው በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ወደብ ከደረሱ በኋላ እንዳይገቡ ተደርገዋል፡፡ ለዚህም የተሰጣቸው ምክንያት ወደብ የደረሱት ተሽከርካሪዎች በኤሌክትሪክ የሚሠሩ አለመሆኑና ይህንንም ካልሆነም ወደ አገር ውስጥ ማስገባት እንደማይቻል ነው።

ይህም በመሆኑ ወደብ ከደረሱ በኋላ ተሽከርካሪዎችን ማስገባት ባለመቻላቸው፣ ያላግባብ የወደብ ኪራይ እየቆጠረባቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ለግብርና ሥራቸው የሚጠቀሙባቸውን ትራክተሮችና ኤክስፖርት የሚደረጉ የግብርና ምርቶችን ለማጓጓዣነት የሚጠቀሙባቸውን ማቀዝቀዣ ያላቸው ተሽከርካሪዎች በኤሌክትሪክ የሚሠሩ መሆን አለባቸው በሚል ተላልፏል የተባለው መመርያ ብዥታ እንደፈጠረባቸው የገለጹት ሌላው አስተያየት ሰጪ፣ የጂይቴክ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የኦፕሬን ሥራ አስኪያጅ አቶ ብስራት ኃይለ ሥላሴ ናቸው፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ትልልቅ ተሽከርካሪዎችን አስገቡ የሚለው ጉዳይ አሠራሩ ግልጽ አይደለም፡፡ ጉዳዩ በኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማኅበር በኩል ክትትል እየተደገበት ቢሆንም፣ እስካሁን አዎንታዊ ምላሽ እንዳላገኘም ጠቁመዋል፡፡ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ብቻ አስገቡ መባሉና ፈቃድ የተሰጣቸው በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ጭምር እንዳይገቡ መደረጉ ኩባንያዎች አዲስ ተሽከርካሪዎችን ለመግዛት የነበራቸውን ዕቅድ እስከ ማዘግየት አድርሷቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለሥራው የሚፈልጓቸውን ተሽከርካሪዎች በሚፈልጉበት ጊዜ እንዳያገኙና ይህም ሥራቸው ላይ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችል የአቶ ብስራት አስረድተዋል፡፡ 

እሳቸው በሚመሩት ኩባንያ ሥር የሚገኙ አብዛኞቹ ተሽከርካሪዎች ረዥም ጊዜ ያገለገሉ በመሆናቸውና እነዚህን ተሽከርካሪዎች ጠግኖ ሥራ ላይ ለማዋል ካለው የመለዋወጫ ዕቃዎች አንፃር አዋጭ የሚሆነው አዲስ ተሽከርካሪ ማስገባት ቢሆንም፣ ማስገባት የሚቻለው በኤሌክትሪክ የሚሠራ ተሽከርካሪ መሆን አለበት መባሉ እንቅፋት እንደሆነባቸው ገልጸዋል። 

ይህም ጉዳዩ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን እንዳይገቡ መከልከል ብቻ ሳይሆን፣ ፈቃድ አግኝተው ወደብ የደረሱ ተሽከርካሪዎችን እስከ ማገድ የደረሰ በመሆኑ፣ ተሽከርካሪዎችን ያስመጡ ኩባንያዎች ላልተገባ የወደብ ኪራይ እየተዳረጉ መሆኑን አመልክተዋል። ከዚህ በፊትም በተመሳሳይ መንገድ ተመሳሳይ ተሽከርካሪዎች አምጥተው ለኪራይ ብቻ ከመቶ ሺሕ ዶላር በላይ የተከፈለበት አጋጣሚም መኖሩን በማስታወስ፣ ሁኔታው በኩባንያዎች ላይ ብቻ ሳይሆን እንደ አገርም ከፍተኛ ጉዳት የሚደርስ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

የመንግሥት የፖሊሲ ውሳኔ ነው ተብሎ ግልጽ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ ሳይኖረው የመንግሥት የፖሊሲ ውሳኔ ነው ተብሎ የተጣለው ክልከላ በሌላ የመንግሥት ተቋም ውሳኔ ወደ አገር እንዲገቡ የተፈቀዱ ተሽከርካሪዎችንም እንዳገደ የሚገልጹት ኃላፊው፣ የመንግሥት አቅጣጫ ነው በሚል ለልማት ሥራ የሚውሉ ትራክተሮችም ሆኑ ማቀዝቀዣ ያላቸው የግብርና ምርቶችን የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች ከወደብ ወደ አገር ማስገባት አለመቻሉን ገልጸዋል። ይህም በዘርፉ ላይ ጫና አሳድሯል ብለዋል፡፡

በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች እንዲበረታቱ መንግሥት የወሰደው ዕርምጃ ተገቢ ቢሆንም፣ ይህንን ለመተግበር ግልጽ የሆነ መመርያ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ብሥራት በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም ካለመፈለግ ሳይሆን አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለኤክስፖርት ምርቶች ማጓጓዣ የሚሆኑ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ገበያ ላይ ማግኘት ከባድና አስቸጋሪ ነው ብለዋል፡፡ 

በተለይ ደግሞ ትራክተሮችም በዚህ አሠራር ውስጥ እንዲያልፉ ማድረግ ተገቢ ነው ብለው እንደሚያምኑ በመግለጽም፣ ክልከላውና ዕገዳው ብቻ ሳይሆን በገበያው ላይ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ትልልቅ ተሽከርካሪዎችና ትራክተሮች ቢገኙ እነዚህ ተሽከርካሪዎች በአብዛኛው የሚሠሩት በገጠራማ አካባቢ በመሆኑ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አግኝተው ሊጠቀሙ ስለማይችሉ በአንድ ጊዜ እንዲህ ያለውን ውሳኔ ማሳለፍ ተገቢ እንዳልሆነ አስረድተዋል። 

በጉዳዩ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር ማኅበር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ እንዲህ ያለው ችግር የገጠማቸው የማኅበራቸው አባላት ጉዳዩ በማኅበሩ በኩል እንዲታይላቸው ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ለሚመለከታቸው አካላት አቅርቦ ክትትል እየተደረገበት ነው፡፡ 

በዚህ ጉዳይ ላይ በቀጥታ የሚመለከተው የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በመሆኑ ማኅበሩ ጉዳዩን በግንባር ቀርቦ የጠየቀ ቢሆንም፣ እነሱም ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ዝርዝር ምላሽ እየጠበቁ መሆናቸውን እንደገለጹላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

መንግሥት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በከፍተኛ መጠን እንዲገቡና እንዲገጣጠሙ በማድረግ በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ከገበያ ለማስወጣት ጠንከር ያለ አቋም እየያዘ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ፣ ‹‹አሁን በሥራ ላይ ያሉት በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? የሚለውም ጥያቄ ብዙዎችን ማሳሰቡ አልቀረም፡፡ 

መንግሥት በዚህ ጉዳይ ጠንከር ያለ አቋም ስላለው፣ አሁን በሥራ ላይ ያሉ በናፍጣና በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ደረጃ በደረጃ እንዲወጡ ለማድረግ ውሳኔ ስለማሳለፉ ታውቋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ከዚህ ቀደም ከተሰጠ ማብራሪያ መረዳት እንደሚቻለውም፣ አሁን ሥራ ላይ ያሉት በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን፣ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ወደ ኤሌክትሪክ የመቀየር ሥራ እንዲሠራ ተወስኖ ይህንን ለማድረግ ውሳኔ ስለማሳለፉ ታውቋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ከዚህ ቀድሞ ከተሰጠ ማብራሪያ መረዳት እንደሚቻለውም አሁን ሥራ ላይ ያሉ በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ወደ ኤሌክትሪክ የመቀየር ሥራ እንዲሠራ ተወሰኖ፣ ይህንን ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡

በግብርና ዘርፍ የተሠማሩ አልሚዎች ግን እንዲህ ያለውን ዕርምጃ በአንዴ ሊተገበር የማይችል፣ መሬት ላይ ያለውን ሁኔታም ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ መሆን አለበት በማለት ይሞግታሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች