Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከደረጃ በታች የሆነ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ገመድ ገበያውን ማጥለቅለቁ የፈጠረው ሥጋት

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ሰፊ ገበያ አላቸው ተብሎ ከሚጠቀሱ ምርቶች መካከል የኤሌክትሪክ ገመዶችና ተያያዥ ምርቶች ናቸው፡፡ ከግለሰብ ጀምሮ በመንግሥት ደረጃ የኤሌክትሪክ መስመሮችን ለመዘርጋት የሚጠቀምባቸው ምርቶች በመሆናቸው ከፍተኛ የገበያ ፍላጎት ያለው መሆኑን እነዚህ ምርቶች የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ አምራቾች ማኅበር ያስረዳል፡፡ 

ፍላጎቱ ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃርም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አምራቾች የሚሸፈን ባለመሆኑ አሁንም አብዛኛው ምርት እየገባ ያለው ከውጭ ነው፡፡ ኢንዱስትሪው እንዲህ ባለ ደረጃ የሚገለጽ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶች ገበያውን ማጥለቅለቃቸው እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

በዚህ ሰፊ ገበያ እንዳለው በተገለጸበት ኢንዱስትሪ ውስጥ ከአምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት በማድረግ ወደ ሥራ የገባው ኤፍቲ የተባለ የቻይና ኩባንያ በኢንደስትሪው ዙሪያ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ እንደተገለጸውም የዘርፉ ተዋንያኖች እንደ ዋነኛ ችግር አድርገው ያነሱት ይህንኑ የጥራት ችግርና ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ነው፡፡ 

ከደረጃ በታች የሆኑ የኤሌክትሪክ ገመዶች ሊያስከትሉ የሚችሉት ከፍተኛ ጉዳት በተለያየ መንገድ የተገለጸ ሲሆን፣ ለጉዳዩ በቶሎ መፍትሔ ካልተበጀለት አደጋው የከፋ ይሆናል የሚል ሥጋታቸውን ሲሰነዝሩ ተሰምቷል፡፡

ይህንን የውይይት መድረክ ያዘጋጀው የኤፍቲ ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር ፉ በሰጡት ማብራሪያ መገንዘብ እንደተቻለውም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በዚህ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ካነሱዋቸው ምክንያት አንዱ በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ጥራት ያለው ምርት በበቂ ሁኔታ እየቀረበ ያለመሆኑን መረዳታቸው ነው፡፡

በቻይና ውስጥ ከ15 ዓመታት በላይ ስለመሥራታቸው የገለጹት ሚስተር ፉ በአንድ ወቅት በቻይና ደረጃቸውን ካልጠበቁ የኤሌክትሪክ ገመድ ምርቶች ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ችግር ብዙ ዋጋ ማስከፈሉን አስታውሰዋል፡፡ ስለዚህ ጥራት ያለው ምርት ወሳኝ በመሆኑ ኩባንያቸው ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶችን በማምረት ተወዳዳሪ በመሆን ገበያ ውስጥ ለመግባት መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ በዕለቱ የተዘጋጀውን የውይይት መድረክ ለማሰናዳት የወደዱትም በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በማወቅ በትብብር ለመሥራትና ያሉ ችግሮችንም መፍትሔ ለማፈላለግ እንዲረዳ ነው፡፡ 

በውይይት መድረኩ ላይ በቀጥታ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥታዊ ተቋማትና የግል ኩባንያዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ ከሌሎች ችግሮች የበለጠ የጥራት ጉዳይ ጎልቶ መውጣቱ ያለውን ችግር ያጎላል ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ አምራቾች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዓብይ ካሳ (ዶ/ር) በዚህ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለው ዋነኛ ችግር ከጥራት ጋር የተያያዘ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡ በውይይት መድረኩ ላይም ይህንኑ አብራርተዋል፡፡ በዚሁ ጉዳይ ላይ ለሪፖርተር በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ችግሩ ምን ያህል ሥር እንደሰደደ አመላክተዋል፡፡ ‹‹ከማኅበራችን ውጭ ያሉ አንዳንድ ኩባንያዎች ከደረጃ በታች የሆነ ምርት እያመረቱ ለገበያ እያቀረቡ ጭምር መሆኑ አጠቃላይ ገበያውን ከመረበሽ ባለፈ በእነዚህ ምርቶች የሚሠሩ ሥራዎች ለአደጋ ተጋላጭ እያደረጋቸው ነው፤›› በማለት ችግሩን ገልጸዋል፡፡  

እንዲህ ያለው እጅግ አደገኛ ሁኔታ ማኅበረሰቡንም ሆነ አገርን እንደሚጎዳ እንደሆነ ያከሉት ዓብይ (ዶ/ር) በተለይ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን በኤሌክትሪክ ኃይል ዝርጋታ ላይ ከፍተኛ አደጋ የሚኖረው ነው፡፡ ለእሳት አደጋዎች መባባስም ከደረጃ በታች የሆኑ የኤሌክትሪክ ምርቶች በእጅ እያሳሱዋቸው እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ችግሩ እየተባባሰ በመሆኑም እነዚህን ከደረጃ በታች የሆኑ የኤሌክትሪክ ገመዶች ናሙና ከገበያ በማሰባሰብ ለሚመለከተው አካል እስከማቅረብ የደረሱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ናሙናው የቀረበላቸው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ሌሎች መሥሪያ ቤቶች በራሳቸውም መንገድ ከደረጃ በታች የሆኑትን ምርቶች በማሰባሰብና አጠቃላይ ሁኔታውን አጥንተው ወደ ዕርምጃ ይገባሉ ተብሎ እየተጠበቀም ነው፡፡ 

በዚህ ኢንዱስትሪ ላይ አለ ብለው የጠቀሱት ሌላው ችግር አንዳንድ ኩባንያዎች በሌሎች ኩባንያዎች ስም ምርቱን ለገበያ እያቀረቡ በመሆኑ ጭምር ነው፡፡ ይህም በአግባቡ የሚሠሩ የማኅበራቸውን አባላት ጭምር ችግር ላይ እየከተቱ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

አንዳድ ከውጭ የሚመጡ ኩባንያዎች ስማቸውን እየቀያየሩ መሥራታቸው የችግሩ አካል ስለመሆኑም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ 

ከደረጃ በታች ተመርተው ለገበያ መቅረባቸው ሳያንስ በገበያ ውስጥ ያልተገባ ውድድር እንዲፈጠር እያደረገ ጭምር ስለሆነ አደጋውን መቀነስ ያስፈልጋልም ይላሉ፡፡ 

በሌሎች ኩባንያዎች ስም ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች የሚሰጡበት ዋጋ ከማምረቻ ዋጋ በታች የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች በመኖራቸው አደጋው በተለያዩ አቅጣጫዎች እየሆነ ስለመምጣቱም አስረድተዋል፡፡

ዘርፉን በተመለከተ አለ ያሉትን ሌላው ችግር ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ‹‹ኬብል ትራንስፎርመር የሚያመርቱ የማኅበሩ አባላት በዋናነት ምርቶቻቸውን እያቀረቡ ያሉት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ለኢትዮጵያ መብራት አገልግሎት በመሆኑ በገቡት ኮንትራት መሠረት ምርትን ለማቅረብ እየተቸገሩ ነው፤›› የሚሉት ዓብይ (ዶ/ር) ይህ እየሆነ ያለውም በውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው፡፡

አንዳንዶቹ የኮንትራት ውሉን ለመሙላት የውጭ ምንዛሪ ያላቸው ላኪዎች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ ጥሬ ዕቃውን እየገዙ የሚያወጡላቸው ጭምር ሲሠሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ይህ ደግሞ የመግዣ ዋጋውን በእጥፍ ስለሚጨምር አዋጭ የሆነ ሥራ ለመሥራት እንዳልቻሉ ይገልጻሉ፡፡ ከጉምሩክ ጋር የነበሩ ችግሮች ግን እየተቀረፉ ነው የሚሉት ፕሬዚዳንቱ የጥራት ጉዳይ ግን በእጅጉ እያሳሰበ ነው ይላሉ፡፡ በውይይቱ ተሳታፊ ከነበሩ የመንግሥታዊ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ተወካይ እንደገለጹት ደግሞ ችግሩ የጥራት ብቻ ሳይሆን በበቂ ሁኔታ ምርቱን ማቅረብ ያለመቻል ነው፡፡ መሥሪያ ቤታቸው አሁን እየተጠቀመ ካለው ምርት 60 በመቶውን ከውጭ የሚያመጣ በመሆኑ ይህን ሰፊ ገበያ ለመሸፈን እንደ ኤፍቲ ያሉ ኩባንያዎች በጥራትም በብዛትም ቢያመርቱ ተጠቃሚ ሊሆኑበት የሚችሉበት ዕድል እንዳለ ጠቁመዋል፡፡ ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር ጥራት ብቻ ሳይሆን መቶ ሜትር ተብሎ የሚሸጥ ጥቅል ገመድ 80 ሜትር  እየሆነ ብዙ ነገሮችን እያበላሸ በመሆኑ ብዙ ችግር ያለበት ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ላይ የኬብል ጥራት ችግር ሁሌም የሚነሳ ቅሬታ ቢሆንም እስካሁን መፍትሔ ያላገኘ ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ሌላው ተሳታፊ ደግሞ በገበያ ውስጥ ከፍተኛ እጥረት መኖሩን ነው፡፡ 

ጥራቱን የጠበቀ የኃይል ማስተላለፊያ ኬብል፣ የኤክትሪክ ፍጆታ የሚቆጥብ ከመሆኑም በላይ፣ የተረጋጋ የኤሌክትሪክ ኃይል በማስተላለፍና በኤሌክትሪክ ከሚሠሩ ከተለያዩ መሣሪያዎች ጋር በመገናኘት የተጠቃሚውን ፍላጎት የሚያረካ መሆኑን ሲገባው ጥራት ያለው ኬብል በተለያየ ምክንያት የሚከሰቱ የኤሌክትሪክ ንዝረቶችን ከመከላከልም አልፎ በተለያየ አካባቢያዊና የአየር ንብረት ተፅዕኖዎች ምክንያት የሚከሰቱ የኤሌክትሪክ ብልሽቶችን የመከላከል አቅም ያለው ነው ያሉት ሚስተር ፉ ኅብረተሰቡም ደረጃውን የጠበቀ ምርት መሆኑን በመለየት ሊገበያይ ካልቻለ ችግር መፈጠሩ አይቀርም ይላሉ፡፡ 

በኢትዮጵያ የኬብል ጥራት ችግርን የሚፈታ ዘመናዊ አሠራር ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጀምር በመግለጽም ይህንንም አቅም የማሳደግ ዕቅድ አላቸው፡፡ በሰበታ ከተማ በሚገኘው ፋብሪካ በአሁኑ ወቅት በወር እስከ 300 ቶን ኬብል የማምረት አቅም እንዳለው የገለጹት ሚስተር ፉ ከዚህ በኋላ ገበያውን ያገናዘበ የማስፋፊያ ሥራ ሊሠሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡   

ኩባንያው የሚያመርተውን ምርት በተመለከተ ከተሰጠ ተጨማሪ ማብራሪያ መረዳት እንደተቻለው በአሁኑ ወቅት ደረጃቸውን የጠበቁ፣ ተፈላጊውን ጥራት ያሟሉ የተለያዩ የኤሌክትሪክ ኬብል ምርቶችንና የኬብል ምርት ውጤቶችን ማምረት የጀመረ መሆኑን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ ካለው ሁለንተናዊ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች የኤሌክትሪክ ፍጆታና የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ኬብሎች ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመምጣቱ ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶች ማምረት ወሳኝ ዓላማው መሆኑን ሚስተር ፉ  ገልጸዋል፡፡ 

በተለይ ለጥራት መጓደል እንደ ዋና ምክንያት የሚነሳው ኬብሎች የሚመረቱበት ጥሬ ዕቃዎች ጥራት ያነሰ መሆንና የኬብል ምርቶች ጥራትና ደረጃን በሚገባ ፈትሾ ማረጋገጫ የመስጠት ጉዳይ እንደ ምክንያት ሊወሰዱ የሚችሉ ነጥቦች በመሆናቸው ይህንኑ ለማረጋገጥ ከዘርፉ ተዋንያኖች ጋር በጋራ የመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ ኬብል የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ብዛት አስካሁን ድረስ በአገሪቱ ያለውን ፍላጎት መሸፈን ያልቻሉ በመሆኑ፣ የኤፍ ኤንድ ቲ ወደ አትዮጵያ መግባት የሚያፎካክር ሳይሆን፣ በትብብር የሚሠራበት ነው ያሉት ዓብይ (ዶ/ር)  በኢትዮጵያ ውስጥ የኮንስትራክሽን፣ የትራንስፖርትና የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች የኤሌክትሪክ ፍጆታና የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ኬብሎች ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት የኢኮኖሚ ባለሙያውና የኤፍቲ አማካሪ አታክልቲ ኪሮስ በዕለቱ ውይይት ትልቅ ችግር ተደርጎ የተነሳው የጥራት ጉዳይ ነውና ይህንን መፍታት የሚቻለው በጋራ በመሥራት ጭምር ነው ብለዋል፡፡ በኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ኬብሎች ጥራት መጓደል ምክንያት የምርቶች ተዓማኒነት ጉዳይና የአገልግሎት ዘመን አጭር መሆን ከተጠቃሚው ጎልተው ከሚሰሙ ቅሬታዎች መካከል በሚገባ ግንዛቤ የተወሰደ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡበት በውይይት መድረኩ ላይ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል፡፡ 

በውይይቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ አክሬዴሽን ጽሕፈት ቤት ተወካይም  የጥራት ችግርን በተመለከተ አሉ የተባሉትን ችግሮች የሚያውቅና መሥሪያ ቤታቸው እየወሰዳቸው ያሉ ዕርምጃዎችን አብራርተዋል፡፡ አያይዞም እንደ ኤፍቲ ያሉ ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን በጥራት ስለማምረታቸው ተከታታይ የሆነ ክትትል የሚደረግ ስለመሆኑ አስታውቀው ችግሩ እየተሠራበት እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች