Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ጉርምርምታ!

ከሳሪስ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። እግርን የሆድ ነገር እያደከመው የሆድ ነገር ያስጉዘዋል። መንገዱ ላይ ደመቅ ብለው ከታተሙ ዳናዎች ይልቅ ዝለው ቀለማቸው የፈዘዙ ይበዛሉ። ኑሮ የከበዳቸው ነዋሪዎች በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ በጭንቀት ይተነፍሳሉ። በአንድ በኩል ኑሮ ሲደቁሳቸው በሌላ በኩል ለልማት ተነሽ መሆናቸው ያስጨንቃቸዋል። ከሆታ ትርምሱ መሀል ታክሲያችን ውስጥ ከተሰየምነው ጥቂት ተሳፋሪዎች አንዱ፣ ‹‹ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል ያሉት እውነት ነው፡፡ ባልበላ አንጀታችን የምንቸልስበት አንሶ ጭራሽ ጭንቀት ጨጓራችንን ይልጠዋል…›› ይላል ጎልማሳው ተሳፋሪ። ‹‹ህም የአዳማጭ ያለህ እያልን ጆሮ የሚሰጠን ሰው እናስሳለን፣ አንተ ደግሞ አረቄና ኑሮን አንድ ላይ ደምረህ ልትፈጀን ነው? ኧረ እንዴት ያለ ዘመን ላይ ነን እናንተ። በግራ አሳይቶ በቀኝ፣ በቀኝ አሳይቶ በግራ የሚታጠፍ በዛ እኮ…፡፡ አለ ይላል የተቀመጠው የአትክልት ነጋዴ መሆኑን የሚናገረው ወዳጁ። ተጀመረ እንግዲህ!

‹‹ቻለው ዘመኑ የመቻቻል ነው…›› አለች ጋቢና የተሰየመች ወጣት። ‹‹ታዲያ ምን እናድርግ በአንዱ ችግር ላይ ሌላ ችግር ሳይረገዝ እየተወለደብን፣ ቀኑ በንትርክና  በጭቅጭቅ ምንም ሥራ ሳንሠራ እያለቀብን እኮ ነው…›› አለ ጎልማሳው ወደ ወዳጁ ዞሮ። ታክሲያችን ቀስ በቀስ እየሞላች ነው። ወግ አሳዳጁና ነገር አነፍናፊውም እንደዚያው ጆሮው እየተከፈተ ነው። ካሰበበት ለመድረስ የትራንስፖርት ችግር መላ ቅጡን ያጠፋበት ነዋሪ፣ እግረ መንገዱን የኑሮውን እንቆቅልሽ ማብላላት የሰርክ ግዳጁ የሆነበት ይመስላል። እያንዳንዱ እንደ ማንነቱ የሚቀዝፈው የሐሳብ ማዕበል ላይ ተሳፍሮም ቢሆን የሚለው አያጣም፡፡ ወያላው ታክሲያችን መሙላቷን ሲያረጋግጥ ‹‹ሳበው!›› ብሎ ዘጋ። ‹ተው ሳበው ሳበው ሳበው መሸብኝ፣ የጆቢራ እራት ግብር አለብኝ› እንዳለው ድምፃዊ ለዕለት ጉዳዩ ያልቸኮለ የለም። ቸኩለንስ ቢሆን መቼ ሆነልን!

መንቀሳቀስ ጀምረናል። የሾፌሩ አነዳድ ከመነሻችን አወዛጋቢ ሆኗል። ‹‹ምነው ወዳጄ ገና ሳንጀምረው ተናገሩ እያሉ አናግረው እንደሚያደናግሩን ሰዎች ታሳቅቀን ያዝክ? ምን አጠፋን?›› አለው ከወጣቷ አጠገብ ጋቢና የተቀመጠ ተሳፋሪ። ‹‹ገና በቅርቡ ነው ትንሽ መኪና መያዝ የጀመርኩት፣ የከባድ መኪና ሾፌር ነበርኩ። አይዞን ቀስ በቀስ አስተካክላለሁ አይደለም እንዴ? እንኳን እኔ ፖለቲከኞቹ ስንት ነገር ሲያበላሹ የማርያም መንገድ እየሰጠን አይደል እንዴ የምንኖረው?›› አለው። በሾፌሩ መልስ አሰጣጥ ወጣቱ ተሳፋሪ ‹ፖለቲካና ኮረንቲ› በሩቁ ባይ ከሆነ ከዚህ በላይ የማይቀጥል ይመስላል። ነገሩ ግን የተገላቢጦሽ ሆነና አረፈው። ‹‹እኔን የሚገርመኝ ግን ሌላ ነው። ከቀላል ወደ ከባድ መሄድ አንድ ነገር ነው። ከከባዱ ወደ ቀላሉ መውረድ ግን እንዴት ነው የሚከብደው? በመስዋዕትነት ለዴሞክራሲ ታገልን ከተባለ በኋላ ሁሉ በእጅ ሁሉ በደጅ ሲሆን እንደገና ወደ ኋላ?›› ቢል ወጣቱ ተሳፋሪ ሾፌራችን ባልሰማ ወደ ወያላው ዞሮ፣ ‹‹የኮሪደር ልማቱ ሲሳለጥ ነቃ እያልን ነው ወይስ ፈዘናል…›› ሲለው ተሳፋሪዎች ገልመጥ ገልመጥ አሉ። ስሜት አይደበቅ እንግዲህ!

ልጁ ሊያነሳ የሞከረው ጨዋታ ተቀባይ በማጣቱ መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡ ተሳፋሪዎች የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የምትመስል ወጣት፣ ‹‹ይመስለናል እንጂ ተቀምጦ ማውራት ሁሌም የሚቀለን፣ ቦታው ላይ ብንሆን እንዴት በከበደን…›› አለች በግጥም። ወዲያው በአንድ ወቅት አጠገቤ ተቀምጦ፣ ‹‹መቼም ዘንድሮ በአጋጣሚም ይሁን በአገጣጣሚ ገጣሚው በዝቷል…›› ያለኝ ተሳፋሪ ትዝ አለኝ። እሱን ሳስብ አጠገቤ ተቀምጣ የነበረች ወይዘሮ፣ ‹‹ሰማህ ወይ ልማቱ አበቃና ግጥም አዲስ የሥራ መስክ ተብሎ ታወጀ እንዴ? ማንም እየተነሳ ገጠምኩኝ እያለ በሰላላ ሐሳቡ እኛንም ስለሉ የሚለን በየሄድንበት አላስቀምጠን አለ እኮ? እንዴት ነው ነገሩ?›› ብትለኝ ያ ያስታወስኩት ተሳፋሪ የላካት መስሎኝ ክው አልኩ። እንዲህ ውስጥ ለውስጥ መናበብ እየቻልን ግን ጥያቄያችን ብዙ መልሳችን ዝምታ የሆነው ለምን ይሆን ግን? እንጃ!

ታክሲያችን መብራት ይዟት ቆመች። ከታክሲያችን አጠገብ ውኃ የመሰለች ዘመናዊ አውቶሞቢል የሚያሽከረክር ጎልማሳ በሞባይል ስልክ ያወራል። ወያላው መስኮቱን ስለከፈተው የሚያወራውን ጥርት ብሎ ይሰማል። ‹‹ስማ ዛሬ የት ነው የምንቆርጠው? የትናንትናው ቤት አልተመቸኝም…›› ይላል። ‹‹እስኪ ማን ነህ መስኮቱን ዝጋው፣ እዚህ አገር በቃ መብላትም መፆምም አይቻልም?›› አለች ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዋ አጠገብ ነጠላ የለበሰች። ‹‹እንዴት ይቻላል? ክፍልፋዩ ከበዛ እኮ ቆየ፣ ለዚህ አይመስልሽም ፉክክሩ አላስቀምጠን ያለው?›› አለቻት ተማሪዋ። ‹‹የምን ፉክክር?›› ቀልቧን ይዞት ኖሮ ለጨዋታ ጓጉታ ስትጠይቃት አጠገቤ የተቀመጠችው ወይዘሮ ጣልቃ ገባች። ጣልቃ ገብ በዛሳ!

‹‹ከሕዝብ በተዘረፈ ሀብት የሚንደላቀቁ እኮ በግዳጅ ይመስል በሚንቀሳቀሱበት ሥፍራ ሁሉ ዘመናዊ ሥጋ ቤቶች እንደ አሸን እየፈሉ ነው። ድሮ ሥጋ ለበዓል ወይም አልፎ አልፎ ድግስ ሲኖር እንጂ፣ እንደ አሁኑ ልክ እንደ ጎመን ማንም እየተነሳ አይበላውም ነበር፡፡ ይብላኝ ለምስኪን አገሬና ለሕዝባችን እንጂ ሥጋ በሊታዎቹ በአርተፊሻል ፕሮቲን የደለበ በሬ እየበሉ የስኳር፣ የደም ግፊትና ባስ ሲልም የካንሰር ደዌ ተጠቂ መሆናቸው እንደማይቀር ከሐኪሞች ሰምቻለሁ…›› ስትል ወይዘሮዋ፣ የአትክልት ነጋዴው፣ ‹‹እኔ ከበፊት ጀምሮ የምለው ይህንን ነው፡፡ የሰው ልጅ በመጠኑ ሥጋ እየበላ ብዙውን ጊዜ አትክልት እንዲበላ፣ ጁስ እንዲጠጣ፣ ስፖርት እንዲሠራ ብመክር ማንም አልሰማ ተብዬ ነበር፡፡ አንቺን ፈጣሪ ይባርክሽ ያልሽው ሁሉ ትክክል ነው…›› ሲላት ታክሲያችን በሳቅ ሁካታ ተነቃነቀች። ወያላችን ሒሳብ ተቀብሎ ሳይጨርስ ሦስተኛው መቀመጫ ላይ የነበሩ ሴቶች ‹ወራጅ› ብለው ወረዱ። ወዲያው አንዲት ጠና ያለች ሴትና ወጣት ልጅ ተሳፍረው ጉዟችን ቀጠለ። ወይ የሥጋ ነገር!

ሴቲቱና ወጣቱ ከደጅ የጀመሩትን ጨዋታ እያፋፋሙት ነው። ‹‹እና እንዴት ነህ? እኔም ሳልጠይቅህ ይኼውልህ ጠፋሁ። አይሞላ የዛሬ ጊዜ…›› ትለዋለች። ‹‹አይ አክስቴ እኔ ነበርኩ መጠየቅ የነበረብኝ እንጂ…›› ብሎ ሒሳብ ሊከፍል ሲል ትንሽ ተጨቃጭቀው የዘረጋውን ብር አጥፎ ኪሱ ከተተው። ‹‹እንዴት ነው ታዲያ እስካሁን አልመጣችም?›› አለች አክስትየው ለአፍታ ዝም ብላ ቆይታ። ‹‹ማን?›› አለ ወጣቱ ስላልገባው። ‹‹ልጅት ናታ፣ ለብቻ ኑሮ እስከ መቼ ነው? ጥሩ ሥራ ይዘሃል፣ ይኼው ብቻህን ስንት ዓመት ባዶ አልጋ እያሞቅክ ትኖራለህ? ሁሉንም ነገር ልመድ፣ ብቻ መኝታ ግን አልመክርህም…›› ስትለው የሰማው ወያላ፣ ‹‹እኔ የምለው አክስቶች በሙሉ የአርሰናል ደጋፊዎች ናቸው እንዴ? ያገኙትን ሁሉ ካላገባህ እያሉ ለማግባባት ሲደክሙ የሚውሉት?›› ብሎ አጉተመተመ። የሰማነው በሙሉ በሳቅ ትንታ እኔን እኔን ተባባልን። ምን ይደረግ ታዲያ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ጎልማሳውና አትክልት ነጋዴው ማታ በመጠጥ ስላጠፉት ገንዘብና ስለሠሩት የግላቸውን ጨዋታ እየተጫወቱ ይሳሳቃሉ። ‹‹ጉድ ነው አንዳንዱ ሰው በቀን የማታ ታሪኩና ጨዋታው ትዝ ይለዋል። አሁን በዚህ ኑሮ እንኳን የማታ አስተዳደርህ የቅድሙ አረማመድህ ይታወስሃል?›› የምትለኝ አጠገቤ ያለችው ወይዘሮ ናት። ይኼን ስትል አንደኛዋ ወጣት ጣልቃ ገብታ፣ ‹‹አልጋ ጠፍቶ እንጂ አሁኑኑ ተኝቶ መታከም ያለበት የአዕምሮ ሕመምተኛ በአገራችን ከ27 በመቶ ይበልጣል መባሉን አልሰማችሁም?›› ብላ ተናገረች። አንዳንዶች እንደ መደንገጥ ብለው ዞረው አዩዋት። ‹‹እውነቴን ነው አልጋ ጠቦን እንጂ ቆመን ስንጓዝ ብርቱ እየመሰልን፣ ልብስ ስንት ጉዳችንን እየሸፈነልን እንጂ የታመምነው እኮ እልፍ ነን ወገኖቼ…›› አለች። ‹‹ታዲያስ አለ ስንል የለም እያሉን፣ መጣ ስንለው ሄደ እያሉን፣ አለቀ ያልነው ገና ተጀመረ እየተባለ በመብራት፣ በትራንስፖርት፣ በመልካም አስተዳደር፣ በሥራ ዕጦት፣ በዚያ ላይ የኑሮው ውድነት ተጨምሮና በኮሪደር ልማቱ ከቀዬአችን እየተፈናቀልን ቆመን መሄዳችን እኮ ተዓምር ነው…›› ብሎ ከአክስቱ ጋር የተቀመጠው ወጣት ሲናገር የመረረው ይመስል ነበር። ወይ ምሬት!

ታክሲያችን ለመቆም ቦታ እየያዘች ነው። ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ሲለን አጠገቤ ተቀምጣ የነበረችው ወይዘሮ፣ ‹‹አልጋው ጥቂት ታማሚው ብዙ…›› ብላኝ ወደ የምትሄድበት ተጣደፈች። እስካሁን ድረስ ዝም ብለው የነበሩ አዛውንት ወደ በሩ እያመሩ፣ ‹‹ጎበዝ ኧረ በባንዲራው? ምንድነው እንዲህ መንጨርጨር? እስካሁን እኮ ችግራችሁን ብቻ ነው የምትለፈልፉት፡፡ ‹እኔ ለአገሬ ምን አደረግኩላት ከማለት ይልቅ፣ አገሬ ለእኔ ምን አደረገችልኝ?› የሚሉት ቧልት ደስ አይልም፡፡ ‹ሰው የሚያጭደው የዘራውን ነው› ሲባል አልሰማችሁም? አዎን የሚታጨደው የተዘራው ብቻ ስለሆነ ትልቁ ነገር ራስን መሞገት ነው፡፡ ከራስ ጋር ሙግት ይገጠም፡፡ ራስን ሳይሞግቱ ወደ ሌላ ማንጋጠጥ አያዋጣም፣ አያተርፍም…›› እያሉ ሲሰናበቱን፣ ‹‹አባታችን አገራችንን እኮ አልረሳንም፣ ነገር ግን ጥያቄዎቻችንና ምላሾቻቸው አልገጥም ብለውን ነው የምናጉረመርመው…›› እያላቸው ወደ ጉዳዮቻችን አዘገምን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት