Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹የከፍተኛ ትምህርት የጥራት ችግሮቹ በመሠረታዊነት ፖለቲካዊና መዋቅራዊ ይዘት አላቸው›› የትምህርት ጥናትና ምርምር...

‹‹የከፍተኛ ትምህርት የጥራት ችግሮቹ በመሠረታዊነት ፖለቲካዊና መዋቅራዊ ይዘት አላቸው›› የትምህርት ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት የጥራትና ሥልጠና ዳይሬክተር በላይ ሐጎስ (ዶ/ር)

ቀን:

ከድኅረ ምረቃ ትምህርት መርሐ ግብሮች መስፋፋት ጋር ተያይዞ ጎልቶ እየታየ ያለው የትምህርት ጥራት መጓደል በትምህርቱ ላይ አደጋ ስለመደቀኑ ይነገራል፡፡ ለችግሩ ምክንያቶች ናቸው የተባሉ በርካታ አስተያየት ይቀርባሉ፡፡

 የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ ባዘጋጀው መድረክ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት በላይ (ዶ/ር)፣ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራሞች መስፋፋት፣ የሥልጠና ጥራት መጓደልና የመግቢያ መሥፈርቶች ከፍ ማለት በዘርፉ ያሳደረውን ተፅዕኖ ጠቁመዋል፡፡

‹‹የከፍተኛ ትምህርት የጥራት ችግሮቹ በመሠረታዊነት ፖለቲካዊና መዋቅራዊ ይዘት አላቸው፤›› ያሉት በላይ (ዶ/ር)፣ ከበርካታ አካባቢዎች የዩኒቨርሲቲ ይከፈትልን ጥያቄዎች መብዛትና ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ጥረት በማድረግ፣ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎችን መክፈትና ከነባር ዩኒቨርሲቲዎች የሙያ መስኮቹና የተዘጋጀበት ሥርዓተ ትምህርት ወይም የትምህርት ሥርዓት መቅዳት ለትምህርት ጥራቱ መቀነስ እንደ ምክንያት የተጠቀሱ ናቸው፡፡

ከአደረጃጀት አኳያ ሲታዩ ተፈጥሯዊ ዕድገቱ ያልጠበቀ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ማደራጀትና ማስፋፋት እንደሚታይባቸው የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ ለምሳሌ ምንም ተሞክሮ ሳይኖረው በቂና ብቁ የሰው ኃይል፣ እንዲሁም ቁሳቁሶችን ሳይሟሉለት አንድን ተቋም ዩኒቨርሲቲ ብሎ መሰየምና በዚሁ ተቋም አሠልጥኖ ለማስመረቅ አብዝቶ መሻትና መጣደፍ የሚታዩ ችግሮች ናቸው፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መስፋፋት ተመሳሳይ የሥልጠና መስክ እንዲፈጠር ማስቻል ብቻ ሳይሆን፣ አንድ ዓይነት ይዘትና ስያሜ ያላቸው መሆን የፕሮግራም ድግግሞሽ በትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖዎች ናቸው፡፡

ያልተጠኑ የ70 እና 30 ውሳኔዎችን ምጣኔ በመከተል የከፍተኛ ትምህርት ሥልጠናዎች ማካሄድ፣ ማለትም 70 በመቶ የሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ 30 በመቶ ደግሞ የማኅበራዊ ሳይንስና ቢዝነስ ሙያዎች ተማሪዎችን እንዲቀበሉ የተወሰነው ውሳኔ፣ ገበያውን ማዕከል ያላደረገ ተመራቂዎች እንዲኖሩና የመቀጠርም ሆነ ሥራ የመፍጠር ብቃት የሌላቸው ተመራቂዎች ከዓመት ወደ ዓመት ቁጥራቸው እንዲበዛ፣ እንዲሁም የሥራ አጥ ቁጥር እንዲጨምር አድርጎታል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ተፈላጊው የሙያ ብቃት ያላቸው መምህራን እጥረት መኖር የማለፊያ መቁረጫ ነጥብ ከፍ ማለትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ለከፍተኛ ትምህርት ጥራት መጓደልና ተማሪዎች የሚፈለገውን ውጤት እንዳያስመዘግቡ ያደረጉ ምክንያቶች ናቸው፡፡

የታዩ ችግሮችን ይፈታሉ ያሏቸውን ነጥቦች በላይ (ዶ/ር) ያስቀመጡ ሲሆን፣ የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት ሊመለከ~ቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራሞች የተከፈቱበትና እያሠለጠኑ ያሉበት ሁኔታ ደረጃቸውን የጠበቁ ስለመሆናቸው ፍተሻ ሊደረግ ይገባል የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ በሌላ በኩል ለሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች አንድ ዓይነት የመግቢያ መሥፈርት ማስቀመጥ ሳይሆን፣ እያንዳንዳቸው የራሳቸውን የመግቢያ መሥፈርት እንዲኖራቸው መሥራት ያስፈልጋል፡፡

በአንድ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ የተለያዩ የትምህርት መስኮች እንደ ልዩ ባህሪያቸው የተማሪ ቅበላ መሥፈርቶቻቸው ማዘጋጀትና ማፅደቅ ይኖርባቸዋል፡፡ የጂኤቲ ፈተና ከባድ ሆኖ የሚዘጋጅ በመሆኑና ፈተናው የመተንበይ ብቃቱ በጣም ጠንካራ ባለመሆኑ የማለፊያ መቁረጫ ነጥቡ አሁን ካለው 80 በመቶ ትንሽ ዝቅ በማለት፣ ከ50 እስከ 60 በመቶ ሆኖ ቢከለስ የጥራት ችግር እንደማያስከትል ሐሳባቸውን አስቀምጠዋል፡፡

የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ቁጥር በፍጥነት እያደገ መሆኑ በዚሁ ጥናት ላይ የተመለከተ ሲሆን፣ በ1992 ዓ.ም. የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች ብዛት 66,763 የነበረው በ2010 ዓ.ም. ወደ 686,668 ከፍ ማለቱ፣ የከፍተኛ ትምህርት መስፋፋትን ያመለከታል፡፡ በሌላ በኩል በ1992 ዓ.ም. የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ቁጥር 959 እና የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ብዛት 10 ብቻ እንደነበሩ በጥናቱ የታየ ሲሆን፣ በ2010 ዓ.ም. ለሁለተኛ ዲግሪ የተመዘገቡ ተማሪዎች 68,976 ሲሆን ለሦስተኛ ዲግሪ የተመዘገቡ ደግሞ 3,369 ነበሩ፡፡

በ2015 ዓ.ም. ለሁለተኛ ዲግሪ የተመዘገቡ ተማሪዎች 61,162 ሲሆን፣ ለሦስተኛ ዲግሪ የተመዘገቡ ደግሞ 5,212 ናቸው የሚሉት በላይ (ዶ/ር)፣ የከፍተኛ ትምህርት መስፋፋት ያመጣውን ውጤት ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

የከፍተኛ ትምህርት መስፋፋት ማኅበራዊና ፍትሐዊነትን በመጠኑ እንዲሻሻል አስተዋጽኦ ማድረጉን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ሴት ተማሪዎች በቅድመ ምረቃና በከፍተኛ ትምህርት ቁጥራቸው እንዲጨምር አድርጓል፡፡ ወደ 10 በመቶ ከፍ እንዲልም ሆኗል፡፡

ይህ ማለት በ1992 ዓ.ም. ከነበረው 22 በመቶ በ2010 ወደ 34 በመቶ ከፍ እንዲል ማድረጉን አመላካች ነው፡፡ ሆኖም የሴት ተማሪዎች ቁጥር 50 በመቶ እስካልሆነ ድረስ፣ አሁንም ምጣኔው አነስተኛ እንደሆነ የሚያስረዱት በላይ (ዶ/ር)፣ እስከ በ2015 ዓ.ም. ባለው መረጃ መሠረት በድኅረ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራሞች የተመዘገቡ ሴት ተማሪዎች ቁጥር በጣም አነስተኛ መሆኑን በጥናታቸው ጠቁመዋል፡፡

በ2015 ዓ.ም ለሁለተኛ ዲግሪ 18 በመቶና ለሦስተኛ ዲግሪ ደግሞ 10 በመቶ ብቻ ተመዝገበዋል፡፡ ይህ ፍትሐዊነቱ አጠያያቂ ያደርገዋል የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ በ2015 ዓ.ም. በመጀመሪያ ዲግሪም ቢሆን የሴት ተማሪዎች ቁጥር 31 በመቶ ብቻ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...