Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርውዝግብ የማያጣው ፖለቲካችንና የመልማት ፍላጎት ልዩነቶቻችን

ውዝግብ የማያጣው ፖለቲካችንና የመልማት ፍላጎት ልዩነቶቻችን

ቀን:

በአስማማው ጌቱ

የቀድሞው ኢሕአዴግ በረዥሙ የአገዛዝ ዘመኑ የሚከተለው አንድ ማስፈራሪያ ብቻ ሳይሆን፣ ‹‹የድህነት ጎርፍ ሊጠርገን ነው›› የሚል የቁጭት መቀስቀሻ አገላለጽ  ነበረው፡፡ በአብዛኛው ከሩቅ ምሥራቆቹ የፈጣን ዕድገት ተምሳሌቶች (እነ ቻይና) የተወሰደው ብሂል ድህነትና ድንቁርናን ፈጥኖ ማምለጥ ካልተቻለ፣ አገርን በናዳ የመጨፍለቅ ሥጋት እንደገጠመው ተጓዥ ቆጥሮ የሚተነትን ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ግን በአገራችን የለውጥ ንፋስ በነፈሰበት ወቅት ጊዜ ያለፈበት ትረካ ሆኗል፡፡ በአገራችን ከሞላ ጎደል አብዛኛውን ሕዝብ አስማምቶ የነበረ ለውጥ ከተጀማመረ ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ምንም እንኳን እየተደናቀፈና በሌላ በኩል የተናጠል የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች በፈጠሩት ችግር ሒደቱ ፈጥኖ ባይሰምርም፣ በመጀመርያዎቹ ጊዜያት የነበረው አገራዊ መነሳሳት ተስፋ ሰጪ ነበር፡፡

በተጠቀሱት ዓመታት በተለይ በምጣኔ ሀብትና ሰላም ረገድ እስካሁንም የሰከነና  ወደ ዘላቂ ዕድገት የሚወስድ ጥርጊያ ጎዳና ገና እንዳልተጀመረ ነው ብዙዎች የሚስማሙበት፡፡ ይህ ደግሞ ከሦስት ዓመት በፊት በተካሄደው አገራዊ ምርጫ ለአምስት ዓመታት መንግሥታዊ ሥልጣንን በኮንትራት ለወሰደው ገዥ ፓርቲ (ብልፅግና) ኪሳራ ሲሆን፣ እንደ አገርም ጉዳቱ የሚያመዝን ክስተት ነው፡፡ ታዲያ መቼ ነው ከመጠራጠርና ከፖለቲካ ሴራ፣ ብሎም ሽኩቻና መባላት ወጥተን በእግራችን መቆም የምንጀምረው ብሎ መነሳት ሲገባ በርካታ ችግሮች ተፈጥረዋል፡፡

በእርግጥ ከለውጥ ወዲህ የውስጥ ሽኩቻና መበላላቱ ለምን ተጋግሞ ቀጠለ ለሚለው ጥያቄ የራሱ ምላሽ ቢኖረውም፣ እስካሁን ድረስ በመንግሥት መዋቅር ውስጥም ሆነ ውጭ ሆነው ‹‹ጭር ሲል አልወድም›› የሚያዜሙ፣ በተፎካካሪው ሜዳ፣ በአክቲቪዝምና ጋዜጠኝነት ስም ያሉ ጽንፈኞች (አሁን አሁን ደግሞ የእምነት ሥፍራ ፖለቲከኞች) ደግሞ ሁሉንም ክስተቶችና ተግባራት ወደ ፖለቲካ ንትርክ በመውሰድ ቀልብ መሥፈሪያ እያደረጉ፣ አገር ከችግር እንዳትወጣ እየተራኮቱ ነው፡፡

በዋናነት እነዚህ ኃይሎች ‹‹ችግሮቻችን የሚፈቱት በጦርነት ብቻ ነው›› ብለው አገራዊ ምስቅልቅል ከፈጠሩ በኋላ እንኳን፣ ምን ያህል ዋጋ እንደተከፈለ የማይረዳ ዜጋ የለም፡፡ ‹‹ችግሩ በጦርነት ብቻ ሳይሆን፣ በዲፕሎማሲና በምክክር ፖለቲካም መፈታት አለበት›› ተብሎ በሁሉም መስክ ለመንቀሳቀስ ሲሞከርም ሴራ መጎንጎኑ አልቆመም፡፡ የሒደቱ ግልጽነት መጓደል ወይም የሽኩቻና የእሰጥ አገባ አካሄዱ መባባስ መታረም አለመጀመሩ ነው አገር ወዳዱን ሁሉ እያሳዘነ የሚገኘው፡፡

ለእዚህ ችግር መቀጠልና ፈጥኖ ወደ ዕድገት ጉዞ አለመመለሳችን ምክንያቱ  ከአበቃቀሉ የተበላሸው የአገረ መንግሥት ግንባታ ጉዞው የራሱን አሉታዊ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ከሁሉ በላይ ሁሉንም ተግባራትና ሁነቶች በእርስ በርስ ሽኩቻና ሕዝብንም ተዋናይ በሚያደርግ የማንነት ፍጥጫ የመመንዘር ልማዳችን ገና አለመታረሙ ጉዞውን እያጓተተው ይገኛል፡፡ የኅብረ ብሔራዊ አገራዊ አንድነት ማነፁ የትውልድ ተልዕኮም እንደሚታሰበው ቀላል አልሆነም፡፡

በሌላ በኩል በውጭ ኃይሎችና የአገር ባላንጣዎቻችን ገፋፊነት ጭምር በሕዝቦች መካከል መጠራጠርና አለመተማመን ለመፍጠር የሚፈጸመው ሴራ ይበልጥ መካረሩ አልተገታም (የግለሰብን ፀብ ሳይቀር ወደ ብሔርና የእምነት ተከታዮች የወል ግጭት አስመስሎ ለማባላት የሚሞክሩ ፅንፈኞች የበዙበት አገር ሆነናል)፡፡ የዚህ አካሄድ  ማብቂያውስ መቼ ይሆን ነው መባል ያለበት፡፡ እስከ መቼስ ከዋናው የለውጥ መንገዳችን ያናጥበናል ብሎ መጨነቅ ግድ ይላል፡፡

ሌላው ቀርቶ ከፖለቲካዊ ውዝግብ ጋር ብዙም የማይገናኙትና የጋራ ሀብታችን  የምንላቸው የሃይማኖት ጉዳዮቻችን የብሽሽቅና የፀብ መንስዔነታቸው እንደ አዲስ መጠንሰሱ ማንንም ሊያስቆጭ ይገባል፡፡ መስቀል፣ ጥምቀት፣ ጁምዓ፣ ኢሬቻ፣ ፊቼ ጨምበላላን… በመሰሉ እሴቶቻችን በጋራ እየደመቅንና ራሳችንን ለሌላው ዓለም በመሸጥ የዕድገት አካል ማድረግ ሲገባ፣ ካለፈው ጊዜ በባሰ ደረጃ ለአሉባልታና ለስስታም ፖለቲካ  አገር ስትጋለጥ ዝም ማለት አይገባም፡፡

እናም እባካችሁ እንደ አገር የሴራ ጉንጎናውና እሽቅድምድሙ ይቁምና ፊታችን ወደ ልማት ይዙር የዛሬው ሂሳዊ ጽሑፌ ምክር ነው፡፡ መንግሥትና አገር  እየመራ ያለው ብልፅግናስ ቢሆን መቼ ነው የምልዓተ ሕዝቡን ትኩረት ወደ ዘላቂ መረጋጋት የሚወስደው የሚለውን ተጠይቅ ማንሳትም ያስፈልጋል፡፡ ከሁሉ በላይ  ፀረ አገር የሆኑ ኃይሎችን ማስታገስ እንደ ምን ይቻላል? ብሎ ማየትም የሁሉም ግዴታ ሊሆን ግድ ይላል፡፡ ከሆደ ሰፊነቱና መነጋገሩ ባሻገር፡፡

በመሠረቱ የመንግሥት ዋነኛው ኃላፊነት የአገር ሴረኞችን እያጋለጠ፣ የውጭ ባላንጣዎችን እየተፋለመ አገርን ማረጋጋት ብቻ አይደለም፡፡ የአገር ሰላምና ደኅንነትን ማረጋገጥ፣ የሕዝቦቸን አብሮነትና መተባበር መገንባት፣ ብሎም የአገረ መንግሥትን ሉዓላዊነትና ነፃነት ዕውን ማድረግ ነው፡፡ እነዚህ መሠረታዊና ወሳኝ ተግባራት ናቸው፡፡ ሲቀጥልም ልማትና ብልፅግናን ማረጋገጥ ሊባል ይችላል፡፡ ይህን ዕውን ለማድረግ ደግሞ በተቀናጀ መንገድ ከላይ እስከ ታች የወረደ አቅጣጫ፣ እንደ አካባቢው ተፈጻሚ ሊሆን የሚችል ዕቅድ በሕዝቡ ውስጥ በዝርዝር መታወቅ አለበት፡፡ ለተግባራዊነቱም ሁሉም መረባረብ የሚችለው በዚህ መንገድ ነው፡፡

ማን ምን መሥራት እንዳለበት፣ የመንግሥት አካላት ብቻ ሳይሆኑ የባለሀብቱና የሕዝቡ ሚናም በግልጽ ታውቆ ለጋራ ውጤት መረባረብ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ዕውን ማድረግ፣ የዕቅድ አፈጻጸምን በየደረጃው መገምገምና ፈጣን ዕርምቶችን መውሰድ ወደ ውጤት የሚወስድ አካሄድ ነው፡፡ ይህ የተለመደ መንግሥታዊና ሕዝባዊ መስተጋብር ተዘንግቶ ገጠር የለ ከተማ፣ ዳር የለ መሀል፣ ደጋ የለ ቆላ በሴረኞችና አተራማሾች የሚፈለፈልን የፖለቲካ አጀንዳ ሲያመነዥጉ መዋልና ማደር ግን ማንንም ሊጠቅም አይችልም፡፡ በፍፁም!!

ሌላው ቀርቶ የአገራችን ምጣኔ ሀብት ቁልፍ የሆነውና ሰፊውን ሕዝብ የተሸከመው የግብርናው ዘርፍ የሙሉ ትኩረታችን ማጠንጠኛ መሆን አለበት፡፡ ስለሆነም የሚመለከታቸው የሴክተሩ አካላት ግምገማና ግንባታ ሊያተኩር የሚገባው በዋና ዋና ሰብሎች፣ በተፋሰስና በመስኖ ልማት… በእንሰሳት ሀብት ልማት… በአፈርና በውኃ ጥበቃ… በማዳበርያ አጠቃቀም… ላይ መሆን አለበት፡፡

ገበያ ተኮር በሆኑ የግብርና ውጤቶችና በውጭ ምንዛሪ ዕድገት፣ የሰብል በሽታና ተባይ ቁጥጥር… የግብርና ቴክኖሎጂ ልማት… በዘርፉ ያለውን የሰው ኃይል ልማት፣ የወጣቶችና የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት… እያጠናከሩ ለመሄድም የድህነትን ናዳ ማስታወስና መላውን ሕዝብ ዳግም ማነቃነቅ ለነገ መባል የለበትም፡፡ በምንገኝበት ወቅት ግን የአሠራርና የአደረጃጀት ብቃት… በዘርፉ የግል ኢንቨስተሮች ተነሳሽነትና ተሳትፎ… የአየር ለውጥ ጎጂ ተፅዕኖን መቋቋም፣ ወዘተ. ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት መደረግ ያለበት ርብርብ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ እንኳን አፍ ሞልቶ የሚናገር የለም፡፡ አልያም የፌዴራሉ መንግሥትና ክልሎች በዘርፉ እየሠሩ ያሉትን በአግባቡ ለሕዝብ እያሳወቁ አይደለም፡፡

ይልቁንም በእርስ በርስ ግጭቶች፣ በጦርነትና በድርቅ ምክንያት ስለተጎዱ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ዕርዳታ፣ ስለመሬት ካሳና ዘመቻ ብቻ በማውራት ላይ ነን፡፡ ይህ ድህነትን የማጥቃት ሳይሆን የመከላከል አካሄድም ዘላቂ መፍትሔ እንደሌለው የመቶ ዓመት አገራዊ ተሞክሯችን፣ ከእኛ አልፎ ሌሎችንም ያስተምራል፡፡ እውነት ለመናገር ከለውጥ በፊትም ቢሆን አገራችን ከጀማመረቻቸው በጎ ተግባራት አኳያ ከኢንዱስትሪና ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የሚጠበቀው ውጤትም ከፍተኛ በሆነ ነበር፡፡ ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ግን እንደ አገር የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ከማስፋፋት ይልቅ በመንግሥት፣ በአገር ውስጥና በውጭ ባለሀብቶች የተገነቡ ኢንዱስትሪዎችን በእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት ማውደም ነው የቀለለው፡፡

ይህን የኋሊት መንገድ ፈጥኖ በማስተካከል መቀልበስ ካልተቻለ ግን ከችግር ለመውጣት አዳጋች መሆኑ አይቀርም፡፡ እውነት ለመናገር እስካሁንም ድረስ ሰላምና መረጋጋት በማጣታቸው፣ የሕዝቡ ባለቤትነት ስሜት በመዳከሙና በመልካም አስተዳደር ዕጦት ባለሀብቱ ትኩረት የነፈጋቸው ስንት አካባቢዎች አሉ፡፡ ይህን አለመቀየር ነው የትውልዱ ውርደት፡፡

እንደ አገር ለዜጎች ተጨማሪ የሥራ ዕድል በአብዛኛው የሚገኘው ከንትርክና ከሽኩቻ ፖለቲካ ሳይሆን፣ ከማኑፋክቸሪንግና ከኮንስትራክሽን ዘርፍ ዓይነቶቹ መስኮች ነው፡፡ ወጣቱን በአነስተኛና ጥቃቅን የማሳተፉ ሒደት ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የግል ኢንቨስተሮች ለወጣቶች የሥራ ዕድል በሚያስገኙ ፕሮጀክቶች ላይ በብዛት እንዲሳተፉ ማድረግ ግድ የሚለውም ለዚሁ ነው፡፡ እናም ግልጽ የማበረታቻ ፓኬጅ ነድፎ ለላቀ ውጤትና ለተሰናሰለ የጋራ ተጠቃሚነት መረባረብ ከመንግሥት የሚጠበቅ ይሆናል፡፡

ለመሆኑ አሁን በምንገኝበት ጊዜ እንደ አገር ለማኑፋክቸሪንግ ዕድገት ወሳኝ የሆኑ ግብዓቶችን የማግኘት አገራዊ አቅማችን ምን ደረጃ ላይ ነው? የማኑፋክቸሪንግ ሴክተሩ ማነቆዎች ምንድናቸው? መፍትሔያቸውስ? አሁን ባለው አካሄድ የአገራችን ኢኮኖሚ ኢንዱስትሪ መርህ ለመሆን የተቀመጠ ጊዜስ አለን? ብሎ ማሰላሰልና ሕዝብን ባሳተፈ መንገድ ፈጣን ዕርምጃ መውሰድ የግድ መሆን አለበት፡፡

በዚሁ ዘርፍ ያሉ የትምህርትና የምርምር ተቋሞቻችን፣ የሰው ኃይላችን የወደቀበትን ሙያዊና አገራዊ ኃላፊነት እየተወ ወደ ማኅበራዊ ድረ ገጽ ሽኩቻና የንትርክ ፖለቲካ እየገባ ያለው ለምንድነው ብሎ ጥልቅ ግምገማ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እውነት ለመናገር አሁን ያለው የለውጥ ኃይል ጊዜ ወስዶ ሙሉ ትኩረቱን ለእንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ትኩረት መስጠት ካልቻለ፣ ፈታኙን ጊዜ ማለፍ ከቶ የሚቻል አይሆንም፡፡ አሁን አሁን ደግሞ እንደ አለፈው ጊዜ ሁሉ መንግሥት የአገሪቱን የዕድገትና የልማት ዕቅድ ጠልፈው ለመጣል የሚገዳደሩትን የሙስና፣ የመልካም አስተዳደርና የኢፍትሐዊነት ነቀርሳዎች ከሥር ከመሠረታቸው መንግሎ ለመጣል መነሳት አለበት፡፡ ከትናንቱ ባለመማር ዛሬ ያለውን መንግሥታዊ መዋቅር ከተጠያቂነትና ግልጽነት መርህ ውጪ ማድረግ፣ መዋቅሩን ከአጠቃላይ ሥርዓቱና አንዳንዴም ከማንነት ጋር እያወዳዱ እንዲወቀስና እንዲታረም አለማድረግም ተያይዞ መውደቅን ያስከትላል፡፡ በፈተና ላይ ፈተና መከተሉም አይቀርም፡፡

ስለሆነም መንግሥታዊ መልካም አስተዳደርና ውጤታማነትን ለመዘርጋት ከላይ አስከ ታች የሕዝቡን ሰፊና ንቁ ተሳትፎ ማነቃቃት ግድ የሚል ይሆናል፡፡ ሕዝቡም በማንኛውም የመልካም አስተዳደርና የልማት ሒደት ውስጥ ሁሉ ከመንግሥት ጎን በገንቢነት ለመቆም መነሳት ይኖርበታል፡፡ በተጀመረው መንገድ ብቻ ሳይሆን፣ ከዚህም በላይ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ማጠናከር የሚቻለውም ከመልካም አስተዳደርና መንግሥታዊ ግልጽነት ጀምሮ፣ የሕዝቡን ተሳትፎ ማስቀጠል ሲቻል በመሆኑ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡

እውነት ለመናገር በየመንግሥት ተቋማት ውስጥ በመልካም አስተዳደር ችግርና በኪራይ ሰብሳቢነት ከዚህ ቀደም የተጋለጡ አሠራሮችና ሹመኞች በስም ለውጥ ብቻ እንደቀጠሉ ናቸው፡፡ በእርግጥ አንዳንዱ መነሳትና መቀየር ያለበት ግለሰብ ተቀይሮ ሊሆን ይችላል፡፡ በሕግ መጠየቅ ያለበትም አገርን ይዞ ወደ ጦርነት ቢገባም በሕዝቡ መገለል ገጥሞታል፡፡ ግን መንግሥታዊ የለውጥ ማዕቀፉ ዘላቂና የተረጋጋ አገረ መንግሥት ለመገንባት የመጭውን ዘመን የሕግ የበላይነትና የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ለድርድር መተው የለበትም፡፡ ከግለሰቦች በላይ አድርጎ መመልከትም ግድ ይለዋል፡፡

ትናንትም ሆነ ዛሬ የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግርን እጅግ ከሚያባብሱት ምክንያቶች በዋናነት የሚጠቀሰው ደግሞ የሥነ ምግባር መጓደል ብቻ ሳይሆን፣ የትምህርት ደረጃ ዝቅተኛነትና የብቃት ማነስም ነው፡፡ በተለያዩ መንግሥታዊና ሕዝባዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለተመደቡበት ኃላፊነት ወይም ፈጻሚነት ደረጃ የሚመጥን ትምህርትና ብቃት የሌላቸው ሰዎች በየቦታው ይበዛሉ፡፡ ሥራቸውን አያውቁትም፡፡ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የቅንነት መጓደሉ ሲታከልበት ደግሞ ሕዝብን እንዴት እንደሚያማርር የሚስተው የለም፡፡ መንግሥት የሚጠበቅበት በሴራ መባላቱን ተወት አድርጎ ይህን መቀየር በሆነ ነበር፡፡

በእርግጥ አንዳንድ የለውጥ አመራሮችና ተከታዮቻቸው በአዲስ አበባ ደረጃ መልካም አስተዳደርን ለማስፋት ያሉትን ችግሮች ከታች እስከ ላይ ድረስ አብጠርጥረው ፈትሸዋል፡፡ የመሬት ይዞታና የባለቤትነት ጉዳዮች ታይተዋል፣ በዕቅድ ተይዘዋል፣ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም አብዛኞቹን ችግሮች ለማቃለል የሚያስችሉ ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ እየተመለሱ የሚያገረሹ ችግሮችን ማስቀረት ግን እየተቻለ አይደለም፡፡ እናም መዋቅራዊና ዘላቂ የማሻሻያ ዕርምጃዎችን ከመውሰድ ውጪ አማራጭ የጠፋበት ጊዜ ላይ መገኘታችን ለመንግሥት ሊገለጥለት ገድ ይላል፡፡

ከዚህ ቀደም የከተማችን አስተዳደር የሥራ አጥነትን ችግሮች ለመፍታት፣ የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችን በማሳደግ አዳዲስ የሥራ ፈጠራ ዕድሎችን ለማስገኘት የተከናወኑ ሥራዎች ነበሩ፡፡ አሁን ግን ያለ ጥርጥር ተቀዛቅዘዋል፣ አልያም ትኩረት ተነፍጓቸዋል፡፡ ወጣቱን ኃይል በተቻለ መጠን ወደ ልማትና የሥራ ፈጠራ ፊቱን እንዲያዞር አለማድረግ ስለባንዲራ፣ አልፎም የሚያወዛግብ ሐውልት ቀረፃ ከመክተቱ ባሻገር በየጥጋጥጉ ሱሰኝነት፣ ሥራ ጠልነትና ውንብድና እንዲበረታ ማድረጉ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ይህን መቀየር ነው የመንግሥት ዋነኛ ኃላፊነት መሆን ያለበት፡፡

ነገሩን አጥበነው እንደ አዲስ አበባ ስናየው የከተማችን ሌላው ችግር ማኅበራዊ ህፀፆቻችን እያደር በቁጥር እያደጉና በዓይነት እየረቀቁ የሚሄዱ መሆናቸው ነው፡፡ አንዱ ህፀፃችን ሌብነት (ስርቆት) ነው፡፡ የከተማዋ ሕዝብ እጅግ በጣም ተቸግሯል፡፡ ሌብነት በዝቷል (መኪና እየሰረቁ አርደው የሚሸጡ ወንበዴዎች ከመኖራቸው አልፎ፣ እንደ አብነት፣ ጭድተራ፣ ልደታና ቄራ በመሰሉ ሠፈሮች ቁልፍ እንቀርፃለን ብለው አስገድደው ገንዘብ የሚቀሙ ቀጣፊዎች በጠራራ ፀሐይ የሚንቀሳቀሱበት ጊዜና አገር ተፈጥሯል)፡፡

በእርግጥ እንደ ዜጋ ‹‹ሌብነትና ውንብድና ይወገድልን›› ስንል መንግሥት ለእያንዳንዱ ዜጋ ወይም ለእያንዳንዱ ኪስ አውላቂ ፖሊስ ይመድብልን ማለታችን አይደለም፡፡ በዩኒፎርምም ሆነ በነጭ ለባሽ ጥበቃ ቢደረግ ሌብነት ማኅበራዊ ህፀፅ ነው፡፡ በቀላሉ ሊወገድ አይችልም፡፡ የመጀመርያው መፍትሔ ሁሉም ሰው ራሱን እንዲጠብቅና አንዱ ሌላውን እንዲጠብቅ፣ ማለትም ሌባው መጥቶ የአንዱን ዜጋ ኪስ ሲፈለቅቅ ከኋላው ያለው ዜጋ መታገል እንዳለበት እርስ በርሳችን ካልተደጋገፍን ተያይዘን የምንወድቅ መሆናችን ግንዛቤ ማስጨበጥ መቻል ነው፡፡ ይህን መቀየር በዋናነት የሕዝብም ድርሻ ነው፡፡

እዚህ ላይ የማይካደው እውነት እንዲህ ያሉ ወንጀሎች በእኛ አገር ብቻ የሚከሰቱ አይደለም፡፡ ግን አገሮች ችግሩን የሚያቃልሉበት ዋነኛው መንገድ ትውልዱን በተቻለ መጠን በስፋት ወደ ሥራ ማስገባት ነው፡፡ እንደ አደጋ ግን የአንዳንዱን አገር ሌብነት ሲያዩት የእኛ አገር ሌብነት ‹‹በስንት ጣዕሙ›› ያሰኛል፡፡ ሥርዓት ለማስያዝ ሊታቀድበትና ሊገመገም ይገባል ለማለት ያህል እንጂ፣ ከሌሎች አገሮች ሌብነቶች አንፃር ሲታይ እንዲያውም የእኛው ይኼን ያህል ደረት የሚያስደቃ አይደለም፡፡

በአጠቃላይ አገራችን ያጣችውን ሰላምና ደኅንነት የማረጋገጥ ተግባር በተገቢው ማጠናቀቅና ዘላቂ ማድረግ ቀዳሚ ተግባራት ቢሆንም፣ ፋታ የማይሰጡ አንገብጋቢ ጉዳዮችም አሉብን፡፡ እነዚህ ከላይ የጠቃቀስናቸውና መሰል ተግባራት አቅም በፈቀደ መጠን እንዲከናወኑ ደግሞ መደማመጥና አገራዊ መግባባትን ማስቀደም ብቻ ሳይሆን ከአሉባልታና መበላላት፣ ከሴራና  ከፖለቲካ መጠላለፍ ነገ ዛሬ ሳንል መውጣት ያስፈልገናል፡፡ ግድም ነው!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...