Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣ ርኅራኄ፣ መልካምነትና ደግነት የሚሉት የሰውነት መገለጫዎችን የሚያሳይ ነው፡፡ ሰውነት ሲÕደል አዛውንቶች ያለ ጧሪ ቀባሪ ይቀራሉ፣ ሕፃናት ያለ አሳዳጊ ሜዳ ላይ ይወድቃሉ፣ ወጣቶችም እጃቸውን ለልመና ይዘረጋሉ፡፡ አረጋውያንን ሕፃናትንና ሌሎች ተጎጂ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ከወደቁበት በማንሳት፣ የዕለት ጉርሳቸውንና የዓመት ልብሳቸውን በመሸፈን መጠለያንና ሌሎች የጤናና የትምህርት ወጪ በማሟላት በጋራ ተሰባስበው እንዲኖሩ የሚሠሩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች አሉ፡፡ ዋና መቀመጫው ጅማ የሆነው ‹‹ሰው ለሰው የበጎ አድራጎት ድርጅት›› በዚሁ ተግባር ከተሰማሩት አንዱ ነው፡፡ ሰው ለሰው በጎ አድራጎት ድርጅት ከልጅነት ጀምሮ በተጠነሰሰ ሕልም የተመሠረተ ነው፡፡ ድርጅቱ ጅማ ከተማ ውስጥ ስላለው ሥራ የድርጅቱን መሥራች ወ/ሮ ዘመናይ አስፋውን፣ አበበ ፍቅር አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ሰው ለሰው በጎ አድራጎት ድርጅት መቼ ተመሠረተ? የድርጅቱን ዓላማ ቢያስረዱን?

ወ/ሮ ዘመናይ፡- ሰው ለሰው በጎ አድራጎት ድርጅት በ2010 ዓ.ም ነበር የተቋቋመው፡፡ ላለፉት ስድስት ዓመታትም በተለይ አረጋውያንና ሕፃናትን ከወደቁበት በማንሳት ሲረዳ ቆይቷል፡፡ የሰው ልጅ በምድር ላይ ካሉ ፍጥረቶች ሁሉ የከበረ ነው፡፡ ከሰው ልጅ በላይ ቅድሚያ ሊሰጠውና ሊረዳ የሚችል ፍጥረት የለም፡፡ በመሆኑም ድርጅታችን ሰውን ከሰው ሳይለይ የተቸገሩትን ሁሉ ከጎዳና፣ ከሆስፒታልና ከተለያዩ አካላት በመቀበል እየተንከባከበ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ከተቋቋመ ጀምሮ ምን ያህል ሰዎችን ከወደቁበት አንስቷል?

ወ/ሮ ዘመናይ፡- ድርጅታችን እስካሁን በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ቢያልፍም፣ 340 አረጋውያንና ሕፃናትን ተቀብሎ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 126 የሚሆኑት ተጥለው የተገኙ ሕፃናት ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ በጎ አድራጎት ሥራ ለመግባት በዋናነት ምን ነበር ያነሳሳዎት?

ወ/ሮ ዘበናይ፡- ገና ተማሪ እያለሁ የተራቡ ሰዎችን፣ የሚለምኑ ሕፃናትንና ተወልደው የተጣሉ ጨቅላ ልጆች ሳይ በጣም አዝን ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሕፃናትና አረጋውያንን ለመንከባከብ ትልቅ ህልም አደረብኝ፡፡ ፈጣሪ የውስጤን ዓይቶ ረዳኝ፡፡ ሥራውንም ስጀምር ከቤተሰቦቼ በተሰጠኝ በራሴ መኖሪያ ቤት ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ማዕከሉ የሚመጡ ሕፃናትና  አረጋውያንን እንዴት ነው የምታገኟቸው?

ወ/ሮ ዘበናይ፡- ሕፃናት ተወልደው የተለያዩ ቦታ ሊጣሉ ይቻላሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ሆስፒታል ብዙ ሕፃናት ተጥለው የሚገኙበት ነው፡፡ ሊያሳክሙ በሚሄዱበት ወቅት ከአቅማቸው በላይ ሲሆንባቸው ሌላ ሰው በማስያዝ መጣሁ ብለው ጥለው የሚሄዱ እናቶች ብዙ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል የተዘጋ ቤት ውስጥ ተከራይተው ጥለው የሚወጡ እናቶች ያጋጥማሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ ሕፃናት ፖሊስ ተረክቦ የተጣለበትን ሰዓት፣ ዕድሜና ሌሎች መረጃዎችን በመመዝገብ ለድርጅታችን ያስረክባል፡፡  

ሪፖርተር፡- በመርጃ ማዕከሉ ውስጥ ያሉ ሰዎች በሚችሉት የሥራ ዘርፍ ወይም ሙያ ተሠማርተው ሥራ እንዲሠሩ ከማድረግ አንፃር ምን ትሠራላችሁ?

ወ/ሮ ዘመናይ፡- አንዳንዶቹ ሲመጡ ዓይናቸው ሙሉ በሙሉ ማየት አይችልም ነበር፡፡ እነዚህን የዓይን ግርዶሽ የነበረባቸውን ሰዎች በሕክምና እንዲታገዙ በማድረግ በደንብ ማየት ሲችሉ ከሚቀመጡ በሚል በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በማሠልጠን ወደ ሥራ እንዲሠማሩ እናደርጋለን፡፡ ለምሳሌ ዘንቢል፣ ሰሌንና ሻማ የሚያመርቱ ወጣቶች አሉ፡፡ በፈሳሽ ሳሙና ዙሪያ ሥልጠና ወስደው የሚሠሩም አሉ፡፡ የሚያመርቱትንም ማዕከሉን ለመጎብኘት የሚመጡ ሰዎች እየገዙ ይሄዳሉ፡፡ ካለፈው ዓመት መጨረሻ ጀምሮ ዳቦ ማምረት ጀምረናል፡፡ ዳቦ በመጋገር ቁርሳቸውን ይጠቀማሉ፣ እንሸጣለንም፡፡ በሥራው የሚሳተፉትና የሚጠቀሙት በማዕከሉ ውስጥ ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በሥራችሁ ፈተና የሆነባችሁ ምንድነው?

ወ/ሮ ዘመናይ፡- የመጀመሪያውና ዋነኛው ችግር ቋሚ በጀት አለመኖር ነው፡፡ የምንንቀሳቀሰው የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አደባባይ መጥተው ከኅብረተሰቡ በሚያሰባስቡት ገንዘብ፣ ከድርጅቱ አባላት በየወሩ ከሚሰባሰብ መዋጮ እንዲሁም በጎ ፈቃደኛ ሰዎች በሚያደርጉት ድጋፍ ነው፡፡ ቋሚ በጀት የለም ማለት ቀለብ የለም ማለት ነው፡፡ ሕፃናትን እየራባቸው ማባበል አይቻልም፡፡ የሕፃናት ወተት ማቅረብ ለእኛ ችግር ነው፡፡ አዋቂዎች ቢርባቸውም በቀን አንድ ጊዜ ተመግበው ሊቆዩ ይችላሉ፡፡ የምንኖረው ኅብረተሰቡ ከእንጀራ ጀምሮ በሚያደርግልን የአስቤዛ ድጋፍ ነው፡፡ በተለይ ለአዕምሮ ሕሙማን የሚሰጠውን መድኃኒት ለማግኘት በጣም ፈታኝ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ አማኑኤል የአዕምሮ ሕሙማን ማዕከል እየመጣሁ ወረፋ ጠብቄ ነው መድኃኒት የምወስደው፡፡ ምክንያቱም መድኃኒታቸው ቆመ ማለት የለፋንበት ዓመት ሁሉ ተበላሸ ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ የአዋቂዎችም ሆነ የሕፃናት መድኃኒት በጣም ፈታኝ ነው፡፡ የትራንስፖርት ዕጦት ሌላው ፈተና ነው፡፡ መንገድ ላይ የወደቁ አረጋውያንን ለማምጣት ተሽከርካሪ ለምነን ወይም ተከራይተን ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የብዙ መሥሪያ ቤቶች ተሽከርካሪዎች ሳር ለብሰው ቆመው ሳይ በጣም ይቆጨኛል፡፡ ለምንድነው? ስል እጠይቃለሁ፡፡ እኛ ሰው ሲሞትብንና ሌሊት ላይ ሰው ሲታመምብን ወደ ሆስፒታል ለማድረስ በጣም እንቸገራለን፡፡ ሳር ለብሰው የተቀመጡ ተሽከርካሪዎች ለበጎ ዓላማ ቢውሉ ስል እመኛለሁ፡፡ ሌላው ችግራችን የአዋቂዎችና የሕፃናት ዳይፐር በጣም ውድ መሆን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የአዋቂዎች ዳይፐር አንዱ ፍሬ ሰባ ብር የገባ ሲሆን፣ ለሕፃናት በፍሬ 15 እና 20 ብር ነው፡፡ ሌሎችም በርካታ የንፅህና መጠበቂያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ እንደዚያ ካልሆነ ታመው ያገገሙ ሰዎች መልሰው የመታመም ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ አንሶላና ብርድ ልብስም ተመሳሳይ ችግሮች ናቸው፡፡ ሁሉም ሙቀትን የሚፈልጉ በመሆናቸው ጥሩ ልብስና መኝታ ያስፈልጋቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በቀጣይ ምን ለመሥራት አስባችኋል?

ወ/ሮ ዘመናይ፡- የቦታ ችግር ነበረብን፡፡ በቅርቡ የጅማ ከተማ አስተዳደር ችግሩን ቀርፎልናል፡፡ የሚቀረን በተሰጠን ቦታ ግንባታ መጀመር ነው፡፡ በቦታው ላይ እንዴትና በምን አቅም መኖሪያ ቤታቸውን እንገንባ? ገንዘቡ ከየት ነው የሚመጣው? የሚለውን ለማከናወን በእንቅስቃሴ ላይ ነን፡፡ የሁሉም ርብርብና ለጋስነት ተጨምሮበት የመኖሪያ ቤታቸው ተገንብቶ ጥሩ መኝታ ላይ እንዲተኙ ለማድረግ እየሠራን ነው፡፡  ለመሥራት የታቀደው ቤት  አምስት ሺሕ ካሬ ቦታ ላይ የሚያርፍ ሲሆን፣ አረጋውያንና የሕፃናት ለየብቻ እንዲሆን የሚያስችል፣ መዝናኛና መፀዳጃ ቤት ያካተተ  እንዲሁም የዕደ ጥበብ ሥራዎችን የሚሠሩበትና የሕፃናት መጫወቻና ሌሎችንም ያካተተ ነው፡፡  ምንም እንኳን የነበረው ሁኔታ በየወቅቱ ቢለዋወጥም፣ አሁን ባለው ሁኔታ ግንባታው 47 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ ባለሙያዎች ነግረውናል፡፡ ይህንን ለማድረግ ሁሉም ሰው እጁን ይዘረጋ ዘንድ ያለውን ያበረክት ዘንድ የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ለማዘጋጀት በአዲስ አበባና በጅማ ታስቧል፡፡

ሪፖርተር፡- ‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› ይባላል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን ሀብት እያላቸው ለድሆች ማካፈልን አልለመዱም፡፡ ለመሆኑ ለመርዳት ወይም ያለውን ለማካፈል መሥፈርቱ ምንድነው?

ወ/ሮ ዘመናይ፡- መልካም ልቦናና ቅን የሆነ አስተሳሰብ ብቻ ነው የሚፈልገው፡፡ እኔ እንዳየሁት ገንዘብ አይደለም የሚያስፈልገው፡፡ ለምሳሌ እኔ ገንዘብ ያለኝ ሰው አይደለሁም፡፡ ተራ አስተማሪ ነበርኩ፡፡ የወደቁትን የማንሳት ሐሳብ ገና የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ነው የተፀነሰው፡፡ መነሻዬም አንድ ሕፃን መንገድ ላይ ተጥሎ ዓይቼ ነው፡፡ በወቅቱ እንዴት ሰው ልጁን ይጥላል ብዬ በጣም አዝኜ ነበር፡፡ እናት እንዴት ወልዳ ልጇን ትጥላለች? በማለት ወደፊት የወደቁ ልጆች በማሰባሰብ አሳድጋቸዋለሁ ስል አስብ ነበር፡፡ ነገር ግን ሳላስበው ወደ ትዳር ገባሁ፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ በተጋባን በአራተኛ ዓመታችን አራስ እያለሁ ባለቤቴ አረፈ፡፡ በዚህም በጣም ተደናግጬ ወደ ቤተሰቦቼ ተመለስኩና ራሴን አረጋጋሁ፡፡ ራሴን ካረጋጋሁ በኋላ በልጅነቴ አስበውና እመኘው ወደነበረው ዓላማዬ ለመመለስ ወሰንኩ፡፡ ምንም ሳይኖረኝ እችላለሁ፣ አደርጋለሁ በማለት ብቻ ጅማ ከተማ ውስጥ ትንሽ መዋዕለ ሕፃናት ከፈትኩ፡፡ በወቅቱ እየሠራሁ ዕቁብ ገባሁና የመጀመሪያዋ እንደወጣችልኝ ወደ አምስት ክፍል ቤት ቀድሜ ሠራሁ፡፡ መኝታና ሌሎች ዕቃዎችን ማሰባሰብ ጀመርኩ፡፡ በየሆቴሉ እየዞርኩ ፍራሽ ሲቀይሩ በማሰባሰብ ብዙ ፍራሽ አገኘሁ፡፡ የሰው ልጅ በቅንነት ከጀመረ የሚፈጽመው እግዚአብሔር ነው፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው መጨነቅ ሳይሆን መጀመር ብቻ ነው፡፡ ሰውን ለመርዳት የተነሳን ሁሉ እግዚአብሔር ይረዳል፡፡  

ሪፖርተር፡- ከጅምሩ ፈታኝ የሆነብዎት ጉዳይ የቱ ነበር?

ወ/ሮ ዘመናይ፡- መጀመርያ አልጋውን፣ ፍራሹንና ሌሎችን አሟልቼ ምግባቸው ላይ በጣም ተፈትኜ ነበር፡፡ ሰዎችን ከጎዳና እየሰበሰብኩ ካመጣሁ በኋላ ምግብ ማቅረብ በጣም ከባድ ነበር፡፡ መጀመርያ አረጋውያንን ነበር ከወደቁበት ለማንሳት የወጣነው፡፡ ነገር ግን ሕፃናትም ተጥለው ማግኘት ጀመርን፡፡ አብረን ማስገባት ስንጀምር በጣም ብዙ ሕፃናት አምጥተን ወተት ከየት እናምጣ? በጣም ስንቸገር አደባባይ ወጥተን ከሕዝቡ መለመን ግድ ነበር፡፡ ዛሬ እዚህ ላይ ሆኜ ሳወራው ቀላል ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን ከባድ ነገር ነበር፡፡ ያኔ የሰው አመለካከትም እንደ ዛሬው ጥሩ አልነበረም፡፡ አንዳንዶች ለሞራሌ እንኳን ሳይጠነቀቁ የሰው ልጅ ሰብስበሽ እያሉ በጣም ያስቸግሩኝ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ሁሉም ሰው ገብቶት እየመጣ ይጠይቀኛል፡፡ በወቅቱ ማንም ምን ይበል የማስበው የጅብ እራት ስለሚሆኑ ልጆች፣ ውኃ ውስጥ ስለሚጨመሩ ሕፃናት፣ ገደል ስለሚገቡ፣ ዝናብና ፀሐዩ ስለሚፈራረቅባቸው አዛውንቶች ነበር፡፡ በመጨረሻም ልፋቴንና ጥረቴን ሰዎች እየመጡ ሲያዩ ይደሰቱ ነበር፡፡ ወተትና ሌሎች ነገሮችን እየያዙ መምጣት ጀመሩ፣ ምን ላምጣልሽ ማለትም ጀመሩና በሁሉም ርብርብ ዛሬ ላይ ደረሰ፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢኮኖሚ በጣም እየተፈተንን ነው፡፡ ቀደም ሲል በቀን እስከ 12 ሺሕ ብር እናወጣ የነበረው በአሁኑ ወቅት ከእጥፍ በላይ ጨምሯል፡፡ ነገሮች ሁሉ ከአቅም በላይ እየሆኑብን ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ በማኅበራዊ ሚዲያዎች እየቀረብን፣ ልጅ ያልወለዳችሁ ልጅ አልወለድንም ብላችሁ እንዳትጨነቁ፣ ፈጣሪ የፈቀደው ነውና የሚሆነው የሰው ልጅ ነው ብላችሁ ሳታስቡ ወስዳችሁ እንደ ልጃችሁ አሳድጉ፣ እያልኩ እየጠሰሁ ነው፡፡ እንደ ችግር ያየሁት አሳዳጊዎች የሚወስዱት ሴቶችን ለይተው ነው፡፡ ወንዶችን አይፈልጉም፡፡ እኔ ግን ልጅ ያው ልጅ ነው፣ ሳትመርጡ ውሰዱ እያልኩ እመክራለሁ፡፡ ወንዶች ደግሞ ትንሽ ከፍ ካሉ ሰው መለየት ከጀመሩ ከሰው ጋር መልመድ አይችሉም፡፡ ከዚህ ቀደም አንድ ሕፃን ነፍስ ካወቀ በኋላ ሰጥቸው ሌሊቱን ሁሉ ሲያለቅስ አድሮ ተመልሷል፡፡

ሪፖርተር፡- ሕፃናቱ ተወልደው እንዳይጣሉና አረጋውያን ጎዳና ላይ እንዳይወድቁ ምን መሠራት አለበት?

ወ/ሮ ዘመናይ፡- መንግሥት ቅድመ መከላከል ላይ በጣም ሊሠራ ይገባዋል፡፡ የሚወልዱት በዕድሜ በጣም ትንንሽ የሆኑ ሴቶች ልጆች ናቸው፡፡ እነዚህ ልጆች እንዳያረግዙ ብዙ አማራጮች ቢኖሩም፣ ግንዛቤው እንዲኖራቸው መንግሥት የሠራ አይመስለኝም፡፡ ወደ ኅብረተሰቡ ገብቶ መሥራት ይኖርበታል፡፡ በተለይ በክረምት ወቅት ጨቅላ ሕፃናት ተወልደው በየቦታው ሲጣሉ ይስተዋላል፡፡ ስለዚህ ክትትል ሊደረግ ይገባል፡፡ ድርጅቱ ከበጀት እጥረት የተነሳ የራሱ የሰው ኃይል መቅጠር አልቻለም፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እየመጡ ልብስ በማጠብ፣ ፀጉር በመቁረጥ፣ ግቢ በማፅዳት፣ ቡና ማፍላትና በማጠጣት ብዙ ያግዛሉ፡፡ ይህ በገንዘብ ቢተመን በጣም ብዙ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ታመው የዳኑ ሰዎች እዚያው ያገለግላሉ፡፡ በዚህ ነው ድርጅቱ ራሱን የሚያስተዳድረው፡፡ በመሆኑም በሚጠበቀው ልክ እየሠራ አይደለም፡፡ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ለእነዚህ ወገኖች የተቻላቸውን ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ቀደም ሲል ጅማ ውስጥ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ያገለገሉ ዕቃዎች ተጠራቅመው ይበሰብሱና በጨረታ ይሸጡ ነበር፡፡ አሁን ግን መንግሥት ለበጎ አድራጎት ስጡ በማለቱ የትኛውም መሥሪያ ቤት ዕቃውን ማስወገድ ሲፈልግ እኛን ይጠራናል፡፡ እኛ ደግሞ የምንቀበለውን ወደ ገንዘብ በመለወጥ የብዙ ወራት ወተት እንገዛለን፡፡ ቀለብ እንሸምታለን፡፡ አሁንም የሚያገለግሉ ዕቃዎችን የሚያስወግዱ ድርጅቶች ካሉ ሰዎችን ለመርዳት ሕጋዊ ፈቃድ ወስደን እየሠራን በመሆኑ ለድርጅታችን ቢያስገቡ መልካም ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

በርካታ ሐኪሞችን የሚፈልገው የጨቅላ ሕፃናት ሕክምና

በኢትዮጵያ የጨቅላ ሕፃናት ሞትን ለመቀነስ ባለፉት አሠርታት የተሠሩ ሥራዎች ለውጥ አምጥተዋል፡፡ ሆኖም በጨቅላ ሕፃናት ሕክምና ዘርፍ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ከነበረው ቢሻልም፣ የጨቅላ ሕፃናት...