Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልአርብቶ አደሮች ዓለም እንዴት ተፈጠረ ይላሉ?

አርብቶ አደሮች ዓለም እንዴት ተፈጠረ ይላሉ?

ቀን:

አርብቶ አደር ማኅበረሰቦች የፍጥረት ሥነ ተረቶች (ሚቶሎጂ) እና አፅናፈ ሰማይ ፍጥረት (ኮስሞሎጂ) የሚያካትቱ የበለፀጉ የቃል ወጎች አሏቸው። እነዚህ የአፍ ታሪኮች በተለያዩ ወገኖች መካከል ሊለያዩ ቢችሉም፣ በአኗኗራቸው ግን እንስሳትና የተፈጥሮ አካባቢን መሠረታቸው እንደሆነ ያንፀባርቃሉ፡፡

በአንድ የፎክሎር (ነገረ ባህል) ድርሳን ውስጥ፣ የአንዳንድ አካባቢዎች ሐተታ ተፈጥሮ ወይም ሥነ ተረት ተዘርዝሮ ይገኛል፡፡ ለማሳያ ያህል ከምሥራቅ አፍሪካ የማሳይን፣ ከምዕራብ አፍሪካ የፉላኒን ማኅበረሰቦች፣ በማስከተልም ከኢጥዮጵያ የደቡቡ ክፍል ከሚገኙት መካከል ያላቸውን ሐተታ ተፈጥሮ እናቀርባለን፡፡

አርብቶ አደሮች ዓለም እንዴት ተፈጠረ ይላሉ? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የቦዲ ማኅበረሰብ (ኢትዮጵያ)

በምሥራቅ አፍሪካ (ኬንያ) ውስጥ በሚገኘው ማሳይ ማኅበረሰብ አፈ ታሪክ መሠረት፣  ኢንካይ (ኤንጋይ በመባልም ይታወቃል) የተባለው አምላክ ዓለምን ፈጠረና በተለይ ለማሳይ ሕዝብ ከብቶችን ሰጥቷቸው፣ በምድር ላይ ያሉ ከብቶችን ሁሉ ጠባቂ አደረጋቸው። ይህ እምነት በማሳይ ባህል ውስጥ የከብቶችን አስፈላጊነትን ያጎላል፡፡

በምዕራብ አፍሪካ በናይጄሪያ፣ ማሊ፣ ጊኒ፣ ሴኔጋልና ኒጀር የሚገኘው የፉላኒ ማኅበረሰብ፣ በባህሉ ውስጥ ማዕከላዊ አካል የሆነውን ስለ አንድ ግዙፍ የወተት ጠብታ የሚናገር ሐተታ ተፈጥሮ (የፍጥረት አፈ ታሪክ) አላቸው። ‹‹የወተት ጠብታ ወደ ድንጋይ ተለወጠ፤ እናም ከዚህ ድንጋይ በዓለም ውስጥ ያለው ነገር ሁሉ ከብቶችን ጨምሮ ተፈጠረ፤›› ይላል፡፡ ከብቶች ለፉላኒ ሕይወት መሠረት ናቸው፡፡ እነዚህ የፍጥረት ተረኮች አርብቶ አደሮች ከከብቶቻቸውና ከአካባቢያቸው/ ከሥነ ምሕዳሩ ጋር ያላቸውን ጥልቅ ግንኙነት የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡ ይህም ሰዎች፣ እንስሳትና ተፈጥሮ እርስ በርስ የተሳሰሩበትን ዓለም ያሳያል ይላል የፎክሎር ድርሳኑ።

አርብቶ አደሮች ዓለም እንዴት ተፈጠረ ይላሉ? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የሐመር ማኅበረሰብ (ኢትዮጵያ)

ሐተታ ተፈጥሮ በደቡብ ኢትዮጵያ

በደቡብ ኢትዮጵያ ከሚገኙት ብሔረሰቦች መካከል በደቡብ ኦሞ ዞን ያሉት የዲሜ፣ ቦዲ፣ ቦና፣ ፀማይ ብራይሌና ሐመር ብሔረሰቦች ስለዓለም አፈጣጠር የየራሳቸው እምነትና እይታ አላቸው፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን፣ በደቡብ ኦሞ ዞን በሚገኙ 16 ብሔረሰቦች የማይዳሰሱ (ኢንታንጀብል) ባህላዊ ቅርሶች ላይ ካደረገው ኢንቬንቶሪ (ቆጠራና ምዝገባ) የተገኙትን አውራ ነጥቦች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

ብራይሌ

የብራይሌ ብሔረሰብ በጥንት ጊዜ በአካባቢያቸው ከነበሩ የተለያዩ ብሔረሰቦች ጋር ይኖሩ እንደነበረና በተለያዩ ምክንያቶች በደረሱባቸው ግፊቶችና ረሀብን ለመሸሽ ለም መሬት ፍለጋ ተሰደው በወይጦ ወንዝ አካባቢ የሰፈሩ ናቸው፡፡ ለረዥም ዓመታት ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር ሳይገናኙ እንደኖሩ ይገልጻሉ፡፡ በዚህም የተነሣ ስለሌላው አካባቢ ያላቸው እውቀት ውስን ነው፡፡ ሆኖም ግን ብራይሌዎች የሰውን ልጅ፣ መሬትንና ውኃን የፈጠረ ዋቆ ጉረንጉቴ የሚባል አምላክ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ የተለያዩ የተፈጥሮ ችግሮች እንደ ድርቅ፣ የውኃ መቀነስ፣ የዓሣ መጥፋትና የንቦች መራቅ ሲከሠቱ ወደ ሰማይ በመመልከት ዋቆ ጉረንጐቴ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ይጸልያሉ፡፡

ቦዲ

በቦዲ ብሔረሰብ እምነት የሁሉ ነገር ፈጣሪ ቱሞ ነው፡፡ ቦዲዎችንና ለእነርሱ ከብቶችን የፈጠረ አምላክ በሰማይ የሚኖረው ቱሞ ነው፡፡ ማኅበረሰቡን ከቱሞ ጋር እንደ ድልድይ የሚያገናኘው መንፈሳዊ አባት ደግሞ ኩሙሩ ይባላል፡፡ ኩሙሩ ከማኅበረሰቡ የተገኘ መንፈሳዊ አባት ቢሆንም ሥልጣኑ እንደ ቱሞ ነው፡፡

በማኅበረሰቡ የሚከሠቱ አለመግባባቶችን የመጨረሻ ውሳኔ ሰጭና የቦዲ መሬት ሁሉ አባት ነው፡፡ የመንፈሳዊ ሥልጣኑ ከዘር ወደዘር ይተላለፋል፡፡ ባላባቱ ሲሞት ሽማግሌዎች በመሰብሰብ አዲሱን ባላባት መርቀው ሥልጣኑን ያስረክባሉ፡፡ ርክክቡም ቀረሻባል ተብሎ ይጠራል፡፡ በማኅበረሰቡ የእርስ በርስ ግጭት ሲከሰት መንፈሳዊ መሪው ያስታርቃል፡፡ ጦርነት ሲከሠት የቦዲ ወንዶችን በማሰባሰብ ደምና ወተት በማቀላቀል በእያንዳንዱ ተዋጊ ፊት ላይ እየመረቀ በመርጨት ለጦርነት ያዘጋጃል፡፡

 በዝናብ መጥፋት ድርቅ ሲከሠት ኩሙሩ ይጸልያል፤ ዝናብ ይዘንባል፡፡ እህል ሲሰበሰብና የግጦሽ መሬት አመቺ ሲሆን፣ ‹‹ባላባቱ ዝናብ አምጥቷል፤ እህል ደርሷል፤ ከብቶች ወፍረው ወተትና ደም እንድንጠጣ አድርጓል፤›› በሚል ከብት በማረድ መንፈሳዊ መሪውን በደም በማጠብ በዓል ይደረጋል፡፡

ፀማይ

በፀማይ ብሔረሰብ እምነት የሁሉ ነገር ፈጣሪ ዋቅኮ ነው፡፡ ሰማይን፣ መሬትን፣ ውኃን፣ ሰውንና ከብቶችን የፈጠረ ዋቅኮ ነው፡፡ ለፀማይ፣ መንፈሳዊ ተግባራትን የሚያከናወንለትና ሕዝቡም ከብቱ እንዲረባለት በሽታም እንዲጠፋለት፣ ዝናብም እንዲመጣለት ዋቅኮን የሚለምን ከፍተኛው መንፈሳዊ መሪ የኤርቦሬ ብሔረሰብ ሃይማኖታዊ መሪው ቃወት ነው፡፡ ሁለቱ ብሔረሰቦች በአንድ ሃይማኖታዊ መሪ መመራታቸው እርስ በእርስ እንዲቀራረቡና በመከባበርና በመረዳዳት እንዲኖሩ አስችሏቸዋል፡፡

ሐመር

በሐመር ብሔረሰብ እምነት የሁሉ ነገር ፈጣሪ አምላክ ቦርጆ ነው፡፡ ቦርጆ በሰማይ የሚኖርና ሰማይና ምድርን ፈጥሮ የሰው ልጆችንና ለእነርሱ መተዳደርያ ከብቶችን መፍጠሩን ብሔረሰቡ ያምናል፡፡ ቦርጆ መልካም ነገሮችን እንደመፍጠሩ በሰው ልጆች ከተቆጣ ድርቅን፣ ረሀብን፣ በሽታንና ጦርነት ሊያመጣ የሚችል በመሆኑ በብሔረሰቡ ይከበራል፡፡ ይፈራል፡፡

ሃይማኖታዊ ተግባር የሚከናወነው በብሔረሰቡ በተመረጠው ቢታ በሚባለው መንፈሳዊና አስተዳደራዊ መሪ ነው፡፡ ቢታ በቦርጆ እንደተመረጠና ሕዝቡን ከቦርጆ ጋር የሚያገናኝ ድልድይ ስለሆነ ይከበራል፡፡ ትዕዛዙና ውሳኔውም ተቀባይነት አለው፡፡ ዝናብ ሲጠፋ፣ በሽታ በወረርሽኝ መልክ ሲከሠት፣ ከብቶች በድርቅ ወይም በበሽታ ሲጠቁ፣ ከአጎራባች ብሔረሰቦች ጋር ግጭት ሲፈጠር ሕዝቡ ፍየልና ማር በማቅረብ ቢታው ቦርጆን እንዲለምን ይጠይቃል፡፡ ቢታው ካርኮና ጋሊ የሚባሉ ቅጠሎች በመያዝ አምላክን ይለምናል፤ ችግር ይወገዳል፡፡ የተከሠቱ ችግሮች ሁሉ እንደሚወገዱለት ብሔረሰቡ ያምናል፡፡

 ዲሜ

በዲሜ ብሔረሰብ እምነት የሰው ልጅ፣ የእንስሳት፣ የዕፅዋት፣ የሰማይና የምድር ፈጣሪ የፊ ነው፡፡ በዲሜ ሰው የማይደርስበትና የተከለከለ ጊሚዚ የሚባል ተራራ አለ፡፡ አምላክና የሞቱ ሰዎች የሙት መንፈስ በዚያ ስለሚኖር ከማኅበረሰቡ መሪ የኪ በስተቀር በዚያ አካባቢ መሔድ የተከለከለ ነው፡፡ የማኅበረሰቡ መንፈሳዊ መሪ የኪ፣ ኢዝሚ ከሚባል ከዲሜ አንድ ጐሣ የተመረጠ ሲሆን፣ በዘሩ በእናትም ሆነ በአባት ከሌሎች አጐራባች ብሔረሰቦች ያልተቀላቀለ፣ ንጹሕ ዲሜ መሆን ይጠበቅበታል፡፡

 በማኅበረሰቡ ድርቅ፣ ረሀብ፣ በሽታና ጦርነት ሲከሠት የኪ የተፈጨ ጤፍ፣ ቂጣ፣ ማር በእንሰት ቅጠል በማሰር፣ ወደ ተራራው በመሔድና ለአምላክ በማቅረብ ለማኅበረሰቡ ከአምላክ /ያፊ/ ምሕረት ይጠይቃል፡፡ ከሌሎች ብሔረሰቦች የጦርነት ሥጋት ሲከሠት የኪ ከብት በማረድና ሞራ በመዘርጋት የጦርነት መምጫ አቅጣጫዎችን በቀስት በመለየት ከየት በኩል ጦርነት ሊመጣ እንደሚችል በመጠቆም፣ ደም ይዞ በመሔድ በየተራራው እየቆፈረ ይቀብራል፡፡ በዚህም የታሰበው ጦርነት ይመለሳል፡፡ የመጣው ጦር ከዲሜ ጋር ውጊያ ቢገጥምም ይሸነፋል ተብሎም ይታመናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...