Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናወልቃይት ለአራት ዓመታት ከፌዴራል መንግሥት የበጀት ድጎማ ባለማግኘቱ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ቅሬታ...

ወልቃይት ለአራት ዓመታት ከፌዴራል መንግሥት የበጀት ድጎማ ባለማግኘቱ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ቅሬታ ቀረበ

ቀን:

  • የአማራ ክልል ምክር ቤት ጥያቄው የፍትሐዊነት ጉዳይ በመሆኑ መልስ እንዲሰጠው ጠይቋል

በአማራና በትግራይ ክልሎች የወሰን ይገባኛል ጥያቄ የሚነሳበት ወልቃይት፣ ከፌዴራል መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት ምንም ዓይነት የበጀት ድጋፍ አለማግኘቱ ተጠቅሶ፣ መፍትሔ እንዲሰጥበት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ ቀረበ፡፡

የበጀት ክፍፍል ፍትሐዊነት በሚል ለምክር ቤቱ ጥያቄ የቀረበው፣ ሰኔ 24 እና 25 ቀን 2016 ዓ.ም. 3ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉባዔውን ባካሄደበት ወቅት ነበር፡፡

በምክር ቤቱ ዓመታዊ ጉባዔ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል አቶ አማረ ሰጤ በሰጡት አስተያየት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋናው ሥልጣንና ኃላፊነት የኢትዮጵያ ሕዝቦች እኩል ተጠቃሚነት መኖሩን ማረጋገጥ ቢሆንም፣ የበጀት ድጎማና የጋራ ገቢዎች አሠራር ላይ የወልቃይት በጀት ለአራት ዓመታት ያለ መፍትሔ መቀጠሉን አቅርበዋል፡፡

የወልቃይትና የራያ አካባቢዎች በኢሕአዴግ አገዛዝ ወቅት በትግራይ ክልል አስተዳደር ውስጥ የነበሩ ሲሆን፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተከሰተ በኋላ አካባቢው  ይገባኛል የሚለው የአማራ ክልል በራሱ በጀት እያስተዳደረው መቆየቱ ይታወሳል፡፡

አቶ አማረ በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹የድንበርና ወሰን ጉዳይ ቀስ ብሎ ሊወሰን ይችላል፡፡ የበጀት ተጠቃሚነት ግን የፍትሐዊነት ጥያቄ ነው፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር በቀጥታም ቢሆን ለወረዳዎች በጀት ሊለቅ እንደሚችል የሚፈቅድ አሠራር አለ፣ በዚያ መንገድ መለቀቅ ይችላል፡፡ ነገር ግን በቀጥታም ሆነ ከአማራ ክልል በጀት ጋር የተላከ የወልቃይት የበጀት ቀመር የለም፤›› ብለዋል፡፡

ፍትሐዊነትን ማረጋገጥ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ተግባርና ኃላፊነት ላይ የተብራራ ቢሆንም፣ ይህ የበጀት ጉዳዩ መልስ ሳያገኝ ለአራት ዓመታት በተከታታይ ጥያቄው ሲቀርብ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የገንዘብ ሚኒስቴር ዓመታዊ በጀትን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርብ፣ ለወልቃይት አካባቢ የሚገባው በጀት እንዲለቀቅ በተለያየ መንገድ በተደጋጋሚ ሲጠየቅ ቆይቷል፡፡ ነገ ሐሙስ ሰኔ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚገኙበት ይፀድቃል ተብሎ ከሚጠበቀው 97.1 ቢሊዮን ብር የ2017 ዓ.ም. ረቂቅ በጀት ውስጥ፣ ለክልሎች ተደግፎ የቀረበው የድጎማ በጀት ከ222 ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ለአማራ ክልል 46.9 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ለትግራይ ክልል 13 ቢሊዮን ብር በጀት ተደልድሎላቸዋል፡፡

ይሁን እንጂ አቶ አማረ የወልቃይትና የሌሎች የማንነትና የወሰን ጥያቄ ያለባቸው አካባቢዎች ለአራት ዓመታት የጋራ ድጎማ በጀት ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱን ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄው ቀርቦ የምክር ቤቱ የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ ጉዳዩ ትክክል መሆኑን ገልጸው፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መነገር እንዳለበት መገለጹንና የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔም አቶ አገኘሁ ተሻገር ተመሳሳይ መልስ መስጠታቸውን አስታውሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ የገንዘብ ሚኒስቴር ሲጠየቅ የሚሰጠው ምላሽ ይህ ችግር የሚፈታው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚያመጣው ቀመር እንጂ ሚኒስቴሩ በጀት የመመደብ ችግር እንደሌለበት እየተናገረ፣ አካባቢው ለአራት ዓመታት ያለ በጀት እንዲተዳደር በመደረጉ መፍትሔ ያስፈልጋል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

‹‹ይህ ጉዳይ ለምን መልስ አይሰጠውም?›› ያሉት የምክር ቤቱ አባል፣ ሌሎች የፖለቲካ ጥያቄዎች ሕዝብን በማማከል ሊመለሱ የሚችሉ ቢሆኑም፣ ሕዝቡን ለአራት ዓመታት ያለ ድጎማ በጀት ማቆየትና መልስ ማጣቱ አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡ አክለውም ይህ ጥያቄ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ካልቀረበ ለማን ሊቀርብ ይችላል? የሕዝቡ ጥያቄ መልስ ይፈልጋል፡፡ ችግሩ የማይታወቅ አይደለም፡፡ ለ2017 ዓ.ም. ችግሩ መፍትሔ ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ከመንግሥት ለውጥ በፊት 24 ሰዓት ኤሌክትሪክ ያገኙ የነበሩ የወልቃይትና የአዲ ጎሹ አካባቢዎች ከለውጡ በኋላ መብራት እንደሌላቸው፣ የቴሌኮም አገልግሎት ያገኙ የነበሩት አሁን ግን እንደማያገኙና ባንኮች እንዳይቋቋሙ፣ የቴሌኮም ኔትወርክ ባለመኖሩ ችግር መኖሩን ተናግረዋል፡፡ ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ በትግራይ ክልል ያሉ አካባቢዎች የተሻለ ነገር ቢታይባቸውም፣ እነዚህ አካባቢዎች ግን አገልግሎት እንደተዘጋባቸው ነው ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ የሁመራ አውሮፕላን ማረፊያ ተዘግቶ መቆየቱን ጠቅሰው፣ የመንግሥት አገልግሎት በአንዱ ወገን እየሠራ በሌላ በኩል እየተዘጋ ፍትሐዊነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚለው ጉዳይ በምን መንገድ ሊገለጽ ይችላል? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ አቶ ኃይሉ ኢፋ በሰጡት ምላሽ፣ የወልቃይትና የሌሎች የወሰንና የማንነት ይገባኛል ጥያቄ ያለባቸው አካባቢዎች የገጠማቸው የቀመር ችግር ሳይሆን የበጀት አስተዳደር ነው ብለዋል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በቀመሩ መሠረት ድርሻ እንዲሰጥ ከማድረግ ውጪ ሌላው ጉዳይ እንደማይመለከተው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ይህ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሚና ባለመሆኑ ጉዳዩ በገንዘብ ሚኒስቴር መፍትሔ እንዲሰጠው ምክር ቤቱ ደብዳቤ መጻፉንና አቅጣጫ ማስቀመጡን አስረድተዋል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹አንድ የምክር ቤት አባል አየር ማረፊያ ቆሟል፣ ኤሌክትሪክ ቆሟል፣  የሆነ ኔትወርክ አይሠራም በሚል ያነሱት ጥያቄ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ሊጠየቅበት አይችልም፤›› ብለዋል፡፡ የምክር ቤቱ ሥራ በፍትሐዊነት መሠረተ ልማት መስፋፋቱን መገምገም መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ያልተሰጠንን ሥልጣን እንድናደርግ የሚቀርበውን ሐሳብ ለመቀበል እንቸገራለን፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

አፈ ጉባዔው የወልቃይት ጠገዴ የበጀት ጉዳይ በገንዘብ ሚኒስቴር በጀት አስተዳደር ምላሽ እንዲሰጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ትዕዛዝ መስጠቱንና መፈጸም ተጀምሮ እንደነበር፣ ነገር ግን በጀቱን የገንዘብ ሚኒስቴር ሲፈልግ የሚሰጠው ሲፈልግ የሚያቋርጠው መሆን የለበትም ብለዋል፡፡

የቀድሞው የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ይልቃል ከፈለ (ዶ/ር) በአመራር ላይ በነበሩበት ወቅት እንዲፈጸም ደብዳቤ ተጽፎ ትዕዛዝ መሰጠቱን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅጣጫ አስቀምጠው በበጀት አስተዳደር እንዲመለስ ተወስኖ የተጀመረና አሁን ለምን እንዲቋረጥ እንደተደረገ ባይታወቅም ጉዳዩ በበጀት አስተዳደር የሚመለስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 የመንግሥት አስፈጻሚው ድጎማው የቆመበትን ምክንያት ሊያብራራ እንደሚገባ ጠቅሰው፣ ‹‹ጉዳዩ የፍትሐዊነት ጥያቄ በመሆኑ መመለስ ያስፈልጋል፣ አካባቢው መጎዳት የለበትም፣ በቀጣይ የምናስተካክለው ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

ሪፖርተር ስለበጀት አመዳደብ ማብራሪያ የጠየቃቸው የገንዘብ ሚኒስቴር የበጀት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ወልዱ፣ የወልቃይት በጀት ስለተባለው ጉዳይ የሚያውቁት ነገር አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ የምክር ቤቱ ጉባዔ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አረጋ ከበደ ባቀረቡት ጥያቄ፣ ውስን ዓላማ ባላቸው የፌዴራል መንግሥት የድጎማ በጀት አፈጻጸሞች ላይ ከዚያ ቀደም ችግሮች ማጋጠማቸውንና አንዳንድ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ግልጽ መሥፈርት ሳያወጡ የመሠረተ ልማትና የሌሎች የፕሮጀክቶች በጀትን እንደሚያሠራጩና ጥቅም ላይ እንደሚያውሉ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ይህ መታረም ያለበት መሆኑን ገልጸው፣ የውስን ዓላማ በጀት ተጠቃሚ አካላትም የበጀቱ አመዳደብ መሥፈርቱንም በግልጽ እንደማያውቁት ተናግረዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሥራ መንግሥት በምን ያህል የፍትሐዊነትና ግልጽነት ደረጃ ሀብት እንደሚጠቀም ለማመላከት ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰው፣ ለአብነትም አንዳንድ ጊዜ ተጨባጭ በሆኑ ምክንያቶች በአብዛኛው በግምት ከፍትሐዊነትና ከተጠቃሚነት ጋር የሚነሱ ቅሬታዎች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡

በፌደሬሽን ምክር ቤት ጉባዔ የተነሳው ሌላው ጥያቄ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሕዝበ ውሳኔ የራሳቸውን ክልል የመሠረቱ አራት ክልሎች ማለትም ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና ደቡብ ኢትዮጵያ የራሳችው የበጀት ክፍፍል ቀመር እንደሌላቸው ተወስቷል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት፣ የፌዴራል ጥቅል ዓላማ ያላቸው የድጎማ በጀትን የማከፋፊያ ቀመር ለመከለስ ወቅታዊ የሆነ መረጃ ዕጦት ማጋጠሙን ተናግረዋል፡፡ በተለይም የአዳዲስ ክልሎች መረጃ በሚገባ ያልተደራጀ መሆኑ ማነቆ እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከአዳዲስ ክልሎች የተደራጀ መረጃ የለም ተብሎ መባሉ ካስከፋቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት፣ የተነሳውን የተደራጀ መረጃ ዕጦት ለመቀበል እንደሚያዳግታቸው የገለጹ ነበሩ፡፡

አቶ ብርሃኑ ዘውዴ የተባሉ ከደቡብ ኢትዮጵያ የተወከሉ የምክር ቤቱ አባል፣ ከነባሩ ክልል ራሳቸውን የቻሉት አራቱ ክልሎች እንደ አዲስ የወጡ ቢሆኑም፣ በተለየ መንገድ አዲስ ሆነው መታየት እንደሌለባቸው ተናግረዋል፡፡ ሁሉም ክልሎች ባላቸውና በሚታወቅ መረጃ ትኩረት ተሰጥቶ በየራሳቸው የቀመር ቋት ባለመኖሩ፣ የተለየ የድጎማ በጀት ቀመር ሊዘጋጅላቸው ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

 የደቡብ ኢትዮጵያ የምክር ቤት አባሏ ወ/ሮ ወላይቴ ቢቶ፣ ‹‹አዳዲስ ክልሎች እየተባለ እስከ መቼ? የራሳቸውን ቀመር ማግኘት ለምን አይችሉም?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ አርብቶ አደሮች የአገርን ድንበር ዋጋ እየከፈሉ እየጠበቁ ነው፡፡ ነገር ግን በበጀት አለመደገፋቸው አግባብ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ጸሐፊ ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት መልስ፣ የመንግሥት ለውጥ ከመደረጉ በፊት ስለፍትሐዊነት ጥያቄ ማንሳትና መልስ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ እንደነበር፣ አሁን ግን ሥርዓት በመዘጋጀቱ ለመጠየቅ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ አክለውም ከለውጥ በፊት ጥያቄ ሲቀርብ፣ ‹‹አያገባችሁም፣ አይመለከታችሁም የሚል መልስ ይሰጠን የነበረ ቢሆንም፣ አሁን የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋታችን 55.9 ቢሊዮን ብር ለውስን ዓላማ ድጎማ በጀት ተላልፏል፤›› ብለዋል፡፡

 ከመንግሥት ሥርዓት ለውጥ በፊት ስለፍትሐዊነት ጥያቄ ቢነሳ ምንም ዓይነት አሠራር እንዳልነበር ጠቅሰው፣ ከ2014 ዓ.ም. ወዲህ ግን ውስን ዓላማ በጀት እንዴትና በምን መንገድ እንደሚሠራጭ በሕግ ተብራርቶ ስለመቀመጡ አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም በአዳዲስ ክልሎች መረጃ አለማግኘትን በተመለከተ ክልሎች ጥያቄ ሲቀርብላቸው፣ መረጃው በከተማ ደረጃ እንጂ በክልል የተደራጀ አለመሆኑን እንደሚገልጹ ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል በጀት ክፍፍል ቀመር ለዘጠኝ ጊዜ መሻሻሉን የጠቀሱት ዋና ጸሐፊው ከሦስት ዓመታት በፊት ይሻሻላል በሚል ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ ተዓማኒ የሆነና ገለልተኛ አካል ያመነጨው መረጃ አለመኖሩን አስረድተዋል፡፡ በጊዜው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ተካሂዶ የበጀት ቀመሩ ይሻሻላል በሚል ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም ቆጠራው ባለመካሄዱ ጉዳዩን እንዳዘገየው አስረድተዋል፡፡

የበጀት ቀመር መረጃ በግምት የሚሰበሰብ ባለመሆኑ አሁን ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባለው መረጃ ብቻ ተመርኩዞ በጀት የሚደለድል መሆኑን ጸሐፊው ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ቀመር አሁን ያለውን ሁኔታ በግልጽ የሚያመላክት ባይሆንም፣ ያለው አማራጭ የፌዴራል መንግሥት የጀመረውን የመረጃ ማደራጀት ሥራ በቶሎ እንዲያከናውንና ቀመሩ እንዲከለስ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...