Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበከፍተኛ ሙስና ሲጠረጠር የተሰወረው ግለሰብ ቦሌ ሥጋ ቤት ከፍቶ ማስታወቂያ ሲያስነግር ተያዘ

በከፍተኛ ሙስና ሲጠረጠር የተሰወረው ግለሰብ ቦሌ ሥጋ ቤት ከፍቶ ማስታወቂያ ሲያስነግር ተያዘ

ቀን:

በከፍተኛ የሀብት ምዝበራ (ሙስና) ጋር በተያያዘ ከተጠረጠሩ 20 ግለሰቦች ውስጥ 14ቱ ክልሉን ለቀው መሰወራቸውን፣ ስድስቱ በቁጥጥር ሥር ሲውሉ አንደኛው ተጠርጣሪ ግን በአዲስ አበባ በቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ ሥጋ ቤት ከፍቶ ማስታወቂያ ሲያስነግር መያዙ ተገለጸ፡፡

በከፍተኛ ሙስና ሲጠረጠር የተሰወረው ግለሰብ ቦሌ ሥጋ ቤት ከፍቶ ማስታወቂያ ሲያስነግር ተያዘ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
አቶ አማኑኤል አብደላ የደቡብ ኢትዮጵያ
ክልል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን
ምክትል ኮሚሽነር

ይህ የተገለጸው የፌዴራል፣ የክልልና የከተማ መስተዳድሮች የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነሮችና የአመራር ኮሚቴ አባላት፣ የዘርፎች ፎረም አባላት፣ እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት፣ ከትናንት በስቲያ ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዳማ ኃይሌ ሪዞርት ሆቴል ተገኝተው የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም በገመገሙበት የውይይት መድረክ ላይ ነው።

ምዝበራው የተፈጸመው በደቡብ ክልል ኢትዮጵያ ሲሆን፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አማኑኤል አብደላ ስለሀብት ምዝበራ ወንጀሉ ለሪፖርተር በሰጡት ገለጻ፣ በአጠቃላይ 35 ሚሊዮን ብር መመዝበሩን ጠቁመው፣ ከዚህ ውስጥ የ20 ሚሊዮን ብር ቼክ ተፈርሞ ከባንክ ለማውጣት ሒደት ላይ መያዙን ተናግረዋል።

ስለድርጊቱ አፈጻጸም ሒደት ሲያብራሩም፣ የሙስና ወንጀሉ የመጀመሪያ ክፍል የተፈጸመው፣ ክልሉ ቀድሞ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሚል መጠሪያና የአስተዳደር ወሰን ተከልሎ በሚተዳደርበት ወቅት 12ኛው ክልል ሊመሠረት የመጨረሻ ሁኔታዎች እየተመቻቹ በነበረበት ጊዜ መሆኑን ተናግረዋል።

ከወንጀሉ ጋር የተያያዘው ተቋም የክልሉ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ቢሮ መሆኑን፣ ቢሮው በየወረዳዎችና ዞኑ ከሚያስገነባቸው ፕሮጀክቶቹ አንዱ በሆነው የቡልቂ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ግንባታ እንደሆነም ተገልጿል።

እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ፣ በዚህ ኮሌጅ ግንባታ ወቅት የተፈጸመው ሙስና መጀመሪያ ባልተፈጸመ ሥራ ክፍያ መስጠትና ከውል ውጪ ክፍያ መፈጸም ሲሆን፣ በሁለተኝነት የተጠቀሰው ደግሞ የግንባታውን ምዕራፍ አንድ ያከናወነው ተቋራጭ አጠናቆታል ተብሎ ክፍያ መፈጸሙ ነው፡፡ ነገር ግን ግንባታ ሳይጠናቀቅ ወጪ የተደረገባቸው የግንባታ ክፍሎች ለምዕራፍ ሁለት ግንባታ በተቀጠረው ተቋራጭ በድጋሚ የተሠራ በማስመሰል አጠቃላይ የተፈጸመ የሀብት ምዝበራ ነው ብለዋል።

አጠቃላይ የሀብት ምዝበራው 35 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 15 ሚሊዮን ብር ቀደም ሲል በተገለጹ መንገዶች ያላግባብ ጥቅም ላይ የዋለና የግለሰቦች ኪስ የገባ መሆኑን፣ ግለሰቦች በሕግ ተጠይቀው ገንዘቡን የማስመለስ ሥራዎችም በሒደት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አቶ አማኑኤል ስለጉዳዩ ለኮሚሽኑ ጉባዔ ባስረዱበት ወቅት፣ ‹‹በፊት ሰው የሚተቸን፣ ባለሙያና ከታች ያለው ሠራተኛ ላይ ብቻ ነው የምታተኩሩት የሚል ነበር፡፡ ዘንድሮ እኛም እስቲ በአዲሱ ክልል አቅማችንን እናሳይ በሚል ሕንፃው አጠገባችን ከነበረው የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ቢሮ ነበር የጀመርነው፤›› ብለዋል።

የተካሄደው ሙስና በማስረጃዎች ተመርምሮ ለሕግ አካል ተላልፎ የተሰጠበትና አሁን ጉዳያቸው በሕግ ከተያዘባቸው 20 ግለሰቦች ጋር የተያያዘው፣ ቢሮው ኮሚሽኑ ያጋለጠውን የሙስና ወንጀል ተከትሎ ከኮሚሽኑ አጠገብ ከነበረበት ሕንፃ ለቆ ወደ ሌላ ሥፍራ ተከራይቶ መሄዱን የገለጹት ኃላፊው፣ ‹‹ቦታ ጭምር ቀይረው ተከራይተው ሄደዋል፣ በርብረን ማስረጃዎችን ስለያዝን ሌላ ቦታ ወጥተው እስከ መከራየት ደርሰዋል፤›› ሲሉም ተናግረዋል።

ይሁንና የክልሉ ኮሚሽን ተጠርጣሪዎችን በሕግ ቁጥጥር ሥር ከማዋል አንፃር የቅንጅትና የአፈጻጸም ተግዳሮቶች እንዳጋጠሙት ተገልጿል።

አቶ አማኑኤል፣ ‹‹ከ20 ተጠርጣሪዎች የተያዙት ስድስት ሰዎች ብቻ ናቸው። አብዛኞቹ ሸሽተው አዲስ አበባ ነው የገቡት። ለምሳሌ አንደኛው ሰውዬ አዲስ አበባ ከተማ መጥቶ ቦሌ ሥጋ ቤት ከፍቶ በመገናኛ ብዙኃን ሲያስተዋውቅ ነው ያገኘነው፤›› ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር የተጠርጣሪው መገኛ አድራሻ ከታወቀ በኋላ ከፖሊስ ጋር በነበረው እንቅስቃሴም አጋጠመ ያሉትን ችግር ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ተጠርጣሪውን ስናገኘው ፖሊስ የተባለው ቦታ ይመጣል። ከዚያ በኋላ ግን እሱን ትተው አውቀው ሌላ ሰው እስከመያዝ ድረስ ነው የደረሱት። ስለዚህ ቅንጅት የለንም፣ ያስፈልገናል፤›› ብለዋል።

‹‹ሌባ በአንድ ክልል ብቻ አይሰርቅም፣ የትም ይሰርቃል፤›› ያሉት አቶ አማኑኤል፣ ሁሉም የአገሪቱ ፀረ ሙስና ኮሚሽኖች እርስ በርስ፣ ከፌዴራልና ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር መቀናጀት እንደሚያስፈልጋቸው አስረድተዋል።

አሥራ አራት ተጠርጣሪዎች እየተፈለጉበት ያለውን የሕግ ጉዳይ በተመለከተ እስካሁን ድረስ ለአዲስ አበባ ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አለማቅረባቸውን ገልጸው፣ ‹‹አሁን ከአዲስ አበባ ጋር በቅንጅት ከሠራን ተጠርጣሪዎቹን ወዲያውኑ በሕግ ጥላ ሥር ለማዋል እንችላለን ብለን እናምናለን፤›› ብለዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...