Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናነዳጅ አከፋፋዮች አምስት መቶ ሺሕ ሊትር የሚይዝ ዴፖ የመገንባት ግዴታ ሊጣልባቸው ነው

ነዳጅ አከፋፋዮች አምስት መቶ ሺሕ ሊትር የሚይዝ ዴፖ የመገንባት ግዴታ ሊጣልባቸው ነው

ቀን:

  • ባለቤቱ እያወቀ የጫነውን ነዳጅ ባልተፈቀደ ቦታ ያራገፈ ተሽከርካሪ ይወረሳል

ነዳጅ አከፋፋዮች በሁለት ዓመት ውስጥ 500‚000 ሊትር የሚይዝ ዴፖ፣ አራት ማደያዎች፣ እንዲሁም በሦስት ዓመታት ውስጥ ተጨማሪ ስድስት ማደያዎችን የመገንባት ግዴታ ሊጣልባቸው ነው፡፡

የነዳጅ ውጤቶችን የግብይት ሥርዓት ለመደንገግ በቅርቡ በወጣው ረቂቅ አዋጅ፣ የነዳጅ ግብይት ተዋናዮችን ማለትም የአስመጪዎችን፣ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት፣ የአከፋፋዮች፣ የማደያዎች፣ የአጓጓዦችና የቀጥታ ተጠቃሚዎች ግዴታ በዝርዝር ተደንግጓል፡፡

በዚህም አዲስ ጀማሪ የነዳጅ አከፋፋዮች ቢያንስ 500‚000 ሊትር ነዳጅ የሚይዝ ዴፖና አራት ማደያዎችን ይዞ ሥራ የመጀመር፣ እንዲሁም የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ከተሰጣቸው ቀን ጀምሮ፣ በሦስት ዓመታት ውስጥ ተጨማሪ ስድስት ማደያዎች የመገንባት ግዴታ እንዳለባቸው የተጠቀሰ ሲሆን፣ ነባር አከፋፋዮችም ተመሳሳይ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡

አከፋፋዮች በቂ የሆነ የነዳጅ ክምችት የሚይዙበት ዴፖ ሊኖራቸው ይገባል በሚል የተቀመጠው ድንጋጌ አስከፊ ባይሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ያሉ ኩባንያዎች የተባለውን ያህል ሊትር መያዝ የሚችል ዴፖ ቢገነቡም የነዳጅ አቅርቦት ባለመኖሩ፣ ኩባንያዎቹ አንድ ላይ በመሆን ዴፖ ቢሠሩ ለአገር እንደሚጠቅምና የተሻለ እንደሚሆን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የተባበሩት ብሔራዊ ፔትሮሊየም አንድ የሥራ ኃላፊ ገልጸዋል፡፡

ኩብንያዎቹ ወደ ኢንቨስትመንት ሲገቡ ከሚሰጣቸው መሬት ውጪ ማበረታቻም ሆነ ለዴፖ ግንባታ የሚውል የመሬት አቅርቦት ኩባንያው በራሱ ጥረት ማግኘት ካልቻለ፣ ምንም ዓይነት ድጋፍ እንደሌለ ጠቁመዋል፡፡ 

‹‹ምንም እንኳን የተባበሩት ብሔራዊ ፔትሮሊየም ከተቋቋመ ረጅም ጊዜ ማለትም ወደ 19 ዓመት ያህል ቢሆነውም፣ አዲስ የሚቋቋሙ ኩባንያዎች መጀመሪያ ላይ ከሚያወጡት ወጪ አንፃር የሚገኘው ትርፍ ዝቅተኛ ነው፡፡ ኢንቨስተሮችም ትርፉ በረጅም ጊዜ ይገኛል በሚል ነው የሚገነቡት፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

በረቂቁ የተቀመጠው ሌላኛው ድንጋጌ አከፋፋዮች በሥራቸው የሚሠራ የነዳጅ ማደያ የተረከባቸውን የነዳጅ ውጤቶች ለመጨረሻ ተጠቃሚ በአግባቡ መሠራጨቱን የመከታተል ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡

የነዳጅ ግብይት ተዋናይ በሚል ግዴታ ከተጣለባቸው መካከል የነዳጅ ማደያዎች ይገኛሉ፡፡ በዚህም የነዳጅ ውጤቶችን ውል ከገባው አከፋፋይ ብቻ በመግዛትና በመረከብ ነዳጅ ማደያው ውስጥ እንዲራገፍ የማድረግ፣ እንዲሁም የነዳጅ ውጤቶችን ከባዕድ ነገሮች ጋር አለመቀላቀል፣ ጥራቱን ሊያጓድል ከሚችል ማናቸውም ድርጊት የመቆጠብና ለመጨረሻ ተጠቃሚዎች በችርቻሮ የመሸጥ ግዴታ እንዳለባቸው ተደንግጓል፡፡

በተጨማሪም የዋጋ ቁጥጥር የሚደረግባቸውን የነዳጅ ውጤቶች አግባብነት ያለው የመንግሥት አካል በወሰነው ዋጋ መሸጥና ለመጨረሻ ተጠቃሚዎች ያልተቆራረጠ የሃያ አራት ሰዓት የሽያጭ አገልግሎት የመስጠት ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡

አስተዳደራዊ ዕርምጃን በሚመለከት በረቂቅ አዋጁ በተቀመጠው ድንጋጌ፣ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን በአዋጁ መሠረት የወጡ ደንቦችን ወይም መመርያዎችን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውንም የግብይት ተዋናይ የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ወይም የግንባታ ፈቃድ ሊያግድ ወይም ሊሰርዝ ይችላል፡፡

በዚህም መሠረት ነባር የግብይት ተዋናይ አዋጁ ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ መሥፈርቶችን አሟልቶ የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ካላገኘ የንግድ ፈቃዱ እንደሚሰረዝ፣ ማንኛውም አከፋፋይ በአዋጁ በተቀመጠው መሠረት የሚጠበቅበትን የነዳጅ ዴፖና ማደያዎች ካልገነባ የንግድ ፈቃዱ ይሰረዛል ይላል፡፡

የወንጀል ቅጣትን በተመለከተም የነዳጅ ውጤቶችን ከተፈቀደው ቦታ ውጪ ያከማቸ፣ ሊሸጥ ከሚገባው ሰው፣ ቦታና የግብይት ሥርዓት ውጪ ሲሸጥ የተገኘ ወይም በመመርያ በተወሰነው መሠረት አደጋ ያስከትላሉ በተባሉ መያዣዎች ሲሸጥ የተገኘ ማንኛውም ሰው የተያዘው የነዳጅ ውጤት ተወርሶ፣ ከሦስት ዓመታት በማይበልጥ ቀላል እስራትና ከሃምሳ ሺሕ እስከ መቶ ሺሕ ብር በሚደርስ መቀጮ እንደሚቀጣ ያስረዳል፡፡ 

በተጨማሪም የነዳጅ ውጤቶችን ሆን ብሎ ከባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል ለግብይት ያቀረበ ማንኛውም ሰው፣ ከሦስት እስከ ሰባት ዓመታት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከመቶ ሃምሳ ሺሕ እስከ ሦስት መቶ ሺሕ ብር በሚደርስ መቀጮ እንደሚቀጣ ተደንግጓል፡፡

የነዳጅ ውጤቶችን ከተፈቀደለት የማጓጓዣ መስመር ውጪ ሲያጓጉዝ፣ ከተፈቀደለት ማራገፊያ ውጪ ሲያራግፍ ወይም ወደ ጎረቤት አገር በኮንትሮባንድ ሲያጓጉዝ፣ የአጓጓዡ ባለቤት ድርጊቱን እያወቀ እንዳይፈጸም ለመከላከል ወይም ለማስቆም ተገቢውን ዕርምጃ ሳይወስድ የቀረ እንደሆነ፣ ተሽከርካሪው ከነዳጅ ውጤቶች ጋር ተወርሶ ከሦስት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እነደሚቀጣ በረቂቁ ተመላክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...