Tuesday, July 23, 2024

ልዩነትን ይዞ ለዘለቄታዊ ሰላምና ጥቅም መተባበር አያቅትም!

መሰንበቻውን በአውሮፓ ታላላቅ ቡድኖች ተጫውተው ያለፉ ዝነኛ የአፍሪካ እግር ኳስ ከዋክብት በኢትዮጵያ ቆይታ አድርገው ነበር፡፡ ዝነኞቹ ንዋንኮ ካኑ፣ ዳንኤል አሞካቺ፣ ታሪቡ ዌስት፣ ካማራና መሰሎቻቸው ነበሩ፡፡ በተለይ ሁለቱ ናይጄሪያውያን ኢትዮጵያ የተገኙበት ዋናው ምክንያት፣ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ካፍን ለማሳመን እንደ አምባሳደር እንዲያገለግሉ እንደሆነ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ይፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ ከግብፅና ከሱዳን ጋር በመሆን የመጀመሪያዋ የካፍ መሥራች ስትሆን፣ የአፍሪካ ዋንጫን ሦስቴ በማዘጋጀትም ትታወቃለች፡፡ ምንም እንኳ ለእግር ኳስ የጋለ ስሜት እንጂ ችሎታው ባይኖርም፣ በአንድ ወቅት ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ በማሸነፍ በታሪክ ተመዝግባለች፡፡ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ለማስተናገድ ዘመኑን የሚመጥኑ ስታዲየሞች፣ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችና ዝግጅቶች አስፈላጊ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አስተማማኝ ፀጥታ እንዲኖር ማድረግ ደግሞ ሌላው መሥፈርት ነው፡፡ የኢትዮጵያን የጠቆረ ገጽታም መለወጥ የግድ ይሆናል፡፡

ከእግር ኳስና ከሌሎች የስፖርት ውድድሮች ዝግጅት በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተመራጭ መዳረሻ እንድትሆን የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች ያስፈልጋሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በስፋት የተጀመረው የኮሪደር ልማት፣ እንዲሁም በሌሎች ከተሞች በጅማሮ ላይ ያለው የማሳመር እንቅስቃሴ በሕዝብ ቅቡልነት አግኝቶ ሲከናወን ልማቱ የጋራ ይሆናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የውጭ እንግዶችን ተቀብለው ለማስተናገድ የሚችሉ በርካታ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች አሉ፡፡ በብዙ ሥፍራዎች የየብስ ትራንስፖርት አስተማማኝ ባይሆንም፣ የአየር ትራንስፖርት እንቅስቃሴን ማስተናገድ የሚችሉ የአውሮፕላን ማረፊያዎች አሉ፣ በተጨማሪም እየተገነቡ ነው፡፡ ከእነዚህ ሥራዎች ጎን ለጎን ለአገር ገጽታ የሚበጁ ተግባራት ሲከናወኑ፣ ለሰላም መጥፋት ምክንያት የሚሆኑ ችግሮች ደረጃ በደረጃ እየተቀረፉ የኢትዮጵያ ገጽታ መለወጥ ይጀምራል፡፡ በየቦታው የሚደረጉ የኃይል መፈታተሾች እንዲያቆሙ የሚያደርጉ ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች ልዩ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ገጽታ እንዲለወጥ በርካታ ሥራዎች የግድ ይላሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል በመላ አገሪቱ ግጭቶችን ማስቆምና ሰላም ማፅናት፣ በኑሮ ውድነት ምክንያት በዜጎች ላይ እየተንሰራፋ ያለውን ድህነት ግስጋሴ መግታት፣ ለሥራ ፈጠራ የሚረዱ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ማቀድ፣ የከተማን ገጽታ ከመለወጥ ጋር ለዜጎች ባለአነስተኛ በጀት የቤት መሠረተ ልማቶች ላይ ማተኮር፣ አገራዊ አንድነቱንና ትስስሩን የሚያናጉ ፖለቲካዊ ትርክቶችን ፈር ማስያዝ፣ ለሕግና ለሥርዓት ቅድሚያ መስጠት፣ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማክበርና ማስከበር፣ ለፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ፀር የሚሆኑ ብልሹ አሠራሮችንና ሙስናን ከሥራቸው ነቅሎ መጣል፣ አድሎኦና ማግለልን ማስወገድና ለአገር ሰላምና ለሕዝብ ደኅንነት በጋራ ተባብሮ መሥራት የሚያስችል ምኅዳር መፍጠር የግድ መሆን አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ገጽታ ከግጭት፣ ከምፅዋት ጠባቂነትና ከተስፋ ቢስነት ጋር ተጣብቆ መቀጠል የለበትም፡፡

በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ ችግር ሆኖ የሚስተዋለው የመተማመን መጥፋት ነው፡፡ እርግጥ ነው በብዙ አገሮች በተለይም ሠልጥነዋል በሚባሉት ጭምር የመተማመን ስሜት እያደር በጣም እየቀዘቀዘ ነው፡፡ ዜጎች በአብዛኛው መንግሥታቶቻቸውን አያምኑም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በምርጫ ጊዜ የተገባ ቃል ስለማይከበር ነው፡፡ በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ፣ በእስያም ሆነ በአፍሪካ በመንግሥታትና በሕዝብ መካከል ያለው ግንኙነት ከመቼውም ጊዜ በላይ እየሻከረ ነው፡፡ በኢትዮጵያም በተለይ ግጭቶች በሚካሄዱባቸው አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ አካባቢዎች በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ልዩነቶች ሰፍተው ይታያሉ፡፡ የምርጫ ጊዜ ሲደርስ ብቻ ሕዝብን በቃላት ከማማለል በላይ፣ በሁሉም አገራዊ ዕቅዶችና ውሳኔዎች ተሳትፎ ሲገደብ ቅሬታና ተቃውሞ ይፈጠራል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ለአገር ሰላምም ሆነ ገጽታ ግንባታ ስለማይጠቅም ቆም ብሎ ችግሮችን ለመቅረፍ መሞከር ያዋጣል፡፡

ኢትዮጵያ በአኅጉርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በልዩ ልዩ ክንውኖች ለመሳተፍ ወደ አደባባዩ ብቅ ስትል፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ ከጥያቄዎቹ መካከል የሚጠቀሱት የአገሪቱ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ፣ የሰላምና የፀጥታ ሁኔታ፣ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያላት ተፅዕኖ ፈጣሪነት ደረጃ፣ ለአገር ውስጥና ለውጭ ኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗ፣ ለሚዲያና ለሐሳብ ነፃነት የምትሰጠው ክብርና መሰል ጉዳዮች ናቸው፡፡ ከዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እስከ ተለያዩ የመብትና ነፃነት ድርጅቶች ድረስ ይዘዋቸው የሚቀርቡ ሪፖርቶች፣ ዘገባዎችና ትንታኔዎች ከላይ የተጠቀሱትን ጉዳዮች በስፋት ስለሚዳስሱ በአገር ገጽታ ላይ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ፡፡ አሁን ያሉ አገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን በቅጡ በመገምገም የሚስተዋሉ ችግሮችን ማረም የግድ ነው፡፡ ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ›› እንደሚባለው ኋላ ማጠፊያው ማጠሩ አይቀርም፡፡

ኢትዮጵያ በሁሉም ዜጎቿ የጋራ ጥረትና ፍላጎት መሠረት መራመድ የሚያስችላት ሥርዓት ቢዘረጋላት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ እመርታ የማሳየት ዕምቅ አቅም ያላት አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያን ከማናቸውም ዓይነት ፍላጎትና ዓላማ በላይ በማድረግ አገራዊ ትስስሩን ማጠናከር ከታቻለ ምንም የሚያግድ ችግር አይኖርም፣ ቢኖርም በጋራ ጥረት ይቀረፋል፡፡ ወደ ዓለም አደባባይ ክንድን አስተባብሮ መቅረብ ሲቻል የሚያዳግቱ ችግሮች በሙሉ በየተራ ይወገዳሉ፡፡ አንዱ በሌላው ላይ የበላይ በመሆን አገር መለወጥም ሆነ ማሳደግ እንደማይቻል በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ኢትዮጵያ ማደግም ሆነ መለወጥ የምትችለው ልጆቿ እንደ ታላቁ የዓድዋ ድል በአንድነት ሲነሱ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ አሁንም አያቅትም፡፡ ኢትዮጵያን ከግላዊና ከቡድናዊ ፍላጎት በላይ ማድረግ ሲቻል የገጽታ ለውጥ ይፈጠራል፡፡ ልዩነትን ይዞ ለኢትዮጵያ ዘለቄታዊ ሰላምና ጥቅም መተባበር አያቅትም!     

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ትርፍ ቢያገኝም የውጭ ምንዛሪ ገቢው ቅናሽ ማሳየቱ ተጠቆመ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የውጭ ምንዛሪ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...