Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከአፍሪካ አገሮች ጋር የንግድ ልውውጥ ለማካሄድ የታሪፍ ማሻሻያ እየተዘጋጀ መሆኑ ተነገረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ስምምነቱ ተግባራዊ ሲደረግ ኢትዮጵያ ልታጣ የምትችለው ገቢ እየተጠና ነው ተብሏል

ኢትዮጵያ በፈረመችው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት መሠረት፣  ምርቶች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ፣ ከታሪፍ ነፃ የሚደረጉበት የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ለማፀደቅ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ብሔራዊ የመተግበሪያ ስትራቴጂን በተመለከተ፣ ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎ ነበር፡፡

ለአፍሪካ አገሮች የገበያ ትስስር ለመፍጠር ከስድስት ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ. 2018 በሩዋንዳ ኪጋሊ የተደረገውን የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት እ.ኤ.አ. በ2019 የፈረመችው ኢትዮጵያ፣ ከ5,800 በላይ የአፍሪካ አገሮች ምርቶችን ከታሪፍ ነፃ ገብተው እንዲሸጡ መስማማቷ ይታወሳል፡፡

ይህንን የስምምነት ክፍል ተግባራዊ ለማድረግ የገንዘብ ሚኒስቴር የታሪፍ ማሻሻያውን በሕግ ደረጃ በማዘጋጀት፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ለማፀደቅ እየሠራበት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ተግባራዊ የማድረግና የመደራደር ኃላፊነት የተሰጠው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የታሪፍ ማሻሻያው የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ በጋዜጣ እንዲታተምና በአፋጣኝ ተግባራዊ እንዲረዳ ፍላጎት መኖሩን በሚኒስቴሩ የዓለም አቀፍና ቀጣናዊ የንግድ ትስስር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታገስ ሙሉጌታ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ሆኖም የታሪፍ ማሻሻያውን የማዘጋጀት ሥልጣን የተሰጠው የገንዘብ ሚኒስቴር በሕግ ማዕቀፍ ደረጃ እያዘጋጀው መሆኑን፣ ይህም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ እንዲፀድቅ እየተሠራበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አገሪቱ ከዚህ ቀደም ከሱዳንና ከደቡብ ሱዳን ጋር የነፃ ንግድ ቀጣና መሰል ስምምነቶችን ፈርማ እንደነበር፣ እ.ኤ.አ. ከ2016 ጀምሮ ግን በነፃ ንግድ ቀጣና ድርድር ውስጥ መቆየቷን የገለጹት አቶ ታገስ፣ በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ የስምምነቱ ሒደቶች አገሪቱ ካሏት የንግድ አሠራር ሥርዓቶች ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ ለማድረግ ጥረቶች እየተካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በአሥር ዓመታት ውስጥ በአፍሪካ አገሮች የተመረቱ 97 በመቶ ምርቶች ከታሪፍ ነፃ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ስምምነት ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ ይህን ግን በየዓመቱ በሚደረግ የማሻሻያ ሒደት ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ 

በነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነቱ ሦስት በመቶ በሚሆኑ ምርቶች ላይ የታሪፍ ማሻሻያው ተግባራዊ እንደማይደረግ፣ ወይም ከታሪፍ ነፃ እንደማይደረጉ ስምምነት ላይ መደረሱ አይዘነጋም፡፡ እነዚህ ምርቶች 193 ያህል ሲሆኑ ሲመረጡም በዋናነት የመንግሥትን የገቢ ግብር ከማስጠበቅ፣ በአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶች ከመሆናቸው፣ እንዲሁም ለጤና ያላቸውን ጉዳት ታሳቢ በማድረግ መሆኑን መሪ ሥራ አስፈጻሚው አብራርተዋል፡፡

ከአፍሪካ አገሮች ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች መጠን አምስት በመቶ ሲሆን፣ ለአፍሪካ አገሮች የሚላከውም አገሪቱ በአጠቃላይ ለውጭ ገበያ ከምታቀርባቸው 20 በመቶ ያህሉ ብቻ መሆናቸው ይገለጻል፡፡ ሆኖም ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነቱ ተግባራዊ ሲደረግ በተወሰነ ደረጃ የግብር ገቢ ልታጣ እንደምትችል ይነገራል፡፡ ምን ያህል ታጣለች በሚል ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው አቶ ታገስ፣ መጠነኛ ገቢ ልታጣ እንደምትችል ቢገመትም በሚኒስቴሩ በኩል ጥናት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

አሁን እየተሠራበት ያለው የትግበራ ስትራቴጂ፣ ‹‹ከነፃ የንግድ ቀጣናው የሕግ ማዕቀፍ ጋር እንዲጣጣሙ ለማድረግ፣ የኢትዮጵያ የትኞቹ ሕጎች መሻሻል ይገባቸዋል? መሻሻልስ ካለባቸው እንዴት ይሻሻሉ? የሚለውን ለመመልከት የሚረዳ ነው፤›› ያሉት በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የጥናት ቡድን መሪ ሙሉጌታ ጌጡ (ዶ/ር)፣ ስምምነቱ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ሊገጥሙ የሚችሉ ጉዳዮችን መመልከት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

‹‹የተሻለ ዕድል ልናገኝበት የምንችለውን አሠራር መዘርጋ ከቻልን፣ ስምምነቱን መፈረም ብቻውን ውጤት ሊያስገኝ አይችልም፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች