Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና የፀረ ሙስና ሥራዎች አፈጻጸም በዕቅድም ሆነ በውጤት ወጥነት የጎደላቸው ናቸው ተባለ

 የፀረ ሙስና ሥራዎች አፈጻጸም በዕቅድም ሆነ በውጤት ወጥነት የጎደላቸው ናቸው ተባለ

ቀን:

  • ከ857 ሺሕ በላይ ሠራተኞችና አመራሮች ውስጥ ሀብት ያስመዘገቡ ከ21 በመቶ በታች ናቸው ተብሏል

በፌዴራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽኖች በአራት የተለያዩ ዘርፎች በ2016 ዓ.ም. የተያዙ ዕቅዶችም ሆነ የተመዘገቡ ውጤቶች ወጥነት የጎደላቸው መሆናቸው ተገለጸ።

በአስቸኳይ ጊዜ ሙስና መከላከል፣ የአገር አቀፍ የሀብት ማሳወቂያና ምዝገባ መረጃ፣ የጥቅም ግጭት መከላከልና የሀብት ማጣራት፣ እንዲሁም የሕግ ማዕቀፍና የመመርያ ማውጣትና ማስፈጸም ሥራዎች በዋናነት የተቀራረበ ውጤት አልታየባቸውም ከተባሉት ዘርፎች ተጠቃሽ ሆነው ቀርበዋል።

ይህ የተገለጸው ሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽኖች አገረ አቀፍ ፎረም አሥረኛ ዙር ጉባዔ ውይይት በአዳማ ከተማ ኃይሌ ሪዞርት ሆቴል ሲካሄድ ነው።

በዕለቱ በፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የአስቸኳይ ሙስና መከላከል ዘርፍ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገዛኸኝ ጋሻው ያቀረቡት የዘርፉ ሥራ አፈጻጸም ውጤት እንደሚያሳየው፣ በበጀት ዓመቱ የመሬት፣ የግዥ፣ የሠራተኞች ቅጥርና ዕድገት፣ ገቢ አሰባሰብ፣ የጨረታ አሸናፊ የመወሰን ሒደት በግብር፣ ከማዳበሪያና ከዕርዳታ እህል ሥርጭት ጋር በተያያዙ ሥራዎች ላይ ሌሎችም በዓይነት ተዘርዝረው ከቀረቡ ሊደርሱ ከነበሩ ጉዳቶች በተጨማሪ፣ በመንግሥት ላይ 2.08 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ የሙስና ወንጀል ድርጊት ሙከራዎች በተደረገ ክትትል በሒደት ላይ እያሉ ማስቆም ተችሏል።

በየደረጃው በክልልም ሆነ በከተማ አልያም በፌዴራል ደረጃ በሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ የልማት ድርጅቶችና ሕዝባዊ ድርጅቶች ሙስና ከመፈጸሙ በፊት አስቀድሞ ሒደት ላይ እያለ ክትትል በማድረግና በመድረስ ሒደቱን በማቋረጥ፣ የመንግሥት ሀብትና ንብረት ከብክነት ማዳን ላይ የሚሠራው በዚህ ንዑስ ክፍል አፈጻጸም ሲገመገም ትግራይና አፋር ክልሎች ምንም ዓይነት ውጤት ሳያስመዘግቡ መቅረታቸው ተገልጿል።

የትግራይ ክልል በሪፖርት አፈጻጸም ወቅት ከ178.9 ሚሊዮን ብር በላይ በአስቸኳይ የሙስና መከላከል ዘርፍ መዳን የቻለ የሕዝብ ሀብት ተብሎ አስመዝግቦ የነበረ ቢሆንም፣ ነገር ግን የተገለጸው ሀብት በወንጀል ምርመራና ክስ ሒደት ያለፈ በመሆኑ በቀድሞ መከላከል ዘርፍ ውጪ እንዲሆን መደረጉ ተገልጿል።

ከዚህ ባሻገር በክልሉ በቅድመ ክትትል ማዳን ስለተቻለ ሀብት ሪፖርት የማሰባሰቡ ሥራ በወቅታዊ ሁኔታዎች፣ በበጀት እጥረት፣ በክልሉ የቅድመ ማጣራትና ክትትል፣ እንዲሁም የምርመራና የክስ ሥራው ተደበላልቆ የሚከናወን ስለሆነ ተለይቶ ሪፖርት ማቅረብ እንዳልተቻለ፣ ከትግራይ ክልል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የመጡ ተወካይ ማብራሪያ ማቅረባቸውም በሪፖርቱ ተካቷል።

በሌላ በኩል በአፋር ክልል ስላለው ሁኔታ ዝርዝር ማብራሪያ ያልሰጡት አቶ ገዛኸኝ በጥቅሉ፣ ‹‹በንዑስ ፕሮግራሙ ሥር የተከናወነ ሥራ የለም፤›› ሲሉ በመግለጽ አልፈውታል።

ከእነዚህ ሁለት ክልሎች ባሻገር ከፍተኛውን የአስቸኳይ ሙስና መከላከል ሥራ በዓመት ውስጥ በ346 ጉዳዮች ላይ ጥናት ማካሄዱ የተገለጸውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽንን በመከተል፣ የአዲስ አበባውን ፀረ ሙስና ኮሚሽን 317 ጥናቶች፣ የፌዴራሉ ፀረ ሙስና ኮሚሽን 102 ጥናቶች፣ እንዲሁም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 86 ጥናቶችና የኦሮሚያ ክልል ኮሚሽን 78 ጥናቶች ማካሄዳቸው ተገልጿል።

በተቃራኒው ዝቅተኛ መጠን ያለው የአስቸኳይ ሙስና መከላከል ሥራዎች ደግሞ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፀረ ሙስና ኮሚሽን አራት፣ በሐረሪ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽን ስድስት፣ በሶማሌ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሰባት፣ በጋምቤላ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽን አሥር፣ እንዲሁም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽን የተካሄደው 12 ጥናቶች ተጠቃሾቹ ናቸው።

በአጠቃላይ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን አፈጻጸም አስመልክቶ በፌዴራል ደረጃ የዘርፉ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገዛኸኝ፣ ‹‹የአስቸኳይ ሙስና መከላከል ሥራ ያለው አረዳድና የአሠራሩም ሆነ የአደረጃጀቱ ሁኔታ ወጥነት የለውም፤›› ብለዋል።

‹‹ሥራው ከሌሎች ሦስት ሥራዎች ጋር ተቀላቅሎ የሚሠራበት አካሄድ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ አንድ የሚያደርግ አሠራር ቢኖር አልያም ደግሞ ተቀላቅለን በወጥነት የምንሠራበት አካሄድ ቢፈጠር የሚል ጥያቄ በሁሉም ክልሎች በሚባል ደረጃ በውይይት ወቅት ተነስቷል፤›› በማለት አስረድተዋል።

የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ በማሳያነት የተጠቀሰው፣ የሐረሪ ክልል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ በ1999 ዓ.ም. የወጣ መሆኑንና 17 ዓመታት ስላለፉት ማሻሻል ያስፈልገዋል ተብሏል።

አቶ ገዛኸኝ፣ ‹‹የአስቸኳይ ሙስና ክፍል አደረጃጀት አንድ ዓይነት እንኳን ባይሆን፣ ተቀራራቢ ቢሆንና በሰው ኃይል ቢሟላ የሚል ጥያቄ በሁሉም ክልሎች የተነሳ ነው፤›› ብለዋል።

ሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. የኮሚሽነሮች፣ የምክትል ኮሚሽነሮች፣ የአመራሮችና የተጋባዥ ባለድርሻ አካላት ውይይት ላይ ሌላ አጀንዳ ሆኖ የቀረበው የጥቅም ግጭት መከላከልና የሀብት ማጣራት ጉዳይ ሲሆን፣ በዚህ ዘርፍም የአፋር ክልል ከሪፖርት ውጪ ሆኖ ተገኝቷል።

የዚህን ዘርፍ ሪፖርት ያቀረቡት የፌዴራሉ ኮሚሽን ተወካይ በአፋር ክልል የሀብት ምዝገባ ክልላዊ አዋጅ ለክልላዊ መንግሥቱ ካቢኔ ቢቀርብም ያልፀደቀ በመሆኑ፣ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

የሐረሪ ክልል በበኩሉ በ2016 በጀት ዓመት 20 የሀብት ማጣራት ሥራዎችን ለማከናወን ቢያቅድም፣ በበጀት እጥረት ምክንያት አንዱንም ሳይሠራ ማሳለፉ ተነግሯል።

የፌዴራል ኮሚሽን የሙስና መረጃ አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፈረዳ ገመዳ ያቀረቡት የሀብት ማሳወቂያና ምዝገባ መረጃም፣ በዘርፉ ውስጥ የሚካተቱ ባለድርሻ አካላት መካከል ያለው ቅንጅት እንደየክልሉ እንደሚለያይና አንዳንዶች ዘንድ ጠንካራ ሌሎች ጋ ደግሞ ደካማ ሆኖ መገኘቱ ተገልጿል።

በዘርፉ አደረጃጀት በኩል በጥቅም ግጭት፣ በሀብት ማረጋገጫና በሀብት ምዝገባ መካከል በየኮሚሽኑ ያለው አደረጃጀት ተመሳሳይ እንዳልሆነ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ለምዝገባ ሥራው የሰላምና የፀጥታ ችግሮች፣ የበጀት እጥረት፣ የተደራጀውን መረጃ ለማሳወቅ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች እጥረትና የሕግ ማዕቀፍ የሌለባቸው ክልሎች አፈጻጸም ጉዳይ ክፍተቶች ሆነው መገኘታቸው ተብራርቷል።

በአቶ ፈረዳ የቀረበውና ሳይገኙ ከቀሩ ከደቡብ ምዕራብ ክልል ተወካይ ውጪ ከአገሪቱ ኮሚሽኖች በተውጣጡ 15 ተወካዮች በተቋቋመ የቴክኒክ ኮሚቴ ተደራጅቶ የቀረበው የሀብት ማሳወቂያና ምዝገባ መረጃ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ በመላ አገሪቱ 855,807 የመንግሥት ሠራተኞችና አመራሮች ሀብታቸው እንዲመዘገብ የተለዩ ቢሆንም፣ ሀብታቸው የተመዘገበው ግን 175,627 ሠራተኞችና አመራሮች ብቻ መሆናቸውን ማለትም ከተለዩት 20.5 በመቶው ብቻ ናቸው።

አቶ ፈረዳ፣ ‹‹በአጠቃላይ ሀብታቸውን ለመመዝገብ ከታቀደው 176,412 ሠራተኞችና አመራሮች አንፃር ሲታይ አፈጻጸሙ 99 በመቶ ነው። ነገር ግን ይህ ከልየታ አንፃር ሲታይ ሀብት ምዝገባው ላይ እየተሠራ አይደለም፤›› ብለዋል።

‹‹ይህ በመረጃ ዕድሳትም፣ ከማቋረጥም ወይም ከልየታም አንፃር ሊሆን ይችላል። ግን ልየታው በራሱ አሁንም ያለቀ አይመስለኝም፤›› ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ ሁኔታ የሀብት ምዝገባና ማሳወቅ ሒደቱ አንዳንዴ በአመራር ሌላ ጊዜ በሠራተኛ ዘርፍ፣ በየክልሉና ከተማ አስተዳደሩ አጠቃላይ ሒደቱ ተመሳሳይ አለመሆኑን የሚያመላክት መሆኑን በኮሚሽኖቹ ተወካዮች ውይይት ወቅት መነሳቱንም ጠቁመዋል።

በየኮሚሽኖቹ ያሉ አደረጃጀቶች የተለያዩ መሆናቸውን የሚያስመዘግቡት ውጤትም እንዲሁ ወጣ ገባነት እንዳለው ተጠቅሷል። ለአብነትም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፀረ ሙስና ኮሚሽን ለዚህ ዘርፍ ራሱን የቻለ ዳይሬክቶሬት ማቋቋሙ የተገለጸ ሲሆን፣ ሀብት በትክክል የማያስመዘግቡንም ወይም ለማስመዝገብ የዘገዩን ተጠያቂ የማድረግ ሥራ መጀመሩን አስረድተዋል።

በዚህም በከተማ አስተዳደሩ 190 ተመዝጋቢዎች በአስተዳደራዊ ቅጣት ተቀጥተው የተመዘገቡ መሆኑን፣ በዚህም 190,000 ብር ገቢ ማስገባቱ ተነግሯል። እንዲሁም ወደ 33 የሚሆኑ ሠራተኞች የሀብት ምዝገባ ሒደት ጥያቄ በማስነሳቱ ለፍትሕ አካላት ክስ መላኩ ተገልጿል።

በሌላ በኩል በአፋር ክልል ሒደቱን ለማስፈጸም የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ፣ 52,000 ሠራተኞችና አመራር ሀብት ለመመዝገብ ልየታ ቢያከናውንም በተግባር ግን ምንም ዓይነት ሥራ አለማከናወኑ ተገልጿል።

በትግራይ ክልል ደግሞ 15,000 ሠራተኞችና አመራሮች ለመመዝገብ ልየታ ተከናውኖ፣ በበጀት ዓመቱ 3,000 ለመመዝገብ ዕቅድ ቢያዝም 1,603 ብቻ መመዝገብ እንደተቻለ ተገልጿል። እንደ አቶ ፈረዳ ገለጻ ይህ የሆነው ዕቅዱን ለማሳካት ከፍተኛ የበጀት እጥረት በማጋጠሙ ነው።

በጋምቤላ ክልል በልየታ 27,335 ሠራተኞችና አመራሮች ዝርዝር መካተቱ ሲገለጽ፣ በዕቅድ 7,026 ተይዟል ማስፈጸም የተቻለው ግን 2,951 ሠራተኛ አመራር የሀብት ምዝገባ ነው ተብሏል።

አቶ ፈረዳ፣ ‹‹በጋምቤላ የፀጥታ ችግር በብዛት እንዳለና ተረጋግቶ መሥራት ችግር እንደሆነ ነው፤›› ብለዋል። ባቀረቡት ሪፖርትም የፀጥታ ችግሮች በአማራ፣ በጋምቤላና በትግራይ ክልሎች ፈተና መደቀናቸውን ይጠቅሳል።

ሰኞ ዕለት በቀረቡ ጥናቶችና ቀጥሎም በተደረጉ ውይይቶች ተገቢው አደረጃጀት አለመኖር፣ የሙስና መረጃዎች ብክነት ማለትም በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል አለመቻል፣ የሙስና መረጃዎች ውጤት አለመረጋገጥ ወይም መረጃዎችን ለሚመለከተው አካል ከተመሩ በኋላ የደረሱበትን ተከታትሎ ማረጋገጥ ላይ ያለ ክፍተት፣ ቅንጅታዊ አሠራር አለመኖር፣ ቀልጣፋ የጥቆማዎች ቅበላ አለመኖር፣ እንዲሁም በነባራዊ ሒደት አብዛኞቹ ኮሚሽኖች ከሙስና ወንጀል ጥቆማ ባለፈ ለፍትሕ አካላት የተላለፉ ጉዳዩች ላይ ያላቸው ሚና ውስን መሆን ከተጠቀሱ ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል ናቸው።

በኮሚሽነሮች፣ በምክትል ኮሚሽነሮችና በአመራሮች መካከል ጉዳዩን በተመለከተ በተደረገው ውይይት የተገለጹትን ግኝቶች በመያዝ ነባራዊ ኩነቶችን ከግንዛቤ ያስገቡ ዕቅዶችንና አሠራሮችን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ከመግባባት ላይ መድረስ መቻላቸው በውይይቱ ተገልጿል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...