Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአዲስ አበባ ምትክ ቦታ ያልተሰጣቸው የልማት ተነሺዎች መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠየቁ

በአዲስ አበባ ምትክ ቦታ ያልተሰጣቸው የልማት ተነሺዎች መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠየቁ

ቀን:

  • ‹‹አንድም ሰው ምትክ ቦታ ወይም ካሳ ሳያገኝ ከቦታው አልተነሳም›› የየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየካ ክፍለ ከተማ ከመለስ ፋውንዴሽን ወደ አዋሬ (አቧሬ) የሚወስድ መንገድ ለመገንባት በቀድሞዎቹ ቀበሌ 23፣ 18 እና ቀበሌ 19 (በአሁኑ ወረዳ 6) በግንፍሌ ወንዝ ግራና ቀኝ የሚገኙ ባለይዞታዎች (ነዋሪዎች)፣ ገሚሶቹ ያለ ማስጠንቀቂያ፣ የካሳ ግምትና ተለዋጭ ቦታ ሳይሰጣቸው መኖሪያ ቤታቸው መፍረሱን፣ የተወሰኑት ደግሞ ባልታሰበ ጊዜ እንደሚፈርስ ተነግሯቸው፣ ከፍተኛ ሐሳብና ችግር ላይ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡ የፈረሰባቸው በዘመድ ቤት፣ በቀበሌ አዳራሽና ወጣቶች ማዕከል ውስጥ አንድ ላይ ታጉረው እንደሚገኙም አክለዋል፡፡

በተለምዶ አዋሬ የሚባለውን አካባቢ ጨምሮ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች የልማት ተነሺ የሆኑ ባለይዞታዎች፣ ምትክ ቦታ ባለማግኘታቸው በዘመድ ቤት ተጠግተው እየኖሩ እንደሆነ በምሬት ተናገሩ፡፡

በአዋሬ ጤፍ ሠፈር አካባቢ ሕጋዊነት ያለው የግል ይዞታ ያላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች፣ መንግሥት በልማት ምክንያት እንዲነሱ ካደረጋቸው በኋላ ምንም ዓይነት ካሳ ወይም ተለዋጭ የምትክ ቦታ እስካሁን ስላልተሰጣቸው፣ ዘመድ ቤት ተጠግተው ለመኖር መገደዳቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ለረዥም ዓመታት በአካባቢው መኖራቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ መንግሥት ‹‹ቦታው ለልማት ይፈልጋል›› በማለት የአንድ ሳምንት የዝግጅት ጊዜ ሳይሰጣቸው ቤታቸውን በላያቸው ላይ ማፍረሱን ገልጸዋል፡፡

በአዋሬ ለረዥም ጊዜ በመኖር አካባቢውን ያቀኑ መሆናቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የሚመለከተው አካልም ሆነ መንግሥት፣ የደረሰባቸውን ችግር በማየት አፋጣኝ ተለዋጭ ቦታ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

‹‹ጤፍ ሠፈር›› ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከ50 ዓመታት በላይ የኖሩ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ እናት፣ ከበፊት ጀምሮ ግዴታቸውን በመወጣት ግብር ይከፍሉበት የነበረውንና ሕጋዊነት ያለው 475 ካሬ ሜትር ይዞታ መንግሥት ነጥቆኛል ይላሉ፡፡

መንግሥት ከሚኖሩበት ቤት እንዲወጡ ካደረጋቸው አንድ ወር መቆጠሩን፣ እስካሁን ‹‹ተለዋጭ ቦታ ይሰጣችኋል ቆዩ›› መባላቸውን እንጂ ቦታ እንዳልተሰጣቸው ያስረዳሉ፡፡

ችግራቸው እንዲታይላቸው የአካባቢውን ወረዳም ሆነ ክፍለ ከተማውን መጠየቃቸውንና እስካሁን አጥጋቢ ምላሽ እንኳን እንዳላገኙ ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት በጣም ችግር ውስጥ ሆነው ዘመድ ዘንድ ተጠግተው እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን አነስተኛ ቤቶች ያከራዩ እንደነበር፣ አሁን ግን ሁሉ ነገር ተገላቢጦሽ እንደሆነባቸውና የዕለት ጉርሳቸውን ካስጠጓቸው ሰዎች እያገኙ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ በአካባቢው ለ30 ዓመታት በመኖር ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ደጉንና ክፉውን አሳልፈናል የሚለው ወጣት ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ መንግሥት የኮሪደር ልማት ብሎ ሲነሳ ታሳቢ ማድረግ የነበረበት ጉዳዮች ሊኖሩ ይገባ ነበር ይላል፡፡ በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ሆነው ሕጋዊ የቦታ ይዞታ ያላቸውን ሰዎች እንዴትና የት ማድረግ አለብኝ የሚለውን ማሰብ ነበረበት ሲልም ያስረዳል፡፡

በአዋሬ አካባቢ በርካታ አቅመ ደካማ አረጋውያን እንዳሉና ለአብነትም የእሱ እናት ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጾ፣ በአንድ ወይም በሁለት ቀናት ልዩነት ውስጥ ዕቃችሁን አውጡ ቤታችሁ ሊፈርስ ነው መባላቸውን ገልጿል፡፡

የመኖሪያ ቤታቸው የአየር ካርታ እንዳለውና በወረዳው የሚታወቅ መሆኑን የሚገልጸው ወጣቱ፣ በአሁኑ ወቅት አቅመ ደካማ እናቱን ይዞ አካባቢው በሚገኝ የወጣት ማዕከል ተጠለሉ መባሉን ያስረዳል፡፡

‹‹የአየር ካርታ ያላቸው ነዋሪዎች ተተኪ ቦታም ሆነ የካሳ ክፍያ አያገኙም፤›› የሚል ጭምጭምታ መስማቱን፣ በአካባቢው በእንዲህ ዓይነት መሰል ጉዳይ ቤታቸው የፈረሱ ሰዎች ቅሬታቸውን ለወረዳውም ሆነ ለክፍለ ከተማው ማስገባታቸውን ይናገራል፡፡

በተለይ መጪው ወቅት ክረምት መሆኑ በርካታ ሰዎችን እንዳሳሰበ የሚናገረው ወጣቱ፣ መንግሥት ይህንን ታሳቢ አድርጎ በልማት ለተነሱ የአካባቢው ነዋሪዎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ይኖርበታል ብሏል፡፡

ከ50 ዓመታት በላይ ወልደው፣ ከብደውና ልጆቻቸውን አሳድገው ብዙ ማዕረግ ያዩበትን ሁለት ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ቤታቸውንና ድርጅታቸውን በሦስት ቀናት ውስጥ አፍርሱ መባላቸውን የገለጹት፣ የቀድሞ ቀበሌ 23 (ወረዳ 6) ነዋሪ እናት ሲሆኑ፣ ልማቱን እንደማይቃወሙ፣ ነገር ግን ሕጉን የጠበቀ ግምትና ምትክ ቦታ፣ እንዲሁም ጊዜያዊ ቢሆንም መቆያ ቦታ ከእነክራዩ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ መንገዱ የሚወስደውን ቦታ ከግምት በማስገባትም ቀሪው ቦታ ላይ ፕላኑን የጠበቀ ግንባታ እንዲያካሂዱ እንዲፈቀድላቸውም ጠይቀዋል፡፡  

በሌላ በኩል ከመገናኛ ወደ ሰሚት አካባቢዎች በሚወስደው መንገድ በርካታ የግል ይዞታ ያላቸው ነዋሪዎች መነሳታቸውን ባለይዞታዎች ተናግረዋል፡፡  

በእነዚህ አካባቢዎች የተነሱ ነዋሪዎች ተለዋጭ ቦታም ሆነ የካሳ ክፍያ እንዳላገኙ፣ በልማት ተነሱ በተባሉበት ወቅት አንዳንድ እናቶች በድንጋጤ ለጭንቀትና ለተለያዩ በሽታዎች የተጋለጡ መሆናቸውንና ይህም በተለያዩ አካባቢዎች መፈጠሩን ምንጮች ተናግረዋል፡፡

በአዋሬ አካባቢም ሪፖርተር ተዘዋውሮ እንደተመለከተው ከሆነ፣ በቀበሌ ቤት የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ወደ ጉራራ፣ የካ አባዶና ላፍቶ አካባቢ የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እንዲሠፍሩ ተደርጓል፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤት የማይፈልጉና የቀበሌ ቤት ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ነዋሪዎች ደግሞ በጊዜያዊነት በአካባቢው በሚገኝ ወረዳና የወጣቶች ማዕከል እንዲጠለሉ የተደረገ ሲሆን፣ መንግሥት በአካባቢው እየሠራቸው ያሉ ቤቶች ግንባታ ሲያልቅ ሙሉ ለሙሉ ወደ መኖሪያ ቤቶቹ እንደሚገቡ ታውቋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ የየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታደለ በቀለ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአዋሬ አካባቢ ትክክለኛ ይዞታ ያላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተለዋጭ ምትክ ቦታና የካሳ ክፍያ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

በአዋሬ አካባቢ የተጀመረው የመልሶ ማልማት እንጂ የኮሪደር ልማት አለመሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፣ በአካባቢውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሰጡት አቅጣጫ መሠረት በጣም የተጎሳቆሉ ቤቶችን በማንሳት ሌላ ቤት እንዲሰጣቸው የማድረግ ጅማሮ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው የግል ይዞታ ያላቸው ነዋሪዎች አራራት በሚባል አካባቢ ምትክ ቦታ እንደተሰጣቸው ገልጸው፣ ለእነዚህ ሰዎች ቤት ሠርተው እስኪጨርሱ ድረስ ለሁለት ዓመታት የሚሆን የቤት ኪራይ ክፍያ ጭምር እንደተሰጣቸው አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በፊት የዕቃ ማጓጓዣ እንጂ እንዲህ ዓይነት ክፍያ መንግሥት አከናውኖ እንደማያውቅ አስታውሰው፣ በአካባቢው የቀበሌ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የኮንዶሚኒየም ወይም የቀበሌ ቤት ከፈለጉ እንደ ምርጫቸው እየተስተናገዱ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

እስካሁን ምን ያህል የካሳ ክፍያ ተከፍሏል? ምን ያህል ሰዎችስ ተነስተዋል? ተብሎ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ ኃላፊው በሰጡት መልስ፣ ‹‹እስካሁን በቁጥር ምን ያህል እንደሆነ አልታወቀም፡፡ ነገር ግን በተሻለ መንገድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየሠራበት ያለ ጉዳይ በመሆኑ፣ አንድም ሰው ጎዳና ላይ አልወደቀም፤›› ብለዋል፡፡

የግል ይዞታ ያላቸው ሰዎች ሕጉ በሚፈቅደው መንገድ እንዲዳኙ በማድረግ ቦታ ለሚሰጣቸው ቦታ በመስጠት፣ የካሳ ክፍያም ለሚያስፈልጋቸው የካሳ ክፍያ እንዲሰጣቸው እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ከቀበና እስከ ዳያስፖራ አደባባይ፣ እንዲሁም በላይኛው በኩል ከመገናኛ እስከ ሲቪል ሰርቪስ ድረስ ያለው ቦታ ጨምሮ ክፍለ ከተማው የሚመለከተው መሆኑንና በእነዚህ ቦታዎች ብቻ የሚገኙ ሰዎች በኮሪደር ልማት እንደተነሱ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...