Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየዕውቀት ፍቅርና ጥማት ያገናኛቸው አባ ጎርጎርዮስና ኢዮብ ሉዶልፍ እነማን ናቸው?

የዕውቀት ፍቅርና ጥማት ያገናኛቸው አባ ጎርጎርዮስና ኢዮብ ሉዶልፍ እነማን ናቸው?

ቀን:

‹‹ለአባ ጎርጎርዮስ ኢትዮጵያዊ በሮምያ ለምትገኘው

ከናንተ ጋር በሮምያ ከተማ በነበርኩ ጊዜ ታላቅ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ ከናንተ ተለይቼ በሄድኩ ጊዜ ግን ሐዘንና ትካዜ አድሮብኛል፡፡ እንደ ጓደኛዬ እወዳችኋለሁ፡ እንደ አባቴም አከብራችኋለሁ፡፡ ጓደኝነታችሁ ከማር የጣፈጠ፣ ፍቅራችሁም በብዙ ዋጋ ከሚሸጠው ዕንቁ የከበረ ነው…››

ይህን የደብዳቤ ቃል በ1649 ዓ.ም. በወርኃ ሐምሌ በፓሪስ ሆኖ የጻፈው ጀርመናዊው ሂዮብ ሉዶልፍ ነው፡፡ ሉዶልፍ ደብዳቤውን የጻፈው መምህሩ አባ ጎርጎርዮስ ባስተማሩት የግእዝ ቋንቋ ነው፡፡ ይህ ከላይ ለተጻፈው መነሻውና ወደ አማርኛ በከፊል የተመለሰው ግእዙ እንዲህ ይላል፡፡

‹‹ለአባ፡ ጎርጎርዮስ፡ ኢትዮጵያዊ ይእዜ፡ በሮምያ፡፡

በከመ፡ በፍሥሓ፡ ዓቢይ፡ ኮንኩ፡ ምስለክሙ፡ በሮምያ፡ ከማሁ፡ በሐዘን፡ ወትካዝ፡ ሖርኩ፡ እምኔክሙ፡፡፡ አፍቀርኩክሙ፡ ከመ፡ ዐርክየ፡ ወአክበርኩክሙ፡ ከመ፡ አቡየ፡፡፡ ዕርክትክሙ፡ ጥዑም፡ እመዐር፡ ወፍቅርክሙ፡ ክብርት፡ እምዕንቊ፡ ዘብዙኅ፡ ሤጡ፡፡፡…››

የዕውቀት ፍቅርና ጥማት ያገናኛቸው አባ ጎርጎርዮስና ኢዮብ ሉዶልፍ እነማን ናቸው? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ሲምፖዚየም ተሳታፊዎች
የፎቶ ዓውደ ርዕ

ደቀመዝሙሩና መምህሩ (ተማሪውና አስተማሪው) በግእዝ የተጻጻፉትን ደብዳቤዎች በዓውደ ርዕይ ኅብረተሰቡ ይመለከተው ዘንድ የቀረበው፣ አዲስ አበባ የሚገኘው የጎተ ኢንስቲትዩት በወርኃ ሰኔ የተወለደውን የኢዮብ ሉዶልፍ 400ኛ ዓመት አስመልክቶ ግንቦት 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ጥናት ወዳጆች ማኅበር (ሶፊ) ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ሲምፖዚየም ላይ ነው፡፡ ሉዶልፍ፣ ከመምህሩ አባ ጎርጎርዮስ ካሰባሰበው መረጃ በመነሳትና በጥንታዊ ብራናዎች ላይ ባደረገው ጥናት፣ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ስለ ኢትዮጵያ የሚናገሩ የተለያዩ መጻሕፍትን አሳትሟል፡፡

በሲምፖዚየሙ ስለ ኢዮብ ሉዶልፍና አባ ጎርጎርዮስ ሥራዎች ጥናታዊ ዳሰሳን፣ የታሪክ ተመራማሪው፣ ሽፈራው በቀለ (ፕሮፌሰር) በ17ኛው ምዕት ዓመት ስለሚነሳው የዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ መሠረቶችና ዘላቂ ትሩፋቶቹ፣ የዕፀዋትና የብዝኃ ሕይወት ተመራማሪው ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር) በኢትዮጵያ ዕፀዋትና እንስሳት ላይ ሉዶሎፍ ስለሠራው ሥራ፣  የፊሎሎጂ ተመራማሪው አባ ዳንኤል አሰፋ (ዶ/ር) የሉዶልፍ የግእዝ መዝገበ ቃላትና ሰዋስው ከኢትዮጵያዊ አቀራረቦች አንፃር አቅርበዋል፡፡

የዕውቀት ፍቅርና ጥማት ያገናኛቸው አባ ጎርጎርዮስና ኢዮብ ሉዶልፍ እነማን ናቸው? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የፎቶ ዓውደ ርዕይ

ኢዮብ ሉዶልፍ ማን ነው?

ከሲምፖዚየሙ መድረክ እንደተገኘው ሉዶልፍ በኤርፈርት በ1624 ተወልዶ በኤርፈርት ዩኒቨርሲቲ ተምሮ ሕክምና እና ሕግ እንዲሁም የምሥራቃዊ ቋንቋዎችን እንደ ዓረብኛ፣ ሱርስጥ (ሲሪያክ)፣ ግእዝ እና ዕብራይስጥ ተምሯል። ከተመረቀ በኋላ ወደ ላይደን፣ ኦክስፎርድና ሌሎች ታዋቂ የአውሮፓ ጥናት ማዕከላት በመሄድ ሠርቷል። በመጨረሻም በፈረንሳይ የስዊድን ኤምባሲ ሲቀጠር አምባሳደሩ የስዊድን ንግሥት አንዳንድ መዛግብትን እንዲመረምር በ1649 ወደ ሮም በላከው ጊዜ ከኢትዮጵያዊ ከአባ ጎርጎርዮስ ጋር ተገናኝቷል፡፡

ሉዶልፍ በሮም ይኖሩ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን መነኮሳት ጋር ባደረገው ግንኙነት በጣም በመመሰጡ ነበር ስለ ኢትዮጵያ ለማጥናት ያለው ፍላጎት የጨመረው። የግእዝ እውቀቱንም አዳብሮ ብዙም ሳይቆይ በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት ባለሙያዎች ከግንባር ቀደሞቹ አንዱ ለመሆን በቅቷል። ‹‹የኢትዮጵያ ጥናት መሥራች›› የሚል ስም ያተረፈው ሉዶልፍ በጣም ዝነኛ ሥራ በ17ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ የታተመው “Historia Aethiopica” ሲሆን፣ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ታሪክና ባህል አጠቃላይ ጥናት ነው። ይህ ሥራ ካጠናቸው የእጅ ጽሑፎች (ብራናዎች)፣ በዚያን ዘመን ከነበሩ ጽሑፎች ያገኘው ዕውቀትና አባ ጎርጎርዮስ ከሰጡት መረጃ የተመሠረተ ነው፡፡ ጎርጎርዮስ ለጀርመናዊው ምሁር ስለ ኢትዮጵያ ባህልና ቋንቋ በዋጋ የማይተመን ዕውቀት አስጨብጠውታል።

የዕውቀት ፍቅርና ጥማት ያገናኛቸው አባ ጎርጎርዮስና ኢዮብ ሉዶልፍ እነማን ናቸው? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ሉዶልፍ ለኢትዮጵያ ጥናት ያበረከተው አስተዋፅኦ በቋንቋና በታሪክ ብቻ የተገደበ አይደለም። ስለ ኢትዮጵያ ሃይማኖትና ጥበብ፣ ስለ አገሪቱ ዕፀዋትና እንስሳት ጽፏል። ከዚህም በላይ የኢትዮጵያን የእጅ ጽሑፎችና ጽሑፎች ሰብስቦ ተርጉሟል። ሥራዎቹ የኢትዮጵያን ባህልና ታሪክ ለአውሮፓው የስኮላርሺፕ ዓለም ለማስተዋወቅና ወደፊት ተመራማሪዎች ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን እንዲያጠኑ መንገድ መጥረጉ ተወስቷል።

ሉዶልፍ በጉዳዩ ላይ በርካታ ሥራዎችን አሳትሟል። በጣም ታዋቂ ሥራዎቹ የግእዝ ሰዋስው ግራማቲካ ኤቲዮፒካ /Grammatica Aethiopica/ (1661)፣ የግእዝ ላቲን መዝገበ ቃላት ሌክሲኮን ኤቲዮፒኮ- ላቲኑም /Lexicon Aethiopico- Latinum/ (1699) እና የኢትዮጵያ ታሪክ ኮመንታሪዩስን ሂስቶርየም ኤቲዮፒካም /Commentarius and Historiam Aethiopcam/ (1681) ይገኙበታል። በጀርመን ጥሪው ሂዮብ ስሙን በግእዝ ሲጽፍ ግን እንደ ኢትዮጵያ አጠራር ‹ኢዮብ› እያለ ነው፡፡ ለምሳሌ ‹‹ዘኢዮብ፡ ሉዶልፍ፡ መዝገበ፡ ቃላት፡ ዘልሳነ፡ ግዕዝ፡ ዘውእቱ፡ ልሳነ፡ መጽሐፍ፡ ዘኢትዮጵያ›› የተሰኘው መጽሐፉ ማሳያ ይሆናል፡፡

እነዚህ ሥራዎች በኢትዮጵያ ጥናት ዘርፍ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደሩና ሉዶልፍ በዚህ አካባቢ ከዋነኞቹ ምሁራን አንዱ እንዲሆን ረድተዋል።

አባ ጎርጎርዮስ ማን ናቸው?

ስለ አባ ጎርጎርዮስ በሲምፖዚየሙ አጋጣሚ የተዘጋጀውና በድረ ገጽ ላይ የወጣው ዜና ሕይወታቸው እንደሚገልጸው፣ በ16ኛው ምዕት ዓመት መገባደጃ የተወለዱት መካነ ሥላሴ ከሚባል መንደር (በአሁኑ ወቅት በደቡብ ወሎ ወረኢሉ ከተማ አቅራቢያ) ሲሆን፣ ታዋቂው መካነ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የሚገኝበት ነው። ፍርስራሹም ዛሬም ይታያል። ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት በነበረው ዘመን ዛሬ በደቡብ ወሎ የተሸፈነው ግዛት ቤተ አምኃራ ተብሎ ይጠራ ነበር።

ጎርጎርዮስ ወደ ካቶሊክ እምነት ከመግባታቸው በፊት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ታዋቂ ሊቅ እንደነበሩ ይታመናል። ገና በለጋ ዕድሜያቸው በጣና ሐይቅ በጣም ዝነኛ ጥንታዊ ገዳማት ውስጥ በአበምኔት ማገልገላቸው ይወሳል፡፡ የሚሲዮናውያን መሪ የነበረው ፓኤዝ ጸሐፊ አድርጓቸው እንደነበረ፣ ይህም የብቃታቸው ምልክት መሆኑ ተጠቅሷል።

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍል በ1966 ዓ.ም. ‹‹አማርኛ ለኮሌጅ ደረጃ የተዘጋጀ›› የሚል መማሪያ ጥራዝ ውስጥ ስለ አባ ጎርጎርዮስ ታሪክ እንዲህ ተገልጿል፡፡

 ‹‹ጎርጎርዮስ በ‹አምሐራ አውራጃ በተለይም በመካነ ሥላሴ፣ በዐሥራ ስድስተኛው ምዕት ዓመት መጨረሻ፣ በ1591 ዓ.ም. አካባቢ ተወለደ፡፡ ስለ አስተዳደጉ፣ ስለ ቤተሰቡ፣ የሕፃንነት ዘመኑን እንዴት እንዳሳለፈ… ወዘተ. ምንም የምናውቀው ነገር የለም፡፡ አብሮት ይወለድ ወይም ከጊዜ በኋላ የመጣ ይሁን ለማጠየቅ አልቻለም እንጂ ጎርጎርዮስ አንከስ ይል ነበረ፡፡ ወደ ሮማ ከሄደ በኋላ ለደቀ መዝሙሩ ለኢዮብ ሉዶልፍ በጻፈለት ደብዳቤ ጎርጎርዮስ ስለ ቤተሰቡና ስለ ትውልዱ የሚከተለውን ይናገራል፡፡

‹‹የተወደዳችሁ ወዳጆቼ፣ ቤተሰቤ ወራዳ አይምሰላችሁ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከሚያስተዳድሩ ገዦች፣ ከመሳፍንት፣ ከጦር አበጋዞች፣ ሿሚና ሻሪ የሚሆነው የኢትዮጵያን ንጉሠ ነገሥት ከሚያማክሩ መማክርት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ነው፡፡ የንጉሡ እንደራሴ ሁነው ያዝዛሉ፤ ይገዛሉም፡፡ እኔም ከንጉሡ፣ ከመሳፍንቱና ከመኳንንቱ ጋራ አግባብ ነበረኝ፡፡››

ሉዶልፍ ስለ ጎርጎርዮስ ጠቅላላ ዕውቀትና ስለ ሰውነቱ የሚከተለውን ጽፏል፡፡

‹‹ስለ ሀገሩ ጉዳይ እጅግ ያውቅ ነበረ፡፡ በቤተ መንግሥት ብዙ ጊዜ የቆየ፣ ንጉሡንም እየተከተለ በየቦታው የሄደ ይመስላል፡፡ ንጉሣዊውን ቤተ ሰብና መሳፍንቱን በሚገባ ያውቃቸው ነበረ፡፡ አንደበቱ የረታ፣ ቀልድ አዋቂ፣ ለሁሉም ትሁት የሆነ፣ የደስ ደስ ያለው ሰው ነው፡፡ የጠየቁትን ሁሉ ሳይሸሽግ ይናገራል፡፡ ያለውን መጽሐፍ ሁሉ ይሰጠኝ ነበር፡፡ እኔም ሊያውቅ ስለሚፈልገው ስለ አውሮፓ ጉዳይ አጫውተው ነበር፡፡››

ጎርጎርዮስ የነበረበት የአሥራ ስድስተኛው ምዕት ዓመት ማብቂያና የአሥራ ሰባተኛው ምዕት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ብጥብጥና ሕዝባዊ ጦርነት የሠፈነበት፣ የዘመኑ ንጉሠ ነገሥት አፄ ሱስንዮስ (1599 -1624) የካቶሊክ እምነት የተቀበሉበት ነበር፡፡ እሳቸው ወርደው ልጃቸው ፋሲል ሲነግሥ (1624-1660) እና ‹‹ፋሲል ይንገሥ፣ ሃይማኖት ይመለስ›› ተብሎ ሲታወጅ ኢየሱሳውያኑም በ1625 ዓ.ም. ከአገር እንዲወጡ ሲደረግ ጎርጎርዮስም አብሯቸው ተሰደዋል፡፡ ሮማ (ቫቲካን) በሄዱበትና በኢትዮጵያው የእስጢፋኖስ ገዳም በተቀመጡ ጊዜ ነው ከኢዮብ ሉዶልፍ ጋር በ1641 ዓ.ም. መጨረሻ የተገናኙት፡፡

‹‹ጎርጎርዮስ ከኢትዮጵያ፣ ሉዶልፍ ከጀርመን አንደኛውን ሃይማኖቱ አሰድዶት፣ ሁለተኛውን የዕውቀት ፍቅር አገብሮት ሁለቱም በሮማ ከተማ ተገናኙ፡፡›› ይላል ጽሑፉ፡፡

ስለ መጀመሪያ ግንኙነታቸው ሉዶልፍ የሚከተለውን ጽፏል፡፡ ‹‹የምፈልገውን ነገር ጎርጎርዮስ ከባልንጀሮቹ ስለተገነዘበ ወዲያው ሮጦ ገብቶ እንግዳ በሆነ ስልት የተጻፈ አንድ ታላቅ የብራና መጽሐፍ ይዞ መጣ፤ እንዳነብም አዘዘኝ …በዚህ ከመሣቅ ሊታገዱ አልተቻላቸውም፤ በተለይም ጎርጎርዮስ፡፡ እሱም እንደ አባ አትናትዮስ ነው የሚያነበው አለ፣ ከርቨርን ማለታቸው ነው… ይሁን እንጂ መተርጐም ስጀምር፣ … ያ ቋንቋ ያለ መምህር ሊጠና በመቻሉ ሳቃቸው ወደ አድናቆት ተለወጠ፡፡››

በዚህ ሁኔታ ነበረ ጎርጎርዮስ ሉዶልፍን ግእዝና አማርኛ ሊያስተምሩት የጀመሩት፡፡ ለረዥም ጊዜ ይነጋገሩ የነበረው በአስተርጓሚ ሲሆን ጎርጎርዮስ ጣሊያንኛ በጥቂቱ በማጥናታቸው ይነጋገሩበት ነበር፡፡ ኋላ ግን የሉዶልፍ የግእዝ ችሎታና ዕውቀት እየተሻሻለና እየተስፋፋ ሲሄድ ሁለቱም ጣሊያንኛውን ትተው ይነጋገሩ የነበረው በግእዝ ነበር፡፡

ሉዶልፍ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ወደ አገሩ ወደ ጀርመን ተመለሰ፡፡ ቢመለስም የእሱና የመምህሩ ከጎርጎርዮስ ጋር ደብዳቤ ይጻጻፍ ነበር፡፡ ሁለቱ አያሌ ደብዳቤ ተጻጽፈዋል፡፡

ጎርጎርዮስ ለአገሩ ቀናዒ ነበረ፡፡ ይህን ስሜቱን በአንድ ደብዳቤ ላይ እንደሚከተለው ከልዩ የሐሤት ስሜት በሚመነጭ በስለምን ስልት አግዝፎታል ይላል ኮሌጅ አማርኛ፡፡

‹‹ምድራዊ ገነት የምትመስለው፣ የሰላምና የፍቅር፣ የጤንነትና የደስታ፣ የውበት፣ የፍሩሃነ እግዚአብሔር ምድር፣ የሙት ልጆች እናት፣ የስደተኞች መጠጊያ፣ የድኾች ምግብ፣ የመንገደኛው ማረፊያ የምትሆነው ውዷ የአባቴ አገር ኢትዮጵያ፡፡››

ሉዶልፍ ወደ ሀገሩ ጀርመን ቢመለስም ሮማ ካሉት ጎርጎርዮስ ጋር በደብዳቤ ከመገናኘት ባለፈ አገሩን መጥተው እንዲጎበኙለት ጋብዟቸው በኑርምበርግ ከተማ ተገናኝተዋል፡፡

ሉዶልፍ እንደጻፈውም ‹‹ቀስ በቀስ አገሩን ተላመደው፤ የጀርመን ቢራም መጠጣት ጀመረ፡፡ ብርታቱን እንደሚመልስለት ይናገር ነበረ፡፡ የጀርመኖቹንም ፖለቲካ እየተመለከተ ያደንቅ ነበረ፡፡ ጎርጎርዮስ የጀርመኖችን አስተራረስ፣ የመኸር አከታተት፣ የክረምት ድርቆሽ አሰባሰብ፣ የእነሱም አሠራር ለሀገሩ እንደሚጠቅም ለደቀ መዝሙሩ ያጫውተው ነበር፡፡ በተጨማሪ በጀርመን ያየው የእርሻ ዘዴ ዕፀዋት እያወደመ የምግብ እጥረት፣ የሰውና የከብት እልቂት የሚያስከትለውን አንበጣም ሊያጠፋው እንደሚችል ይናገር ነበረ፡፡

ጀርመኖችንና ሥራቸውን ቢያደንቅም ጎርጎርዮስ በጀርመን አገር ያየውን ሁሉ እንደ ወንጌል ቃል አሜን ብሎ የሚቀበል ሰው አልነበረም፡፡ የሐያሲ ዓይን ነበረው፡፡ በተለይም ስለ ሀገሩ ስለ ኢትዮጵያ የሚጽፉት የውጭ ሀገር ጸሐፊዎች በጽሑፋቸው ውስጥ ስለሚያሳዩት ግልብነት ያዝን ነበረ ይላል የዩኒቨርሲቲው ጥራዝ፡፡  

‹‹አውሮፓውያን የጽሑፍ እከክ ያሳክካቸዋል፤ እውነትም ይሁን ሐሰት ሳያጣሩ የሰሙትን ሁሉ ጽፈው ያትማሉ፡፡ ይህንኑ ጠባያቸውን የሀገሩ ሰዎች አያውቁም ነበረ፡- አውቀው ቢሆን ኑሮ ተርጓሚዎቻችን፣ በትክክል እንዲረዱት የሚጠይቋቸውን ጥያቄዎች በጥንቃቄ ይመልሱ ነበረ፤›› ይል ነበረ፡፡

ለአሥራ ሰባተኛው ምዕት ዓመት አማርኛ በማለፊያ አብነትነት የሚጠቀሰው ግጥሙ እንዲህ ይላል፡፡ ሉዶልፍ በመጽሐፉ ‹‹ዘአባ ጎርጎርዮስ ድርሰት በአምኃርኛ›› በሚል ርዕስ ሥር ነው ያሰፈረው፡፡

ስንቱን፡ ተናግሬ፡ እፈጅ፡ የረዳሽኝ፡ እርዳታ፡

ነገር፡ እያገኘኝ፡ ጽኑዕ፡ ኅብዙኀ፡ ቦታ፡

ሰኣሊተ፡ ምሕረት፡ ማርያም፡ ይፈጀው፡ እንደኈን፡ እንጂ፡ ዝምታ፡

ከጽውሐት፡ ዠምረሽ፣ እስከ፡ ማታ፡

ስምሽን፡ ጸርቼ፡ ብጮኽ፡ ኍለ፡ ግዜ፡ ሐንደ፡ ግዜ፡ ሳትይኝ፡ ቈይታ፡

ወትሮ፡ ስትፈጽሚ፡ ግዳጄን፡ በተርታ፡

እጅጉን፡ ይመስገን፡ እንኪያስ፡ አምላኬ፡ እግዚአብሔር፡ የኍሉ፡ ጌታ፡

ጠበቃ፡ የሰጠኝ፡ አንችን፡ አብስሎ፡ ጸላት፡ ቢነሣብኝ፡ ለፋታ፡

ድኻሜን፡ ዐውቆ፡ እንዳልረታ፡

እንዳገለግልሽ፡ እኔም፡ በተቻለኝ፡ ጾታ፡

እመቤቴ፡ ሰጠኍሽ፡ ማኍታ፡፡

እንደ ኮሌጅ አማርኛ ማብራሪያ፣ ከዚህ በላይ የተጠቀሰው የጎርጎርዮስ ድርሰት የተደረሰው በግጥም ሆኖ የስንኙ ምጣኔ የመውድስ ሐረግ ነው፡፡ ግጥሙ ለእመቤታችን የቀረበ ነው፡፡

የአባ ጎርጎርዮስ ዓውደ ሕይወት በሰባ ፈሪ ዕድሜያቸው ያበቃው እ.ኤ.አ. በ1658 (1651 ዓ.ም.) ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ፣ በሜዲትራኒያን ባህር በአሌፖ ወደብ (በአሁኗ ሶሪያ)  በደረሰባቸው የመርከብ አደጋ ነው፡፡ አሌፖ የሚገኘው የፈረንሣይ ቆንሲልም ማስቀበሩ ተመዝግቧል፡፡

ለአባ ጎርጎርዮስ መታሰቢያ የሚያቆምላቸው ማን ነው?

በውይይት መድረኩ ላይ ከተነሱት ጥያቄዎች አንዱ፣ አውሮፓውያኑ ኢትዮጵያ ላይ ያተኮሩት ለምንድን ነው? የሚለው ነው፡፡ ለዚህ ምላሽ የሰጡት የብዝኃ ሕይወት ተመራማሪው ሰብስቤ (ፕሮፌሰር) አንደኛው ምክንያት ያሉት መንግሥቱ የክርስቲያን መንግሥት ነው ብለው ስለሚያስቡ፣ ‹‹የፕሬስተር ጆን አገር›› (የንጉሡ የካህኑ ዮሐንስ አገር) የሚል አመለካከት መፍጠራቸው ነው፡፡

በተጨማሪም በዓለም ደረጃ ጥሩ ቦታ የሚባሉ እህሎች የሚመረቱባቸው ወይም የተለመዱባቸው ቦታዎች ተብለው ከሚጠቀሱት ኢትዮጵያ በዓለም ካሉት ስምንቱ አንዷ መሆኗ፣ በሜዲትራኒያን አካባቢ ያሉ አገሮችን ጨምሮ ብዙ የምግብ ዕፀዋት ከተፈጠረባቸው/ከተላመደባቸው ውስጥ ስለምትገኝ ኢትዮጵያ ላይ አተኩረዋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የብዝኃ ሕይወት ማዕከል በመሆኗ፣ የግብርና አመራረቷ በጣም የተለየ ስለሆነና ከሌሎች አገሮች ጋር የምትወዳደር በመሆኗ ሕዝቡም የተለየ ዕውቀት የሥልጣኔ መነሻ አለው ብለው ማሰባቸው ነው ኢትዮጵያን ለማጥናት የፈለጉት፡፡

‹‹የሂዮብ ሉዶልፍን 400ኛ ዓመት ዘንድሮ የምናከብረው ከኢትዮጵያዊው ካህን አባ ጎርጎርዮስ ጋር በማስተሳሰር ነው፤›› ያሉት የገተ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ፔትራ ራይሞንድ (ዶ/ር) ስለ ኢትዮጵያ የሚያጠኑ ሁሉ ሁለንተናዊ የሆነውን የኢዮብ ሉዶልፍን አስተዋጽዖ ችላ ማለት አይችሉም ብለዋል፡፡

የሉዶልፍ የግእዝ ላቲን፣ የአማርኛ ላቲን መዛግብተ ቃላት፣ የኢትዮጵያ ታሪክና ሌሎች ኅትመቶች ለቋንቋ፣ ለባህልና ለሃይማኖት ጥናት የማይገመት ዋጋ አላቸው ያሉት ዳይሬክተሯ፣ የኢዮብ ሉዶልፍ ምርምርና ኅትመቶች ያለ ኢትዮጵያዊው መነኩሴና ሊቅ አባ ጎርጎርዮስ እገዛ እውን ሊሆኑ አይችሉም ነበር ሲሉ አስምረውበታል፡፡

 

በመድረኩ አንድ ተሳታፊ በጀርመን ለኢዮብ ሉዶልፍ መታሰቢያ ማዕከል እንደመሠረታችሁት ሁሉ ለአባ ጎርጎርዮስስ ምን ሠርታችኋል ብለው ጠይቀው ነበር፡፡

ዳይሬክተሯ ራይሞንድ ምላሻቸውን በጥያቄ መልሰውታል? ‹‹እናንተስ [ኢትዮጵያ] ለአባ ጎርጎርዮስ ምን ሠርታችኋል? ይህን የመታሰቢያ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ለማካሄድ እንኳን ጠይቀን በጎ ምላሽ አላገኘንም፤›› ብለዋል፡፡

ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉት ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር) እንዳስገነዘቡት፣ ለመሆኑ እኛስ በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው? ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አድርገናል መጠየቅ ያለበት ነው፡፡

ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ ምድር ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ ገጽ ያለው ትልቅ መጽሐፍ እውን ያስደረጉ ስለሆነ ክብር እንደሚገባቸው፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋምም ሊያስባቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ጀርመኖቹም ቢሆኑ አባ ጎርጎርዮስ ከሉዶልፍ ጋር ባንድነት የሚወሱበት ምልክትም በሉዶልፍ ማዕከል ውስጥ ቢያስቀመጡ ጥሩ ነው በማለት ጭምር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...