Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊኑሮ በክረምት

ኑሮ በክረምት

ቀን:

‹‹ሥራ ማስታወቂያ ከሚለጠፍበት ሰሌዳው ፊት ቆሜ

ደግሞ ክረምት መጣ፣ ደግሞ ዝናብ ጣለ አጀብ ነው የእኔ ዕድሜ፡፡…

… አያውቅም ይህ ዝናብ፣ የጎጆዬ ጣራ ሰማይ እንደሆነ

 በክረምቱ መግባት ከሰማዩ ይበልጥ ቤቴ እንደዳመነ

አያውቅም ይህ ዝናብ!

ሲጠብቁኝ ውለው እኔን ተስፋ አድርገው በረሃብ የሚያድሩ

ዓይነ ሥውሯ እማ፣ እግር አልባው አባ ቤቴ እንደነበሩ፡፡››

ይህ ግጥም ዘላለም ምሕረቱ ‹‹እውነትና ክረምት›› በሚል ርዕስ ከቋጠረው ስንኝ ላይ የተቀነጨበ ነው፡፡ በጥቂቱም ቢሆን በክረምት፣ የሕይወትን ገጽታ ሊያሳየን ሞክሯል፡፡

ክረምት፣ ሥርወ ቃሉ ‹‹ከረም፣ ከረመ›› ከሚለው የግዕዝ ቃል ሲሆን፣ ትርጉሙም ወርኃ ዝናብ፣ ወርኃ ነጎድጓድ፣ ዘመነ ባህር፣ ዘመነ አፍላግ፣ ዘመነ መብረቅ ማለት ነው፡፡ ዘመነ ጠል፣ ዘመነ ደመና፣ ዘመነ መብረቅ ማለት ነው፡፡ (ጥዑመ ልሳን ካሳ፣ ‹‹ያሬድና ዜማው›› 1981፣ ገጽ 53)

የክረምት ወራት ተብሎ የሚታወቀው ከሰኔ 26 እስከ መስከረም 25 ያሉት ጊዜያቶች ሲሆኑ፣ ክረምት በባህሪው በከባድ ዝናብና ፅልመት የሚታወቅ ነው፡፡ ሰኔ ግም ሲል ገበሬው ሞፈሩን ተሸክሞ ለእርሻ የሚነሳበት፣ ተማሪውም የዓመቱን የትምህርት ዘመን አጠናቆ ዕረፍት የሚያደርግበትና ወጣቶች በበጎ አገልግሎት ሥራዎች ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን የሚከውኑበት ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የክረምቱን መምጣት ተከትሎ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች በየጎዳናውና ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች እንደ በቆሎ እሸት፣ ድንች፣ ባቄላና ሽምብራ ያሉ የምግብ ዓይነቶችን እየጠበሱና እየቀቀሉ በትኩሱ ለተጠቃሚው የሚያቀርቡበት ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል ፍቅሬ ማቲዎስ አንዱ ነው፡፡

ፍቅሬ፣ የበቆሎ እሸት እየቀቀለ በሳሪስ ጎዳናዎች ላይ መሸጥ ከጀመረ ሦስት ወራት ሆነውታል፡፡ በዚህም ሥራ ከራሱ አልፎ ገጠር የሚገኙ አቅመ ደካማ ቤተሰቦቹን እየደገፈ ይገኛል፡፡

የበቆሎ እሸቱን ከመርካቶ በጅምላ እስከ 1,500 ብር እንደሚገዛ፣ አንዱን በቆሎ እሸት ለሁለት በመክፈል እየቀቀለ ግማሹን እስከ 20 ብር እንደሚሸጥ ይናገራል፡፡

ጎዳና ላይ ቀቅሎ በሚሸጠው የበቆሎ እሸት የቤት ኪራይና የምግብ ወጪውን ከመሸፈን ባሻገር፣ በቀን የሁለት መቶ ብር ዕቁብ እየጣለ ይገኛል፡፡

የአንድ ልጅ አባት መሆኑን የሚናገረው ፍቅሬ፣ ልጁ ከቤተሰቦቹ ጋር ክፍለ ሀገር የሚኖር ሲሆን፣ በወር ከ1,000 እስከ 1,500 ብር ይልካል፡፡ ከዚሁ ሥራ ከሚያገኘው ገቢም 4,000 ሺሕ ብር የቤት ኪራይ ይከፍላል፡፡ ገጠር የሚገኙ ቤተሰቦቹ ሕክምና ሲያስፈልጋቸውና ችግር ሲገጥማቸው እየደገፋቸው እንደሚገኝም ይናገራል፡፡

በቀን እስከ 400 ብር ለከሰል ግዥ እንደሚያወጣ የሚናገረው ወጣቱ ቁርስ፣ ምሳ፣ እራትና የዕቁብ ብር ጥሎ ከወጪ ቀሪ ከሁለት እስከ ሦስት መቶ ብር በቀን ያገኛል፡፡

እንደ ፍቅሬ፣ ሰው በብዛት በቆሎ እሸት የሚገዛው በብርድና ቅዝቃዜ በተለይም በክረምት ወቅት ነው፡፡ በበጋ የሰው የመግዛት ፍላጎት እምብዛም ነው፡፡

ውልደትና ዕድገቱ ወላይታ ሶዶ መሆኑን የሚናገረው ወጣቱ፣ ‹‹የአዲስ አበባ ሰው እሸት ይወዳል፣ እኔም እሸት በመሸጥ ራሴን እያስተዳደርኩና ቤተሰቦቼን እየደገፍኩ እገኛለሁ፤›› ይላል፡፡

ክፍለ ሀገር ስለ በግለሰብ ተቀጥሮ በሞተር ሳይክል ዕቃና ሰው ከቦታ ቦታ የማመላለስ ሥራ መሥራቱን፣ በዚህም የሚያገኘውን ገንዘብ በየሳምንቱ ለባለቤቱ እንደሚያደርግ ሆኖም ሥራው ከዕለት ወደ ዕለት በመቀዛቀዙና ሠርቶም ገቢ የሚያደርገው ለቀጣሪዎቹ በመሆኑ ድካም እንጂ ትርፉ ብዙም ስላልነበረ የራሱን ሥራ ለመሥራት እንዲወስን አድርጎታል፡፡

ከተቀጣሪነት በመውጣት የራሱ ገቢ የሚያገኝበትን ሥራ ለመጀመር አዲስ አበባ መምጣቱንና በቆሎ እሸት እየቀቀለ በመሸጥ ሥራ ላይ መሰማራቱን፣ በሥራውም ደስተኛ መሆኑን ይገልጻል፡፡

 በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ‹‹ሃና ማርያም›› እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ያገኘናቸውና የተቀቀለ ድንች በመሸጥ የሚተዳደሩት ሌላዋ አስተያየት ሰጪያችን ወ/ሮ ዚነት መሐመድ ናቸው፡፡

ወ/ሮ ዚነት እንደሚናገሩት፣ በአካባቢው የባቄላ፣ የሽምብራና የገብስ ቆሎ መሸጥ ከጀመሩ ዓመት አልፏቸዋል፡፡ ጊዜው ክረምትና ብርድ በመሆኑ የሰዎች ምርጫ እንደ ድንች ቅቅል ያሉ ትኩስ ነገሮችን ነው፡፡ እሳቸውም ድንች እያዘጋጁ ለተጠቃሚ ያቀርባሉ፡፡

የተቀቀለውን ድንች በበርበሬ (በሚጥሚጣ) እየለወሱ ለደንበኞቻቸው በሳህን በ30 ብር ሒሳብ እንደሚሸጡና ከባለቤታቸው ጥቂት ገቢ ጋር በመደመር ሁለት ልጆቻቸውን እንደሚያሳድጉ ይገልጻሉ፡፡

እንደ ወ/ሮ ዚነት፣ በቀን እስከ 15 ኪሎ ግራም ድንች ይሸጣሉ፡፡ የተጠቃሚው ቁጥርም ከቀን ይልቅ ወደ ምሽት አካባቢ ይጨምራል፡፡

የስምንትና የአራት ዓመት ሴት ልጆች እንዳሏቸው፣ ልጆቻቸውንም ‹‹መጋቢት 28›› የሚባል የመንግሥት ትምህርት ቤት እንደሚያስተምሩ፣ ‹‹ሥራን ሳልመርጥና ሳልንቅ በመሥራት፣ ልጆቼን ለትልቅ ቦታ የማድረስ ፍላጎቴም ኃላፊነቴም ነው፤›› ይላሉ፡፡

‹‹ሠርቶ የሚያድር ሰው፣ ከሰው በታች አይሆንም›› የሚሉት ወ/ሮ ዘሃራ፣ በሚያገኙት ገቢ ኑሯቸውን ሸፍነው እንደሚኖሩ ይናገራሉ፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...