Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ስሜትና ምክንያት!

ሰላም! ሰላም! ያኔ በንጉሡ ዘመን አሳምነው ገብረ ወልድ የሚባል ዝነኛ ጋዜጠኛ የሚያዘጋጀው ‹‹መወያየት መልካም›› የሚባል የሬዲዮ ዝግጅት ነበር አሉ፡፡ በዚህ ዝግጅት ላይ ለአገር ይጠቅማል የተባለ ነገር እየተነሳ ውይይት ይደረግበታል ቢባልም፣ መንግሥትን የሚመለከት ተቃውሞ እንዳይሰማ ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረግ ነበር አሉ፡፡ ይህ የምነግራችሁ ታሪክ ለዚህ ዘመን ትውልድ አስገራሚ ባይሆንበትም፣ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ እንደነገረኝ ከሆነ ብዙዎች ያለፉበት እውነት ነው፡፡ ለነገሩ ዛሬም የመነጋገሪያ ቻናሉ በዝቶ እንጂ፣ በመደበኛው የመንግሥት ሚዲያም ሆነ በፓርቲ ቁጥጥር ሥር ባሉት ሚዲያዎች አሳዳሪን መዳፈር አይቻልም፡፡ የሆነ ሆኖ ግን የሕዝብ ብሶት ሲገነፍል እንዲተነፍስ ሲባል ብዙ ነገር ይወራል፡፡ ድሮም ቢሆን ሕዝቡ ምን እንዳለ ለማወቅ አየሩ ነፃ ይደረግ ነበር ይባላል፡፡ ከዛሬ አንድ ዓመት በፊት ምሽት ቤቴ ጠባብ ሳሎን ውስጥ ተቀምጬ በቴሌቪዥኑ የቀረበው ግን ሰውነቴን ወሮት እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ ‹‹ባለሥልጣናትም ሆናችሁ ባለሀብቶች እናንተ እየበላችሁ እኛ አንራብም…›› ያለው ብሶተኛ ድምፅ ካልተሰማ ምን ሊሰማ ነው ታዲያ ነበር ያልኩት ለራሴ፡፡ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ከራሴ ጀምሮ በኑሮ ውድነት ሳቢያ የሰፊው ሕዝብ ብሶት ጣሪያ ለመንካቱ ብዙ መልፋት አያስፈልግም እላለሁ፡፡ ሁሉም ነገር ፍንትው ብሎ ይታያል!

ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ያኔ በዘመነ ኢሕአዴግ አንድ የነገረኝ ነገር ዛሬም አይረሳኝም፡፡ ‹‹መንግሥትን ተጠግተው እየበለፀጉ ያሉ ባለጊዜዎች ነገር አንድ ካልተባለ ኢትዮጵያ ውስጥ ነውጥ መነሳቱ አይቀሬ ነው…›› ነበር ያለኝ፡፡ እውነት ነው እነ አጅሬ ኢሕአዴጎች መቶ በመቶ ምርጫ አሸነፍን ባሉ በጥቂት ወራት ውስጥ ምድር አርድ ተቃውሞ ተነሳ፡፡ ኢሕአዴጎች ላይ ታች እያሉ ተቃውሞውን ለማዳፈን ቢራወጡም መጨረሻቸው ደርሶ ነበርና ታሪክ ሆኑ፡፡ በተለይ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ቅርብ ወዳጆች እየተፈላለጉ አገር የዘረፉበት ምዕራፍ ሲዳፈንባቸው በዓይናችን አየን፡፡ ግና ምን ይሆናል በእነሱ እግር የተተኩ ሌቦች ያንን አስነዋሪ ታሪክ ለመድገም ጊዜም አልፈጀባቸውም፡፡ ይኸው አሁን ደግሞ ሌብነት፣ የፍትሕ ዕጦትና አስመራሪ የኑሮ ውድነት ሕዝቡን ቀስፈው ይዘውታል፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ታሪክ ራሱን ይደግማል ማለት ይኸው ነው…›› ነበር ያለኝ፡፡ አይደለም እንዴ!

አንድ ምሬተኛ ወዳጄ ደግሞ፣ ‹‹አንበርብር በሕግና በሥርዓት ማስተዳደር ሲያቅት ቦታውን ለተረኛ መልቀቅ የግድ ነው…›› የሚለው አባባል አለው፡፡ እኔ ደግሞ ተረኛ የሚባለው አባባል አይዋጥልኝም፡፡ ማንም እየተነሳ በብሔርና በእምነት የሚቧደንበት ተረኝነት ያበሳጨኛል፡፡ ለአገር አንዳችም እሴት ሳይጨምሩ መሬት እንደ ድፎ ዳቦ እየተካፈሉ የሚበለፅጉ ጅሎች አገር ያጠፋሉ እላለሁ፡፡ ምሁሩ ወዳጄም፣ ‹‹ሠርቶ ማሳየት እየተቻለ ሰርቆ መንጎማለል ነውር ነው…›› ይለኛል፡፡ እኔ በበኩሌ ያለ ልፋት የሚበላ እንጀራ ያቅራል የሚል እምነት ስላለኝ ሌብነት ፀያፍ ነው የምለው፡፡ የሚያፀይፍ ድርጊትን መፀየፍ ያቃታቸው እንምራችሁ ሲሉን ያመኛል፡፡ ቅዱስ መጽሐፉ፣ ‹‹የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው›› ይላል፡፡ እኔም በማይም አንደበቴ፣ ‹‹በመልካም ሥነ ምግባር ታንፆ አገርን ማገልገል ሌላው ጥበብ ነው…›› እላለሁ፡፡ የሰሞኑ ‹‹የሀብት ማስመለስ›› ረቂቅ አዋጅ ብዙዎችን ቢያስደነግጥም፣ እኔ ግን በአግባቡ ከታወጀ ለአገር መድን ነው እላለሁ፡፡ ማንም እየተነሳ በጠፍ ጨረቃ የሀብት ማማ ላይ የሚሰቀልበት ጊዜ ማብቃት አለበት እላለሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ ሕጉ ሁሉንም በእኩል ማየት አለበት፡፡ የሚሰማ ካለ ይስማ!

እስኪ ወደ ሌላው ወጋችን እንመለስ፡፡ ዓረፍተ ነገሩ ሳይቀር ባለቤት አልባ በሆነበት ዘመን፣ ዘንድሮ እኮ አመልካችና ተመልካች ብዙ እየተዛዘብን ነው። ተመልካች እኔ፣ አመልካች ማንጠግቦሽ መሆኗ ነው፡፡ ያለ ልማዷ እስኪ ወሬ እንስማ እያለች ማታ ማታ ዜና ትከፍትብኛለች። ደህና የዋልኩት ሰውዬ ሰምቶ ማለፍ አልችልምና የማይመስል ነገር የሰማሁ ሲመስለኝ ቀይሪው አልቀይርም በሚል ተኳርፈን ማምሸት ነው። ‹‹ሰው ሕገ መንግሥት ይሻሻል እያለ ይወያያል አንተ…›› ብላ ታያይዘኛለች። ሰባ በመቶ የሚሆነው የእኛ ሰው የሚሞተው በማያገባው እየገባ ነው የሚሉ ፖስቶች አንብባችሁ ይሆን? እውነት ያለው አባባል ይመስላል። በሌላውስ እሺ አያገባኝም ብሎ መሸሽ ይቻል ይሆናል፡፡ ገንዘብ ሲሆን ግን ምን ታደርጋላችሁ? ዘላችሁ ‹‹ዳይቭ›› መግባታችሁ አይቀርም። ዋሸሁ? በተለይ ደግሞ እንደ አገራችን ባለግዙፍ አኃዝ የበጀት አመዳደብ ዜና ስትሰሙ የሚያስችላችሁ አይመስለኝም። ከአገር በላይ ምንም የለማ። አለ እንዴ? እና እንዳልኳችሁ አንድ ምሽት እኔና ማንጠግቦሽ ዜና እያየን ነው። የግድ ነዋ!

ለዴሞክራሲያዊ አቅም ግንባታ ይህን ያህል ሚሊዮን ብር ተመደበ ሲባል ያንሳል ብለን አጨበጨብን። ቀጥሎስ? ለትርኪ ምርኪ ነገሮች ይህንን ያህል ሚሊዮን ብር የቁሳቁስ ግብይት መደረጉን ስሰማ ግን በበኩሌ አልዋጥልህ ብሎኝ ጠገብኩ ብዬ ከማዕድ ተነሳሁ። ‹‹የአንተን ትራፊ የሚበላ የለም ጨርስ እንጂ…›› ስባል፣ ‹‹ግዴለም በሚቀጥለው የበጀት ድልድል እጨርሰዋለሁ…›› ስላት ማንጠግቦሽ፣ ‹‹ከደላላነት ይልቅ የፖለቲካ ሰብዕና ግንባታ ጀምረሃል…›› ብላ አኮረፈች። መቼም ይኼ ሚሊዮን የሚባል ስም የማይፈታው ነገር የለም። ብላት ብሠራት ኩርፊያዋን አላቆም አለች። ‹‹ነገ ሁለት ሚሊዮን ብር ኮሚሽን የሚያስገኝ ሥራ አለብኝ ሰላም ስጭኝ…›› ብዬ ቆጣ አልኩ። ኩርፊያዋም ጭቅጭቃችንም ቆመ። እንግዲህ አስቡት? እኔ እንኳን የሚስቴን ኩርፊያ ለማስቆም ሁለት ሚሊዮን ከጠራሁ፣ መንግሥትማ የሕዝብ እንባ ለማበስ ገና ምኑን በጀተው? ይብላኝ ለኦዲተሩ እንጂ!

የገንዘብ ነገር ሲነሳ የሁላችንም ልብ ይንጠለጠላል፡፡ ወሬው ሁሉ የምግብና የሌሎች ሸቀጦች ዋጋ ንረት በሆነበት አገር ውስጥ፣ ገንዘብ የልባችን ምት አካል ባይሆን ነው የሚደንቀው፡፡ ገንዘብ ለማግኘት ሲባል ላቡን ከሚያንጠባጥበው ባተሌ ጀምሮ የአገር ማጅራት እስከሚጠቀልለው ድረስ፣ በዚህ ዘመናችን ብዙ እያየን ለመሆናችን ማስረጃ ፍለጋ መባዘን አያስፈልግም፡፡ በቀደም ዕለት አንዱ ከክፍለ ከተማ እየተናደደ ሲወጣ አገኘሁት፡፡ አስቁሜው ምን እንደሆነ ስጠይቀው፣ ‹‹በቀደም ዕለት እዚያ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ምድረ ሌባ እያልክ ማንን ስታሳጣ ነበርና ነው ዛሬ የመጣኸው ብሎ አንዱ ሹም ከቢሮው አስወጣኝ…›› ሲለኝ፣ ‹‹ምን ነካህ ብልፅግና ፓርቲ ከሕዝቡ በቀረቡልኝ ጥያቄዎች ላይ ተመሥርቼ በዕቅድ ላይ የተመሠረተ ዕርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅቻለሁ አለ እኮ…›› ብዬ ስነግረው ከት ብሎ ሳቀብኝ፡፡ ‹‹አንበርብር ስንት ነገር ታውቃለህ ሲባል አላዋቂ ለምን ትሆናለህ…›› ካለኝ በኋላ፣ ‹‹ሰዎቹ እኮ ላይና ታች ሥራቸው ለየቅል ነው…›› ብሎኝ በቆምኩበት ጥሎኝ ሄደ፡፡ የባሰ አታምጣ!

እንዲያው አንዳንዴ የወሬ አድባር ምን ቢቀየማችሁ አንድ ነገር እንድትሰሙ ወይ እንድታዩ ሳያደርጋችሁ አይውልም። ነገሩን ነው እንጂ እኔም እኛን የመሰለ ወሬ አምላኪ የወሬ አድባር ይቀየመናል ብዬ አይደለም። ይህችን ርዕስ ሁልጊዜ ሳላነሳባችሁ ቀርቼ አላውቅም መቼም። ምን ላድርግ እንዲያው ነገረ ሥራችን ዝም የሚያስብል አልሆን ስላለብኝ እኮ ነው። ሰሞኑን በየሄድኩበት ሰው ሲወያይ የምሰማው ነገር ሁሉ ሊያስቀኝ እየከጀለ፣ መልሶ እያበሸቀኝ እንዲሁ ስቃጠል ሰነበትኩ። በቀደም አንድ ካፌ እንደ አቅሚቲ ሻይ ይዤ ተጎልቼ ወጭ ወራጁን ሳስተውል አጠገቤ የተቀመጡ ሦስት ሰዎች ጨዋታቸው ተጀምሮ እስኪያልቅ የሚገርም ነበር። ልብ በሉ እንግዲህ ሰዎቹ መልሰው መላልሰው ያው አንድ ዓረፍተ ነገር እየደጋገሙ አዛሉኝ። ‹አቤት ሊሞዚን!› ‹አይ ቪኤይት!›፣ ‹ወይኔ መርሴዲስ!› ሲሉ ደጋግመው ድንገት ብው አልኩ። በአንድ በኩል ሕዝባችን ኑሮ እያቃጠለው መድረሻ አጣሁ ይላል፡፡ በሌላ በኩል ቧልተኞች ምንም እንዳልተፈጠረ ያደናብሩናል፡፡ ያደናብራቸውና!

ቆይ እውነት እዚህ አገር ይህን ያህል የወሬ ተነሳሽነት እያለ ቢያንስ ደህና ወሬ የማይወራበት ምክንያት ምንድነው? በዞረ ድምርና በምርቃና ስለሕግ አረቃቅና አወጣጥ የሚያዝጉንን መብለጥ ባለብን ጊዜ፣ የተሻለ ሐሳብና ራዕይ ማዋጣት ባለብን ጊዜ ምንጩ በማይታወቅ ገንዘብ የሚግበሰበስ አውቶሞቢል ብርቃችን ነው? ግዴለም ማውራቱን እናውራ። ምናለበት ካፌውን ሞልተነው የምንውለውን ያህል ቢያንስ ስለመሠረታዊ ችግሮቻችን ውይይት ቢለምድብን? ኧረ የወሬም ጡር አለው፡፡ ‹‹አይ እማማ ኢትዮጵያ፣ እኛ ልጆችሽ ከችግርሽ ብዛትና ከድህነትሽ ጥልቀት የተነሳ የሌቦች ሀብት ቆጣሪ ሆነን እንቅር?›› ያለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው። ‹ተወው የእኛን ነገር›፣ ‹አታንሳ ስለእኛ!› ባዩ በዝቶ ለውጥ ከየት ሊመጣ ነው? ‹ልብህን ማን ወሰደው? ልብህን ማን ሰረቀው? ቁልፉንስ?› ቢሉት አሉ ‹መቼ?› አለ አሉ። ጎበዝ እንዲህ ዓይነት መዓተኞች ናቸው እኮ እግራቸውን አንፈራጠው ለሕመማችን ጭምር መድኃኒት ሊያዙልን የሚቃጡት፡፡ በሽተኞች!

ብቻ በየሄድንበት መላመድ እንችልበታለን። በተለይ ሐሜትና አሉባልታ ከሆነ ፍቅራችን ይደራል። የዘመናችን ወፈፌዎች ወይ አያልፉ ወይ አያሳልፉ ተገትረን ቆመን ልናድር መሆናችን የተገነዘብኩት የሰማሁትን ሰምቼ ስጨርስ ነው። ‹‹እኔ የማውቀው ሕግ የሰው ልጅ አገልጋይና አቅጣጫ ጠቋሚ ሆኖ ነው እንጂ አትለፍ፣ አትቀመጥ፣ አትቁም እያለ የነፃነት ፀር ሲሆን አይደለም…›› ብሎ ሳይጨርስ አንዱ ሌላው ተቀብሎ፣ ‹‹ሁላችንም የምናውቀው እንዲያ ነው ወንድሜ። ይልቅ ሊገርምህ የሚገባው ስንት ከሕግ በላይ መኖር የለመደ ባለበት አገር ተራው ሰው ላይ ጥቃቅንና አነስተኛው ሕግ በርትቶ መተግበሩ ነው። ‹ምንድነው ስትል?› ‹ቢሮክራሲ› ትባላለህ። ይሠሩልናል ብለን የሾምናቸው ሹማምንት እኛ ከኑሮ ጋር የሞት የሽረት ትግል ላይ እንዳለን እያዩና በሞቀ ቤታቸው ተቀምጠው፣ የሕግ የበላይነትን እስከ ማስተማር ይደፍሩናል…›› ብሎ ይናገራል። የቻለ እንግዲህ አደባባይ ወጥቶ ካልተናገረ ማን ይናገር መባል የለበትም እንዴ? አለበት እንጂ!

መሰነባበቻችን ላይ ነን። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ በጥብቅ እፈልግሃለሁ ብሎ ደውሎልኝ ነበር። ወደ ተለመደችዋ ግሮሰሪያችን አመራሁ። ‹‹ምንድነው እሱ?›› አልኩት ገና ከመድረሴ፣ በጤና ስላልመሰለኝ ነው። ጠዋት ሲስቅ ያያችሁት ሰው ማታ ቀብሩን ድረሱ በሚባልበት ጊዜ ጤናውን ካልተጠራጠርኩ ምኑን ልጠራጠር ኖሯል? እንደ ፖለቲካና ኑሮው ከፍ ዝቅ፣ እንደ ኑሮአችን አቋም ከፍ ዝቅ፣ የሰውንም ጤና እንዲህ ነው ብሎ መናገር ከባድ ሆነ እኮ። ታዲያ እንደ ገመትኩት ሳይሆን፣ ‹‹ኧረ ደህና ነኝ። ብቻ የዚህች ግሮሰሪያችን ነገር አስደንቆኝ ነው። ትዝ ካለህ እኛ መምጣት የጀመርን ሰሞን ባዶ ነበረች…›› ሲለኝ፣ ‹‹አሁን ለዚህ ነው እንደዚያ እፈልግሃለሁ ብለህ ስሮጥ የመጣሁልህ?›› ብዬ አኮረፍኩት። አፍንጫዬን ነፍቼ የትም እንደማልደርስ ሲገባኝ ፈገግ ለማለት ፈለግኩ፡፡ ግን እንዴት? ለካ ማስመሰልም ከባድ ነው!

‹‹አንበርብር እኔማ ሰው ያለ አንድ ነገር ባንኮኒ ላይ አይሰየምም የሚል እምነት ስላለኝ፣ ስለዚህ ብሶት ስለወለደው የመጠጥ ገበያ የታዘብኩትን ላካፍልህ ነው…›› አለኝ። ‹‹የምን ብሶት?›› ስለው ከካሌንደር የተሰረዘው ግንቦት ሃያ ትዝ እያለኝ፣ ‹‹የፍትሕ መጓደል ብሶት፣ የቤት ዕጦት ብሶት፣ የኑሮ ውድነት ብሶት፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ብሶት፣ በአጠቃላይ የኑሮና የፖለቲካ ብሶት በዝቷል፡፡ ለመሆኑ ሕግ ሥራ ላይ ቢውል ይህ ሁሉ ብሶት የሚቃለል ይመስልሃል?›› ሲለኝ፣ ‹‹ሥራ ላይ ለማዋል እኮ ፈቃደኝነት ያስፈልጋል…›› አልኩታ ቱግ ብዬ፡፡ ብሶት እንዲህ ያደርጋል እንዴ? ግን ምን ቱግ አስባለኝ? የምን ደርሶ መገንፈል ነው? ‹‹አንበርብር አይዞን፣ ዕርጋታና ማስተዋል የጎደለው ቁጣ ለማንም አይበጅም፡፡ ይልቁንም ብሶት በተደራጀና በሰከነ መንገድ ብልቱ እየተመረጠ ከእነ መፍትሔው ሲቀርብ፣ ለምላሽ የሚጠበቀውን መንግሥትም ነቃ ያደርገዋል…›› ሲለኝ፣ ‹‹ሰዎቹ አልሰማ ብለው በለመዱት መንገድ ሲነጉዱ የምን መለማመጥ ነው…›› እያልኩ ቁጣዬ ሲግል ሳቀብኝ፡፡ ከቁጣዬ በረድ ብዬ የሳቁን ምክንያት ሳሰላስል ለካ አብዝቼዋለሁ፡፡ እኔም የችግሩ አካል እስከሆንኩ ድረስ ለመፍትሔው እፈለጋለሁ አልኩ፡፡ ስለዚህ ስሜት ሳይሆን ምክንያት መቅደም አለበት፡፡ ከዚያ ደግሞ ሙያ በልብ ነው፡፡ ከአጉል ስሜት ምክንያት እንዲሉ፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት