Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊመፍትሔ የራቀው የከተማው ትራንስፖርት

መፍትሔ የራቀው የከተማው ትራንስፖርት

ቀን:

እናት የልጆቻቸውን ልብስ ሲያጥቡ አምሽተው እኩለ ሌሊት ሲሆን ነበር በሥራ ሲባዝን የዋለ ጎናቸውን ያሳረፉት፡፡ በቀጣዩም የሥራ ቀን መነሳት ከነበረባቸው አንድ ሰዓት ዘግይተው ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት ገደማ ከእንቅልፋቸው ይነቃሉ፡፡

ወ/ሮ አስቴር እንዳለ በተደጋጋሚ ከሥራ በማርፈዳቸው ከመሥሪያ ቤታቸው ከበድ ያለ ማስጠንቀቂያ ደርሷቸዋል፡፡ በድጋሚ ካረፈዱ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ከወዲሁ እያሰቡ ነበር የልጆቻቸውን  ቁርስና ምሳ አዘጋጅተው ለመውጣት የተጣደፉት፡፡

‹‹አርፍጄ በመነሳቴ የልጆቼን ምግብ በአግባቡ ሳላዘጋጅ ለራሴም ሳልቋጥር ነው ከቤት የወጣሁት፤›› ያሉት ወ/ሮ አስቴር፣ ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት ከቤት ከወጡ በኋላ አሥር ደቂቃ በእግራቸው ተጉዘው ነበር ረጅሙን የታክሲ ሠልፍ የተቀላቀሉት፡፡

ሰዓቱ እየነጎደ ነው፣ ሠልፉም ከነበረበት ነቅነቅ አላለም፡፡ ወ/ሮ አስቴርም ከመሥሪያ ቤታቸው የሚጠብቃቸውን ቅጣት እያሰቡ በሐሳብ ፈረስ ተጉዘው ከአለቃቸው ጋር እያወሩ ነው ታክሲ የሚጠብቁት፡፡

መደበኛ የሥራ ሰዓትን አሳልፎ በመግባት ሰበብ መደርደር ከአለቃ ግልምጫና ቁንጥጫ አይታደግምና ታክሲ አጥቼ፣ መንገድ ተዘጋግቶና ሠልፉ በዝቶ የሚሉት ምክንያቶች ከመደጋገማቸው የተነሳ በአለቆች ዘንድ ተዓማኒነታቸውን አጥተዋል፡፡

ከካራ እስከ መገናኛ አንድ ሰዓት ገደማ እንደወሰደባቸው የሚናገሩት ወ/ሮ አስቴር፣ ከመገናኛ ሜክሲኮ ለመድረስ ሌላ ውጣ ውረድ ሌላ ሠልፍ እንደሚጠብቃቸው ይገልጻሉ፡፡

‹‹መንገድ ሳይዘጋጋና መደበኛ የትራፊክ ፍሰት በሚኖርበት ወቅት ከ25 ደቂቃ በላይ አይፈጅም ነበር›› የሚሉት እናት፣ ከመገናኛ ሥራ ቦታቸው ሜክሲኮ ለመድረስ እስከ አንድ ሰዓት መጓዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከካራ መገናኛ፣ ከመገናኛ ሜክሲኮ በማቆራረጥ በ3፡30 ደቂቃ በሥራ ገበታቸው ቢገኙም 30 ደቂቃ ማርፈዳቸው አልቀረም፡፡

በሰዓቱ ባለመገኘታቸው ቅጣት ሊጠብቃቸው እንደሚችል በማሰብ ዘወትር እንደሚጨነቁ የሚናገሩት ወ/ሮ አስቴር፣ ከዚህ በኋላ ቅጣቱ ምናልባትም ከሥራ መባረር ከሆነ የልጆቻቸው ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ከሚችሉት በላይ እንደሆነባቸው ይናገራሉ፡፡ 

አርፍደው ሥራ መግባታቸው ብቻ ሳይሆን ቁርሳቸውን ሳይበሉ እየተጣደፉ ከቤት  በመውጣታቸውና ለረጅም ሰዓት ተሠልፈው በመቆየታቸው፣ ሥራቸውን በአዲስ ጉልበት ሳይሆን ድካም በተጫጫነው ሁኔታ ነው እንዲጀምሩ የሚገደዱት፡፡ ከሥራ ሲወጡ የሚጠብቃቸውን ሠልፍና እቤታቸው ስንት ሰዓት ሊገቡ እንደሚችሉ ሲያስቡ ደግሞ ከወዲሁ ድካም እንደሚሰማቸው ያክላሉ፡፡

የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን እንደ ወ/ሮ አስቴር ከንጋት እስከ ምሽት የሚባዝኑ ሰዎች በርካታ ናቸው፡፡

ሰሞኑን ከወትሮው በተለየ በመዲናዋ ረዣዥም የታክሲ ሠልፎች ይታያሉ፡፡ ይህም በተለይ ሠራተኞች በሰዓቱ በሥራ ገበታቸው እንዳያገኙ፣ ወደ ቤታቸው በጊዜ ለመግባትም እንዳይችሉ እያደረገ ስለመሆኑ እየተናገሩ ነው፡፡

መንገዶች ከመዘጋጋታቸው የተነሳ በእግር መሄድን የመረጡ ተሳፋሪዎችም አልጠፉም፡፡ የመንገድ መዘጋጋት ከሥራ ማርፈድ ብቻ ሳይሆን ለድካምና ለተጨማሪ ወጪ እንደሚዳርግ የሚናገሩት አቶ ሀብታሙ ፈለቀ ናቸው፡፡

አቶ ሀብታሙ በሥራ ምክንያት ከሳሪስ ተነስተው እስከ ቦሌ ድረስ መመላለስ የዘወትር ተግባራቸው ነው፡፡ ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት ተነስተው ሦስት ሰዓት ላይ ሥራ ቦታቸው እንደሚደርሱ፣ በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ በሚያስተውሉት የታክሲ ሠልፍ በእጅጉ እንደሚገረሙ ተናግረዋል፡፡

በተለይ ጊዜያዊ ቢሆንም የኮሪደር ልማት ከተጀመረ ወዲህ ያለው የመንገድ መጨናነቅ በጣም የከፋ መሆኑን፣ በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የሚታየው ግርግርና ረዥም የታክሲ ሠልፍ መፍትሔ ካልተበጀለት የሚዘለቅ እንዳልሆነ፣ በተለይ ደግሞ በሥራ ደክመው ውለው የሚጠብቃቸው ሠልፍ ከዋሉበት በላይ እንደሚያደክማቸው ገልጸዋል፡፡

አሽከርካሪዎች በበኩላቸው፣ እየታየ ላለው የትራፊክ መጨናነቅ በዋናነት ሁለት ምክንያቶችን ይጠቅሳሉ፡፡ የመጀመሪያው ከሰሞኑ በመዲናዋ የተከሰተው የነዳጅ እጥረት ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ በኮሪደር ልማት ምክንያት የተለያዩ መንገዶች ዝግ መሆናቸው ነው፡፡

 አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አሽከርካሪ፣ መንገድ ዝግ በመሆኑና ነዳጅም በመጥፋቱ ተሽከርካሪው ተበላሽቷል በማለት ከአራት ቀን በላይ በቤቱ መቆየቱን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

ከዚህ በላይ ሌሎች አሽከርካሪዎችም ሁኔታው ሲያስመርራቸው መቆም ቢፈልጉም፣ የመንገድ ትራንስፖርት እንዲሠሩ ስለሚያስገድዳቸው ብቻ እንደሚመጡ ተናግሯል፡፡

እስከ ምሽት ለመሥራት አስቸጋሪ በመሆኑ እሱን ጨምሮ ሌሎች አሽከርካሪዎች በጊዜ ወደ ቤታቸው እንደሚገቡ የተናገረው ወጣቱ፣ መንገዱ ተስተካክሎና ነዳጅ በበቂ ሁኔታ ከተገኘ እሱም ሆነ የሥራ አጋሮቹ ኅብረተሰቡን ከጠዋት እስከ ማታ ለማገልገል ዝግጁነት አላቸው ብሏል፡፡

 ከትራፊክ መጨናነቅ ጋር ተያይዞ በኅብረተሰቡ የሚነሱ ችግሮች በአንድም ሆነ በሌላም መልኩ ከኮሪደር ልማት ጋር የሚገኙ መሆናቸውን አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የመንገድ ትራንስፖርት ኃላፊ  ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹ችግሮቹ ከኮሪደር ልማት ጋር የተገናኙ በመሆናቸው በዚህ  ዙሪያ ምንም ነገር ማብራራት አልችልም፤›› ሲሉ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...