Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹የሕዝብ ፈንድ ለትምህርት›› ንቅናቄ ይፋ ሆነ

‹‹የሕዝብ ፈንድ ለትምህርት›› ንቅናቄ ይፋ ሆነ

ቀን:

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር በትምህርቱ ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ አጋዥ ይሆናል ያለውን ‹‹የሕዝብ ፈንድ ለትምህርት›› (Go Public Fund Education) ዘመቻ ይፋ አድርጓል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2022 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ያካሄደውን የትምህርት ትራንስፎርሜሽን ጉባዔ ተከትሎ የተቀመጠውን ‹‹የሕዝብ ፈንድ ለትምህርት›› አቅጣጫ ኢትዮጵያ መቀላቀሏ፣ የትምህርቱን ዘርፍ እየተፈተኑ የሚገኙ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያግዝ ማኅበሩ አስታውቋል፡፡

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዘመቻው አካሄድ ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡

እንደ ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ ማኅበሩ ይፋ ያደረገው የሕዝብ ፈንድ ለትምህርት ዘመቻ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ላስጀመሩት ‹‹ትምህርት ለትውልድ›› ንቅናቄ አጋዥ ይሆናል፡፡

የትምህርት ጥራት ደረጃ በእጅጉ ችግር ውስጥ ለመሆኑ ማሳያዎች ስለመኖራቸው ያስታወሱት ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ ለአብነትም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ውጤትን አንስተዋል፡፡

ለውጤቱ ማሽቆልቆል ከመምህራን ጋር የተያያዙት የመምህራን ሥልጠና ክፍተቶችና ተያያዥ ጉዳዮች ዓብይ መሆናቸውን፣ የትምህርት ግብዓት በእጅጉ አሳሳቢ መሆን፣ የትምህርት ቤቶች ደረጃ በሚጠበቀው ልክ አለመሆንና ሥርዓታዊ ችግር እየሆነ የመጣው የተጭበረበረ የትምህርት ማስረጃ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከችግሮቹ ለመውጣት ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ የሚያስፈልግ በመሆኑም ማኅበሩ የበኩሉን ለመወጣት በዕቅድ እየሠራ ሲሆን፣ ሰሞኑን ባካሄደው 11ኛው የትምህርት ጥራት ኮንፈረንስም እንደ ከዚህ ቀደሙ በትምህርት ዙሪያ በምሁራን ጥናቶች አስቀርቧል፡፡

 በኮንፈረንሱ የሚቀርቡ ጥናቶች ለትምህርት አካላትና ለፖሊሲ አውጪዎች እንደሚላክ፣ ሆኖም ጥናቶችን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ አንዳንድ ማሻሻያዎች በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ተግባራዊ አለማድረግ መኖሩን አክለዋል፡፡

ለትምህርቱ ጥራት መጓደል አንዱ ለሆነው የትምህርት ግብዓት እጥረት ገንዘብ እንደሚያስፈልግ፣ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑንና በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ መሳተፋቸውን፣ ሆኖም ትምህርት ቤቶች ካለባቸው ክፍተት አንፃር ማኅበሩ ከ11ኛው የትምህርት ጥራት ኮንፈረንስ ጋር አያይዞ የሕዝብ ፈንድ ለትምህርት ዘመቻ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

ቀጣይነት ባለው በዚህ ዘመቻ ማኅበረሰቡ እንዲገነዘብና እንዲደግፍ፣ ፋብሪካ ከፍተው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠሩ ባለሀብቶችም ከሚያገኙት ሀብት በፍትሐዊነት ለትምህርት ድጋፍ እንዲያደርጉ ማስቻል የዘመቻው አንድ አካል መሆኑን አክለዋል፡፡

በመላ አፍሪካ የትምህርት ጥራት ችግር መሆኑን፣ ከዘላቂ የልማት ግቦች አንዱ በሆነው የትምህርት ዘርፍ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካም ሆነ አንዳንድ የዓለም አገሮች ከሚጠበቀው በታች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሥርዓተ ትምህርቱ መሻሻሉ፣ የትምህርት ግብዓቶች እንዲሟሉ ንቅናቄዎች መጀመራቸው መልካም መሆኑን ተናግረው፣ ከዚህ ጎን ለጎን በሰላም ዕጦት ምክንያት በትምህርት ቤቶች የሚደርሰውን ችግር መቅረፍ፣ በተወሰነ ደረጃ ችግራቸው የተፈቱ በሚመስሉና በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ የማደራጀትና የመገንባት ሥራ መሥራት፣ አሁንም ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ችግር መፍታት ታሳቢ እንዲደረግና በርካታ ችግሮች ቢኖሩም ያለው አማራጭ ትምህርት ስለሆነ ሁሉም ተባባሪ ሆኖ መሥራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

ዮሐንስ (ዶ/ር) ጥናቶችን ዋቢ አድርገው እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ 86.7 በመቶ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸው አንደኛና ሁለተኛ (ዝቅተኛ ዕርከን) ላይ ሲሆኑ፣ ሰባት ትምሕርት ቤቶች ብቻ አራተኛ (ትልቁን) ደረጃን አሟልተዋል፡፡

70.5 በመቶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸው አንድና ሁለት ላይ ሲያርፍ፣ አራት ትምህርት ቤቶች ብቻ የደረጃ አራት መሥፈርትን ያሟላሉ፡፡

የአንዳንድ የትምህርት ቤቶች ገጽታም ቢሆን፣ ተማሪዎችን ለማስተማርም ሆነ ለመምህራን ምቹ አይደለም፡፡ ማኅበሩ በራሱ በኩል ክፍተት ያሉባቸውን ትምህርት ቤቶች እንደ አቅሙ ለማገዝ ከአባላት በተገኘ ገንዘብ 560 ሺሕ ብር በማውጣት ዕገዛ አድርጓል፡፡

የመሠረተ ልማት አለመሟላት፣ የፀጥታ ችግርና የፈንድ እጥረት ዘርፉን ከፈተኑ ተግዳሮቶች ሲጠቀሱ፣ እነዚህን ለመቅረፍ የተጀመሩ ኢንሺየቲቮች ተስፋ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...