Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹ከሁሉ በፊት ሰው ይቀድማል›› ወጣት ቤተልሔም አስፋው

‹‹ከሁሉ በፊት ሰው ይቀድማል›› ወጣት ቤተልሔም አስፋው

ቀን:

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል ብሒል አለ፡፡ ሰው ከወደቀበት እንዲነሳ፣ ከገጠመው ችግር እንዲወጣ፣ ከደረሰበት ሐዘን እንዲፅናናና ከስብራቱ እንዲያገግም የሰዎች ድጋፍና ዕገዛ የግድ የሚል ቀን ይኖራል፡፡ በዚህ ወቅት በጎ፣ ቀና፣ መልካምና ሩኅሩኅ ልብ ያላቸው ሰዎች እንደ ወርቅ ነጥረው ይወጣሉ፣ የግለሰቦችን የመከራ ቀንበር ይሸከማሉ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቁስላቸውንም ያክማሉ፡፡

በሕይወታቸው በጎ በመሥራትና መልካም በማድረግ አቅመ ደካሞችንና ችግረኞችን እየደገፉ ከሚገኙ በርካቶች መካከል ወጣት ቤተልሔም አስፋው አንዷ ናት፡፡

ቤተልሔም የ17 ዓመት ወጣት ስትሆን፣ ነዋሪነቷም በአሜሪካ ቨርጂኒያ ነው፡፡ ‹‹በ2009 ዓ.ም. በአሥር ዓመቴ ከቤተሰቦቼ ጋር ለዕረፍት ወደ ኢትዮጵያ በመጣሁበት ወቅት ጎዳና ላይ የወደቁ፣ የሚለምኑና የተቸገሩ ሕፃናትን ሳይ ውስጤ ተነካ፡፡ ከዚህ ቅፅበት ጀምሮ እነዚህን መሰል ልጆች በምችለው ሁሉ ለመርዳትና ካሉበት ችግር ለማውጣት የድርሻዬን ማበርከት እንዳለብኝ ተሰማኝ፤›› ትላለች፡፡

በወቅቱ ይህንን ሐሳብ ለእናትና አባቷ ስትነግራቸው፣ ‹መልካም ሐሳብ ነው፣ ዕድሜሽ ከፍ ሲል የተቻለሽን ሁሉ ታደርጊላቸዋለሽ› የሚል ምላሽ እንደሰጧትና እንዳበረታቷት ታስታውሳለች፡፡

በ2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል የነበረው ጦርነት በሰዎች ሕይወት ላይ ያስከተለውን ሰብዓዊ ቀውስ ከዜናና ከቤተሰቦቿ ስትሰማ፣ በጦርነቱ ምክንያት ለችግር የተጋለጡትን ወገኖች የምትረዳበትና የምትደግፍበት ጊዜ መሆኑን በመረዳት ለበጎ ሥራ መነሳቷን ትገልጻለች፡፡

በጦርነቱ ምክንያት ለአደጋ የተጋለጡና ችግር ላይ የወደቁ ሕፃናትን ለመደገፍ ድረ ገጽ በመክፈትና ‹‹ጎ ፈንድ ሚ›› በማቋቋም በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ 6,055 ዶላር ማሰባሰብ መቻሏን ትገልጻለች::

ቤተልሔም እንደምትናገረው፣ በሰኔ 2014 ዓ.ም. በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ዘዴዎች ያሰባሰበችውን ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ይዛ መጥታለች፡፡  በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው ደብረ ብርሃን ለሚገኙ 208 ሴቶች ለስድስት ወራት የሚያገለግል የንፅህና መጠበቂያ ፓዶች፣ ሳሙናና የውስጥ አልባሳትን ገዝታ ሰጥታለች፡፡ ለ52 ወንዶችም ለስድስት ወራት የሚያገለግላቸው ሳሙናና አልባሳትን አስረክባለች፡፡

በተጨማሪም ባህር ዳር ለሚገኘው ዘጌ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 982 አጋዥ የትምህርት መጻሕፍትን፣ አንድ ቴሌቪዥን፣ አንድ ዲሽና ሪሲቨር፣ አንድ ዴስክቶፕ ኮምፒዩተርና አንድ ፕሪንተር መስጠቷንም ትናገራለች፡፡

በምትኖርበት አሜሪካ፣ ቨርጂኒያ ግዛት አርባ ኢትዮ አሜሪካውያን ወጣቶችን በማሰባሰብና ክለብ በማቋቋም፣ በየወሩ 10 ዶላር እንዲለግሱ በማድረግ፣ በጦርነት ተፈናቅለው ደብረ ብርሃን የሚገኙ 11 ልጆችን በቋሚነት በየወሩ እየደገፈች እንደምትገኝም አክላለች፡፡

እንደ ወጣቷ፣ የመሠረተችው ክለብ የተቸገሩትን ከመርዳትና ከበጎ ሥራ ባሻገር የኢትዮጵያን ባህል፣ ታሪክ፣ ባህላዊ ምግቦችና ተፈጥሯዊ መስህቦቿን ለሌሎች በማስተዋወቅ ረገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል፡፡

‹‹አሁን ጥሩ ሕይወት በመኖር ላይ እገኛለሁ፡፡ ነገር ግን የዕድሜ እኩዮቼ፣ ሕፃናትና ሴቶች መንገድ ላይ ወድቀው ሳይ አዝናለሁ፡፡ ፈጣሪም የወደቀን እንድናነሳ፣ የታመመን እንድንጠይቅና የተቸገረን እንድንረዳ ፍላጎቱ ነው፤›› ትላለች፡፡

በሰኔ 2016 ዓ.ም. በ‹ጎ ፈንድ ሚ› ያሰባሰበችውን 6,291 ዶላር በ‹ስለ እናት የበጎ አድራጎት ድርጅት› ውስጥ ለሚገኙ ሕፃናትና እናቶች ድጋፍ እንዲውል አድርጋለች፡፡

በድርጅቱ ለሚገኙና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ለሦስት ወራት የሚሆን ጤፍ፣ የዳቦ ዱቄት፣ ዘይት፣ ኒዶ ወተት፣ ሽሮ፣ በርበሬ፣ ደብተር፣ ዳይፐርና የአስቤዛና የንፅህና መጠበቂያዎችን ለግሳለች፡፡

የበጎ አድራጎት ድርጅቱን የመረጠችውም በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ያሉ፣ በተለይም የአዕምሮና የአካላዊ ዕድገት ችግር ያለባቸውን ሕፃናትና እናቶችን የሚንከባከብ በመሆኑ ነው፡፡

‹‹ከሁሉ በፊት ሰው ይቀድማል፣ ለሰው ችግር ቀድመህ ስትደርስ መንፈስህ በደስታ ይሞላል፤›› የምትለው ቤተልሔም፣ ችግር ላይ የወደቁ ሕፃናትና ሴቶችን ለማገዝ ስትነሳ ብዙዎች ዕገዛ አድርገውላታል፡፡ ከእነዚህ መካከል ሮታሪ ክለብ አንዱ መሆኑን ትጠቅሳለች፡፡

ከፍተኛ ትምህርቷን ለመማር የኖርዝ ካሮሊና አት ቻፔል ሂል ዩኒቨርሲቲን  መቀላቀሏን የምትናገረው ቤተልሔም፣ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ የማጥናት ፍላጎት እንዳላት ገልጻለች፡፡

በቀጣይ የራሷን የበጎ አድራጎት ድርጅት በመመሥረት፣ የተቸገሩና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖችን በመላ አገሪቱ እየሄደች ለማገዝ ዕቅድ አላት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...