Wednesday, July 24, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የመስኖ ውኃ አጠቃቀምና አስተዳደር

በዮሐንስ ገለታ (ዶ/ር) እና በሽብሩ ተድላ (ፕሮፌሰር ኤሜሪተስ)

መግቢያ

ሳይንሳዊ አስተሰሰብን፣ ብሎም የሳይንስን ዕውቀት በማኸዘብ (ብዙ ሰው በቀላል መንገድ እንዲገነዘብ ማድረግ)፣ በምክንያት ላይ የተመሠረቱ፣ ብዙ ጠቃሚ ተግባራትን የሚያከናውን ኅብረተሰብ ለመመሥረት ይቻላል፡፡ ለሰው ልጅ ጥቅምን የሚያበረክቱ የቁስ አካል ይዘትና ሁኔታ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መተንተንና ለንባብ ማቅረብ፣ የሳይንሳዊ አስተሳሰባችንን እና ሳይንሳዊ  ዕውቀታችንን ማዳበር ይቻላል፡፡

ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የመስኖ ውኃ አጠቃቀምና አስተዳደር | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የቤዝን መስኖ (Basin Irrigation)

በዚህች ጽሑፍ ስለ መስኖ ውኃ አጠቃቀምና አስተዳደር ስናወሳ፣ ስለአካባቢው በቂ ሳይንሳዊ ግንዛቤ ማንገብ እንደሚገባም እናወሳለን፣ ይህም የሳይንሳዊ አስተሳሰብን ተግባር ያዳብራል፡፡ የሳይንስ ዕውቀታችንን ባዳበርን መጠን፣ የተፈጥሮ ሀብታችን ሥልታዊ አጠቃቀም እናጎላለን፡፡

የመስኖ ልማት ሳይንሳዊ ክንዋኔ

በመሠረቱ ውኃ ከዕፀዋት አካል፣ በአማካይ ከ90% (ከዘጠና በመቶ) ድርሻ አለው፡፡ ውኃ በተፈጥሮ ከብዙ ፈሳሾች በላቀ ሁኔታ ኬሚካላዊ ውሁዶችን የማሟሟት ባህርይ አለው፡፡ ዕፀዋት በውኃ አሟሚነት ባህርይ ታግዘው ነው በስሮቻቸው አማካይነት ተፈላጊ የሆኑ የሚኒራል ግብዓቶችን ከአካባቢው አፈር የሚያገኙ፡፡ እንዲሁም በፀሐይ ኃይል ታግዞ የሚስተናገደው የምግብ ፍብረካው ሒደት፣ ማለት ብርሃን አስተፃምሮ (Photosynthesis) በውኃ አማካይነት ነው የሚተገበር፡፡  

ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የመስኖ ውኃ አጠቃቀምና አስተዳደር | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በትልም / በቦይ / መስኖ (Furrow Irrigation)

ስለ ሒደቱ ያለንን ግንዛቤ እንዲረዱን ሁለት ስንኞችን  (ስለ  ዕፀዋት፣ እንዲሁም ሃመልሚል/ ክሎሮፊል) እናውሳ፡፡

            ዕፀዋት

የሒደቶች ቁንጮ፣ የክስተቶች ታ’ምር፤

ውኃን በቀጭን ሥር፤

ንጥረ-ነገር ካፈር፤

ቀምሮ ለማቅረብ፣ ብሎም ለመመገብ፤

ያ’ለምን በሙሉ፣ የእንስሳት ስብስብ፡፡

ሃመልሚል/ ክሎሮፊል (chlorophyll)  

ሰብስቦ በትጋት፣ አጉዞ በምስጢር፤

በፀሐይ አንጥሮ፣ ምግቦችን መቀመር፤

አካልን መገንባት፤

ሕይወትን ማፋፋት፤

የእንስሳትን ሁሉ፤

በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ (ከበይ ወደ ተበይ)  ሁሉም እንዳመሉ፡፡

ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የመስኖ ውኃ አጠቃቀምና አስተዳደር | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የጠብታ መስኖ(Drip Irrigation)

የምግብ ፍብረካውን የሚያንቀሳቅሰው ኃይል ከፀሐይ ይገኛል፡፡ ጥሬ ዕቃውም፣ ከአየር ካርቦን ዳይኦክሳይድ (CO2) እና ከአፈር (በዕፀዋት ሥሮች አማካይነት) በተገኘ ምጥነላዊ (“ምጥን+ህላዊ”) ንጥረ ምግብ  (nutrient) የዳበረ ውኃ ነው፡፡ የፋብሪካውም ሒደት ብርሃን አስተጻምሮ (Photosynthesis) ይባላል፡፡ ይህ ሒደት አንዱና ዋናው የምድራዊ ተዓምር ሊባል ይችላል፡፡ በተጨማሪ ሕይወትን፣ የእንስሳትንም ሆነ የዕፀዋትን፣ ካለ ውኃ ለማለም ያዳግታል-አካላቸው ውስጥ በብዛት የሚገኘው ውኃ ስለሆነ፡፡ ለዚህም ነው የመስኖ ውኃ ለአዝርዕት ልማት የሚያስፈልገው፡፡

በሕያው አካል የሚካሄዱ ኬሚካላዊ ውህደቶችም ካለ ውኃ ሊታሰቡ አይችሉም፡፡ ውኃ በዕፀዋት አካል ውስጥ የአካል ሙቀት እንዳይንር ይቆጣጠራል፣ እንዲሁም ዕፀዋትን መጋቢ የሆኑ ሒደቶች የአፈር ኬሚካላዊ (Chemical)፣ፊዚካዊ (Physical)  እንዲሁም ሕይወታዊ (biological) መስተጋብሮች  እንዲከናወኑ ያመቻቻል፡፡

ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የመስኖ ውኃ አጠቃቀምና አስተዳደር | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የዝናብ መሰል (Sprinkler Irrigation)

“ተግባረ ረቂቅ” (capillary action) ውኃ በረቂቅ የዕፀዋት ሥሮች አስተናጋጅነት፣ ወደ ዕፀዋት አካል እንዲሰርጉ ያደርጋል፡፡ ውኃ በስርገት (Osmosis) ታግዞ፣ የመሬትን ስበት ተቋቁሞ ነው ወደ ረቂቅ የዕፀዋት ሥራ ሥር የሚገባው፡፡ ሆኖም ቀጣይ በዕፀዋት አካል ውስጥ ያለው የውኃ ጉዞ፣ በዕፀዋት አካል ጋር ውኃ የሚያደርገው “ጥብቀት” (Adhesion)፣ “አሳሪ ኃይል” (Cohesion Force) ተስተናግዶ ነው፡፡  ውኃ እና ንጥረ ነገር (ሚኒራሎች/ Minerals)  አቀባባይ በሆነው አካል “በዛይለም” (xylem) ነው ወደ ላይ ከሚገኙት ዕፀዋት አካል፣ ወደ ቅርንጫፎች፣ ብሎም ወደ ቅጠላ ቅጠል እንዲደርስ የሚደረገው፡፡

የመስኖ ልማት በኢትዮጵያ

የመስኖ ውኃ አስተዳደርን በተመለከተ በአገራቸን ኢትዮጵያ  በተቋምና በግለሰብ ደረጃ ሰፊና በዛ ያሉ የምርምር ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፣ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ እነዚህ ጥናቶች የተከናወኑት በብዛት የውጭ አገር ባለሙያዎችና ውጤታቸውም የቀረበው በውጪ አገሮች ቋንቋ፣ በተለይም በእንግሊዝኛ ቋንቋ መሆኑ፣ የምርምር ውጤቶቹ ወደ ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚዎች በሚፈልገው ደረጃ መድረሰ አልቻሉም። የዚህ ጽሑፍ አንዱ ዓላማ ይህን የተደራሽነት ውስንነት ከመቅረፍ አንፃር አነስተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ፣ የመስኖ ውኃ አጠቃቀምንና አስተዳደርን በተመለከተ የተወሰነ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያለመ ነው። በተጓዳኝም ከላይ እንደተወሳው ሳይንስ ለማኸዘብ የታለመ ጽሑፍ ነው፡፡

የመስኖ ውኃ አሰተዳደርና አጠቃቀም በጥቅሉ ሲታይ የአጠቃላይ ውኃ ሀብት አስተዳደር አካል ሆኖ፣ መለስ ባለ መልኩ ለመስኖ እርሻ ከወንዝ የተጠለፈን፣ በግድቦችና በሌላ የማጠራቀሚያ (ሰው ሠራሽ ኩሬ፣ ታንከሮች) ዘዴዎች የተጠራቀመን፣ ወይም ከከርሰ ምድር (ጥልቅ/ቅርብ ርቀት ካለው ጉድጓድ) የተወሰደን ውኃ፣ በአግባቡ ውጤታማ ሥራ ላይ ማዋልን የሚመለከት ዋነኛ የውኃ ዘርፍ ተግባር ነው። ይህ የመስኖ ውኃ አስተዳደር ከዋና የውኃ ምንጭ የወሰድነውን ውኃ (ለምሳሌ ከወንዝ) በአግባቡ የመጨረሻው የመስኖ እርሻ መሬትና ውኃ ፈላጊው ተክል ዘንድ ማድረስና ተክሉ ውኃን በተፈላጊው መጠን በተፈለገው ጊዜ (በጊዜ ገደብ በተከለለ) በተፈለገ ሁኔታ [መራራቅ (Interval)] ማድረስን ያካተተ ነው።

የአንድ አገር የመስኖ ሀብት የመስኖ መሬትን፣ የውኃ ሀብትንና አልሚውን ማኅበረሰብ የሚያቆራኝ (ያካተተ ነው) ተግባር ነው። በዚህ መሠረት የመስኖ መሬት ሀብታችንን በተመለከተ የተለያየ የውኃ ማቅረቢያን ዘዴ፣ ቴክኖሎጂንና የመሬት ተዳፋትነትን ታሳቢ በማድረግ ጥናቶች  ከ5 እስከ 21 ሚሊዮን ሔክታር ድረስ ያደርሱታል።

የኢትዮጵያ ውኃ ሀብት የአገሪቱን የቆዳ ስፋት ከአንድ በመቶ በታች (0.7%) ብቻ የሚሸፍን ሲሆን፣ ከመስኖ ሀብትነት አንፃር 135 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ (ቢሜኩ) ወራጅ ውኃ፣ 12.5 ቢሜኩ ጥቅም ላይ መዋል የሚችል በተፈጥሮ ሐይቆች የተከማቸ ውኃ፣ 34 ቢሜኩ በሰው ሠራሽ ማጠራቀሚያዎች የተጠራቀመ ውኃ (የህዳሴ ግድብ ታሳቢ ሲደርግ 74 ቢ.ሜ.ኩ ውኃ በተጨማሪነት መያዝ ይቻላል) እና በተጨማሪም 60 ቢሜኩ የከርስ ምድር ውኃ ሀብት አላት (አንድ ሜትር ኪዩብ አንድ ሺሕ ሊትር ነው)።

አሁን የኢትዮጵያ የመስኖ ልማት ሽፋን የደረሰበትን ደረጃ ስንመለከት፣ በትንሹ አለ ከሚባለው አምስት ሚሊዮን ሔክታር አነስተኛ የመስኖ ልማት ሽፋን፣ ስድስት መቶ ሺሕ (600,000) ሔክታር፣ መካክለኛና ከፍተኛ መስኖ ልማት አምስት መቶ ሺሕ (500,000) ሔክታር አካባቢ የሚደርስ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ከአንድ ሚሊዮን ሔክታር ትንሽ ከፍ ባለ መጠን እንደሚደርስ ይገመታል (በኢትዮጵያ አነስተኛ መስኖ ማለት እስከ 200 ሔክታር መሬት የሚሸፍን፣ መካከለኛ መስኖ የሚባለው ደግሞ ከ200 እስከ 3,000 ሔክታር የሚሸፍን፣ እንዲሁም ትልቅ የመስኖ ልማት የሚባለው ደግሞ ከ3,000 ሔክታር በላይ ሽፋን ያላቸውን የመስኖ ልማትን የሚገልጥ ነው)። ይህም የለማው መሬት አለን ተብሎ ከሚታሰበው ከአነስተኛው የመስኖ የመሬት ሀብት አንፃር ከ25 በመቶ ያልበለጠ መሆኑን ያመለክታል።  ይሁን እንጂ ይህን የመስኖ ሽፋን በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ወደ 2.6 ሚሊዮን ሔክታር ለማድረስ ዕቅድ ተይዞ በተግባር በመተርጎም ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ሲሆን የአገሪቱን የመስኖ ልማት ሽፋን ወደ 52 በመቶ ስለሚደር ግብርና ገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ  የሚኖረውን አስተዋፅኦ በከፍተኛ ደረጃ ሊያሳድገው ይችላል።

የመስኖ ልማት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው አቅም ከፍተኛ ነው። የአነስተኛ መስኖ ልማት ለአገሪቱ የእርሻ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) 4.46 በመቶና ለአጠቃላይ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ደግም 1.97 በመቶ አስተዋፅኦ የሚያደርግ ሲሆን፣ መካከለኛና ትልልቅ መስኖዎች ደግሞ ለእርሻ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት 1.26 በመቶ እና ለአጠቃላይ ኢኮኖሚው ደግም 0.5 በመቶ የአገር ውስጥ ምርት አስተዋጽኦ አላቸው። ጠቅለል ብሎ ሲታይ የመስኖ ልማት ውጤት 5.7 በመቶ በእርሻ ላይ  እና 2.5 በመቶ ደግሞ በአጠቃላይ ኢኮኖሚ ውስጥ ድርሻ አለው።

የመ ውኃ አጠቃቀም

በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በኢትዮጵያ የመስኖ ልማት የሰው ልጆችን አሁናዊ የምግብና የኢንዱስትሪ ግብዓት ፍላጎት ከ40 እስከ 50 በመቶ ድረስ የሚሸፍን መሆኑን የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ። ኢትዮጵያን በተመለከተ እየተስፋፋ እየመጣ ያለው የመስኖ ልማት በምግብ ሰብል አገሪቱን ለማስቻል ያለውን ሚና እየጨመረ መምጣቱን ማሳያ ነው። በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመስኖ ስንዴ ልማት የአንበሳውን ድርሻ እየወሰደ መሆኑና ይህ የልማት ክፍል በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል በሚያደርገው ጥድፊያ  ምን ያህል የጎላ ሥፍራ የተሰጠው መሆኑን ያስገነዝባል።

የአነስተኛ መስኖው የአገሪቱን የአትክልትና ፍራፍሬ በተለይም እንደ ሽንኩርት፣ ድንች፣ ቲማቲም፣ ጎመንና ሌሎች ተመሳሳይ አትክልትን ፍላጎት በማሟላት ያለውን ሚና እስካሁን ተኪ አልተገኘለትም። ከዚህ በተጨማሪም የአነስተኛ መስኖ ልማት ለገጠር አካባቢ ማኅበረሰብ፣ በተለይም ለወጣት ሴቶች፣ ትልቅ የሥራ ዕድልን ያበረክታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአነስተኛ ማሳ ላይ ሕይወቱን ለመሠረተው አርሶ አደር ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ይሆናል፣ የተሻለ የአመጋገብ ስብጥር እንዲኖረው ብሎም  ጤናው የተጠበቀ እንዲሆን ይረዳል።

ከላይ ለመጥቀስ የተሞከሩትና  ሌሎች ተጨማሪ ጥቅሞች የመስኖ ልማት የውኃ ፍጆታ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በኢትዮጵያ ከሌሎች የኢኮኖሚ ክፍሎች ጋር ሲወዳደር ከፍተኛ እንዲሆን አድርጎታል። በዓለም አቀፍ  ደረጃ ጥቅም ላይ መዋል ከሚችለው የዓለም የውኃ ሀብት 70 በመቶውን የመስኖ ልማት የሚወስደው መሆኑን የዓለም ባንክ ከአሥር ዓመት በፊት ገደማ የተደረገ የጥናት ሰነድ ሲያሳይ፣ የኢትዮጵያ ሁኔታም ከዚህ የተለየ አይደለም።

አዳዲስ መሬቶች በመስኖ ልማት ተደራሽ እየሆኑ፣ የመስኖ መሬት እየሰፋ ሲሄድ፣ የመስኖ ልማት ውኃ ድርሻ አሁን ካለው ይጨምራል፡፡ ስለሆነም በአነስተኛ የውኃ ሀብታችን ላይ የሚያሳድረው ጫና እየከበደ ይሄዳል፡፡ በተጠቃሚዎች መካከልም የግጭት ምክንያት እየሆነና ተጨማሪ ችግሮችን እየወለደ እንደሚሄድ ይታመናል። ሊከሰት የሚችለውን ችግር ለመቋቋምና የመስኖ ልማት ለሰው ልጆች የሚያበረክተውን (በምግብ ሰብል ራስን መቻልን፣ የኢንዱስትሪ ግብዓትነትን)፣ አዎንታዊ ሚና ከማጎልበት አንፃር የመስኖ ውኃ አጠቃቀም በተገቢ ፖሊሲና አስተዳደር እንዲታቀብ እንዲበረታታ፣ እንዲሁም በቴክኖሎጂና በመስኖ እርሻ ክህሎት እንዲደገፍ ማድረግ ይገባል።

የመስኖ ልማት ያለው ከፍተኛ አወንታዊ ሚና እሙን ቢሆንም፣ የውኃ አስተዳደሩና አጠቃቀሙ ተገቢውን ትኩረት ካላገኘ ግን ጥፋቱም ከፍተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ በመስኖ ማልማት ሒደት፣ ውኃ በአግባቡ አለመጠቀም የእርሻ መሬትን በመሸርሸርና ጨዋማ በማድረግ ማሳን ያመክናል፣ የውኃ ሀብትን ያባክናል፣ በተጨማሪም በሥነ ምኅዳር ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ያደርሳል። በዚህ ምክንያት  ለመስኖ ውኃ ሀብት አጠቃቀምና አስተዳደር ተገቢውን ትኩረት መስጠት ይገባል፡፡ የሚሰጠው ትኩረት ልማቱ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት መግታትና የጎንዮሽ ጉዳቱን መቀነስ ግዴታ መሆኑን መገንዘብን ያካትታል፡፡ ይህም እንዴት እንደሚስተናገድ በዚህ ጽሑፍ በመጠኑ ለመዳሰስ እንሞክራለን።

የመስኖ ውኃን ማሳ ላይ የማቅረቢያ ዘዴዎች

የመስኖ ውኃን ከዋናው ምንጭ (ለምሳሌ ከወንዝ) በማውጣት ማሳ ድረስ ማድረሻ የተለያዩ መንገዶች አሉ። ከእነዚህም አንዱ ክፍት ቦይ (Open Canal) የሚባለው ዓይነት ነው፡፡ ክፍት ቦይ በሁለት መንገድ፣ ማለት አንደኛው ዓይነት በአፈር ብቻ፣ ሁለተኛው ዓይነት ከኮንክሪት ወይም ከግንብ (የድንጋይ ሲሚንቶ አሽዋ ውህድ) የሚገነባ ነው፡፡ አንደኛው ዓይነት (በአፈር ብቻ የሚገነባው ቦይ)፣ ውኃን በቦዩ ወለልና በቦዩ ግድግዳ ወደ መሬት በቀላሉ እንዲሰርግ ያደርጋል፣ ለትነትም ያጋልጣል፣ ስርገትም ሆነ ትነት ውኃው ለተፈለገው ተግባር እንዳይውል ያደርጋል፡፡ እንዲሁም ለመሰበርና ውኃ ለመስረቅ ቀላል ከመሆኑ አንፃር ከፍተኛ የውኃ ብክነት የሚታይበት የውኃ ማጓጓዣ ዘዴ ነው።

ሁለተኛው ዓይነት (በኮንክሪት ወይም በግንብ የታነፀው) ውኃ ማጓጓዣ ዘዴ፣ ውኃ ወደ መሬት መስረግን ያስወግዳል፣ ሆኖም  በትነት የሚጠፋው ውኃ ግን ከአፈር ከተገነባው ቦይ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ በተፈጥሮ ከአነስተኛ እስከ መካካለኛ የውኃ ትነት ለሚከሰትባቸው አከባቢዎች፣ ስርገትን የሚከላከል የኮንክሪት ወይም የግምብ ውኃ ማጓጓዣ ዘዴ ተመራጭ ዘዴ ሲሆን፣ የአፈር ቦዮች ግን በመስኖ ልማት መጠቀም አስገዳጅ ሁኔታ ከሌለ በስተቀር የሚመከሩ አይደሉም።

ሦስተኛው ዓይነት የውኃ ማጓጓዣ የገንዘብ አቅምን፣ የመሬት አቀማመጥንና አካባቢያዊ ሥነ ምኅዳርን መሠረት የሚያድርግ ሲሆን፣ ይህም ሙሉ በሙሉ ውኃን በቧንቧ (ቱቦ) የማስተላለፍ ዘዴ የሚጠቀም የውኃ ማጓጓዣ ነው። ይህ ዘዴ ስርገትን፣ ትነትንና ስርቆትን የሚያስወግድ ውኃ ቆጣቢ የውኃ ማጓጓዣ ዘዴ ነው። ከላይ እንደተወሳው፣ ይህ ዘዴ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ያልበለፀጉ አገሮች ኢኮኖሚያቸውን የሚፈታተን ከመሆኑ አንፃር አስገዳጅ ከሆነበት ቦታ ውጪ ለመጠቀም አዳጋች ነው።

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ያልበለፀጉ አገሮች ከድንጋይ ግንብ የሚሠራውን ወይም የኮንክሪት ቦዮችን በመጠቀም የውኃ ሀብታቸውን ብክነት በመቀነስ በተሻለ ሁኔታ ለማስተዳደር ይችላሉ። ከሙያዊ ግምት ተነስተን አገራችን የአነስተኛ መስኖ ልማት ዋና (Primary canal) እና ሁለተኛ  ቦይ (Secondary canal)  የውኃ ማስተላለፊያዎች ከ60 እስከ 70 በመቶ የእፈር ቦዮች (Earthen Canal) ናቸው። ይህም በውኃ ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ከፍተኛ የውኃ ብክነት እንዳለ የሚያሳይ ነው። ብዙ የዚህ ዘርፍ ጥናቶችና ውጤቶች እንደሚያመለክቱት፣ በዋናው የመስኖ ውኃ ማስተላለፊያ መስመር ላይ የውኃ ብክነቱ እስከ 50 በመቶ እንደሚደርስ ይገመታል።

የመስኖ ውኃን ለተክሎች የማቅረብ ዘዴ

ማሳ ላይ በተለያየ ዘዴ የደረሰን ውኃ ለተፈላጊው ሰብል እንዲደርስና ሰብሉም ተጠቃሚ መሆን እንዲችል የተለያዩ ዓይነቶች የውኃ ማሰራጫ ዘዴዎች አሉ። ከእነዚህም መካከል ዋነኞቹ ውኃን በተለያየ ቁስ ቀድቶ የማጠጣት ዘዴ፣ በማጥለቅለቅ ውኃን የማጠጣት ዘዴ (Flood Irrigation)፣ “የቤዝን” መስኖ (Basin Irrigation) /መሬትን በገበቴ መልክ /ቋት/ በማድረግ የማጠጣት መስኖ ዘዴ፣ የድንበር መስኖ /መሬትን በማጠር  የማጠጣት/ ዘዴ (Border Irrigation)፣ በትልም / በቦይ / መስኖ የማጠጣት ዘዴ (Furrow Irrigation)፣ በጠብታ መስኖ የማጠጣት ዘዴ (Drip Irrigation)፣ በዝናብ መሰል መስኖ የማጠጣት ዘዴ (Sprinkler Irrigation) ናቸው። የውኃ ማሰራጫ ዘዴን ለመወሰን የመስኖ መሬቱን አቀማመጥ (Topography)፣ የሚለማው መሬት የአፈር ዓይነት (Soil Type)፣ የመሬቱ ተዳፋትነት ልክ (Slope)፣ የመስኖ ውኃው ጥራት፣ በተለይም የጨዋማነት ልክ፣ (Water Quality-Salinity)፣ የሚለማው የሰብል ዓይነት (Irrigated Crop Type)፣ የመስኖ ተጠቃሚዎች የመስኖ ልምድን ታሳቢ በማድረግ ሊሆን ይገባል።

አሁንም የአገራችን ኢትዮጵያ የአነስተኛ መስኖ መሬቶችን የውኃ ማከፋፈያ ዘዴ ብንመለከት፣ መቶ በመቶ ሊባል በሚቻል ደረጃ የቦይ ውኃ ማጠጣት ዘዴ የሚተገበርባቸው ናቸው ተብሎ ይወሰዳል። ይሁን እንጂ በገበሬ ደረጃ ይህ አሁን በአነስተኛ መስኖ መሬት ላይ እየተተገበረ ያለው ከሳይንሳዊ አመዳደብ ዘዴ አንፃር ሲፈተሽ የቦይ ውኃ ማጠጣት ዘዴ (Furrow) ነው ለማለት የሚያስችግር ነው፡፡ ድርጊቱ ወደ ቤዝን፣ የድንበር መስኖና “ቦርደር መስኖ” የሚጠጋ ውኃ የማጠጣት ዘዴ ነው። ይህ ዘዴ ከላይ ውኃን ወደ ማሳ ለማቅረብ እንደምንጠቀምበት ዘዴ፣ ውኃን በተለያየ መልኩ ለብክነት የሚያጋልጥ ውኃ አጠቃቀም (አጠጣጥ) ዘዴ ነው።

የተክሎችን ውኃ ፍላጎት

በመስኖ ውኃ አስተዳደርና አጠቃቀም ውስጥ ውኃን ወደ ማሳ ከማቅረብና በማሳ ላይ ውኃን በማከፋፈልና ለሰብል ከማቅረብ በተጨማሪ ለአንድ ሰብል ሊስጥ የሚገባው አጠቃላይ የውኃ መጠን፣ (አትክልቱ የሚያስፈልገው የውኃ መጠን)፣ በምን ያህል ጊዜ? ምን ያህል ውኃ (Quantity)? በተወሰነ የጊዜ ገደብ፣ ለስንት ጊዜ (Frequency)? በስንት ቀን ልዩነት (Interval)? የሚሉት ሌሎች ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው። እነዚህን ቁልፍ ጉዳዮች በአግባቡ በሥራ ላይ ማዋል ካልተቻለ የመስኖ ልማት ጥፋት የጎላ ሊሆን (ጎልቶ ሊከሰት) ይችላል።

 ሰብሎች ፍሬያማ ለመሆን የተለያየ ድምር የውኃ መጠን (Crop Water Requirement) ይፈልጋሉ። ለአንድ ሰብል የዕድገት ዘመን የሚያስፈልገውን ውኃ በአንድ ጊዜ ማቅረብ የማይቻል ስለሆነ፣ በመስኖ ሰብሉ የሚፈልገውን ውኃ በጊዜ በመከፋፈል፣ በአንድ የማጠጣት ጊዜ ሊለቀቅ የሚገባውን ውኃ መጠንና የማጠጣት ጊዜ በመወሰንና፣ በቦይና በትልም ውስጥ በመልቀቅ ውኃን ለሰብል ማቅረብ የመስኖ ውኃ አጠቃቀም ዕውቀትና ክህሎት ይፈልጋል። በአገራችን በዚህ ዕውቀትና ክህሎት የሠለጠነ ባለሙያ ቢቻል በመስኖ ፕሮጀክቶች ደረጃ ካልሆነም በቀበሌ ደረጃ  ያለመኖርና ገበሬ የዚህ ክህሎት ባለቤት እንዲሆን ደጋግሞ አለማሠልጠን፣ በተገቢው ደረጃ አለማገዝ የመስኖ ውኃ አጠቃቀማችንን ኮሳሳ/ ተልካሻ አድርጎታል። ይህም ለከፍተኛ የውኃ ብክነት ያጋለጠን ሲሆን የቅርብ ጊዜ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የመስኖ ልማቶቻችን ውጤታማነት ከ40 እስከ 50 በመቶ  ያላለፈ (ያልዘለለ) ነው።

የመስኖ ልማት አስተዳደር

የአነስተኛ መስኖ ልማትን በተመለከተ፣ ልማቱ ውጤታማ እንዲሆን፣ ልማቱን የሚያስተናግድ ጠንካራ ተቋሞች፣  እንዲሁ ተግባራዊ መሆን የሚችል የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፍ መመሥረት ግዴታ ነው።  

በአሁኑ ጊዜ የመስኖ ልማት ውኃ አስተዳደር ወጥ አይደለም፣ ሆኖም የአነስተኛ መስኖ ልማት ኃላፊነት (የመስኖ ውኃን በማሳ ላይ ማድረስና ማሰራጨት) በአመዛኙ የክልልና የወረዳ አስተዳደሮች ሚና ነው። ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ የመስኖ አስተዳደር ከትልልቅና ከአነስተኛ መስኖ ልማትና ከባለቤትነት አንፃር የተለያዩ ናቸው። 

ትልልቅና መካከለኛ መስኖዎች በአብዛኛው ባለቤትነታቸው የመንግሥት፣ ወይም የኩባንያና ባለሀብት የግለሰቦች (ሀብታም ግለሰቦች) ከመሆናቸው አንፃር አስተዳደራቸውም እንዲሁ መንግሥታዊ ወይም ኩባንያዎች እንዲሁም ግለሰቦችን መሠረት ያደረገ ተቋማዊ አስተዳደር ነው። ይህም የተሻለ የሕግ ማዕቀፍ በቂ የሰው ኃይልና ዕውቀት፣ መሣሪያዎች (ማሽነሪዎች) ቁሶች ያለው እንዲሆን ያግዘዋል። ከዚህ አንፃር ትልልቅ መስኖዎች የተሻለ የመስኖ አስተዳደርና የተሻለ ውጤታማ የመስኖ ውኃ አቅርቦትና አጠቃቀም እንዲኖራቸው አግዟል። ይህ ዓይነቱ አስተዳደር ከአነስተኛ መስኖዎች ጋር ሲተያይ በአንፃራዊነት የተሻለ የመሆን ዕድልን አበርክቷል።

አነስተኛ የመስኖ ልማቶች በአብዛኛው ባለቤትና ተጠቃሚዎቹ ትናንሽ ገበሬዎች ሲሆኑ በእነዚህ በመስኖ ተጠቃሚዎች በሚደራጁ (በሚመሠረት) የመስኖ ውኃ ተጠቃሚዎች ማኅበር የሚመሩ ሲሆን፣ በግለሰብ አርሶ አደር ደረጃም የሚተዳደሩ የመስኖ ልማቶችም አሉ። እነዚህ በመስኖ ውኃ ተጠቃሚዎች የመስኖ ልማቶች የውኃ ማጠጣት ተራቸው፣ ከዋናው ቦይ ወይም አቅራቢያቸው ካለው የውኃ ቦይ የሚወስዱት የውኃ መጠን በጋራ በማኅበሩ የሚወስን ነው። ይህ ለአንድ ገበሬ የሚደርስ የውኃ መጠን የገበሬውን የመስኖ መሬት ልክ ብቻ ግምት ውስጥ ያስገባ እንጂ፣ ሌሎች መመዘኛዎችን ለምሳሌ የሰብል ዓይነት፣ የአፈር ዓይነት፣ የሰብል የዕድገት ደረጃንና ሌሎችም መመዘኛዎችን ከግምት አያስገባም። ለዚህ ክስተት እንደ ዋና ምክንያትነት የሚነሳው በዕውቀትና በክህሎት የተገነባ የሰው ኃይል አለመኖሩ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የመስኖ ውኃ ክፍያ አለመኖርና ይህንን በተግባር ለማዋል የሚረዳ የሕግ ማዕቀፍና የውኃ መለኪያ ቁሶች (Water Measuring Structures and Tools) አለመኖር ዋነኛ ተግዳሮቶች ናቸው።

በአገራችን ኢትዮጵያ የአነስተኛ መስኖ ውኃ ተጠቃሚዎች ማኅበራትን የማቋቋሚያ ሕግ በፌደራልና በክልል ደረጃ ያለ ቢሆንም፣ ሕጉን፣ በተለይም ከውኃ አስተዳደርና አጠቃቀም አንፃር ወደ መሬት ለማውረድ ብዙ ተግባራትን ማከናወን ያስፈልጋል። አሁን በሚታየው ደረጃ ለማኅበራቱ ሕጋዊ ዕውቅና ከመስጠት ባለፈ፣ በውኃ አጠቃቀም ላይ ያሉ ክፍተቶችን ከማረም/ ከማስተካከል አንፃር የሚታይ ጉልህ እንቅስቃሴ የለም። በአንድ ወንዝ ላይ የሚገኙ የመስኖ ተጠቃሚዎች ሊኖራቸው የሚገባውን የውኃ መጠን መብት፣ ብከላ ሁኔታና ሌሎችንም መብቶችና ግዴታዎች በሕግ አስፍሮ/ በሕጉ መሠረት አለመተግበር፣ የመስኖ ልማት አካባቢዎችን ለውኃ ብክነት፣ ብክለት፣ ብሎም ለሚከሰቱ ተግዳሮቶች  አጋልጦታል። 

የአነስተኛ መስኖ ውኃ ተጠቃሚዎች ማኅበራት ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ ከመሆናቸው አንፃር ራሳቸውን በገቢና በባለሙያ እንዲያጠናክሩ ይጠበቃሉ። ይሁን እንጂ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በአሁን ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት የአነስተኛ መስኖ ውኃ ተጠቃሚዎች ማኅበራት ከአባሎቻቸው ለመስኖ ልማት ውኃ አቅርቦት ማንቀሳቀሻ በአማካይ ከ200 እስከ 2,000 የኢትዮጵያ ብር በሔክታር ከመሰብሰብ ያለፈ ተግባር ሲያከናውኑ አይታዩም። መለስተኛ የዳሰሳ ጥናቶች እንደሚያሳዩት አንድ አነስተኛ የመስኖ ተጠቃሚዎች ማኅበር በአካባቢ ባለሙያዎች ጥገና እና ኦፕሬሽን ለመከወን በዓመት 3,000 እስከ 5,000 የኢትዮጵያ ብር በሔክታር ሊሰበስቡ እንደሚገባ ያመለክታል። አሁን በማኅበራቱ የሚሰበሰበው ገንዘብ አነስተኛ መሆንና መንግሥትንና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ለተለያዩ የጥገና እና የኦፕሬሽን ወጪ እንዲሸፈኑ ተስፋ ማድረግ በውኃ ብክነት ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖዎች አሳድሯል።

በመስኖ ልማት ተግባር መወሰድ የሚገባው ጥንቃቄ

ለመስኖ ልማት አወንታዊ ተፅዕኖ  ከአሉታዊ ተፅዕኖዎች የተሻለ መረጃ፣ ግንዛቤ እንዳለ ይታመናል፡፡ ስለ ተግዳሮቶች ያለው መረጃ፣ ግንዛቤ በጣም ውስን ነው፡፡ ምክንያቱም የሕዝብ ሚዲያዎች ስለ ተግዳሮቶች ሲያወሱ አይሰማም፡፡ የመስኖ ልማት የተሻለ ገቢ፣ ብሎም በቂና ተመጣጣኝ ምግብ ማግኘትን ሲያበረክት፣ እንዲሁም የተሻለ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ያበረክታል፡፡ ጥንቃቄ ካልተደረገ፣ የመስኖ ልማት ብዙ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን ሊያስከትል ይችላል፡፡

ከላይ እንደተወሳው፣ ኢትዮጵያ የተወሰኑ በመስኖ የምታለማቸው አካባቢዎች፣ በተለይ በአዋሽ ሸለቆ አሉ፡፡ የሚተገበረውም የመስኖ ዘዴ አብዛኛው ዘመናዊ አይደለም፣ ባህላዊ ነው፡፡ የባህላዊው ዘዴ የመስኖ ወኃ አጠቃቀም፣ ከሚፈለገው/ከሚያስፈልገው ውኃ በላቀ የውኃ መጠን መጠቀምን ያስከትላል፡፡ ይህም ዘዴ የራሱን ችግር አዝሎ ይመጣል፣ ለምሳሌ ጨዋማነትን (Saline/ Soil Salinity)፣ የውኃ አዘል (Water-Logging)  አካባቢ መከሰትን፣ ወዘተ ሊያስከትል ይችላል፡፡

በዚህም መንስዔ በፊት የመስኖ እርሻ ተግባር ይካሄዱባቸው የነበሩ  አካባቢዎች፣ ቦታዎች፣ ልማት-አልባ ባድማዎች ሆነዋል፡፡ በብዛት ለመስኖ ተግባር የዋለው መሬት ቆላ አካባቢ ነው፣ ስለሆነም ውኃ በቀላሉ ይተናል፡፡ መጠኑ ቢለያይም ምንም ዓይነት ውኃ ጨዋማ ነው፡፡ ውኃው ሲተን በአፈሩ ላይ የሚቀረው ኬሚካላዊ ውሁዱ፣ በውኃ ሟሙቶ የነበረው ጨው ነው፡፡ የመስኖ ውኃ ከአፈሩ ላይ ሲተን፣ አፈሩ ላይ የሚቀረው ደቃቅ ጨው ነው፣ በሒደት የጨው መጠን በጣም ከፍ ይልና አፈሩ ጨዋማ ሆኖ ይመክናል፣ ምርት-አልባ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ የመሬት ሽፋን ከ44 ሚሊዮን ሔክታር ገደማ (36 በመቶ ያህል) “ለጨዋማነት” የተጋለጠ ነው ይባላል፡፡ ከዚህም 11 ሚሊዮን ሔክታር ገደማ፣ በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ በብዛት የሚያስከትለው “የጨዋማነት” ችግር የተተበተቡ ናቸው፡፡

 የመስኖ ልማት ሲታቀድ አብሮ መጠናት/ መታሰብ ያለበት ሊያስከትል የሚችለው ተግዳሮት ጭምር መሆን ይገባል፡፡ ይህም ጥናት የመስኖ ልማቱን ጥቅምና ሊያስከትል የሚችለውን ተግዳሮት ጭምር በቅድሚያ ተገንዝቦ፣ የመስኖ ልማት ተገቢው ጥንቃቄ ተደርጎ መተግበር ይኖርበታል፡፡ ይህም ተግባር በዓለም ዙሪያ በአገራችን ጭምር ተግባራዊ እየተደረገ ነው፣ ጥናቱም በመስኖ ማልማት፣ በአካባቢ ማኅበራዊ ሁኔታ ላይ ያለው አሉታዊ ተፅዕኖ፣ ብሎም ሊያስከትል የሚችለው የጤና ተግዳሮትን ያካተተ ነው፣ ተግባሮችም በአካባቢና በጤና ሊያስከትል የሚችለው ተፅዕኖ (Environmental and Health Impact Assessment-EHIA) በአካባቢና በማኅበራዊ ይዘት ሊያስከትል የሚችለው ተፅዕኖ (Environmental and Social Impact Assessment-ESIA) በመባል ይታወቃሉ፡፡

በጥናቱ ግንዛቤ መወሰድ ያለበት ስለ ብዙ የአካባቢ ሁኔታዎች ሲሆን፣ ዋናዎች፣ ውኃ ከየት ነው የሚገኘው? ለመስኖ ማልሚያነት የሚወሰድ (ከወንዝ፣ ከግድብ፣ ከጉድጓድ፣ ወዘተ) ነው? ለመስኖ የምንጠቀምበት ውኃ ለመስኖ ልማት የቱን ያህል ተስማሚ ነው? በመስኖ የሚለማው መሬት ነባራዊ ሁኔታው ምን ይመስላል? ወዘተ መሰል ናቸው፡፡ ተገቢ ጥናት ካልተደረገና በቂ መረጃ ተገኝቶ፣ ችግሩን ለማስተናገድ የሚችል ዘዴ ተግባር ላይ ካልዋለ፣ እንደ ሁኔታው አፈሩ ከጊዜ በኋላ ጨዋማ (Saline/ Soil Salinity)፣ እንዲሁም ውኃ አዘል (Water-Logging) ሆኖ ማሳው ሊመክን ይችላል፡፡

ከስድስት ሺሕ ዓመት በፊት በሜሶፖታምያ በግብርና የሚተዳደረው ማኅበረሰብ የኤፍራጥስ ወንዝን በመቀልበስ፣ ለመስኖ ልማት ይጠቀሙበት ነበር፡፡ የአካባቢው አራሾች ለብዙ ዘመን ብዙ የስንዴና የገብስ ምርት ያገኙ ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ አፈሩ ጨዋማ ሆኖ መከነ፣ ማሳዎችም  ምርት አልባ ሆኑ፡፡ የታሪክ ባለሙያዎች በዚያን ጊዜ የነበረው ገናና ሥልጣኔ የኮሰሰው፣ በአፈሩ ጨዋማነት መንስዔ የአካባቢው ሕዝብ በረሃብ ስለተጠቃ ነው ይላሉ፡፡ በአራል ባህር (Aral Sea) አካባቢም (ካዛኪስታን፣ ኪርጊኪስታን፣ ወዘተ) በ19ኛው ምእት ዓመት አካባቢ ተመሳሳይ ችግር ተከስቷል፡፡

ዘመናዊ የመስኖ እርሻ በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ፣ በስልት ካልተስተናገደ በጤና ላይ ብዙ ተግዳሮቶችን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ነባራዊ የሆነው የአካባቢ ሁኔታ ስለሚቀየር፣ ለምሳሌ ቆላማና በረሃ ቀመስ የነበረ አካባቢ መስኖ ውኃ ገብ ስለሚያደርገው፣ ቀደም ሲል በአካባቢው የነበሩ ሕያው አካላት፣ አዲሱን ሁኔታ ለመቋቋም ያዳግታቸው ይሆናል፡፡ እንዲሁም ውኃ ለማቆር፣ ለማከፋፈል የሚመሠረቱ ግንባታዎች (ግድቦች፣ ቦዮች፣ ወዘተ)፣ በተመቻቸው ሁኔታ ላይ ተመርኩዞ፣ ሰዎች እንዲሁም እንስሳት በአካባቢው ይሰፍራሉ፡፡ ስለሆነም የአካባቢው ውኃ በሰገራና በሽንት ለመበከል ይጋለጣል፣ ይህም በጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖች ያስከትላል፡፡ ለምሳሌ ኮሌራ፣ ለተስቦ፣ ብሎም ለተቅማጥ መንስዔ ይሆናል፡፡ ከውኃ ጋር የተቆራኙ የዓይን እንዲሁም የቆዳ በሽታዎችም ይከሰታሉ፡፡ በሽታ የሚያስተላልፉ (ወባ፣ ትላትል/  Filariasis/ River Blindness) ሦስት አፅቄዎች (Insects) እና ቢልሃርዚያ አቀባባይ የሆኑ ቀንድ አውጣዎች መራቢያ ሆኖ ያገለግላል፣ በሒደትም በሽታ በሰፊው ይሠራጫል፡፡

ለዚህ ጉዳይ ምሳሌ ይሆነን ዘነድ የወመንጅ የሸንኮር አገዳ የመስኖ እርሻ ያስከተለውን የአንጀት የቢልሃርዝያ (Bilharziasis/Schistosomiasis) መስፋፋት/ሥርጭት እናውሳ፡፡ የሸንኮር አገዳ የመስኖ ልማት ከመጀመሩ በፊት፣ በአካባቢው የቢልሃርዝያ በሽታ መኖሩ አይታወቅም ነበር፡፡ በሽታው ከነበረበት አካባቢ በበሽታው የተለከፉ ሠራተኞች ወደ አካባቢው እንዳመጡት ይገመታል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1964 በአካባቢው አንድ የኩባንያው ሠራተኛ ልጅ በሰገራ ምርምራ በበሽታው እንደተለከፈ ተደረሰበት፡፡ በ1980 በአካባቢው ከነበሩ ልጆችና ወጣቶች መካከል 20% (ሃያ በመቶ) በበሽታው እንደተለከፉ፣ በ1990 ደግሞ እንደ ዕድሜያቸው ከ5 እስከ 14 ዓመት የነበሩ ልጆች 82% (ሰማንያ ሁለት በመቶ) በበሽታው መለከፋቸው ግንዛቤ ተገኘ፡፡ ይህንን ግኝት መጥቀሱ ግንዛቤ ያዳብር ይሆናል ብለን እንገምታለን፡፡

በግብርና ልማት ሒደትም፣ ለእርሻ ምርታማነት ለማጎልበት፣ ተባይ ለመከላከል፣ አፈርን ለማቅለዝ፣ ወዘተ የሚረጩ ኬሚካላዊ ውሁዶች፣ በመስኖ የሚለማውን አፈር ነባራዊ ሁኔታዎችን ያቃውሳሉ፡፡ በዚህ ሒደት የአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ይቀየራል፣ ለውጡን መቋቋም የማይችሉ ሕያው አካል ለውድመት ይጋለጣሉ፣ ብዝኃ ሕይወት ይወድማል፡፡

የአፈር ጨዋማነት የሚታከመው፣ ግማሽ ሜትር ገደማ ወደ ውስጥ ተቆፍሮ በተቀበሩ የተበሳሱ (ብዙ ቦታ በሥርዓት የተበሱ ቀዳዳዎች/ውስን ክፍተቶች ያሉዋቸው) የኮንክሪት ወይም ፕላስቲክ ቱቦዎችን ቀብሮ፣ ከላይ አፈሩን በውኃ በማጠብ ነው፡፡ በዚህ ዘዴ አፈሩ ውስጥ የነበረው ጨው ሟሙቶ በውኃ ታጥቦ ወደ ተበሳሱ ቱቦዎች ገብቶ በመጨረሻ ጨዋማው ውኃ ከማሳው ሊከላ ይችላል፡፡ ይህ ዘዴ ከፍተኛ ወጪን እንደሚያስከትል መገመት አያዳግትም፡፡ ከዚህ በፊት በዚህ ዘዴ የታከሙ በአዋሽ ሸለቆ የሚገኙ የእርሻ ማሳዎች አሉ፡፡

ማጠቃለያ

በአገራችን የመስኖ ልማት መስፋፋት ተስፋ ሰጪ በሆነ መልኩ እያደገ ስለሆነ የሚያበረታታ ተግባር ነው። ይህም አገሪቱ በምግብ ሰብል ራሷን ለመቻል፣ የተሰባጠረ ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት ለመገንባት፣ በገጠር ደረጃ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንዲሁም የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በአስተማማኝ ደረጃ ለማምረት ትልቅ ሚና እንዲኖረው የሚያደርግ ነው። ይህን ጠቀሜታ ዘላቂነትና አስተማማኝነት እንዲኖረው ለማድረግ፣ ለመስኖ ልማት ሊደረግ የሚገባው የሕግ፣ የፖሊሲ፣ የተቋም፣ የገንዘብ፣ የሙያና የቴክኖሎጂ ድጋፍ ወሳኝ ናቸው። በተለይም የመስኖ ውኃ አስተዳደርና አጠቃቀም ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው።

ቀጣዩ የዓለም ጦርነት የውኃ ጦርነት ነው እየተባለ በሚዘመርበት ዓለም፣ ለውኃ አስተዳደራችንና አጠቃቀማችን ልዩ ትኩረት አለመስጠት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይዞ ከሚመጣው ችግር ባለፈ በአቅራቢያችን የአፈር መሸርሸርን፣ የአፈር ጨዋማነትን፣ የመሬት መጎዳትንና የሥነ ምኅዳር መዛባትን፣ የአካባቢ ማኅበረሰቦችን ግጭት፣ ወዘተ የሚያስከትል መሆኑን ልብ ማለት ይገባል። የመስኖ ልማት የሚፈለግ ጥቅሙ ከፍተኛ፣ አንኳር የዕድገት አጋዥ መሆኑ አይካድም፣ ግን ሲተገበር በጥንቃቄ፣ በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ መሆን ይገባዋል፡፡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያሻል፣ አለዚያ  “A Curse With A Blessing” (በምርቃት የተጋረደ እርግማን) ሊሆንብን ይችላል፡፡ የማልማት ሒደቱ ይህንን ሊደርስ የሚችል ችግር በጥሞና ተገንዝቦ፣ እየተስተዋለ መተግበር ይገባዋል፡፡

ማንኛውም ዓይነት የልማት ተግባር፣ የመስኖ ልማትንም ያካትታል፣ ዕውቀትንና ክህሎትን መሠረት አድርጎ መተግበር ይገባዋል፡፡ ችግርን ለተከታይ ዘመን፣ ትውልድ፣ አስተላልፎ ማለፍ አይገባም፡፡ ‹‹የአንድ ዘመን ምቾት፣ የወደፊት ዘመን መከራ መንስዔ፣ ያንዱ ዘመን ዘፈን ለተከታይ ዘመን ሐዘን መሆን የለበትም››፡፡ ተከታይ ዘመን፣ ትውልድ አለ/ይኖራል ብለን ማሰብ ያሻናል፡፡ ለዚህ ተግባር ግንዛቤ ትረዳን ዘንድ፣ አንድ የበዕውቀቱ ሥዩምን ግጥም በግርድፍ ዘርፈን፣ ጽሑፉን እንቋጭ፡፡

አንች ኮርቻ ሰፊ፣ ጣውላውን አቅጥኝ፣ ጠርዙን አለስልሽ፤

የአንዱ ፍጡር ወንበር፣ ላንዱ ፍጡር ቀንበር መሆኑን አትርሽ፡፡

ከአዘጋጁ ጸሐፊዎቹ ሽብሩ ተድላ (ፒኤችዲ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕይወት (ባዮሎጂ) ኢመረተስ ፕሮፌሰር፣ ዮሐንስ ገለታ (ዶ/ር) የመስኖ ተግባራት ተመራማሪ ሲሆኑ፣ በርካታ የምርምር ሥራዎቻቸውን አሳትመዋል፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊዎቹን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻዎቻቸው shibrut@gmail.com፤ yohketi@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles