Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅልጄ ሆይ!

ልጄ ሆይ!

ቀን:

ልጄ ሆይ፤ አንተ አስቀድመህ በሰው ላይ አትነሣ፤ ሰው በአንተ ላይ ቢነሣብህ ግን እንዳትሸነፍ ጠንክረህ መክት፡፡ እምነትህንም በእግዚአብሔር ላይ አድርግ፡፡

ልጄ ሆይ፤ ሰው ሳይኖር ብቻህን ከሴት ጋር አትነጋገር፡፡ ባሏ አለመኖሩን በደጅ ጠይቀህ ከደጅ ተመለስ እንጂ ወደ ቤት አትግባ፡፡ ሰው ሳይኖር ብቻህን ከሴት ጋር የተነጋገርህ እንደ ሆነ ግን፤ ምንም ሌላ ምስጢር ባይኖራችሁ በመነጋገራችሁ ብቻ መጠርጠር አይቀርም፡

ልጄ ሆይ፤ እስቲ ያለፉትን ሰዎች ሁሉ አስባቸው፡፡ እነዚያ ሁሉ ጀግኖች ሁሉም መሬት ሆነዋል፡፡ እነዚያ ሁሉ ዓለመኞች፤ እነዚያ ሁሉ ቀልደኞችና ፌዘኞች፤ እነዚያ ሁሉ ግፈኞች፤ እነዚያ ሁሉ በድኃ ላይ የሚስቁና የሚሳለቁ ሁሉም መሬት ሆነዋል፡፡ እነዚያ ሁሉ ድሆች ሲበደሉ፣ ሲያዝኑ፣ ሲያለቅሱ ካንዱ ሀገር ወደ ሌላው ሀገር ሲሰደዱ፣ ሲራቡ፣ ሲጠሙ፣ ሲታረዙ የነበሩ መሬት ሆነዋል፡፡

ስንት ሰዎች የነበሩ ይመስልሃል?

የድኃ እንባ ሲፈስ የወንዝ ውኃ የሚፈስ የሚመስላቸው ስንት ሰዎች ነበሩ፡፡ ድኃ ሲጮህ ውሻ የሚመስላቸው ስንት ሰዎች ነበሩ፡፡ ድኃ ታስሮ ወይም በሌላ ጭንቅ ነገር ተይዞ ሲሞት የወፍ ግልገል የሚሞት የሚመስላቸው ስንት ሰዎች ነበሩ፡፡ ጉልበት ካለን ብለው በደካሞች ላይ ያሰቡትን ሁሉ የሚሠሩ ስንት ሰዎች ነበሩ፡፡ ሰውን ለማጥፋት እጅግ የሚጥሩ ሰውን ካላጠፉ እንቅልፍ የማይወስዳቸው ስንት ሰዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ከዚህ ቀድሞ የነበሩት ሁሉም መሬት ሆነዋል፡፡ ከመሬት የተገኘ ሁሉ መሬት ስለ ሆነ ወደ መሬትም የማይመለስ ስለሌለ እኛም ነገ እንደዚያው እንሆናለን፡፡ስለዚህ በማናቸውም ምክንያት ቢሆን፤ የሰው ደስታውና አዘኑ እጅግ አጭር መሆኑን በጣም እወቅው፡፡

ልጄ ሆይ፤ ሰው ምንም ብልህና አዋቂ ቢሆን በራሱ ሥራ ብቻ ራሱን ችሎ እንደማይኖር ዕወቅ:: ነገር ግን ሁሉም በየሥራው ጸንቶ እርስ በርሱ በሥራ ይፈላለጋል:: ስለዚህ ሰውን ሁሉ አክብረህ ኑር እንጂ ሰውን አትናቅ ሥራውንም አትንቀፍ::

ልጄ ሆይ: አካልህና ልብስህ ዘወትር ንጹህ ይሁን:: እጅህን ለሥራ: ዓይንህን ለማየት: ጆሮህን ለመስማት ፈጣኖች አድርግ:: አፍህን ግን በጠንካራ ልጓም ለጉመህ ያዝ:: አረጋገጥህ በዝግታ አነጋገርህ በለዘብታ ይሁን:: ያልነገሩህን አትስማ: ያልስጡህን አትቀበል: ያልጠየቁህን አትመልስ:: ሽቅርቅር አትሁን: ንብረትህ ተጠቅላላ ይሁን: ምግብና መጠጥህ በልክ ሆኖ ያው የጠዳና የጣፈጠ ይሁን::

ልጄ ሆይ ፈቃደ ሥላሴ፤ አሳብ አታብዛ፤ ወደ ፊትም ምን ነገር ይመጣ ይሆን ብለህ አትጨነቅ፤ ምንም አሳብና ጭንቀት ብታበዛ የሚሆን ነገር ሳይሆን አይቀርም፡፡ ወደ ፊትም እሾማለሁ፤ እሸለማለሁ፤ ብለህ በአሳብህ ደስ አይበልህ፡፡ ለሰውም አትናገር፤ ምናልባት ከተናገርህ በኋላ ሳታገኘው የቀረህ እንደ ሆነ ታላቅ ኀፍረት ይሆንብሃልና፡፡ ወደ ፊት የሚያናድድ ሥራ አትሥራ፡፡ በገዛ እጅህ በሠራኸውና ባለፈው ሥራ አትናደድ፡፡ ልጄ ሆይ፤ ጌታ ለመሆን ትፈልግ እንደ ሆነ ጌትነት ማለት ያለ አሳብና ያለ ጭንቀት መኖር ነው፡፡ አሳብህም ሁሉ ከሞትህ በኋላ ወዲያኛው ዓለም ስለሚሆነው ስለ ነፍስህ ነገር ይሁን እንጂ በዚህ ዓለም በሥጋህ ስለሚሆነው ነገር እጅግ አትጨነቅ፡፡

– ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ‹‹ለልጅ ምክር ለአባት መታሰቢያ›› (1924)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...