Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ወደ አውሮፓ ገበያ የሚላኩ የግብርና ምርቶች ላይ ጠንከር ያለ ቁጥጥር መጀመሩን ባለሥልጣኑ አሰታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ ኅብረት የሚላኩ ምርቶችን የአውሮፓ ኅብረት ባወጣቸው ጥብቅ መሥፈርቶች መሠረት ፈትሾ ለመላክ የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ጠንከር ያለ ቁጥጥር መጀመሩን አሰታወቀ። 

ባለሥልጣኑ እየጠበቁ ያሉ ዓለም የንግድ ሕጎችንና መሥፈርቶችን አሟልቶ መላክ የሚያስችል ሥርዓት በመዘርጋት የግብርና ምርቶችን ከእርሻ ጀምሮ ከአገር እስኪወጣ ደረስ የቁጥጥርና የምርመራ ሥራ መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

የኢትዮጵያ አበባ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ማኅበር ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመፈተሽ የሚያስችሉ መሣሪያዎች ባለፈው ረቡዕ ለኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ባስረከበበት ወቅት እንደተገለጸው በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥብቅ የሆኑ የጥራት ደረጃ መሥፈርቶች እየወጡ በመሆኑ ከኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ከአገር ከመውጣታቸው በፊት ዓለም አቀፍ መሥፈርቶችን ያሟሉ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ጥብቅ ፍተሻ ማድረግ መጀመሩን አስረድቷል።

የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወንድአለ ሀብታሙ እንዳመለከቱት የአውሮፓ ኅብረት ያወጣው ጠንካራ ሕግ በመሆኑ የኢትዮጵያ ምርቶች ወደ ውጭ ከመላካቸው በፊት እዚሁ በመመርመርና መሥፈርቱን ማሟላት አለማሟላታቸውን በመለየት ግድ ሆኗል፡፡ 

የፍተሻ ሥራው ዘመናዊ መሣሪያዎችን የሚጠይቅ በመሆኑ በዕለቱ ከኢትዮጵያ አበባ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ማኅበር የተደረገላቸው የመሣሪያ ድጋፍ ትልቅ ዕገዛ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ምርትን ዝም ብሎ መላክ አገርን ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን የሚገልጹት ዳይሬክተሩ እየወጣ ባለው መሥፈርት መሠረት ኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ ከምትልከው ምርት 25 በመቶው እዚያ ከደረሰ በኋላ ምርመራ የሚደረግበት ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም የአገር ውስጥ የቁጥጥር ሥራን በማጠናከር መሥፈርቶችን የማያሟሉ ምርቶች ወደ ውጭ ገበያ ከመላካቸው በፊት እዚሁ እንዲቀሩ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል። ደረጃ የማያሟሉ ምርቶችን ማስቀረት ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ መሥፈርቶችን ማሟላት ያልቻለ የግብርና ምርት ወደ አውሮፓ ገበያ እንዳይላክ የማገድ ዕርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል።

ተቋሙ አዲስ ቢሆንም ወደ አውሮፓ የሚላኩ ምርቶችን በተቀመጠው ደረጃ የተመረቱ መሆናቸውን የማረጋገጥ ሥራ መጀመሩን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ባለሥልጣኑ እንዲህ ያለውን ዕርምጃ የሚወስደው የአውሮፓ ኅብረት በአንድ እርሻ ላይ የተገኘን ችግር በሌሎችም ላይ የሚወሰድ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ይህ እንዳይሆን ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን እንደገለጸው በአሁኑ ወቅት እየወጡ ያሉ ሕግጋትን በመከተል መሥፈርቶቹን እያሟሉ እንዲላኩ ባለሥልጣኑ ያካሄዳቸው ድርድሮችና ንግግሮች የተወሰነ ውጤት እያስገኙ ቢሆንም ከዚህም በኋላ በጥንቃቄ ሥራዎችን መሥራት የሚያስፈልግ መሆኑን የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ገልጸዋል፡፡ 

‹የዓለም ንግድ ከመቼው ጊዜ በላይ ከባድ መሆኑንና መሰል የንግድ ሕጎች እየወጡ ያሉት በአውሮፓ ብቻ ሳይሆን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጭምር በመሆኑ ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶች ጥራትና ደረጃ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ የግድ መሆኑን አስረድተዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተለይ ከዕፀዋት ምርቶች ጋር በተመለከተ ኢንተርናሽናል ፕላንት ፕሮቴክሽን ኮንቬንሽን ሕጉን 192 የሚሆኑ አንቀፆች እንዲሻሻሉ የተደረጉበት በመሆኑ የንግድ ሥራው ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ሆኗል ብለዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች