Monday, July 22, 2024

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ማሻሻያ አዋጅና ለዋጋ ግሽበት የሚኖረው መፍትሔ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያ የብር የመግዛት አቅም መዳከም የጀመረው ከመቼ ጀምሮ ነው የሚለው ለብዙዎች ሩቅ ሆኖ የሚታይ ይመስላል፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በ1998 ዓ.ም. የበጀት መዝጊያ ዕለት በፓርላማ፣ ‹‹ወገብን ጠበቅ አድርጎ ማሰር ነው የሚበጀው፤›› ብለው ከተናገሩበት አጋጣሚ ጋር ብዙዎች ያያይዙታል፡፡

የቀድሞው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር አቶ ሱፊያን አህመድ፣ ‹‹የዋጋ ግሽበት በእኔ የሥልጣን ዘመን የሚረጋጋ አይመስለኝም፤›› ብለው እንደተናገሩት ሁሉ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መንግሥት ዘመን ቋጠሮው የተፈታው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት በአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ዘመንም ልጓም አጥቶ ተሻግሮ፣ በዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጊዜም ሽምጥ እንደጋለበ ነው እየተባለ ይጠቀሳል፡፡

አንዳንዶች የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ምልክቱ የታየው መጀመሪያ በቡና ላይ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የመለስ ዜናዊ መንግሥት የቡና ላኪዎች መጋዘንን መበርበርና ነጋዴዎችን ወደ ማደን እስኪገባ ድረስ ቡና በአንድ ወቅት ከገበያው ጠፋ፡፡ ቀጥሎ የገበያ ግርግር የተስተናገደባቸው ምርቶች ደግሞ ሽንኩርትና ቲማቲም ነበሩ፡፡ በሳንቲምና በጥቂት የብር ኖቶች ይገዙ የነበሩት እንደ ሽንኩርት ዓይነት ምርቶች ከገበያ ጠፉ ተብሎ

በርካታ ግርግር ተፈጠረ፡፡ የጨውና የበርበሬ ጉዳይ ግን ከሁሉም ጎላ ብለው ይታወሳሉ፡፡ አንድ ሰሞን ጨውና በርበሬ ጠፉ ተብሎ ለሁለቱ ምርቶች የገበያ ሠልፍና ግርግር ተፈጠረ፡፡

ኪሎው በሳንቲም ቤቶች ለብዙ ዘመናት ሲሸጥ የኖረውና በኢትዮጵያ ከሁሉም ሸቀጥ በላይ እጥረት ሊገጥመው የማይችል የተባለለት ጨው በድንገት ከገበያ መታጣቱ፣ የኢትዮጵያን ገበያና ግብይት አይገመቴነት የጠቆመ የመጀመሪያው ደወል ነበር ይባላል፡፡

ቀጥሎ የእጥረትና የዋጋ ንረት ሰለባ መሆን የጀመሩት ደግሞ ስኳርና ዘይት ነበሩ፡፡ እነዚህ ምርቶች ላይ የታየው የገበያ ትርምስ ከፓርላማ እስከ ኩሽና የደረሰ ነበር፡፡ ‹‹ደርግ ኅብረት ሱቅ እያለ በየቀበሌው ለሚከፋፈል ስንዴ፣ ማካሮኒ፣ ፓስታ፣ የዱቄት ወተት፣ ፋፋና ስኳር ሕዝቡን ለራሽን ሲያሠልፍ የኖረ አስመራሪ የእጥረት መንግሥት ነበር›› እያለ ለረዥም ጊዜ ፖለቲካ ሲሠራበት የቆየው ኢሕአዴግ፣ በመጨረሻ እሱም በተራው ለዘይትና ለስኳር በየሸማቾች ሱቅ ደጃፍ ተሠለፉ ሲል የታየበት አጋጣሚ በስኳርና በዘይት አጥረት ተፈጠረ፡፡

ሲሚንቶ ላይ የታየውና ለረዥም ጊዜ የዘለቀው እጥረትና የዋጋ ንረት በኢትዮጵያ አዲስ ዓይነት የአየር በአየር ንግድ ሲፈጥር መታየቱ ይነገራል፡፡ ከኤሌክትሪክ አቅርቦት መቆራረጥ እስከ ፋብሪካዎች ማሽን ብልሽት ብዙ ዓይነት ምክንያት ሲደረደርበት የቆየው የሲሚንቶ ግብይት፣ የዋጋ መቃወስና እጥረት በስተመጨረሻ ሥር የሰደደ የንግድ አሻጥር ሰንሰለት እንደፈጠረ በይፋ እስከመታመን መድረሱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ በእነዚህ ሁሉ ክስተታዊ በነበሩ የገበያ ግርግሮች መካከል በሒደት ዋጋቸው ወደ ሰማይ ሽቅብ የወጣ ምርቶችና አገልግሎቶች ተበራክተው ነበር፡፡ በሳንቲም ቤቶች ይገኙ የነበሩ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ወደ ብር ኖቶች ተቀይረዋል፡፡ ከጤፍ እስከ ቢራ፣ ከዳቦ እስከ ሥጋ፣ ከሱሪ እስከ ጫማ፣ ከወተት እስከ ውስኪ፣ ከለስላሳ እስከ ቀይ ወጥና ዱለት በሁሉም ዓይነት ምርት፣ ሸቀጥና አገልግሎት መስክ የሸማቾችን ኪስ የሚፈታተን የዋጋ ልዩነት በገበያው በሒደት መታየት ቀጥሎ ነበር፡፡

በዚህ ሁሉ ዑደት ግራ ለተጋባውና መኖር እየከበደው ለመጣው ሕዝብ የሚነገሩት ምክንያቶችም ሆኑ የሚሰጡ ምላሾች ግን እዚህ ግባ የሚባሉ አለመሆናቸውን ነው በሒደት የታየው፡፡ አቶ መለስ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፈጣን ዕድገት በማስመዝገቡ የተነሳ ነው የዋጋ ንረቱ የተፈጠረው የሚል አመክንዮ ሰጡ፡፡ በሒደት ይህን አሻሽለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፍጥነት በማደጉና የሕዝቡ ኑሮ መዋቅራዊ በሆነ መንገድ እየተለወጠ በመምጣቱ የተፈጠረ ለውጥ ስለመሆኑ ገለጹ፡፡ ቡና በጨው ከመጠጣት ወደ ስኳር መጠጣት አርሶ አደራችን ተሸጋግሯል የሚል ምሳሌም ሲያቀርቡ ታዩ፡፡ ይህን ምሳሌ በስተኋላ በዓብይ (ዶ/ር) ዘመን ጠላ በስኳር ወደ መጥመቅ ተቀይሮ ቀረበ፡፡ ከመለስ ጀምሮ እስካሁን ባለው ሒደት የዋጋ ንረትም ሆነ የኑሮ ውድነት መንስዔ በሚል ነጋዴውና ገበሬው ሲረገሙ መኖራቸው የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡

ነጋዴው ምርት ይሰውራል እጥረት ይፈጥራል፣ እንዲሁም ዋጋ ያንራል ተብሎ የአገር ጠላት እስኪመስል ተረገመ፡፡ አንድ ሰሞን ይባስ ብሎ የዋጋ ትመና ጣሪያ ወጣበት፡፡ የዋጋ ተመን ጣሪያ ሳይሆን የትርፍ ህዳግ ማውጣቱ የተሻለ መፍትሔ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች መከሩ፡፡ መንግሥት ግን በጠላትነት የፈረጀውን ነጋዴ መቅጣት ስለነበር ዓላማው በውሳኔው ፀና፡፡ ይህ በሆነ በጥቂት ጊዜ ግን ምርት የሚባል በገበያው ማግኘት አበሳ ሆነ፡፡ እነ ሳሙና ሁሉ ዋጋቸው ጣሪያ ላይ ወጣ፡፡ መንግሥት የኋላ ኋላ ነገሩ እንደማያስኬድ ስለገባው የዋጋ ጣሪያ (Price Cap) ሕጉን አነሳ፡፡ ነጋዴው ምርት ደባቂና የዋጋ ንረት መንስዔ ነው የሚለው እርግማን በሒደት ደግሞ ወደ አርሶ አደሩ ተላከከ፡፡ ኢሕአዴግ ዋነኛ ማኅበራዊ መሠረቴ ነው የሚለውን አርሶ አደር ምርት ደባቂ ብሎ እስከ መፈረጅ ደረሰ፡፡ ይህ አመክንዮ ደግሞ ዛሬም በዓብይ (ዶ/ር) አመራር ዘመን ቀጥሏል፡፡

አርሶ አደሩ ማዳበሪያና የምርት ግብዓት በድጎማ እያገኘ፣ እንዲሁም ተገቢውን ግብር ሳይከፍል እየኖረ ነገር ግን ያመረተውን ምርት ወደገበያ አላወጣም እያለ ይደብቃል በሚል ለገበያ አለመረጋጋት ዋና ተወቃሽ ሲሆን ይታያል፡፡ አቶ ተመስገን ዘውዴና አቶ ቡልቻ ደመቅሳ አባል በነበሩበት የቀድሞ የፓርላማ ዘመን፣ ጠንካራ የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ ጉዳዮች ክርክሮች ይሰሙ ነበር፡፡ ከእነዚህ ጊዜዎች ጀምሮ መንግሥት የማያሳምኑ ምክንያቶችን መደርደሩን በማቆም፣ በኢትዮጵያ የዋጋ ንረት መሠረታዊ መነሻ ምክንያት በሆነው በፊስካልና በሞኒተሪ ፖሊሲ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርግ ጠንካራ ውትወታ ይደረግ ነበር፡፡

መንግሥት በመሠረተ ልማት ግንባታና በኢኮኖሚ ማሳደግ ስም ወጪ ስለማብዛቱ በሰፊው መተቸት ጀምሮ ነበር፡፡ ያለቅጥ የጨመረውን ወጪም ለመሸፈን ሲል ከብሔራዊ ባንክ በሰፊው መበደር ስለመቀጠሉ (ገንዘብ ስለማተሙ) በርካቶች አንስተው፣ ይህን ለዋጋ ንረት መሠረታዊ መነሻ የሆነ ችግር ዕልባት እንዲያበጅለት ሲወተውቱ ቆይተዋል፡፡

ይህን ሙግትም ሆነ ወቀሳ ሊቀበለው ያልፈለገው የጊዜው መንግሥት ግን በፊስካልና በሞኒተሪ ፖሊሲ ቁጥጥር ላይ የተለየ ዕርምጃ ሲወስድ አልታየም፡፡ በዚህ የተነሳም የዋጋ ንረቱን ምጣኔ ወደ አንድ ዲጂት አኃዝ የማውረድ ግብ በእነዚህ ዓመታት እንደ ዕቅድ ተደጋግሞ ቢያዝም፣ ነገር ግን የሚባለው ሳይሳካ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ለረዥም ጊዜ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ፈተና ሆነው እስካሁን መዝለቃቸው ይነገራል፡፡ ‹‹The Challenge of Inflation and Financing Development in Ethiopia a Kaleckian Approach with Empirical Result›› በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ለውጥ ላይ ጥናት ያቀረቡት ዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር) እና ክብሮም ታፈረ የአገሪቱን የዋጋ ግሽበት መነሻ ምክንያቶች ጠለቅ ብለው መርምረዋል፡፡

ሁለቱ ባለሙያዎች ባደረጉት ምርምር በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከ2000 ዓ.ም. በፊት በነበሩት 50 ዓመታት የዋጋ ንረት ዓመታዊ ጭማሪ ወይም ለውጥ ከአምስት በመቶ በታች በሆነ አኃዝ ላይ የተገደበ እንደነበር አረጋግጠዋል፡፡ የኢትዮጵያ ግሽበት በየዓመቱ እጅግ ዝቅተኛ የሚባል ጭማሪ ሲያሳይ ቆይቶ እ.ኤ.አ. ከ2000 በኋላ በነበሩት ዓመታት ግን አስደንጋጭ ለውጥ ማሳየት መጀመሩን ይናገራሉ፡፡

እ.ኤ.እ. በ2008 ለምሳሌ 60 በመቶ ላይ የዋጋ ግሽበቱ መድረሱንና በተለይ የምግብ ሸቀጦች ግሽበት ምጣኔ እስከ 80 በመቶ ማሻቀቡንም ያስታውሳሉ፡፡ የዋጋ ግሽበቱ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ማደግ የጀመረው ከምርጫ 97 በኋላ፣ በተለይም ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም ወዲህ እንደሆነ ባለሙያዎቹ አስቀምጠዋል፡፡

ይህ አሳሳቢ የዋጋ ግሽበት ጭማሪ ያሠጋው መንግሥት በተከተሉት ዓመታት ንረቱን ለመቆጣጠር ጥረት ያደረገ ቢሆንም፣ ነገር ግን በእነዚህ ዓመታትም ቢሆን ከ26 በመቶ አማካይ አኃዝ በታች ግሽበቱ መውረድ አለመቻሉ በጥናቱ ተቀምጧል፡፡ ጥናቱ እንዳስቀመጠው ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በፊት በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ጉዳይ ችግር አልነበረም፡፡ ይህ ደግሞ የሆነው ከኢሕአዴግ ዘመን በፊት የነበሩት መንግሥታት በተከተሉት ጥብቅ ተቋማዊ ቁጥጥር ያለው በፊስካልና በፋይናንስ ፖሊሲ ለረዥም ዘመን ሲሠራበት በመቀጠሉ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ከ1997 ዓ.ም. በኋላ በነበሩት ዓመታት ልማታዊ መንግሥት ነኝ የሚለው የኢሕአዴግ መንግሥት ይህን ጥብቅ የፊስካልና የሞኒተሪ ፖሊሲ በማንሳቱ የተነሳ የዋጋ ንረቱ በአስደንጋጭ ፍጥነት መጨመሩን ጥናቱ ይገልጻል፡፡ ኢኮኖሚውን ከአሥር በመቶ በላይ በሆነ ባለሁለት አኃዝ ለአሥር ተከታታይ ዓመታት ሲያሳድግ መቆየቱን መንግሥት ይገልጽ ነበር፡፡ ይህ የዕድገት አኃዝም ቢሆን የተጋነነና ከስድስት ወይም ሰባት በመቶ የማይዘል ነበር ይላል ጥናቱ፡፡ ያም ሆኖ ይህን ዕድገት ለማምጣት መንግሥት የፈጠረው የፋይናንስ ምንጭ ግን የማክሮ ኢኮኖሚውን ሥርዓት የሚያናጋ የዋጋ ግሽበት የሚፈጥር እንደነበር ጥናቱ ይጠቁማል፡፡

መንግሥት ከ1997 ዓ.ም. ወዲህ በነበሩት ዓመታት ወደ 66 በመቶ ወጪውን ከብሔራዊ ባንክ በሚገኝ ብድር ነበር የሚሸፍነው፡፡ ወደ 15 በመቶው ደግሞ ከውጭ በሚገኝ ዕርዳታ ሲሆን፣ ቀሪው 19 በመቶ ደግሞ ከውጭ ብድር እንደነበር በጥናቱ ተመላክቷል፡፡

መንግሥት ሰፊ በጀቱን ከብሔራዊ ባንክ ከሚገኝ ምንጭ መሸፈኑ ደግሞ የብር ኅትመትን (የአዲስ ገንዘብ ወደ ገበያው መቀላቀልን) እንዲጨምር ያደረገ መሆኑን ነው ጥናቱ ያመለከተው፡፡ መንግሥት የጥሬ ብር ኅትመትና ሥርጭትን በሚጨምር ሁኔታ ከብሔራዊ ባንክ መበደሩ ሳያንስ፣ በአበዳደሩ ላይ ልቅ የሆነና በሕግ ያልታሰረ አሠራር መከተሉ፣ በኢትዮጵያን ለረዥም ዓመታት ለዘለቀው የዋጋ ግሽበት ችግር ዋና ምንጭ እንደሆነ ነው የሁለቱ ባለሙያዎች ጥናት በትኩረት የሚያወሳው፡፡

ይህን የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት ዋና መነሻ ልል የፊስካልና የሞኒተሪ ፖሊሲ ነው የሚለውን ሙግት መንግሥት ለመቀበል ለብዙ ዓመታት ሲያመነታ ቆይቷል፡፡ ይህ ደግሞ አገሪቱ ካለባት የምርት አቅርቦት እጥረት፣ ፈጣን የሕዝብ ቁጥር መጨመርና የኢኮኖሚ በሚባለው ፍጥነት አለማደግ ችግር ጋር ተዳምሮ፣ ቀውሱን እንዳከፋው ነው የሚነገረው፡፡

መንግሥት የዋጋ ንረቱን ዋና አባባሽ የሆነውን ችግር ወደ ጎን ብሎ ችግሩን በገበሬውና በነጋዴው ላይ ለማላከክ መሞከሩ ደግሞ ፈታኝ እንደነበር ይወሳል፡፡ በዓለም የሚታየው የገበያና የኢኮኖሚ ሁኔታ የማይተነበይ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ መንግሥት የዋጋ ንረቱን መነሻ ውጫዊ ለማድረግ የሄደበት ርቀትም ለችግሩ መፍትሔ የማፈላለጉን ጥረት እንደፈተነው ነው የሚነገረው፡፡

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምሕረቱ ግን ለዚህ ጉዳይ ዕውቅና የሰጡት ነው የሚመስለው፡፡ ከአሥር ወራት ቀደም ብሎ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የዋጋ ንረት ላለፉት በርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ ከባድ የማክሮ ኢኮኖሚ ፈተና ሆኖ መቆየቱን አምነዋል፡፡ ‹‹ባለፉት አሥር ዓመታት የዋጋ ንረት በአማካይ ከ16 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ በአማካይ ከ30 በመቶ በላይ ዕድገት አሳይቷል፡፡ የዋጋ ንረት በደሃው የኅብረተሰብ ክፍል የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ብዙ ጉዳት አለው፡፡ የዋጋ ንረት ለረዥም ጊዜ በቆየ ቁጥር አሁን በኢትዮጵያ እንደሆነው ሥር የሰደደ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥጋት ይፈጥራል፡፡ የዋጋ ንረት ይኖራል የሚለው ሥጋት በራሱ ለዋጋ ንረት መባባስ ምክንያት ይሆናል፤›› ሲሉ በዚያ መግለጫ የተናገሩት ገዥው፣ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ጥብቅ የፊስካልና የሞኒተሪ ፖሊሲ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ቃል ገብተው ነበር፡፡

ከአምስት ወራት ቀደም ብሎ ደግሞ ከብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ባንኩ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር ዋና ትኩረቱ አድርጎ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም በስድስት ወራት ውስጥ የዋጋ ንረት ምጣኔ ላይ አንፃራዊ ቅናሽ መመዝገቡን አምነው ነበር፡፡

 ‹‹በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን የብድር ዕድገት በ14 በመቶ ገተነዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት የሚሰጠውን የቀጥታ ብድርም በ75 በመቶ ቀንሰነዋል፡፡ ባንኮች ወደ እኛ ለብድር ሲመጡ የምናስከፍለውን ወለድ ምጣኔ ወደ 18 በመቶ አሳድገነዋል፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴርም ጥብቅ የፊስካልና የሞኒተሪ ፖሊሲ መከተል ጀምሯል፡፡ የመንግሥት የሀብት አጠቃቀምን ከብክነት በፀዳ መንገድ ለመምራት የሚያስችሉ ጥብቅ አሠራሮች ተዘርግተዋል፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ ማሞ፣ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር በወሬ ሳይሆን ተጨባጭ ዕርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስረድተው ነበር፡፡ እሳቸውም ሆኑ መንግሥት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ተጨባጭ ዕርምጃዎችን መውሰድ ስለመጀመራቸው ብዙ ቢናገሩም፣ ነገር ግን እስካሁንም የኢትዮጵያን ገበያ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ተጭኖት ይገኛል፡፡

መንግሥት በግልጽ ባያምነውም የሰሜኑ ጦርነት ተፅዕኖ፣ በየአካባቢው የሚካሄዱ ግጭቶች፣ እንዲሁም መንግሥት በሰፊው ከቀጠለው የግንባታና የፕሮጀክቶች ወጪ ጋር ተደራርበው የዋጋ ንረቱ ሕዝቡ መሸከም ከሚችለው በላይ እንዲሆን አድርገውታል የሚለው ሙግት በሰፊው ይወሳል፡፡ ይህም ሆኖ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ባወጣቸው አዳዲስ አዋጆችና የአሠራር ማሻሻያዎቹ የዋጋ ንረቱን በመሠረታዊነት የሚፈቱ ዕርምጃዎችን አካቶ ማቅረቡ ትልቅ ዕርምጃ እየተባለ ነው፡፡

በተለይ አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ማሻሻያ አዋጅ ከዚህ ቀደም ለረዥም ዓመታት ሲሠራበት የቆየውንና ለዋጋ ንረት ዋና መነሻ ነበር ሲባል፣ በቆየው አሠራር ላይ ጠበቅ ያለ የማሻሻያ ድንጋጌ ይዞ መቅረቡ እየተመሠገነ ነው፡፡

የብሔራዊ ባንክ ግብ የፋይናንስና የዋጋ ንረትን ማረጋጋት እንደሆነ በመጥቀስ የሚንደረደረው አዲሱ ረቂቅ አዋጅ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጡ አዋጆችም ይህንኑ ግብ ለማሳካት በሚያስችል መንገድ በየጊዜው ማሻሻያ ሲደረግባቸው መቆየቱን ያትታል፡፡ ብሔራዊ ባንክን መጀመሪያ ያቋቋመው ቻርተር ቁ.30/1955 ከወጣ በኋላ በ1955፣ በ1968፣ በ1986 እና በ2000 የወጡ የገንዘብና የባንክ አዋጆች መኖራቸውን ይጠቅሳል፡፡ እነዚህ አዋጆች የወጡባቸው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ዐውዶች የተለያዩ ቢሆንም፣ ለብሔራዊ ባንክ ቁልፍ ሚናና ተቋማዊ ህልውና ዕውቅና የሰጡ እንደነበሩ ይጠቁማል፡፡ የብሔራዊ ባንክን ሥልጣንና ኃላፊነት፣ የባንኩን አስተዳደር፣ ባንኩ ከሌሎች የመንግሥት አካላት ጋር የሚኖረውን ግንኙነትንም የሚወስኑ ሕጋዊ ማዕቀፎችን በግልጽ ያብራሩና ያስቀመጡ፣ የባንኩን ካፒታል ያሳደጉ እንደነበሩም ይገልጻል፡፡

እነዚህ አዋጆች ብሔራዊ ባንኩ ከመንግሥት ጋር የነበረውን ግንኙነት በምን መንገድ እንደወሰኑ አንድ በአንድ ያብራራል፡፡ በ1955 ዓ.ም. የወጣው የገንዘብና የባንክ አዋጅ ባንኩ ከመንግሥት ጋር ያለውን ግንኙነት ሲዘረዝር፣ ባንኩ ለመንግሥት የሚሰጠው ቀጥታ ብድር መጠን መንግሥት ባለፈው ዓመት ከሰበሰበው ገቢ 15 በመቶ እንዳይበልጥ የሚያዝ ሲሆን፣ በብድሩ ላይ ከሦስት በመቶ ያልበለጠ ዓመታዊ ወለድ እንደሚከፈልበትና ብድሩ የበጀት ዓመቱ ባለቀ በስድስት ወራት ውስጥ መከፈል እንዳለበት ይደነግጋል ይላል፡፡

አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ማብራሪያውን ሲቀጥልም በ1968 ዓ.ም. የወጣው የገንዘብና የባንክ ሥርዓት ቁጥጥር አዋጅ በበኩሉ፣ መንግሥት ከባንኩ የሚወስደውን የብድር መጠን ካለፈው በጀት ዓመት ገቢ ከ25 በመቶ እንደማይበልጥ ከማድረግ ውጪ የወለድ ተመኑም ሆነ የብድር መመለሻ ጊዜው ከ1963 ዓ.ም. አዋጅ ጋር ተመሳሳይ እንዲሆን አድርጎታል ይላል፡፡ የ1963 ዓ.ም. ያለውን አዋጅ ይዘት ግን ሳይዘረዝር ነው ያለፈው፡፡ ቀጥሎ የሚያነሳው በ1986 ዓ.ም. የወጣው የገንዘብና የባንክ አዋጅም ከብሔራዊ ባንክ የሚለቀቀው የቀጥታ ብድር መጠን መንግሥት ባለፉት ሦስት ዓመታት ከሰበሰበው አማካይ ገቢ ከ15 በመቶ እንደማይበልጥ፣ ብድሩም በቀጣይ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ ማለቅ እንዳለበት፣ ወለዱንም ባንኩ በገበያ ዋጋ እንደሚወስን ያስቀመጠ እንደሆነ ረቂቅ አዋጁ ያመለክታል፡፡

ቀጥሎ የመጣው ያለው አዋጅ ቁጥር 591/2000 ግን ቀደም ሲል የወጡ አዋጆችን ያሻሻለ ሲሆን፣ የመንግሥትና የብሔራዊ ባንክ የብድር ግንኙነት ገደብ ባለው መንገድ እንዳይመራ ያደረገ መሆኑን በግልጽ ይጠቁማል፡፡ በ2000 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ ባንኩ ለመንግሥትና ለፋይናንስ ተቋማት ብድር እንደሚሰጥ ከመግለጽ ውጪ ለመንግሥት በሚሰጠው ቀጥታ ብድር ላይ ግን ምንም ገደብ ሳይጥል በለሆሳስ ያለፈ የመጀመሪያው አዋጅ ነው ሲልም፣ አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ማሻሻያ አዋጅ አስቀምጦታል፡፡

ይህ በ2000 ዓ.ም. የወጣ አዋጅም ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበትን የሚቆጣጠርበትን አቅም ያዳከመ እንደነበር ጠቁሞ፣ አካሄዱ የዋጋ ንረትን አባባሽ መሆኑን ነው ያመለከተው፡፡ ይህን ለመቀየር አዲስ የአዋጅ ማሻሻያ ማስፈለጉን የጠቆመው አዋጁ በዚህም መሠረት፣ ‹‹በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 27 መሠረት ብሔራዊ ባንክ በጥሬ ገንዘብ ፍሰት ላይ የተመሠረተ ጊዜያዊ የኦቨር ድራፍት አገልግሎት ከ12 ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ተመላሽ የሚደረግ ብድር ለፌዴራል መንግሥት ሊሰጥ ይችላል፡፡ የብድር መጠኑም ካለፉት ሦስት የበጀት ዓመታት አማካይ ዓመታዊ የፌዴራል መንግሥት የአገር ውስጥ ገቢ ከ15 በመቶ መብለጥ የለበትም፤›› ቃል በቃል ሲል አዲስ የብድር ገደብ ማውጣቱን ይደነግጋል፡፡

ይህ አዲስ የሕግ ማሻሻያ በኢትዮጵያ ያለቅጥ በተንሰራፋው የዋጋ ንረት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ ስለመሆኑ ማብራሪያ የተጠየቁት የቀድሞ ከፍተኛ የባንክ የሥራ ኃላፊ የሆኑት አቶ እሸቱ ታዬ፣ የብሔራዊ ባንክ አቋም እንደ ዜጋም ሆነ እንደ ፋይናንስ ባለሙያ በእጅጉ የሚያስደስት ሆኖ እንዳገኙት ነው የተናገሩት፡፡

‹‹ለረዥም ጊዜ ለመንግሥት በቀጥታም ሆነ ቀጥታ ባልሆነ መንገድ የሚሰጠው ብድር ገደብ እንዲበጅለት ሲጠየቅ ቆይቷል፡፡ ብሔራዊ ባንኩ በአዲሱ አዋጁ የመንግሥት የሦስት ዓመታትን ጥቅል የኢኮኖሚ ገቢ አይቼ ነው የዚያን 15 በመቶ ብድር የምሰጠው፣ ይህም ተንከባላይ አይደለም፣ ብድሩን ሲከፍል ብቻ ነው ተጨማሪ ብድር መጠየቅ የሚችለው ማለቱ በእኔ ግምት ደፋርና ለውጥ የሚያመጣ ድንጋጌ ነው፤›› ሲሉ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

የብሔራዊ ባንክ አዋጅ ባንኩ ከመንግሥት፣ ከባንኮች፣ ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮችና የፋይናንስ ተቋማት ጋር እንዲሁም ከግለሰቦች ጋር ጭምር የሚኖረውን ግንኙነት የሚወስን እንደሆነ የጠቆሙት አቶ እሸቱ፣ አዲሱ ሕግ በትክክል ከተተገበረ ትርጉም ያለው ለውጥ በዋጋ ንረት ላይ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡

‹‹የባንኮችን የብድር ጣሪያ ከ14 በመቶ በላይ እንዳይሆን ብሔራዊ ባንክ ክልከላ አድርጎ ነበር፡፡ ይህን ያደረገው ደግሞ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር እንደነበር አስታውቋል፡፡ ባንኮችን ብድር ከልክሎ መንግሥት በሚበደረው ገንዘብ ላይ ገደብ ካላስቀመጠ ግን ለዋጋ ግሽበቱ መሠረታዊ አባባሽ ምክንያት የመንግሥት ብድር ነው ተብሎ ይፈረጃል፡፡ አሁን ግን በባንኮች በኩል ግለሰቦች በሚያገኙት ብድር ላይ ቁጥጥር ከማድረግ ጎን ለጎን በመንግሥት አበዳደር ላይም ቁጥጥር አቅቷል፡፡ ይህ በሁለቱም መንገድ በመንግሥትም በግለሰቦችም ተበዳሪነት ላይ ቁጥጥር የሚያደርግ ነው ማለት ነው፡፡ እስከ 2026 ባለው ዓመት ብሔራዊ ባንኩ የዋጋ ግሽበትን እስከ አሥር በመቶ ባለው አኃዝ ለማውረድ ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት ታስቦ የወጣ አዋጅ ይመስለኛል፤›› በማለትም አቶ እሸቱ ሐሳባቸውን አክለዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ይህ በአዲሱ አዋጅ የፌዴራል መንግሥት ከባንኩ የሚበደረውን ብድር መገደቡ በብዙዎች ዘንድ እየተደነቀ ቢሆንም፣ ከዚሁ ጎን ለጎን ግን ሥጋት የሚያነሱ ወገኖች አልጠፉም፡፡ ከእነዚህ አንዱ የሆኑት የኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ዋሲሁን በላይ አዲሱ አዋጅ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ ሊበደርባቸው የሚችልባቸው ምክንያቶች ተብለው የተዘረዘሩትን አመክንዮዎች ያጣቅሳሉ፡፡ ‹‹መንግሥት ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ማለትም ያልተጠበቀ የማኅበረሰብ ጤና፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ ድርቅ ወይም አግባብነት ያለውን ሕግ መሠረት አድርጎ የታወጀ አጠቃላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና በፌዴራል መንግሥት ገቢ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ጉልህ የውጭ ኢኮኖሚ ለውጦች በተከሰቱ ጊዜ ይህን ጊዜያዊ ችግር ለመቅረፍ ሲባል፣ ብሔራዊ ባንክ ተጨማሪ ብድር ለመንግሥት የሚሰጥበትን አግባብ ደንግጓል›› ተብሎ የተቀመጠውን ንዑስ ድንጋጌ የሚያወሱት አቶ ዋሲሁን፣ ‹‹ኢትዮጵያ ከእነዚህ ችግሮች ወጥታ የምታውቀው መቼ ነው፤›› ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ አዋጁ የመንግሥት ብድርን በሚመለከት ገደብ ካስቀመጠ በኋላ ይህን ሁሉ የመበደሪያ ቅድመ ሁኔታ መደርደሩ፣ በተጨባጭ የአዋጁ ገደብ ትርጉም ኖሮት እንዳይሠራ የሚያደርግ መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡

‹‹ከዚህ ቀደም ፍራንኮ ቫሉታ ተብሎ ከየትም ባመጣችሁት ዶላርም ቢሆን መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን ከውጪ ብታስመጡ ከቀረጥ ነፃ እንዲገባላችሁ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ዶላር ያገኛችሁበትንም ምንጭም አልጠይቅም የሚል አሠራር መንግሥት ተገበረ፡፡ ከሰሞኑ ባወጣው የንብረት ማስመለስ አዋጅ ላይ ግን ይህን አፍርሶት ጭራሽ አሥር ዓመት ወደኋላ ተመልሼ ያገኛችሁትን ዶላር ምንጭ በደረሰኝ ካላረጋገጣችሁ ንብረታችሁን እስከ መውረስ ልሄድ እችላለሁ የሚል ድንጋጌ አስቀመጠ፤›› በማለት ምሳሌዎችን የጠቃቀሱት አቶ ዋሲሁን፣ ሕጎች እርስ በእርስ የሚጣረሱ ወይም በተጨባጭ ወደ መሬት መውረድ ካልቻሉ ባይወጡ እንደሚሻል ነው ሐሳባቸውን የሰጡት፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ ባሉት አጭር ዓመታት በግምት ከ30 በላይ የብሔራዊ ባንክና የገንዘብ ሚኒስቴርን አሠራሮች የሚቀያይሩ የሕግ ማሻሻያዎችና መመርያዎች እንደወጡ የጠቀሱ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የፋይናንስ ባለሙያ በበኩላቸው፣ ይህ መመርያና ሕግ በፍጥነት የመቀያየር አባዜም የማክሮ ኢኮኖሚውን ሕመም ጠቋሚ ምልዕክት ነው ብለዋል፡፡

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ አዋጅም ወዲያው የሚቀየር ወይም በተለያዩ እንቅፋቶች የማይሠራ ሳይሆን፣ በተጨባጭ የአገሪቱን ዋና ሕመም የዋጋ ግሽበትን የሚያክም መሆኑ በቅርቡ በተጨባጭ እንደሚታይ ግምታቸውን ሰጥተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -