Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አምራች ኢንዱስትሪዎች በቀናት ውስጥ የቦታና የቤት ግብር ካልከፈሉ ይታሸጋሉ መባሉ ቅሬታ አስነሳ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር አዲስ ያወጣው የቦታና የቤት ግብር ተመን እንዲያስተካክልላቸው ጥያቄ ያቀረቡ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምላሽ ሳያገኙ ግብሩን በቀናት ውስጥ ካልከፈሉ ድርጅቶቻቸው እንደሚታሸጉ የሚገልጽ ደብዳቤ እንዲደርሳቸው መደረጉ እንዳሳሰባቸው ተገለጸ፡፡

ከኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው የከተማ አስተዳደሩ አዲስ ባወጣው አዋጅ መሠረት አምራች ኢንዱስትሪዎቹ እንዲከፍሉ የተጠየቁትን የቦታና የቤት ግብር በሦስት ቀናት ውስጥ ካልከፈሉ እንደሚታሽኑ የሚገልጸው ደብዳቤ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ እንዲደርሳቸው እየተደረገ ነው፡፡ 

ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት አምራች ኢንዱስትሪዎች በአዋጁ ላይ የተቀመጠውን የግብር መጠን መክፈል እንደሚቸገሩ ጠቅሰው ላቀረቡት አቤቱታ ከከተማ አስተዳደሩ ምላሽ እንደሚሰጣቸው ተገልጾላቸው ይህንኑ እየተጠባበቁ ባሉበት ሰዓት የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ፍሬ ግብሩን እስከነ ቅጣቱ እንዲከፍሉ ደብዳቤ እንዲደርሳቸው አድርጓል፡፡ 

በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ግብሩን ካልከፈሉም ድርጅቶታቸውን ወደ ማሸግ ዕርምጃ እንደሚገባ ማሳወቁ አምራች ኢንዱስትሪዎችን እንዳሳሰበም የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አበባየሁ ግርማ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

ምክር ቤቱ የአባላቱን ቅሬታ በመያዝ በሕጉ ላይ የተቀመጠውን ግብር ተመን አምራች ኢንዱስትሪዎቹ መክፈል እንደማይችሉ በመግለጽ ሕጉ ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ በተደጋጋሚ ሲሟገት ነበር፡፡ 

የቦታና የቤት ግብሩ አምራች ኢንዱስትሪውን ባገናዘበ ሁኔታ ለብቻው ራሱን የቻለ ተመን ሊወጣለት ይገባል በማለት ምክር ቤቱ የአባላቱን ቅሬታ በተደጋጋሚ ጊዜ ለከተማ አስተዳደሩ ማቅረቡን ያስታወሱት አቶ አበባየሁ፣ ለቀረበው ጥያቄ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ምላሽ ሳይሰጠው ቆይቶ አሁን ላይ አምራች ኢንዱስትሪዎቹ ግብሩን ከነ ቅጣቱ እንዲከፍሉ መጠየቃቸው ተገቢ አለመሆኑን አመልክተዋል፡፡ 

ከዚህ ግብር ጋር ተያይዞ አሉብን ያሉትን ችግሮች በዝርዝር በደብዳቤና በግንባር በመቅረብ ማስረዳታቸውንና ይህንንም ተከትሎ ጉዳዩን የሚመለከት ኮሚቴ ተቋቁሞ ምላሽ እየተጠበቀ ሳለ የከተማ አስተዳደሩ የገቢዎች ቢሮ አምራች ኢንደስትሪዎቹ ግብሩን እንዲከፍሉ ማስጠንቀቁና የማሸግ ሙከራዎችን መውሰዱ አሳሳቢ እንደሆነባቸው አቶ አበባየሁ ገልጸዋል፡፡ 

አቤቱታቸውን ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት ጀምሮ ለምክትል ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ለአዲስ አበባ ፋይናንስ ቢሮ፣ ለአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሁሉ ማሳወቃቸውን፣ ከዚህም በተጨማሪ የዘርፍ ምክር ቤቱ አመራሮችና ተወካዮች በግንባር በመቅረብ ጭምር አስረድተው እንደነበር ከአቶ አበባየሁ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ 

በእንጥልጥል ላይ ያለው ጉዳይ መቋጫ ሳያገኝ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የቤትና ቦታ ግብር ስላልከፈላችሁ በሚል የሦስት ቀን የጊዜ ገደቡ እንዳለቀ በኋላም አንዳንድ ኢንዱስትሪዎችን ለማሸግ የተደረገው ሙከራ አምራቾችን ተረጋግተው ሥራቸውን እንዳይሠሩ ማድረጉንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ የእሸጋ ሙከራ የተደረገባቸው ኢንዱስትሪዎች ሳይታሸጉ የቀሩት ሠራተኞች እንዳይታሸግ ባደረጉት መከላከል እንደነበር የገለጹት አቶ አበባየሁ እንዲህ ያለው ሁኔታ ቅር እንዳሰኛቸው አመልክተዋል፡፡ 

ድርጊቱ መደናገጥን ስለፈጠረ የዘርፍ ምክር ቤቱ ይህንኑ ለሚመለከታቸው አካላት ቢያሳውቅም ምንም የተለየ ምላሽ ማገኘት እንዳልቻለ ገልጸዋል።

ድርጅቶቹ እንደሚታሸጉ የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ከደረሳቸው በኋላ የምክር ቤቱ ተወካዮች ወደ ገቢዎች ቢሮ በመሄድ ስለሁኔታው ያስረዱ ቢሆንም፣ ቢሮው ግን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. የሚፈለግባቸውን እንዲከፍሉ የሚሰጠው ጊዜ የቀናት ብቻ እንደሆነ መግለጹ አምራቾች የበለጠ እንዲሠጉ አድርጓቸዋል፡፡ 

አሁን ባለው ሁኔታ ለአምራቾቹ የቀረበው ጥያቄ ፍሬ ግብሩን እንዲከፍሉ ብቻ ሳይሆን ቅጣትም የተካተተበት በመሆኑ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ከባድ እንደሚሆን ገልጸዋል።

አስተዳደሩ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ለዚህ ጉዳይ እልባት ካልሰጠ የገቢዎች ቢሮ ማምረቻዎቹን ሊያሽግ ስለሚችል በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ችግር ላይ ሊወድቁ ይችላሉ ተብሏል፡፡ 

እንዲህ ያለው ችግር ጎልቶ ታይቶ የነበረውም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ኢንዱስትሪዎቹ በብዛት በሚገኙበት ወረዳ 12፣ 9፣ 7 እና 10 ውስጥ ነው፡፡ 

የአምራች ኢንዱስትሪዎቹ የጠየቁት ግብሩ ቀሪ እንዲሆንላቸው ሳይሆን አምራች ኢንዱስትሪ መሆናቸውን ያገናዘበ ታሪፍ እንዲወጣላቸው መሆኑን የገለጹት አቶ አበባው፣ የቦታና የቤት ግብር አዋጁ ላይ የተቀመጠው ታሪፍ የመኖሪያና የሥራ ቦታን ታሳቢ አድርጎ የተቀረፀ መሆኑን አስረድተዋል። ስለሆነም አምራች ኢንዱስትሪዎችን ያገናዘበ ታሪፍ ለተይቶ እንዲወጣ ይውጣ ያቀረቡት ጥያቄ አግባብ መሆኑን እና ይህንንም የከተማ አስተዳደሩ የተቀበለው ሐሳብ እንደነበር ነገር ግን በመሀል ግብሩን ከነ ቅጣቱ እንዲከፍሉ የወሰነበት ምክንያት እንዳልገባቸው ጠቅሰዋል፡፡

ኢንዱስትሪዎቹ ሰፊ ቦታ ይዘው የሚሠሩ በመሆኑ በአዲሱ ሕግ የተቀመጠውን የጣራ ግብር ተመን ባለው ሁኔታ ይክፈሉ ከተባለ ካላቸው አቅም አንፃር ተፈጻሚ ሊሆን እንደማይችልም እየገለጹ ነው፡፡ 

አሁን ባለው አካሄድ ግብሩን ያልከፈሉ አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ አብዛኞቹ ኢንዱስትሪዎች ይታሸጋሉ የሚል ሥጋት ያደረባቸው አቶ አበባየሁ፣ ጉዳዩ የአስተዳደሩን ፈጣን ምላሽ የሚጠይቅ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ 

ከዚሁ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የቦታና የቤት ግብር አሁን በወጣው ተመን  መሠረት እንዲከፍሉ የተወሰነባቸው አምራች ኢንዱስትሪዎች ሌላው ቅሬታ ከተወዳዳሪነት አንፃር የሚፈጠረው ተፅዕኖ ነው፡፡ 

ይህም ኢንዱስትሪዎቹ ባሉባቸው አካባቢዎች ተመሳሳይ የሆነ ሥራ በክላስተር ተደራጅተው ማምረቻ ቦታ ከመንግሥት ተከራይተው የሚሠሩ አምራቾች ይህ ግብር የማይመለከታቸው መሆኑ ነው። በግል ይዞታቸው የሚሠሩት ግን ግብር እንዲከፍሉ መደረጋቸው ተወዳዳሪነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚያሳርፍ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችም እየቀረቡ ካሉት ጥያቄዎች ጋር እንዲታዩ አባላቱ ጥያቄ እየቀረቡ መሆናቸውን ከአቶ አበባየሁ ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ 

ይህ ችግር ጎልቶ የሚታየው አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ሲሆን በዚህ ክፍለ ከተማ ወደ 200 የሚሆኑ አምራች ኢንዱስትሪዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ የሞባይልና የቴሌቪዥን መጣጠሚያዎች፣ የኤሌክትሪክ ኬብል ማምረቻዎች ይገኙበታል፡፡ በእንጨት፣ ብረታ ብረት፣ በኬሚካል፣ የእምነበረድና መሰል ማምረቻዎችም በዚህ የኢንዱስትሪ አካባቢ ውስጥ በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ 

ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ለኢንዱስትሪዎቹ እየደረሰ ያለው የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ደብዳቤ ከመሬት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በተላለፈላችሁ የልኬት ተመን መሠረት ክፍያ እንድትፈጽሙ የውሳኔ ማስታወቂያ የደረሳችሁ ቢሆንም ይህ ደብዳቤ ወጪ እስከሆነበት ድረስ ያልተከፈለ መሆኑን ያትታል፡፡ 

አያይዞም በታክስ አስተዳደር አዋጁ መሠረት ደብዳቤው ከደረሳቸው ቀን ጀምሮ በሦስት ውስጥ የቤትና የቦታ ግብሩን እንዲከፍሉ የሚያስጠነቅቅ ነው፡፡ 

‹‹ክፍያውን የማይፈጽሙ ከሆነ የንግድ ድርጅትዎን በጊዜያዊነት ከማሸግ ጀምሮ ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ዕርምጃዎች ልንወስድ የምንችል መሆኑን ማሳወቅ እንደወዳለን፤›› የሚል ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች