Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የኮሪደር ልማቱ መልካም ጎኖች ይጎልብቱ ጉድለቶቹም በፍጥነት ይታረሙ!

‹‹አዲስ አበባን እንደ ስሟ እናደርጋታለን!›› በሚል ተነሳሽነት የተጀማመሩ ሥራዎች የሚደገፉ ናቸው፡፡ ጨከን ብሎ ከተሠራ በአጭር ጊዜ ከተማን መለወጥ  እንደሚቻል እየተመለከትን ነው፡፡ የኮሪደር ልማቱ ይህንን እውነት እንድንመሰክር እያደረገን ነው፡፡  

የኮሪደር ልማቱ የአዲስ አበባ ከተማ ገጽታን ከመለወጥና ዓይነ ግቡ ከማድረግ ባሻገር፣ ፕሮጀክቱን ለማስፈጸም የተተገበሩ አሠራሮች ለሌሎች ፕሮጀክቶች እንደ ምሳሌ መወሰድ የሚችል ነው፡፡ ከፕሮጀክቶቹ ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ነዋሪዎች ምትክ ቦታ የመስጠትና ካሳ ለሚገባቸውም በፍጥነት ተገቢውን ክፍያ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው መባሉም በበጎ የሚታይ ነው፡፡

የካሳ ክፍያው ከዚህ ቀደም ከነበረው ልማድ በተለየ ሁኔታ እንዲቀርብ መደረጉና ይህንንም በፍጥነት መፈጸም መቻሉ በራሱ እንደ ጥሩ ልምድ የሚወሰድ ነው፡፡ አንዳንዶች ‹‹ከወደቀና ከዘመመ ቤት›› ወደ ፅዱ ‹‹የኮንዶሚኒየም ባለቤት›› መሸጋገር መቻላቸውን ሲገልጹ መስማት በራሱ እሰየው ያሰኛል።

ከሥራ ባህል አንፃርም ‹‹ጀንበር ሲያዘቀዝቅ ሥራ መሥራት አይቻልም›› የተባለ ይመስል፣ ለዘመናት አብሮን የቆየውን ክፉ ልማድ መቀየር የሚችል መሆኑን አሳይቷል፡፡ በቀን ብቻ ይሠሩ የነበሩ ሥራዎች በምሽት ጭምር መሠራት እንደሚቻል የታየበትና ለሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችም ልምድ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ 

ከተማዋን ከማዘመን አንፃር እየተተገበሩ ያሉ ፕሮጀክቶች ሌላም ነገር አሳይተውናል፡፡ ይህም ከይዞታ ውጪ ባልተገባ መንገድ የተገነቡ አጥሮችና ግንባታዎች ሲፈርሱ የአካባቢው ትክክለኛ ገጽታ እንዲወጣ ያደረጉ ቦታዎችም ታዝበናል፡፡ 

እንዲህ ያለው ዕርምጃው ሕገወጥ የሆኑ ግንባታዎቹና ተያያዥ ፕሮጀክቶች መስመር እንዲይዙ አድርጓል ሊባል ይችላል፡፡ ስለዚህ ይህ የኮሪደር ግንባታዎችና ተያያዥ ፕሮጀክት ከተማዋን ከማሳመር ባሻገር፣ ከተማዋን የጋረዱ ሽፍንፍኖች እንዲገለጡ አድርጓል፡፡ 

የኮሪደር ልማቱ መልካም ጎኖች እንደታዩበት ሁሉ ከልማቱ ጋር ተያይዘው የታዩ ችግሮችም አሉና ዕርምት ያስፈልጋቸዋል፡፡ አንዳንድ ዕርምጃዎችም የሚጎረብጡ ስለመሆናቸው ታዝበናል፡፡ አንዱ የኮሪደር ልማቱ በሚያልፉባቸው አካባቢዎች ተነሺዎቹ በጥድፊያ እንዲነሱ መደረጉንና አንዳንዶችም በቂ ካሳ አለማግኘታቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ለተነሺዎች በቂ ግንዛቤ ቀድሞ ካለመስጠት ጋር ተያይዞ ሲፈጠር የምናየው መጨናነቅም የችግሩ አካል ነው፡፡  

ተጠናቅቀዋል ወይም እየተጠናቀቁ ነው በተባሉ የኮሪደር ልማት መስመሮች ላይም ተጨማሪ ፈረሳዎች እየተካሄዱና ሊካሄዱ እንደሚችሉ እየተገለጸ ነውና ይህም ነዋሪዎች ተረጋግተው ሥራቸውን እንዳይሠሩ እንቅፋት መሆኑም ይገለጻል፡፡ ሥራው በጥናት ላይ ተመሥርቶ የተጀመረ ከሆነ የሚፈርሱ ግንባታዎችን ቀድሞ በመለየት መከናወን ሲገባው ከሥር ከሥር አዲስ ዲዛይን በማውጣት ተጨማሪ ግንባታዎችን ለማፍረስ መነሳት ተገቢ አይደለም፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ አካባቢዎች ‹‹የሚፈርስባችሁ እዚህ ድረስ ነው›› ተብሎ ከፈረሰ በኋላ፣ አዲስ አጥር አጥረው የተቀመጡ ባለይዞታዎች እንደገና አፍርሱ የሚባሉበትንም ሁኔታ እያየን ነው፡፡ እንዲህ ያለው ጉዳይ ከዚህ በኋላ እንዳይደገም ካልተደረገ ቅሬታ ሊፈጥር እንደሚችል ማሰብ ያስፈልጋል፡፡  

አንዳንድ ቦታዎች ላይ አሁንም ተጨማሪ ቦታ ለማግኘት የግለሰቦችና የኩባንያዎች ቤቶችንና ሕንፃዎችን ለማፍረስ እየተወሰደ ያለው ዕርምጃም ቢሆን የሚጠቁመን ክፍተት መኖሩን ነው፡፡  

አንዳንድ ድርጅቶች በጥድፊያ ተነሱ የሚባሉ በመሆኑ ቦታውን ከለቀቁ በኋላ ባገኙት ምትክ ቦታው ሥራቸውን ለማስቀጠል እየተቸገሩ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ዕቅድ ተለውጦ ይሁን አይሁን በማይታወቅ ምክንያት ከፈረሳ ድንዋል የተባሉ ግንባታዎች ሰሞኑን እንደሚፈርሱ የተገለጸላቸው ባለይዞታዎች እየተወሰደ ባለው ዕርምጃ ቅሬታቸውን እያቀረቡ ቢሆንም መልስ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ 

ሌላም እናክል፣ የከተማዋን ውበት ለመጠበቅ ሲባል ሰፋ ያለ የተሽከርካሪ መንገድ፣ የእግረኛና የሳይክል መንገዶች ተሠርተዋል፡፡ እነዚህ መንገዶች አምረዋል፡፡ መንገዶቹ የበለጠ ውበት የሚኖራቸው ከሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ሌላ የትኛውም ተሽከርካሪ መንገዶች ላይ ማቆም ሲከለከል ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ መንገዶቹ ታሳቢ ያደረገ በተወሰነ ርቀት የተሽከርካሪዎች ማቆሚያ (ፓርኪንግ) ግድ ይላል፡፡ አሁን እንደሚታየው ግን ከተጠናቀቁና እየተጠናቀቁ ባሉ መስመሮች ላይ በቂ ፓርኪንግ የለም፡፡ በዚህ ላይ በመንገዶቹ ላይ ተሽከርካሪዎች መቆም የለባቸውም ተብሎ የትራፊክ ምልክቶች እየታየ ነው፣ ትራፊኮችም እየቀጡ ነው፡፡ 

በቂ ፓርኪንግ ባልተዘጋጀበት ሁኔታ መኪና ማቆም መከልከልና ሲቆሙ መቅጣት ምን ያህል ተገቢ ነው? እነዚህ መንገዶች ላይ ተሽከርካሪ መቆም ከሌለበት በቂ ፓርኪንግ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ፕሮጀክቱን የሚመሩ ኃላፊዎች እንዲህ ያሉ ክፍተቶችን እየደፈኑ ከቀደሙ ችግሮች ትምህርት እየወሰዱ ማስተካከያ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ 

አስተዳደሩ ቀጣይ የኮሪደር ልማቶችን በሌሎች የከተማው ክፍል የሚያስፋፋ ከመሆኑ አንፃር፣ በመጀመሪዎቹ ምዕራፎች የታዩ ክፍተቶችና ቅሬታዎችን የማረም ኃላፊነት አለበት፡፡ ነዋሪዎችም ብዙ ዋጋ የተከፈለባቸውን እነዚህን ፕሮጀክቶች መንከባከብ ግድ ሊላቸው ይገባል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን የከተማዋን ገጽታ ለመለወጥና ምቹ የኑሮ ቦታ እንዲኖር በማድረግ ጥረት ውስጥ የሚደገፍ ቢሆንም ቅሬታዎችን የሚያበራክቱ ተግባራትን መቀነስ ያስፈልጋል፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት