Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ሥራችን ተከብሮ እየሠራን ነው ብዬ አስባለሁ›› ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር

ቀደም ሲል በተለያዩ ተቋማት በኃላፊነቶች ሲሠሩ የቆዩትና 2014 .. የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን በዋና ኦዲተርነት እንዲመሩ የተሾሙት  / መሠረት ዳምጤ፣ በኦዲት ክፍተቶች ላይ በሚደረጉ ውይይቶች ጠንከር ያሉ አስተያየቶች በመስጠት ይታወቃሉ፡፡ / መሠረት የመንግሥት ተቋማት የፋይናንስና የክዋኔ ኦዲት መሻሻል እያመጣ ቢሆንም፣ አሁንም ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት መገንባት እንዳለበት፣ የተጠያቂነት ሥርዓቱ ተጠናክሮ የተቋማት የኦዲት ውጤት ንፁህ ውጤት እስኪመጣ ድረስ በሥ ሙሉ ዕርካታ አላገኝም ይላሉ፡፡ ዋና ኦዲተሯ አጠቃላይ የኦዲት ሥራና የመንግሥት ተቋማት የፋይናንስና ክዋኔ ሒደትን በተመለከተ ከሲሳይ ሳህሉ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ 

ሪፖርተር:የዋና ኦዲተርነት ኃላፊነት ከያዙ ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በኃላፊነቱ ምን ዓይነት ጉዞ እያደረጉ ነው?

/ መሠረት:- የሚገርምህ እኔ ዕድለኛ ነኝ ብዬ መናገር እችላለሁ፡፡ ምክንያቱም በአጋጣሚ ከአቶ ገመቹ [የቀድሞ ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ] ጋር አብሬ ለስድስት ዓመታት ሠርቼያለሁ፡፡ ከተጠያቂነት ጋር በተያያዘ የነበረው ሁኔታ ሲታይ፣ ተቋማት በነበራቸው ቁመና ላይ አስተያየት ለመስጠት አይቻልም፣ የኦዲት ክፍተትም ሆነ ችግር ያለባቸው ደግሞ ግኝቶች ላይ ትኩረት አይሰጡም ነበር፡፡ አሁን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በቂ ነው ባይባልም ለውጦች አሉ፡፡ እኔ ይህን እንደ ጥሩ ጅምር አድርጌ እወስደዋለሁ፡፡ በአጠቃላይ ግን መጀመሪያ ሥራ ስጀምር ሠራተኞችን ሳልይዝ ስኬታማ መሆን እንደማልችል ተረድቼያለሁ፡፡ በርከት ያሉ አሳሪ መመርያዎች ነበሩ፡፡ ስድስት መመርያዎችንና አንድ ተጨማሪ አዲስ መመርያ አሻሽለን ወደ ሥራ አስገብተናል፡፡ ሌላው በፌዴራልና በክልል ዋና ኦዲተሮች መካከል የነበረው ግንኙነት የላላ ነበር፡፡ እኔ ለውጥ አመጣሁበት ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁንም ከክልሎች ጋር በፈጠርነው ግንኙነት ሥልጠና መስጠት ጀምረናል፡፡ የሥልጠና ክፍሉ ራሱን ችሎ እንዲቋቋም አድርጌዋለሁ፡፡ ከዚህ በፊት ሥልጠና የሚሰጠው ኦዲተሩ ከኦዲት ሥራው እየተፈናቀለ፣ አንዳንዴ ደግሞ እኛ በማናውቀው ሁኔታ ራሳቸው አሠልጣኞቹ በግል ከክልሎች ጋር እየተነጋገሩ ከተቋሙ ዲሲፕሊን ውጪ በሆነ መንገድ ነበር፡፡ አሁን ግን የሥልጠና ክፍሉንና ሥልጠናውን ይፋዊ አድርጌው ከክልሎች ጋር ግልጽ ግንኙነት ፈጥረንና አደራጀተን የሚፈልጉትን ሥልጠና እንሰጣቸዋለን፡፡ ቀድሞ በግል የሚደረጉ ግንኙቶች ግን የእኛን ተቋም ሥራ ይጎዱ ነበር፡፡ ያንን አሁን አስቁመናል፣ ይህ አንድ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡

ሌላው ከደመወዝ ጋር በተገናኘ ነው፡፡ አሁን ያለው ደመወዝ በቂ ነው ብዬ ባላስብም ሠራተኞች ከቀደመው የተሻለ ነገር ያገኛሉ፡፡ የዋና ኦዲተር ሥራ ስኬታማ የሚሆነው ማንም ጣልቃ አይገባበትም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚተገበር ስታንዳርድ አለው፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ የኦዲት አሠራር ደግሞ አስገዳጅ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉም አፍሪካ ውስጥ ያሉ የኦዲተሮች ማኅበርም አባል ናት፡፡ ስለዚህ በስትራቴጂካዊ ዕቅዳችን በሙያ የተደገፈ አድርገን ነው እየሠራን ያለነው፡፡ ከዓለም አቀፉ ስታንዳርድ ጋር የሚናበብ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ነው፡፡ ተቋሙ ውስጥ ማንም ጣልቃ ሳይገባበት ሙያውን መሠረት አድርገን ስለምንሠራ ሥራችን ውጤታማ ነው፡፡ በዚህም እስካሁን በምናቀርባቸው ሪፖርቶች ይህን አወጣችሁ፣ በምንናገራቸው ነገሮች ይህን ተናገራችሁን የሚል ወቀሳ አይመጣብንም፡፡ እኔ በአንድ ተቋም ወይም አካል የሆነ ነገር ብደረግ ደግሜ አልናገርም፣ ወይ ሥራውን እተወዋለሁ እንጂ፡፡ ስለዚህ በማቀርበው ሪፖርት ይህን ለምን አቀረብሽ አልተባልኩም፡፡ ከእኔ በፊት የነበሩት አቶ ገመቹም አልተባሉም፡፡ አሁንም ልበ ሙሉ ሆነን ነው የምናቀርበው፡፡ ምክንያቱም የምናቀርበው ሪፖርት በማስረጃ የተደገፈ እውነታ ነው፡፡ ስለዚህ ሕገ መንግሥቱ የሰጠንን መብት እየተገበርን ነው፡፡ እኛ ፈልገን ብቻ ሳይሆን ምክር ቤቱ ይህን እንድናደርግ ፈቅዶልናል አስፈጻሚውም ይህን ዕድል ሰጥቶናል፡፡

ሪፖርተር:መታዊ የኦዲት ሪፖርት እየቀረበ ያለው የቀጣይ መት ረቂቅ በጀት ሊፀድቅ ትንሽ ጊዜ ሲቀረው ነው በጀት ተልድሎ ለምክር ቤት ከመላኩ በፊት ኦዲት ቀሞ መቅረብ የለበትም? ይህ አሠራር ትክክለኛ ነው ብለው ያስባሉ?

/ መሠረት:- ትክክል ነው፣ አሁንም በጀቱ አልፀደቀም እኮ፡፡ ምክንያቱም የእኛ ሪፖርት ሳይቀርብ በጀት አይፀድቅም፡፡ አሁንም በቂ ጊዜ አለው፣ በጀቱ ላይ ውይይት ለማድረግ ጊዜ አለ፡፡ የእኛን ሪፖርት መነሻ አድርገው ሪፖርቱን ከተመለከቱ በኋላ ነው በጀቱ ላይ ተወያይተው የሚያፀድቁት፣ እሱን ለማድረግ አሁንም ጊዜ አለ፡፡

ሪፖርተር:የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትመንግሥት ወጪ አስተርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢነት በተፎካካሪ ፓርቲ የተያዘ ነበር፡፡ ነገር ግን ቋሚ ኮሚቴውን ይመሩት የነበሩት ግለሰብ ከታሰሩ በኋላ ብሳቢበገዥው ፓርቲ አባል ተይዟል። ይህ መለዋወጥ በኦዲት ግኝት ውይይትና ቁጥጥር ሥራ ላይ ምን ችግር ፈጠረባችሁ?

/ መሠረት:- እንግዲህ የሌሎች አገሮች ልምድም የሚያሳየው ይህን ነው፡፡ እስካሁን ድረስ በነበረው ልምድም፣ ከዚህ በፊት በኢሕአዴግ ዘመንም የገዥው ፓርቲ አካል ያልሆኑ እንዲመሩ ተብሎ የተመረጡ ተወካዮች ነበሩ፡፡ ይኼኛው ፓርላማ ሥራ ከጀመረ ወዲህም አቶ ክርስቲያን [ታደለ] ነበሩ፣ አሁን ብልጽግና ሆኗል።

እንግዲህ ይህን በተመለከተ ፓርላማውን ብትጠይቅ አይሻልም? ፓርላማው ነው የሚሾመውም፣ የሚያስቀምጠውም፡፡

ሪፖርተር:ከሥራችሁ አንፃር የፈጠረባችሁ ማነቆ አለ?

/ መሠረት:- እኛ ከሥራችን አንፃር ተፅዕኖ የፈጠረብን ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም እኔ ማስተላለፍ የምፈልገውን መልዕክት እያስተላለፍኩ ነው፣ እንዳላስተላልፍ ያገደኝ ነገር የለም፡፡ በአጋጣሚ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙትም የኦዲት ልምድ ስላለቸው ሙያው ላይ ብዙ ትኩረት ስለሚሰጡ ያን ያህል ክፍተት ብዙ አላጋጠመንም፡፡ ምናልባት የሰው ለውጡና ጉዳዩ ለሦስተኛ ወገን ሊሆን ይችላል ጎልቶ ሊታይ የሚችለው፡፡ የሰብሳቢነት ቦታ በተፎካካሪ ፓርቲ መያዙ በሌሎች አገሮች ያለው ልምድ የሚያሳየውም ይህንን ነው፡፡ ነገር ግን ይህ መሆኑ የበለጠ የሚጠቅመው ለመንግሥት ጥንካሬ ነው፣ ለማንም አይደለም፡፡ መንግሥት የበለጠ ተዓማኒ ሆኖ እንዲታይና እንዲሠራ ያደርገዋል፡፡ ከአሠራር አንፃር ግን እኔን ያወከኝና ተፅዕኖ የፈጠረብኝ ነገር የለም፡፡

ሪፖርተር:ዋና ኦዲተር የተቋማትን የፋይናንስ የክዋኔ ኦዲት አከናውኖ ሲያበቃ የኦዲት ግኝቶቹ ምንም ዓይነት ውጤት ይኑራቸው ለሕዝብ መቅረብ አለባቸው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ የኦዲት ሪፖርቱ ላይ ውይይትና ግምገማ ስታደርጉ ሕዝብ እንደማይሰማቸው ተደርገው በዝግ የሚከናወኑ አሉ፡፡ የእናንተን የሥራ ውጤት ሕዝብ አለማወቁ በዝግ መደረጉ አግባብ ነው ብለው ያምናሉ? የለፋችሁበትን ሥራ ግብር ከፋዩ ሕዝብ ካልሰማው እንዴት ይሆናል?

/ መሠረት:- በነገርህ ላይ በእኛም ስታንዳርድ ያገኘነው የኦዲት ውጤት አገር የሚያፈርስ ከሆነ እኔም አላወጣውም፡፡ ለሚመለከተው አካል እሰጣለሁ እንጂ ሪፖርቱ ወደ ሕዝቡ ቢገባ ምን ያመጣል የሚለው ታሳቢ ይደረጋል፡፡ አሁን እኛ የሠራነውንና ያገኘነው ሪፖርት ሁለንም ይፋ አናደርግም፡፡ ቀድመን ሪፖርት ሳናወጣ ጥንቃቄ መደረግ ያለበት ላይ ቀድመን ለሚመለከተው አካል እናቀርባለን፣ ዕርምጃ ይወሰዳል፡፡ ሁሉም የሚሠራው ሥራ  ሚዲያ ላይ ስለማይወጣ ነው፡፡ ነገር ግን ለመደበቅ ተፈልጎ አይደለም፡፡ አሁን ለምሳሌ እኔ የማቀርበውን ሪፖርት አንተ የምትረዳበትና ታች ያለው ሌላው ማኅበረሰብ የሚረዳበት ሁኔታ አንድ አይደለም፡፡ ስለዚህ አንዳንዴ በሚወጡ መረጃዎች የግንዛቤ አቅማችን እኩል ባለመሆኑ የሚያሳድሩት ተፅዕኖና ለሕዝብ የሚያስተላልፉት መልዕክት አገርም ሊያፈርስ ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሪፖርትን መነሻ አድርጎ ያልሆነ ነገር ውስጥ ሊከት ይችላል፡፡ ይህን ግን ከጥንቃቄ እንጂ ከሌላ ዕሳቤ የመጣ አይለም፡፡

ሪፖርተር:ስለዚህ እነዚህ ሪፖርቶች ሲቀርቡ በዝግ የምታካሂዱትፓርላማው ውስጥ ሚዲያ እንዳይገባ ተስማምታችሁ ነው ማለት ነው? ለአብነት በቅርቡ የገንዘብ ሚኒስቴርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ላይ የነበረውን ዝግ ስብሳባ መጥቀስ ይቻላል?

/ መሠረት:- እኛ ሚዲያ ይግባ አይግባ የሚል አይመለከትንም፡፡ እኛ ከሚዲያ ጋር ምንም ሚና የለንም፡፡ ጥሪ የሚያደርገው ምክር ቤቱ ነው፡፡ ምንም ጊዜም ቢሆን ሚዲያ ኖረም አልኖረም የምንሰጠው አስተያየት አንድ ነው፡፡ ዋናው ዓላማችን ችግሩ እንዲሻሻል በመሆኑ የእኛ አስተያየት ሚዲያ በመኖሩና ባለመኖሩ የተለየ አይሆንም፡፡ እኛ የራሳችን ጉዳይ ከሆነ ነው ሚዲያን የምንጋብዘው፡፡

ሪፖርተር:በየዓመቱ የኦዲት ሪፖርት መጨረሻ ለመደበኛ የምክር ቤቱ ስብሰባ ስታቀርቡ የምክር ቤቱ የአሠራርና የሥነ ሥርዓት ደንብ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጪ ያሉ ከፍተኛ የመንግሥት ሚኒስትሮችና ሹመኞች መገኘት እንዳለባቸው በግልጽ ይደነግጋል፡፡ አንዳንድ አባላትም ሪፖርት በሚቀርብበት ወቅት የሚገኙት ሚኒስትሮች በጣም ውስን መሆናቸውን በመጥቀስ ለምን አይገኙም እያሉ ይጠይቃሉ፡፡ በዘንድሮ ሪፖርት ከ20 በላይ ሚኒስትሮች፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ሌሎችም ጭምር የተገኙት ከአምስት የማይበልጡ መሆናቸውን ጠቅሰው አባላት ለምን እንደማይገኙ ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡ ይህ እየተደጋገመ የመጣ አለመገኘት ጉዳይ አግባብ ነው? ይባክናል የሚባለውን በቢሊዮን የሚቆጠር የታክስ ከፋዩን ገንዘብ ሪፖርት ተገኝተው ለምን አይከታተሉም?

/ መሠረት:- ይህንን ፓርላማውን ብትጠይቅ አይሻልም? ሕጉ እንደዚያ ነው የሚለው፡፡ የሚጠራቸውም ምክር ቤቱ ነው፡፡ የሚጠየቀውም ራሱ ስለሆነ ማለቴ ነው፡፡ ምክንያቱም የእኔ ኃላፊነት ያዘጋጀሁትን የኦዲት ሪፖርት ለምክር ቤቱ ማቅረብ ነው፡፡ ይመስለኛል ሁሉም ተጠርተዋል፡፡ እንግዲህ ይህንን ምክር ቤት ነው ሊያየው የሚገባው፡፡ የሚገርምህ መምጣት አለመምጣት እኔን ባይመለከተኝም፣ ነገር ግን ሌላ አስቸኳይ ሥራ ገጥሞኝ ነው ብለው የቱሪዝም ሚኒስትሯ ይቅርታ ባለመገኘቴ ብለውኛል፡፡ ይኼንን አውቃለሁ፡፡ ከምንም በላይ ግን ጉዳዩን በተመለከተ ምክር ቤቱ ነው መጠየቅ ያለበት፡፡ እኔ ከሚኒስትሮቹ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ስለሌለኝና ማን? የት? ለምን? የሚለው መረጃ የለኝም፡፡ የቱሪዝም ሚኒስትሯ ግን በሥራ መደራረብ ምክንያት ባለመገኘቼ በጣም አዝናለሁ ብለውኛል፣ ይህ አሁን ለእኔ ለውጥ ነው፡፡

ሪፖርተር:በቅርቡ ዓመታዊ የኦዲት ሪፖርት ሲያቀርቡ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የሠራተኞች ደመወዝን በተመለከተ በተለይ በቢሊዮን የሚቆጠር የአገር ሀብት ኦዲት ለማድረግ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ባለቡት አካባቢ ጭምር ለመስክ ራ የሚወጡ ኦዲተሮች የቁርስ፣ የምሳ፣ የእራትና አልጋ የቀን አበላቸው 300 ብር ነው ይስተካከል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ይህ ምን ችግር ፈጠረባችሁ?

/ መሠረት:- በመጀመሪያ ሪፖርተር ጋዜጣን በዚህ ጉዳይ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ በሪፖርቴ እንደ ማነቆ ለምክር ቤቱ ያቀረብኩትን ጉዳይ በዘገባ ሠርታችሁ አይቻለሁ፡፡ ይህንን በተመለከተ የፌዴራል ዋና ኦዲተርን ጥቅማ ጥቅም የሚወስንልን ተጠሪነታችን ለምክር ቤቱ በመሆኑ፣ ራሱ ምክር ቤቱ ነው ደመወዝና ጥቅማ ጥቅማችን የሚያፀድቀው፡፡  በዚሁ ምክር ቤት ይህን በምናቀርብበት ጊዜ በደንባችን የተቋቋመው የደንብ ኮሚሽን አለን፡፡ የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይም ጡረታ የወጣ ፕሬዚዳንት፣ ከግል ኦዲተሮችና ከዋና ኦዲተሮች ጸሐፊ ሆኖ የሚሠራ ኮሚቴ አለ፡፡ እኛ ጥናት አጥንተን ለዚህ ኮሚቴ አቅርበን ባለፈው ዓመት ፀድቋል፡፡ ከፀደቀ በኋላ የኮሚቴው ሰብሳቢ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ [ምሕረት] ናቸው፡፡ በእሳቸው ታይቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ፓርላማው ደግሞ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶት እሱም ተቀብሎናል፡፡ ከዚያ ለምክር ቤቱ ከተመለሰ በኋላ ምክር ቤቱ ጉዳዩ በጀት የሚጠይቅ ስለሆነ ለገንዘብ ሚኒስቴር ጉዳዩ እንዲታይ መርቷል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን የውኃ ሽታ ሆኖ የቀረው፡፡ የደረሰበትን ማየት አልቻልኩም፡፡ እዚህ ላይ ነው ያለው። ጉዳዩን በተመለከተ ሳናቋርጥ እየጠየቅን ነው፣ ግን እስካሁን አልተወሰነም፡፡ በነገርህ ላይ ይህ ውሳኔ ባለፈው ክረምት የተወሰነ ነው፡፡ አሁን ይህ ውሳኔ በዚህ ዓመት ቢፀደቅ እንኳን በአምናውና በዘንድሮው መሀል ያለው የገንዘብ አቅም የሚታወቅ በመሆኑ መልስ አግኝቶ ቢመጣም አያረካኝም፡፡ ምክንያቱም አምና ተጠንቶ የታቀደው ገንዘብ ዘንድሮ የመግዛት አቅሙ ወርዷል፣ እንግዲህ ጥረታችን እንቀጥላለን። እኔም ይመለሳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡   

ሪፖርተር:መልስ ባለማግኘታችሁ ምን ጫና ፈጠረባችሁ?

/ መሠረት:- በሥራችን ላይ የፈጠረብን ጫና ትልቅ ነው፡፡ ኦዲተሮች ይለቁብናል፣ ደግሞ የሚሄዱት መሀል ላይ ያሉት ናቸው፣ እነዚህ ኦዲተሮች ላይ ብዙ ሠርተንባቸዋል አቅማቸውን ለማሳደግ ለፍተንባቸዋል፣ ነገር ግን ኑሮን መሸከም አቅቷቸው ይለቃሉ፡፡ የዋና ኦዲተር ኦዲተሮችን ማንም ይፈልጋቸዋል፣ የፋይናንስ ተቋማት እጃቸውን ስመው ነው የሚቀበሏቸው፡፡ እንዲያውም እኛ ዘንድ የሥራ ነፃነት ስላላቸው ይቆያሉ እንጂ ገንዘቡን ወደው አይደለም የሚቆዩት፡፡ መጨረሻ ላይ ኑሮን መቋቋም ሲያቅታቸው ጥለውት እየሄዱ ነው፡፡ እኛ ላይም ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሮብናል፡፡ ይህ ቢስተካከል ከዚህ የተሻለ ጥሩ ሥራ መሥራት እንችላለን፡፡ ሁልጊዜም እንደምለው ለዚህ ተቋም ትንሽ ተሰጥቶ ብዙ ይጠበቃል፡፡ መንግሥት ይህንን ችግር አይቶ ያስተካክለዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ እንግዲህ አብረን እንታገላለን፡፡  

ሪፖርተር:የዋና ኦዲተርሪያ ቤት በአጠቃላይ ከሚሠራው የኦዲ ሥራ ባሻገር፣ በሁሉም የመንግሥት ተቋማት የኦዲት ዳይሬክተር የሚባል ክፍል አለ፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ ተቋማት ያለው የኦዲት ክፍተትተቋማቱ ኦዲተር የለም ወይ ያስብላል በሚል በምክር ቤት አባላትም በውጭም ባሉ ሰዎች ይነገራል? ይህን ጉዳይ እናንተ እንዴት ትመለከቱታላችሁ?

/ መሠረት:- በተቋማት ኦዲተሮች አሉ፡፡ እንግዲህ ለውጥ ያለባቸውን ተቋማት አሉ፡፡ መሻሻል አለ፡፡ የሁሉም ተቋማት ኦዲተሮች ላይ ችግር የለም ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም አንዳንዶች አለቃቸውን የሚመስሉ ይኖራሉ፡፡ እንደ መሪው ይለያያሉ፡፡ በመርህና በስታንዳርድ የሚሠሩ አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ከአለቆቻቸው ጋር የሚመሳሰሉ አሉ፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን እኛም እንሥራው የተቋማት ኦዲተሮችም ይሥሩት ስታንዳርዱ አንድ ነው፡፡ እኛ ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ለአሥር ተቋማት የኦዲትና የፋይናንስ ኃላፊዎች ለክልሎች ጭምር ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ ለውጥም እያየንበት ነው፡፡ እንዳልከው ግን የአንዳንዶች ግኝት ያሳፍራል፡፡

ሪፖርተር:ልዩ ኦዲት ታከናውናላችሁ፣ ነገር ግን በምክር ቤቱ ሲቀርብ ታይቶ አይታወቅም፡፡ አሠራሩ ምንድነው? ዓይነት የኦዲት ሪፖርት ለምን ግልጽ አይሆንም?

/ መሠረት:- ልዩ ኦዲትን አንደኛ የሚጠይቀን ፍርድ ቤት ነው፡፡ ፍርድ ቤት ይህን ሥሩልኝ ይላል፡፡ ይህ ሪፖርት ለምክር ቤት ቢቀርብም ምክር ቤቱ የኦዲት ክፍተት የተገኘበት አካል ይታሰር፣ ይውረድ ማለት አይችልም፡፡ ምክንያቱም የሚመራው ይህን ሥራ ለሚያከናውነው የፍትሕ ተቋም ነው፡፡ አሁን መታወቅ ያለበት ልዩ ኦዲት እንዲያው ሰው እንዲያውቀው ካልሆነ በቀር ምክር ቤቱ ውስጥ ገብቶ ምን ያደርጋል? ነገር ግን ልዩ ኦዲት ካካሄድንባቸው ተቋማት በዓመታዊ ሪፖርት በዝርዝር በርካቶችን እንጠቅሳለን፡፡ ለምንድነው ልዩ ኦዲት ይፋ የማይደረገው? አንደኛው ኦዲት ተደራጊ ተቋማት ላይ በልዩ ኦዲት የተደረጉ አካላት በፍትሕ ተቋማት ስለሚፈለጉ ዝርዝር መረጃ ቀድሞ እንዲወጣ አይፈለግም፡፡ ልዩ ኦዲት የሚጠይቁን አካላት ዓቃቤ ሕግ፣ ፌደራል ፖሊስና ፍርድ ቤት ናቸው፡፡ ሠርተን እንልክላቸዋልን፣ ወደ ዕርምጃ የሚገቡትም እነዚህ ተቋማት ናቸው፡፡

ሪፖርተር:ስለዚህ የኦዲት ይደረልን ጥያቄውም ከእነዚህ ተቋማት የሚመጣ ነው ማለት ነው?

/ መሠረት:- የልዩ ኦዲት ጥያቄ በእነዚህ ተቋማት የሚመጣ ነው፡፡ አንዳንድ ተቋማት ራሳቸው የሚያቀርቡልን ጥያቄዎች አሉ፡፡ የእነሱን ጥያቄዎች ተቀብለን ሠርተን ለፍትሕ ተቋማት ነው የምንልከው፡፡ አንዳንዴ የልዩ ኦዲትን ውጤት ግለሰቦች ይጠይቁናል፡፡ ነገር ግን መረጃው እንዳይወጣ ስለሚፈለግ የምንሰጠው ለሚመለከታቸው የፍትሕ ተቋማት ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር:–  ከዚህ ቀደም አቶ ክርስቲያን ታደለ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በነበሩበት ወቅት የደኅንነት ተቋማት የኦዲት ጉዳይ ተነስቶ ነበር፡፡ እንዲያውም እነዚህ ተቋማትን ለማየት ሕጉ መሻሻል ካለበት እንዲስተካከል ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡ ምናልባት ከአገር ደኅንነት ጋር የተገናኙ ጉዳዮች ይኖራሉ ነገር ግን አሠራሩ ግልጽነት የጎደለው ነው መባሉን በተመለከተ ምን ይላሉ?

/ መሠረት:- በነገራችን ላይ እኔም አንተም አገራችን ስትኖር ነው የምንኖረው፡፡ አንተም አገር ሰላም ስለሆነች ነው ይህን ጥያቄ እየጠየቅኸኝ ያለው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ተቋማትም ከአገር ደኅንነት አንፃር ነው ኦዲት ተደርገው መረጃው እንዲወጣ የማይደረገው፡፡ መረጃው ቢወጣ አደጋ ስላለው ነው በአዋጅና ደንብ የተገደቡት፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም ኦዲት እንድናደርግ ይጠይቁናል፡፡ እኛ ግን በአጋጣሚ ኦዲት ሲደረግ የሆነ መረጃ ቢወጣ ኃላፊነት ማን ይወስዳል በሚል ዝም እንላለን፡፡ ስለዚህ ከአገር ደኅንነት አንፃር ስለሆነ እኛም አልፈለግንም፡፡ ግን ቢሆን የሚመከረው እነዚህን ተቋማት በሌሎች አገሮችም እንደሚታየው አንድ ራሱን የቻለ ተቋማቱን ኦዲት የሚያደርግ አካል ወይም ከእኛ ቢፈጠር፣ እነሱን ኦዲት አድርጎ ለሚመለከተው አካል ቢላክ ነው፡፡ ነገር ግን ጉዳዩን በአሉታዊነት ባይነሳ ደስ ይለኛል፡፡ እንደተባለው ገንዘቡ የግብር ከፋዩ ሕዝብ ነው፣ ነገር ግን ሚስጥራዊነቱን በጠበቀ መንገድ ቢከናወን የተሻለ ነው እላለሁ፡፡  

ሪፖርተር:የዋና ኦዲተር  መሥሪያ ቤት ሥልጣንና ተግባር ላይ እንደተብራራው ይህ የኦዲት አድራጊ ተቋም ዕርዳታ ብድርና ጦታ ኦዲ ያደርጋል ይላል፡፡ ከዚህ ጋር በተገናኘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/) የሚያከናውኗቸው ፕሮጀክቶች ከዕርዳታ፣ብድር ወይምስጦታ ጋር የተገናኙ ስለመሆናቸው በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቶች በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠብት የሚፈስባቸው ናቸው፡፡ በምክር ቤቱ በተለያዩ ጊዜያት ይህ ጥያቄ ሲነሳ ነበር፡፡ ዋና ኦዲተር በዚህ ረገድ የሄደበት ርቀት ካለ ቢያብራሩልን?

/ መሠረት:- መጀመሪያ ለእንዲህ ዓይነት ነገር ሕግ መውጣት አለበት፡፡ ምክንያቱም ዋና ኦዲተር ኦዲት ሲያደርግ ሕጉ ይህን ይላል፣ ይህን ለምን አልሆነም የሚለውን በሕጉ በተቀመጠለት መሠረት ነው የሚሠራው፡፡ ስለዚህ ምክር ቤቱ ስጦታ እስከ ምንነው? ዕርዳታ እስከ ምን ድረስ ነው? የሚል ሕግ ማውጣት አለበት፡፡ ያ ሕግ ሲቀመጥ እኛ ከዚያ ሕግ ተነስተን ያ ሕግ ተጣሰ የሚለውን ልንሠራ እንችላለን፡፡ እሱን የሚያብራራና የሚገዛ ሕግ ስለሌለ እሱ መጀመሪያ መውጣት አለበት፡፡ ከዚያ ውጪ ከዚህ በፊት ካልኩት ሌላ የምልህ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈትን ቤት ኦዲት ስናደርግ ዩኒቲ ፓርክንና አንድነት ፓርክን፣ የጽሕፈት ቤቱን የፋይናንሻል ስቴትመንት ውስጥ ስላገኘን ኦዲት አድርገናል፡፡ እንዲያውም በዚህ የኦዲት ክትትል ያገኘነው ሌላ ተቋም የሚማርበት ነው፡፡ የሰው ንክኪ የሌለው በኤሌክትሮኒክ ዘዴ የተሰበሰበ ገንዘብ ነው፡፡

ሪፖርተር:ጥያቄው በብዛት የሚነሳው በተለይ የገንዘቡ ምንጭ ምንድነው ተብሎ ነው፡፡

/ መሠረት:- ይህ ጥያቄ እኮ ዋና ኦዲተር አይደለም የሚጠየቀው፡፡ እሳቸውን ለምን አትጠይቋቸውም? ምክንያቱም እኔ በተሰጠኝ ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት የፌደራል ዋና ኦዲተር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ያፀደቀውን በጀት ነው ኦዲት የሚያደርገው፡፡ ግን እንዳልኩህ ሰው ለምን እዚያ ላይ ብቻ እንደማያተኩር አይገባኝም እንጂ፣ የሚሰበሰበው ገንዘብ በሥርዓት ነው የሚተዳደረው፡፡ ከመንግሥት ካዝና የተወሰደ ገንዘብም አላየሁም፡፡

ሪፖርተር:ለምክር ቤቱ የኦዲት ሪፖርት ሲያቀርቡ ቢሮ ባለመስጠቱ ምክንያት ኦዲት ያልተደረገ ተቋም እንዳለ ገልጸው ነበር፡፡ ምክንያቱ ምንድነው?

/ መሠረት:- በዚህ ተቋም ያለውን ነገርና እምነቴን በግልጽ ላስረዳህ፣ የተቋሙ ችግር አልነበረም፡፡ አንድ ተቋም በጀት ሲመደብለት ኦዲት ለመደረግ ዝግጁ መሆን አለበት፡፡ በጀት እየተጠቀምኩ ለኦዲት ገንዘብ የለኝም ማለት ፍትሐዊ አይደለም፡፡  ምክንያቱም በጀት የወሰደ ተቋም ገንዘቡ የግብር ከፋዩ ሕዝብ በመሆኑ ኦዲት ማስደረግ አለበት፡፡ ምክንያቱም ለራሱ በሚሠራው ልክ ኦዲቱንም በዚያው ልክ ግልጽ መሆንና በሩን ክፍት ማድረግ አለበት፡፡ ነገር ግን ይህ ተቋም የገጠመው ነገር የቢሮ እድሳት ላይ የነበረ በመሆኑ ሰነዶችን በአንድ ላይ አስቀምጦ መለየት ባለመቻሉና ከአቅም በላይ ስለሆነበት ነው፡፡ እንቢተኝነትም አይደለም፡፡ ነገር ግን በመርህ ደረጃ በጀት የወሰደ ተቋም ኦዲተር ሲመጣ ቢሮ ተከራይቶም ቢሆን ዝግጁ መሆኝ አለበት፡፡

ሪፖርተር:በተደጋጋሚ የኦዲት ክፍተት ከሚታይባቸው ተቋማት የገዘፈው ግድፈት የሚታየው ዩኒቨርሲቲዎች ነበሩ፡፡ አሁን ምን ዓይነት ገጽታ ይዘዋል በኦዲት ግኝታችሁ?

/ መሠረት:- ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ አንዱ የአሁኑ የትምህርት ሚኒስትር በዩኒቨርሲቲዎች ላይ ቁጥጥር ሲያደርጉ በኦዲት ሪፖርት ላይ ተመርኩዘው ነው፡፡ እዚህ ላይ በሚወሰዱት ዕርምጃዎች ምክንያት ለውጥ አለ፡፡ ሌላው ግን ከዚህ በፊት የሕግ ጥሰቶችን በተለይም ማስረጃ ሳይኖር የሚደረግና ሳያስፈቅዱ የሚደረጉ ግዥዎች የሚሉትን፣ በዴቢትና በክሬዲት ላይ ስናስቀምጥ የፋይናንስ ስቴትመንቱ ላይ ችግር የለውም፡፡ ድሮ እነዚህ ተጨምረው ነበር አስተያየት ተሰጥቶት የሕግ ጥሰት የሚባሉት፣ አሁን እሱ ቀርቷል፡፡ ያ ስለቀረ ባለፈው ዓመትም ዘንድሮም ለውጥ አለ፡፡ እንዲያው ሰውኛ እንዳይሆን ሥጋት አለብኝ እንጂ ሚኒስትሩ እየተከታተሉ ነው፡፡ ነገር ግን ተቋማዊ ቢሆን መልካም ነው፣ በዚህ ክትትል መሠረት ግን ጥሩ እየሄደ ነው፡፡

ሪፖርተር:በኦዲት ሪፖርት ላይ አንዳንድ ተቋማት ገንዘቡ በመንግሥት ተደልድሎ ሲያበቃ፣ ነገር ግን ለተቋሙ ባለመላኩ እንደ ችግርና ክፍተት እየታየብን ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ይህን ክፍትተ በኦዲት ክትትላችሁ እንዴት አገኛችሁት?

/ መሠረት:- ይህንን እንግዲህ የገንዘብ ሚኒስቴር ነው ሊያብራራው የሚችለው፡፡ ነገር ግን መታወቅ ያለበት በጀት በሚያዝበት ወቅት አቅምን ባገናዘበ መንገድ ከግብር ምን ያህል አገኛለሁ? ከብድርና ከዕርዳታ ምን አገኛለሁ? የሚለው ታሳቢ ተደርጎ ነው ለእያንዳንዱ ተቋም በጀት መመደብ ያለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ እኔ የምለው ምንድነው የገንዘብ ሚኒስቴር በጀት ሲያስብ አብሮት ታሳቢ ሊያደርገው የሚገባው ምንድነው? ለተቋማቱ መልቀቅ ያለበትን ነው፡፡ የማያስተላለፍውን በጀት ለተቋማት ደልድሎ በመያዙ እኛ ላይ ተቋማት ቅሬታ እያቀረብን ነው፡፡ ያልተሰጠንን፣ ያልተለቀቀልንን በጀት አልተጠቀማችሁም ተብሎ እንደ ክፍተት እየታየብን ነው ይላሉ፡፡  በአንፃሩ በጀት ያልተሰጣቸውና ያልተለቀቀላቸው የሚያነሱት ምንድነው? እኛ የምንጠቀመው በጀት አጥተን ሌሎች ሳይጠቀሙ ይመልሳሉ በሚል የሚነሳ ቅሬታ አለ፡፡ በጀት የማይጠቀሙት ውስን ናቸው፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን መጀመሪያ በጀት በሚያዝበት ጊዜ የአገሪቱን አቅም ታሳቢ በማድረግ በትክክል ሊገኝ የሚችልን ገንዘብ ግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት፡፡ ይህ ባለመደረጉ ክፍተት እየተፈጠረ ነው፡፡ በዚያ ላይ ኢኮኖሚው የሚያመነጨው ገንዘብ በልኩ ይሰበሰባል ስለሚባለው እርግጠኛ አይደለሁም፣ ያ ቢሆን እኮ የበጀት ጉድለት አይገጥምም፡፡ ገቢዎች ዘንድ ስትመለከት በየዓመቱ ከሚያቀርበው ዕቅድ ገንዘብ በአመዛኙ ይሰበስባል፡፡ ነገር ግን ብዙ ነገር ወደ ታክስ ሥርዓት አልገባም፡፡ እንዲያውም ብድር ውስጥ ከመግባት ግብር ቢሰበሰብ ብዙ ችግር ይቀረፋል፡፡

ሪፖርተር:የኦዲት ክፍተቶች ላይ ሕግ አውጪውም ሆነ ሕግ አስፈጻሚው አካል ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው ይጠበቃል፡፡ በዚህ ረገድ ለኦዲት ሪፖርት በሚሰጧቸው ምላሾችና በሚወሰዱት ዕርምጃዎች ይረካሉ?

/ መሠረት:- የእኔ እርካታ በምፈልገው ልክ ነው ልልህ አልችልም፡፡ ግን የመጡ ለውጦች ያስደስቱኛል፡፡ ከዚህ በፊት ያላየናቸው ለውጦች ስለመጡ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እፈልጋለሁ፡፡ አንድ የኦዲት ክፍተት የተገኘበትን የተቋም ኃላፊ ከሥልጣን ከማንሳት የዘለለ ሥራ ሊሠራ ይገባል፡፡ ለምሳሌ የቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የአደጋ ሥጋትና አመራር ኮሚሽን ኃላፊዎች ተጠያቂ የሆኑት በኦዲት ነው፡፡ ነገር ግን የሚሠራው ሥራና ተጠያቂነቱ በቂ ነው ማለት አልችልም፡፡ ሙሉ እርካታ እንዴት ላገኝ እችላለሁ? አንዳንዱን ኦዲት ሳነብ እሳቀቃለሁ፡፡ ቢሆንም ጅምሮች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡፡ እነሱ ተጠናክረው ሲቀጥሉና ሁሉም ተቋማት ንፁህ ሲሆኑ፣ እኔም ከስህተት የፀዳ ሪፖርት ሳቀርብ ነው ልረካ የምችለው፡፡   

ሪፖርተር:የዋና ኦዲተር ሕጎች ለሥራ አመቺ ናቸው፡፡ አላሠራ ያላችሁ ሊሻሻል የሚገባው ሕግ አለ?

/ መሠረት:- ልናሻሽለው ያሰብናቸው አሉ፡፡ አሁን መዋቅር እያጠናን ነው፡፡ ይህ ሲደረግ የሚነካኩ ነገሮች አሉ፡፡ ነገር ግን በእኛ አሠራር ዓለም አቀፍ የኦዲት መርሆችንና ስታንዳርዶችን ስለምንከተል ችግር የለብንም፡፡ በአዋጅ መደገፍ ያለበትን መዋቅር ግን አጥንተን ከሠራን በኋላ የሚስተካከሉ ይኖራሉ፡፡ እኔ እንዲያውም መስተካከል ያለበት ነገር ተቋማት የግዥ ሕጉ አሳሪ ነው ይላሉ፡፡ ይህ እንግዲህ በቀጣይ ሁሉም ግዥ በኤሌክትሮኒክ ሥርዓት በሲስተም ከሆነ ይስተካከላል፡፡ ከሚፀድቀው አገራዊ በጀት ወደ 75 በመቶ የሚሆነው ግዥ ላይ የሚውል ነው፡፡ ይህ ደግሞ በኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት እንዲመራ ከተደረገ ትልቅ ችግር ያቃልላል፡፡ እኔም ከዚህ የፋይናንስ ኦዲት ወጥቼ በሌሎች አገሮች እንዳለው ወደ ክዋኔ ኦዲት እሄዳለሁ፡፡ ምክንያቱም የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓት ይህንን መልክ ያስይዘዋል፡፡ በዚህ መንገድ ቢተገበር ሙስና ይቀንሳል፣ ተቋማቱንም እረፍት ይሰጣል፡፡  በዚህ አሠራር ችግሩ በመሠረታዊነት ይቀረፋል የሚል እምነት አለኝ፡፡  

ሪፖርተር:አጠቃላይተቋማችሁ የገጠማችሁ ማነቆና ሊስተካከሉ የሚገባቸው ችግሮች አሉ?

/ መሠረት:- እኔ ትልቁ ማነቆ ብዬ የማነሳው ለኦዲተሮች አበል፣ በተለይም አሁን  ባለው የኑሮ ውድነት ምክንያት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የሚያስተካክለው ካልሆነ ትልቁ ችግር እሱ ነው፡፡ ኦዲተሮች በጣም እየተቸገሩ ነው፡፡ ኦዲተሮች ሄደው የሚያናግሩት ሚኒስትርን ነው፡፡ ነገር ግን ለብሰው የሚገቡት ልብስ በሥራ የነተበ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ችግር ነው፡፡ በመሆኑም ምንም እንኳ ችግሩ አገራዊ ቢሆንም እሱ ከተፈታ የኦዲት ሥራውን እንደፈለግኩ ለመሥራት እችላለሁ፡፡ ሌላው ነገር ይህ የተጠያቂነት አሠራር እየተጠናከረ ሲመጣ ሰነድ በወቅቱ አምጡ ሲባል በርካቶቹ እስከ መጨረሻው ይታገላሉ፡፡ ነገር ግን አንዳንዶች በወቅቱ አያቀርቡም እሱ መስተካከል አለበት፡፡ ሌላው እንደ አገር ባለው የፀጥታ ችግር ኦዲተሮች ተንቀሳቅሰው መሥራት ይቸገራሉ፡፡ ከዚህ ባለፈ እንደ ዋና ኦዲተር የተለየ ችግር የለብንም፡፡ ሥራችን ተከብሮ እየሠራን ነው ብዬ አስባለሁ፡፡   

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ሻሸመኔ ከተማ ማደጋቸውንና መማራቸውን፣ በአግሮ ሜካኒክስ በዲፕሎማ...

‹‹የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሥራቸውን በነፃነት ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ እንዲያከናውኑ ዋስትና የሚሰጣቸው ሕግ የለም›› አቶ አመሐ መኮንን፣ የሕግ ባለሙያና የመብት ተሟጋች

ለበርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በፍርድ ቤት በመሟገት የሚታወቁት የሕግ ባለሙያ፣ ጠበቃና የመብት ተሟጋቹ አቶ አመሐ መኮንን የፈረንሣይና  የጀርመን መንግሥታት በጋራ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የላቀ...

‹‹የአጎራባች ክልሎች የሰላም ዕጦት በእኛ ላይ ሸክምና ጫና ፈጥሮብናል›› ከአቶ ባበከር ሀሊፋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ

አቶ ባበከር ሀሊፋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶ ገነት ኮሌጅ በፎረስትሪ ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው አጠናቀዋል። ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም....