Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትብረቷ አገር ወዴት?

ብረቷ አገር ወዴት?

ቀን:

(ማጠቃለያ)

በታደሰ ሻንቆ

ሀ) ለፅንፈኝነት-ለማናህሎኝነት ሁለት ሞት

ቃታ እየሳበ ሲያደማን የቆየው ፅንፈኛነትና ማናህሎኝነት ለሕዝብ ደንታ-የለሽ ዝቅጠቱ ገጦና አለኝ የሚለውን የጭካኔ ቆበር ሁሉ ሕዝብ ላይ አንጠባጥቦ፣ የመጀመሪያ ሞቱን እየሞተ ነው፡፡ ጭፍን መፋጀትንም ሆነ መበታተንን የኢትዮጵያ ሕዝቦች እንቢኝ ብለው፣ በተጋድሏቸው እዚህ ያደረሱትን አገራዊ ብረትነታቸውን በሰላማዊ ግንባታ ደግሞ ማጠንከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የአገራዊ ምክክራቸው ሁነኛ ዓላማ የጠመንጃና ‹‹የነፃ አውጪነት›› ታሪክ በተዘጋበት አኳኋን፣ መኗኗር በሚችሉበት ሥርዓት አገራዊ ቤታቸውን ማደራጀት ነው፡፡ ቤትን በሚያኗኑር ሥርዓት የማደራጀት ጉልላታዊ ክንዋኔም፣ በሰፊ መግባባትና ምልዓታዊ ድምፃቸው የራሳቸው ባደረጉት ሕገ መንግሥት አገረ መንግሥታቸውን ማነፅ ነው፡፡ ከሞላ ጎደል አገር አቀፍ ፍላጎታቸውንና ድምፃቸውን የሚወክልና በእነሱ ፍላጎት ብቻ የሚሻሻል ሕገ መንግሥት፣ ሕዝቦች አክብረው የሚገዙለትና ማንም እንዳይረግጠው የሚጠብቁት ይሆናል፡፡ እስከ ተገዙለትና እንዳይረገጥ እስከጠበቁትም ድረስ ሕገ መንግሥታቸው ጠባቂያቸው ይሆናል፡፡

ሁሉም (መሪም፣ መንግሥትም፣ ዜጎችም) ከሕግ በታች የሆኑበት ትድድር፣ ሕይወትና ዕድሜ ሊያገኝ የሚችለው ደግሞ፣ የሕዝቦቻችን ኑሮ ፍትሐዊ ልማት መተሳሰብ መደጋገፍ መከባበር የሚራጭበት ሲሆን፣ የኢትዮጵያቸው ግስጋሴ የጋራ ትልማቸው የጋራ ልፋታቸውና የጋራ ጥቅማቸው፣ የጋራ ኩራታቸውና ዝማሬያቸው መሆን ሲችል ነው፡፡ የእነዚህ ነገሮች የተሳላ ክንውን በጽሑፍ ላይ ተሰካክቶ እንደተቀመጠው በተግባር ላይ ቀላል አይደለም፡፡ ከመሪዎችና ከፓርቲዎች ባለፈ ደረጃ፣ ወደ ኋላ የሚስቡ ሸርተቴዎች የት የት እንዳሉ አውቆ መራቅንና ድጦችን ለማድረቅ መሥራትን ይጠይቃል፡፡

ጅምር ድላችንን ከብሔር ጋር ካገናኘነው፣ ‹‹የእኔ ብሔር/አካባቢ ሰው ሲመራ ኢትዮጵያ ተንደረደረች፤ ከእነ እንትናማ ጉራ ምን እንዳተረፍን አየነው…›› የሚል ጅምላ መናናቅ/መሸራደድ ውስጥ መኖር ከቀጠልን ያደረግነው ለውጥ የመናናቅና የጉራ ቦታን መቀያየር ብቻ ይሆናል፡፡ ድጡ አለና ተመልሶ በአዙሪት ውስጥ የመውደቅ አደጋ ከእኛው ጋር ይቆያል፡፡ ፈሪነትንና ጉብዝናን ባለድልነትንና ተሸናፊነትን የመሳሰሉ ነገሮች አገርም ሆነ ብሔር የሌላቸው መሆናቸውን ያላወቀ ድንቁርና ከእኛ አስተሳሰብ ገና አልተራገፈም ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ጥፋቶችን ካንፀባረቅን፣ ቀደም ሲል ባየናቸው የብሔርተኛነትና የማናህሎኝነት የጋራ ፀባያት ውስጥ ከመዳከር አለማምለጥ ይሆንብናል፡፡

የብሔርተኛ ፓርቲ ገዥነትን ይዞ ከመልከ-ብዙ ጭቆኛዎች መላቀቅ አይቻልም፡፡ ‹ብሔርተኝነትና ትምክህት ምንና ምን› በሚል ርዕስ ሥር ያወሳናቸው ችግሮች እንዲኖሩ ይፈቀድላቸዋል፡፡ ሥራ ከፋቾች በብሔረሰባዊ ማንነት ሳይንጓለሉ ወይም እንንገዋለላለን ብለው ሳይሠጉ መዋዕለ ንዋይ የማፍሰሳቸው ነገር ለችግር ይጋለጣል፡፡ መብቶች፣ ፍትሕና አስተዳደር በአድልኦ የሚጎሳቆሉበት ዕድል አብሮን ይቆያል፡፡ ከአድልኦ ጣጣ በተጨማሪ ስስትና ተስፋፊነት ከብሔርተኝነት ጓዳ አይታጡምና ሰላምን የሚጎዱ ችግሮች ከፌዴሬሽኑ አባል አካባቢዎች ርቀው አይርቁም፡፡

የብሔርተኝነትንና የትምክህትን መዘዞች እስከ ወዲያኛው መገላገል የምንችለው ‹‹ለጨዋነት/ለጌትነት የተፈጠሩ፣ ለድህነት ለባርነት፣ ለፋቂነት ለቁጢት በጣሽነት፣ ወዘተ የተፈጠሩ ሰዎች አሉ›› ብሎ እስከማመን ድረስ አሮጌነት ውስጥ የተገተሩ አስተሳሰቦችን የሥራ ስብጥር ባስከተለ ህዳሴና ሥልጡንነት እየነቀነቀን የማራገፍ ሥራ ስንሠራ ነው፡፡ ይህ አነጋገር ትምህርት በአግባቡ ያልጎበኛቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚመለከት ይመስላል፡፡ ‹‹ለጨዋ ልጆችና ለባለ ፀጎች የተፈጠሩ/የሚሆኑ ሥራዎችና ትምህርቶች አሉ፣ ለመናጢዎች የተፈጠሩ ሥራዎችና ትምርቶች አሉ›› የሚል አስተሳሰብ የዚያው ኮፒ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ በተማረው ዘንድ ሳይቀር በመንግሥት ውስጥ ጭምር ለረዥም ጊዜ ተንሰራፍቶ የኖረ ነው፡፡ እኔ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በተከታተልኩበት አጠቃላይ ትምህርት ቤት ውስጥ በስምንተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት (90 ቤት) ያመጡ ተማሪዎች (በሌላ አነጋገር፣ ከጥሩ ትምህርት ቤቶች የመጡ የደልዳላ ቤተሰብ ልጆች ክምችትና በሰቃይነት ለመደባለቅ የቻሉ የደሃ ልጆች በቀጥታ ይመደቡ የነበሩት የቀለም ትምህርት ውስጥ ነበር፡፡ የዚህ መስክ ተማሪዎች የሚዘጋጁት የአሥራ ሁለተኛ መልቀቂያ ፈተናን ተሻግረው በዩኒቨርሲቲ ትምህርት እንዲገፉ ነበር፡፡ በቢሮ ነክ በሙያና በቴክኒክ የሚሠለጥኑ ተማሪዎች ደግሞ (ከፍተኛ ባልሆነ የስምንተኛ ክፍል ማለፊያ ውጤት የገቡ) በመሠረቱ የሚዘጋጁት ለሥራ ቅጥር ነበር፡፡ አራት ዓመት ሙያ ተምሮ ወደ ሥራ የሚሄድበት መስክ በውስጠ ታዋቂ የደሃ ልጆች መስክ ተደርጎ የሚቆጠር ነበር፡፡ በኢሕአዴግ ጊዜ የመጣው ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ለዲግሪ ትምህርት የማያስገባ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን ወደ ሙያ መስኮች የማሠማራት ነገርም ከንቀት አዙሪቱ ውጪ አልነበረም፡፡ አሁን የተጀማመረው የትኛውም የትምህርት መስክ ሳይናቅና በጉዞ ርዝማኔ ሳይታጠር የብስል ዕውቀት/ሙያና የፍልሰፋ መፍለቂያ እንዲሆን የማደራጀት ጉዞ፣ ከቀድሞ ጀምሮ ሲንከባለል የመጣ ትምህርት ድረስ የዘለቀ የንቀትና የመኮፈስ ችግርን የሚያዳክም ነው፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የትጥቅ ትግልን የትጥቅ አመፅንና ወታደራዊ የመንግሥት ግልበጣንና ጭፍን የንፁኃን ጥቃትን ግዙፍ ነውር አድርጎ የማዳከምም ሥራ፣ ከትጥቅ ጋር የተያያዙ ብዙ ነገሮች ያላቸውን ተያያዥ ጦስ በደንብ መረዳት ይጠይቃል፡፡ ደምን በደም የመመለስ ባህልን (በተለይም የገዳይ ዘመድ በተባለ ሰው ላይ የሚፈጸም ብቀላን) ተማርን የምንባል ብዙ ሰዎች በአሮጌነቱ እንጸየፈዋለን፡፡ በዛሬ ታሪካችን ውስጥ፣ በብሔር ወገን ላይ ደረሰ የተባለ ጥቃትን ‹‹ፈጸመ›› በተባለው ብሔር ላይ ለማወራረድ እየተባለ በንፁኃን ላይ ሲፈጸም የነበረ ግፍ፣ በደንብ ካስተዋልነው፣ ደምን በደም የመመለስ ዘመድ ነው፡፡ ‹‹ደም የማውጣት›› ባህልን ንቀን ትተን የጅምላ/የደቦ ግፎችን ለማድረቅ የሚበጅ ሥራ ሠራን ማለት አንችልም፡፡ ለመገዳደል ታሪክ/ለአማቃቂ የትጥቅ ትግል (ከዚያም ባለፈ በትውልድም ሆነ በአገር ላይ ለተፈጸሙ በደሎች) ሐውልት የሆኑ የፓርቲ ስሞችን ታቅፈን የጠመንጃ ፖለቲካንና ነፃ አውጪነትን አሰናበትነው ብሎ ማለት እርስ በርሱ ይፋረሳል፡፡ የጠመንጃ ትግልን ትተው ወደ ሕጋዊ/ሰላማዊ መድረክ የሚገቡ ቡድኖችም፣ የኢትዮጵያ ህዳሴ የውስጥ ሕመም ሆኖ መቀጠልም ሆነ በአሮጌ ቁናነት መናቅ ካልፈለጉ፣ ጠመንጃን/አመፅንና ሕገወጥነትን የሚያንፀባርቁ ስሞቻቸውን ወድደው መቀየር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከአማፂነት ሠፈር ወደ ሕጋዊነት ሠፈር የሚመጡ ቡድኖች አጠራራቸውን ከሕግ ጋር እንዲያስማሙ በሕግ ማስገደድ አሁን ጊዜው ላይሆን ይችል ይሆናል፡፡ እነሱ የጠመንጃ ታሪካቸውን እያሞካሹ ከአሮጌ ስማቸው ጋር ለመቆየት ቢወዱ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦችና አገረ መንግሥታቸው የማይቀለበስ ህዳሴ ውስጥ እስከገቡ ድረስ፣ ጠመንጃን በትዝታ የሚያመሰኩ ቡድኖች በአሮጌ ቅሪትነት በሕዝብ መረሳትን የመረጡ ከመሆንና ከመክሰም አያመልጡም፡፡

ኢትዮጵያ በቁሳዊና በሰብዓዊ ልማት የምታሳየው ግስጋሴ እንደ አገር መታበይ ውስጥ ከጣለንም፣ ከንቀትና ከትዕቢት፣ ከነገረኛነትና ከበዳይነት ወጥመድ አላመለጥንም፡፡ የዓለማችን ግንኙነቶች አፍሪካ ላይም ሆነ፣ እስያና ላቲን አሜሪካ ላይ ብናስተውል፣ በቴክኖሎጂና በወታደራዊ አቅም የጎለበቱት ኃያላን ዘንድ ምን ያህል ዕብሪትና ኢፍትሐዊነት እንዳለ መገንዘብ አያዳግትም፡፡ ኢትዮጵያ በእነሱ መንገድ ከተጓዘች (የተዳፈሯት የመሰሏትን አገሮች በትንሽ በትልቁ ‹‹ዋ!›› ማለት ውስጥ ከገባች፣ ለውስጥ ሰላሟም ጠንቅ ትሆናለች፡፡ ኢትዮጵያ በአገራዊ ስኬቷና ጥንካሬዋ የመኩራትና በትምክህት የመወጠር ልዩነቱ ከጠፋባት፣ በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ሰላሟን መንከባከብ ከባድ ሥራ ይሆንባታል፡፡ በአኅጉር ደረጃ ልትጫወት የሚገባትን አዎንታዊ ሚና ለመጫወት ትቸገራለች፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ያላት ሞገስም ክሳት ያገኘዋል፡፡ ኢትዮጵያ የውስጥና የውጭ ግንኙነቶቿን ‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ›› በሚባል ብልህነት መጥቀም የምትችለው በግስጋሴዋ ውስጥ ሥልጡንነትን ካልዘነጋች ነው፡፡ ማለትም፡- የሰው ልጅንና ተፈጥሮን አክባሪነትን፣ አርቆ አስተዋይነትን፣ ለነገርና ለግጭት ከመቸኮል ይልቅ ለሰላም/ለውይይትና ለመደጋገፍ ሆደ ሰፊ መሆንን የዜጎቿና የመንግሥቷ መታነጫ ማድረግ ነው፤ የባህል አብዮት፡፡

ለ) አብዮትና ሥልጣኔ ስንል…

ስለአብዮት በየመዝገበ ቃላቱ አስገራሚ ዓይነት ግልብ ትርጉሞች አሉ፡፡ በታጠቀ ኃይል/አመፅ የመንግሥት ሹም ሽር ማካሄድን ሁሉ አብዮት ብለው የሚደነግጉ አሉ፡፡ የዚህ ዓይነት መዝገበ ቃላዊ መሥፈሪያዎች ይዘው፣ በሶሻሊዝም ግንባታ ይነግድ የነበረ ወታደራዊ- ‹ኢሠፓ›ዊጥፈራ (‹ቶታሊቴሪያን› አገዛዝ)፣ በብሔረሰቦች ነፃነትና በፌዴራሊዝም በሚነግድ ከበረሃ በመጣ ወታደራዊ ጥፈራ መተካቱን (ያውም ኢትዮጵያ እንደ አገር የአንድ ብሔርተኛ ቡድን ይዞታ እስከ መሆን ድረስ አገረ መንግሥታዊ አውታሯ የተሰነገበትን ክስተት)፣ አብዮት ብሎ መጥራት የሚፈልጉ መጥራታቸውን ይቀጥሉ፡፡ የዚያ ዓይነት ክርክር ውስጥ መግባት የዚህ ጽሑፍ ፍላጎት አይደለም፡፡ እዚህ ጽሑፍ ውስጥ የምናወራለት አብዮት ስለኅብረተሰብ አብዮት ነው፡፡

አስተዋልነውም አላስተዋልነውም በጥገና ለውጥ መልክ ውስጥ ኅብረተሰብ አቀፉ ለውጥ ዛሬ ተጀምሯል፡፡ በዚህ የለውጡ ዘመን ውስጥ ከቁንጮ ገዥነት የተንሸራተተ ቡድን ለከፈተው ግዙፍ ጦርነት ኢትዮጵያ የተጋለጠችው፣ በ1980ዎች ውስጥ አገረ መንግሥታዊ የታጠቁ ዓምዶቿ በአንድ ቡድን ቁጥጥር ውስጥ በመውደቃቸው ምክንያት ነበር፡፡ ኅብረተሰብ ተጠራርቶ ባካሄደው አገራዊ ተጋድሎና ድል ኢትዮጵያ በአንድ ሒደት አራት ድሎች/የድል ሒደቶች ተቀዳጀች፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በምልዓት ተነቃንቀው አገራቸውን ከብተና አዳኑ፡፡ አገረ መንግሥታቸውን ከአንድ ቡድን ይዞታነት አላቀቁ፡፡ ከመቼውም ጊዜ የላቀ የሕዝቦች ውዴታ ወኔና ኅብረ ብሔራዊ ጥንቅር በተገማሸረበት አኳኋን የእኔ የሚሉትን አገረ መንግሥታዊ የታጠቀ አውታር ገነቡ፡፡ አገረ መንግሥታዊ የአውታሮች ህዳሴያዊ ግንባታው ዛሬም አድማሱን እያሰፋ ቀጥሏል፡፡ ከተበጣጠሰ (ባለቤትና ባይተዋር የሚል ክፍፍል ከፈጠረ) ብሔርተኛ የአዕምሮ ሙሽት ወደ ኅብረ ብሔራዊ የእኩልነት-የመተሳሰብ-የመከባበር ሙሽት በመሸጋገር ጉዞ ውስጥም ሁሉን አቀፍ ኅብረተሰባዊ የአገር ፍቅር ንቃተ ህሊናው እየተገነባ ነው፡፡ ይኸውናም፣ ኅብረተሰቡ በአገራዊ ምክክር ሰፊ መግባባት ላይ ተመሥርቶ ሕገ መንግሥታዊ የኑሮ ሥርዓቱን የሚያበጃጅበትንም ሒደት ተያይዞታል፡፡

ኅብረተሰብን ወደፊት ከሚያራምድ ለውጥ ጋር ከ2010 ዓ.ም. አንስቶ እዚያም እዚያም በመሰሪ የውስጥና የሩቅ እጆች ቅንብር እየፈነዱ ሲወጥሩን የቆዩ ጠመንጃ ገብ ቡድናዊ ቀውሶች ከብሔርተኛነትና ከማናህሎኝነት ብልሽቶቻችን የመጡና እንደ ሁኔታው እነሱን በማሾር የውስጥና የውጭ መሰሪዎች የተቀናበሩባቸው ተንኮሎች ጭምር ነበሩ፡፡ ዕይታን አስተካክሎ እውነተኛ ችግሮችን አቅርቦ በማየት ፈንታ የደረሰውን ምስቅልቅል ሁሉ በ1966 አብዮት ‹‹ተራማጅነት›› ውስጥ ከታየ እግዜርን መካድ ጋር መልሶ መላልሶ ማያያዝ ራስን በማታለል ፍቅር መጠመድ ነው፡፡ እዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ውስጥ ስለተሽከረከርን ወደ ፈጣሪ ይበልጥ አንቀርብም፡፡ ወይም ‹‹ኮሙዩኒዝም›› የሚባለውን ነገር አንበቀለውም፡፡ ይህንን በሌላ ገጹ እንመልከተው፡፡ በዘመነ አብዮት ተከስቶ የነበረው ‹ፈጣሪ የለም› ባይነት ዛሬ ተንኖ ከሞላ ጎደል ኅብረተሰባችን አማኝ ነው፡፡ ትናንትና ተራማጅ ከነበሩና ዛሬም ከማርክሲዝም የተገኙ ጥሩ ነገሮችን የሚያደንቁ ብዙ አማኒያንን አውቃለሁ፡፡ ዛሬ አማኒነት በሠፈነበት ጊዜ ግን ብዙ ከአማይነት የተጣላ ጭካኔና ግፍ ቁምስቅል ሲያስቆጥረን ታየ፡፡ ምሥራቁንና ማርክሲዝምን የሚኮንኑትም አውሮፓና አሜሪካ፣ ላይ ላዩን አማኝ ይምሰሉ እንጂ በአያሌው ከሃይማኖት እየተራራቁ የመጡ ናቸው፡፡ ተራርቀውም ግን እነሱ በሌሎች አገሮች ጉዳይ ውስጥ ጣታቸውን እየደነቆሉና እያመሱ በመሣሪያ ሽያጭ የሚከብሩ ሆነው ሳለ፣ በሥርዓትና በሕግ የሚመራ የውስጥ ኑሯቸው ከሞላ ጎደል አልተናጋባቸውም (ማለትም፣ እየዘነጉት የመጡት ፈጣሪ ኅብረተሰባቸው ላይ ቅጣት አላወረደባቸውም)፡፡ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምስቅልቅል በፈጣሪ ክህደት የሚያመካኙ ሰዎች ለዚህ እንቆቅልሽ አሳማኝ ማብራሪያ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፣ አለዚያም ስህተታቸውን ለማስተዋል መፍቀድ ይገባቸዋል፡፡ በምዕራባዊ ርዕዮተ ዓለም አፍቅሮትና አምላኪነት ውስጥ ሆነን ምሥራቃዊ ነገሮችን ስለኮነንን ከጥገኛ አመለካከት ያመለጥን ባለ ነፃ አስተሳሰብ አንሆንም፡፡ የምሥራቃዊ ጎራ አምላኪ በመሆንም በምዕራብ ዓለም ውስጥ ያሉና የሚያስፈልጉንን የሥልጣኔ ፍሬዎች ከመቀበልና ከመጠቀም አናመልጥም፡፡ ልክ እንደዚያው ምሥራቁን ስለጠላን ከምሥራቅ የመጡ የሥልጣኔ ፍሬዎችን ከውስጣችን መንጥረን አናባርራቸውም፡፡

በየካቲት 1966 ዓ.ም. የተከፈተው ዘመነ አብዮት የሕዝባዊ ሥልጣን መንገድን ስቶ ከመጨንገፉ በመለስ፣ ዛሬም ድረስ ያሉ ወደፊትም የሚያድጉ ኅብረተሰባዊ ድሎችን ተጎናፅፏል፡፡ የጉልተኛ/ባላባታዊ የኢኮኖሚ ግንኙነት በኢትዮጵያ ላይመለስ የተሰናበተ አሮጌ ነገር ነው፡፡ ይህ የኅብረተሰብ ድልና ዕርምጃ አንድ አካል ነው፡፡ የፈለገ የምንጠላው ነገር ቢኖር፣ በሶሻሊስት ነክ ሥነ ጽሑፎች አማካይነት ስለመደቦች ምንነት፣ ስለሶሲዮ-ኢኮኖሚያዊ ሥርዓቶች ፀባያት፣ ስለፍልስፍና፣ ስለዓለም ታሪክና የትግል ታሪኮች፣ ስለብሔረሰቦችና ስለቋንቋዎች እኩልነት፣ ስለሃይማኖቶች እኩልነት፣ ስለሃይማኖትና መንግሥት የመለያየት ጥያቄ፣ ስለሰው ልጆች እኩልነት፣ ስለሴቶች ፈርጀ-ብዙ መብቶችና ፆታዊ እኩልነት፣ ስለተባበረ ትግልና ስለዓለም አቀፋዊነት የተገኙት አዳዲስ ግንዛቤዎች በአጠቃላይ ዕውቀት ደረጃ የንቃተ ህሊና እመርታ አስከትለዋል፡፡ ሰብዕናችንን አበልፅገዋል፡፡ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ዕመርታዊ ዕድገት እንዲያሳይ አስችለዋል፡፡ የዚያን ዘመን የንቃተ ህሊና ዕድገትን የቀማመሱ የዚያ ዘመን ወጣቶችና ታዳጊዎች በዛሬ ዕድሜያቸው ያላቸው የፍትሐዊነት አመለካከት ርዝራዥ አነሰም በዛ ከዚያ ዘመን ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የዚያ ዘመን በጎ ግንዛቤዎች ለዛሬም የሚዳብሩ እንጂ የሚሻሩ አይደሉም፡፡ ያኔ ከርረው በተያዙ ዕሳቤዎችና በተጠማመዱ ሠልፎች አማካይነት ‹‹አብዮተኛና አድሃሪ/ፀረ አብዮተኛ…›› እየተባባሉ የተከተለውን መጠፋፋትና ለዛሬ የተላለፈውን ጠንቅ ለመንቀፍ፣ የግድ በዚያ ጊዜ የተገኙ አዎንታዊ የንቃተ ህሊና ሀብቶችን ሁሉ ወደ ገደል መስደድ የለብንም፡፡ ያኔ የተገኙ ዕይታን ያሰፉ በጎ ማኅበራዊ ንቃቶች ይበልጥ እየጠሩ መጎልበትና መቀጠል ያልቻሉት፣ ስህተት ስለነበሩ ሳይሆን፣ ኅብረ ብሔራዊ ፖለቲካ ተጠማምዶ ቃታ ለመሳብ በተቻኮሉ ጥፋቶች ተንኮታኩቶ ብሔር/ብሔረሰቦች ላይ ከተተከሉ የሽምቅ ቡድኖች በቀር የትግል ሜዳው ኦናውን ስለቀረ ነበር፡፡  

በዛሬ ጊዜ ኅብረተሰባችን ውስጥ የደረሱ ንፁኃንን ያልማሩና ሆን ብለው ያጠቁ ጥፋቶች፣ በትናንትናው ተራማጅነት ውስጥ ከነበረ ለሕዝብና ለፍትሕ መቆርቆር የፈለቁ ፈፅሞ አልነበሩም፡፡ ባለፈ ታሪክ ላይ እየተብሰለሰሉ ከመኖር እንውጣና ዛሬና ነጋችንን እናቃና ሲባል፣ ወደ ኋላ 150 ዓመት ተሽቀንጥሮ እዚያ ውስጥ መልወስወስን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን፣ የ1960ዎቹን ትውልድ የችግራችን ሁሉ መነሾ ያደረገ አማራሪነትንም የሚጨምር ነው፡፡ ከረዥም ዘመን ጦረኝነትና ከ1960ዎቹ አብዮተኛነት ተቀባብለው የመጡት፣ ለመጠማመድና ለመቀናደብ የመቸኮልችግሮቻችን ዛሬም አሉልን፡፡ በእነዚህ ችግሮች እየተሰነከሉ ከመዳፋት ለመገላገል ከፈለግን፣ ማተኮር ያለብን እነሱን በማቃለል ተግባር ላይ ነው፡፡ ፕሮፌሰር አሸብር ተድላ ከጉሬዛም ማሪያም እስከ አዲስ አበባ በተሰኘ መጽሐፉ ገጽ 6 እስከ 7 ላይ፣ በጣሊያን ወረራ ዘመን ቢቸና ውስጥ በአንድ ዘመዱ ቤተሰብ ላይ የደረሰውንና ድርጊቱ ከደረሰበት ከአንድ ዘመዱ የሰማውን ይተርክልናል፡፡ በዚያ ትረካ መሠረት ለዘመዱ ቤተሰብ እራት የተሰናዳውን ወጥና እንጀራ ባንዳ ሳይመሽ ዘርፎ ይበላዋል፣ የተጠራቀመ ወተት ንጠውና ቅቤ አውጥተው በአጓትና በአይብ ሊበሉ ሲሉ ደግሞ ፋኖዎች መጥተው ቅቤውን ተቀብተው የተዘጋጀውን ይበላሉ፡፡ በዚያ መሀል የአባወራውን መበሳጨት ያስተዋለ አንድ ፋኖ ‹‹ለእናንተ ብለን እኮ ነው ሌሊት በብርድ ቀን ጫካ ለጫካ የምንንከራተተው፤ ጭራቅ እንዳይበላችሁ›› ይላል፡፡ አባወራው ለዚህ የነበረው ምላሽ፣ ‹‹ልጆቼ በልተው ቢያድሩና እኔን ጭራቅ በበላኝ›› የሚል ነበር፡፡ በፋሺስት ጣሊያን ጊዜ የነበረው የፋኖ ተጋድሎ በጊዜው በነበረው ሥርዓተ ኑሮ የሚመዘን ቢሆንም፣ የዛሬው ‹‹ፋኖ››ነትና የሸኔ ‹‹ነፃ አውጪነት›› የተያያዙት ዘርፎ በልነት ብቅለቱ፣ ከ1960ዎች አብዮተኛነት ይልቅ፣ ከዛሬው የዘቀጠ ብሔርተኛ ፅንፈኝነትና ከትናንት ተንኳትቶ ዛሬም በውስጣችን ካለው የሽፍትነት ልማድ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ያጋለጠን ደግሞ የልሒቃኖቻችን የተራዘመ ድቀትና ስንፈት ነው፡፡

በሕጋዊ ዓውድ ውስጥ የታጠቀ ኃይልን የማደራጀት/የመጠቀም መብትና ኃላፊነት የመንግሥታዊ አውታር ብቻ የሆነባትን፣ የዜጎች መብቶችና ግዴታዎች መከበር ሥርዓታዊ የሆነባትንና በሕዝቧ የተስማማ ፍላጎት የተቀረፀች ኢትዮጵያን አፅንቶ የመገንባት ጉዳይ፣ ፈርጀ ብዙ አብዮትን የማካሄድ ጉዳይ ነው፡፡ የነፃ አውጪነትና የአማፂነት/የሽፍትነት ባህልን የማራገፍ፣ የሕዝብ ለሕዝብ የተደጋገፈ ትስስርን የመገንባት፣ ብቃትና ችሎታ ለስብጥር ሲባል መስዋዕት የማይሆንበትን አቅም በሁሉም ማኅበራዊ ዥንጉርጉርነት ውስጥ የማሟላት፣ ቢሮክራሲያዊ ትብትቦችንና ሙስናን በቅልጥፍና፣ በብቃትና በሥነ ምግባር ቀጣይነት የማሸነፍ ነገሮች ሁሉ ኅብረተሰብ አቀፍ ሥራዎችን ይፈልጋሉ፡፡ የእነዚህ ሁሉ ጉዳዮች ዒላማ ኅብረተሰብ ላይ የማይነጥፍ የባህልና የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ነው፡፡ ይህ ለውጥ የመንግሥት አመራርን፣ የመሥሪያ ቤቶችን፣ የትምህርት ቤቶችን፣ የልሒቃንን፣ የመረጃና የመገናኛ አውታሮችን የተሳላ እንቅስቃሴና እድሳትን ይሻል፡፡

በየዘርፉ የሚፈለጉ ሥራዎችን እዚህ መዘርዘር አይቻልም፡፡ ግን ህዳሴያችን ምን ያህል ባለ ብዙ ገጽ እንደሆነ ጥቂት ነገሮችን በማንሳት ማሳየት ይቻላል፡፡ የኅብረተሰባችን የአገር ወዳድነት ንቃተ ህሊና አገር ስትነካ ሆ ብሎ ከመነሳት፣ ከስሜታዊ ኩራትና በዘፈን ከማወደስ ብዙም ርቆ የሄደ አይደለም፡፡ የፈረንጅ ነገርን በጭፍን ከመቅዳት መርጦ ወደ መቅዳት አልተራመደም፡፡ የውጭ ሸቀጥ ተጠቃሚ መሆን የሥልጣኔ ማሳያና መከበሪያ የሆነበት አላዋቂነት ዛሬም እንደተንሰራፋ ነው፡፡ በአገር ውስጥ ያሉ የውጭ ኩባንያዎች ደንበኛነትን ከኩባንያዎቹ ሥራ አስፋፊ መሆን አለመሆን ጋር ማገናዘብማ ገና አልተነካም፡፡ በየፈርጁ ልናሳካቸው የምንፈልጋቸው ለውጦች ሁሉ ደግሞ ከአገር ወዳድነታችን የነቃ (ብሔራዊ ጥቅሙን ያወቀ) መሆን ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ለዚህ ነው፣ ከእስያኑ አካሄድና ስኬት ኩረጃ ለማድረግ ስንሞክር በእኛና በእነሱ መካከል ያለውን የጮካነት ልዩነት መርሳት የሌለብን፡፡

ዘፈኖቻችን፣ ፊልሞቻችንና ሚዲያዎቻችን የፈረንጅ ቅጂ የመሆን ምርኮኝነት ውስጥ እንዳሉ ሆነው የምንፈልገውን ለውጥ ማሳካት አንችልም፡፡ የለውጥ ንቅናቄ፣ ስብከት የማጦፍ ጉዳይ አይደለም፡፡ የሕዝብ ሚዲያዎች ባሏቸው ሰዎችና በሚያቀርቧቸው ዝግጅቶች/ውድድሮች የብቃትና የጥራት ማነስ መታያ ሆነው፣ ስለብቃት ቢሰብኩ ከንቱ ነው፡፡ ከስብከት ይልቅ በሳልና የሕዝብን አምሮት የሚሞላ ነገር ለማቅረብ መቻልና የብቃትና የጥራት ምሳሌ ለመሆን መቻል በራሱ ለውጥን ያዛምታል፡፡ ሽልማት ባለው ዘፋኞችን አብቅቶ የማሸነፍ ውድድር ላይ፣ ተወዳዳሪ አሠልጣኞችና ዕጩዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያሳዩትና የብቃት ዕርምጃ ብቻ ተመርኩዞ ሕዝብ እንዲፈርድ ምሳሌ ከመሆንና ይህ አመዛዘን በሕዝብ እንዲለመድ ከመጣር ፈንታ፣ ‹‹ምረጡን!›› ባይነቱ የአሠልጣኝን ዝናና የተወዳዳሪን መገኛ ሠፈር እስከ መመርኮዝ ከተንሰፈሰፈ (እንዲህ ያለ ሠፈርተኛነት ውስጥ ለመግባትም የገፋን ፈረንጆቹ ሲያደርጉት ማየታችን ከሆነ)፣ የሚፈለገው ለውጥ አልገባንም ማለት ነው፡፡

የተዋጣላቸው የፊልም ሥራዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን ሥራዎች፣ ውይይቶችና የጽሑፍ ሥራዎች በአንድ ጊዜ ገፀ-ብዙ የለውጥ ዕርምጃን መቆስቆስ ይችላሉ፡፡ አንድ ምሳሌ ላቅርብ፡፡ ፕሮፌሰር አሸብር ተድላን በአካል አላውቀውም፡፡ እዚህ የጠቀስኩትን የሕይወት ጉዞ መጽሐፉን በማንበብ ግን አዛውንቱን ምሁር አበጥሬ አውቄዋለሁ፡፡ መጽሐፋ ውስጥ ባገኘሁት ማንነቱም ቀልቤ ‹‹ጋሼ/አብዬ›› ያለው ሰው ነው፡፡ የምናወራለት የአስተሳሰብና የባህል ለውጥ እንዴት ያለ እንደሆነ፣ የፕሮፌሰሩ መጽሐፍ ሳይናገር ያስተምረናል፡፡ መጽሐፉ በቋንቋ የተቀናበረ ፊልም ነው፡፡ ወጣቶቻችን ይህንን ፊልም በደንብ አጣጥመው (ላይ ላዩን ሳይጋልቡ) ቢያዩት፣ ሁለገብ አብዮት ውስጥ የመግባት ጅምር ይሆንላቸዋል፡፡ እንዴት ያለ ለውጥ ላይ ለመድረስ መጣጣር እንዳለባቸውም ይገለጽላቸዋል፡፡

የፕሮፌሰሩ መጽሐፍ ከተከተረች ጠባብ የኑሮ ሥፍራ ተነስቶ ዓለም ውስጥ እስከ መዋኘት የረዘመ ሕይወት ውስጥ የሚያስጉዝ ነው፡፡ የተከተረ ኑሮ ምን ያህል አስተሳሰብንና ህልምን እንደሚያጠብ፣ ምን ያህል የሰብዕና ግንባታን እንደሚያኮሰምን በምናብ እየኖሩ እንዲያዩት ያስችላል፡፡ ከጠባብ ሕይወት ወጥቶ ብዙ የሰዎችና የልምዶች ስብጥር ያለበት ሰፊ ሁኔታ ውስጥ ሲገባ ደግሞ፣ ዥንጉርጉር ልምድና የትምህርት ዕድገት ምን ያህል ሰብዕናን በብዙ ፈርጅ እንደሚሞርድ ያሳያል፡፡ ከሙረዳ ሒደቱም ያቋድሳል፡፡ የፕሮፌሰሩ የሰዎች ተራክቦ አሰፋፉ (በፖለቲካ አቋም፣ በፖለቲካ ቡድድን፣ በትምህርት ደረጃ፣ በኑሮ ደረጃ፣ በብሔር/በአካባቢ ልጅነት ያልታጠረና የማይሠፈር መሆን)፣ በወዳጆቹ ውስጥ ያሉ በጎ ነገሮችን ከእነ ዕንከኖች ጭምር እያስተዋለም ሳይወሸክት የመኗኗር ችሎታው፣ በራሱ ላይ ያሉ ድክመቶችንና ገመናዎችን ለመናገር ያለው ድፍረት በራሱ ቅሰሙኝ የሚል ነው፡፡ ሰፊ አመለካከትና ሰፊ የሰዎች ተራክቦ ውስጥ መግባት እንዴት እንደሚጠቃቀሙ በፕሮፌሰሩ ልምዶች አማካይነት እናስተውላለን፡፡ ምክንያታዊ አስተሳሰብ ምን እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በምክንያትና በመረጃ መሥራት ምን ያህል ለአገር መቆርቆርን እንደሚጠቅም እንማራለን፡፡ በመንግሥት አለመመቸት ምክንያት ለአገር የመሥራት ተልዕኳችን መጉበጥ እንደሌለበት እናያለን፡፡ በፊት በር መጥቶ መግባት የማይቀመስ ሲሆን እንዴት በጓሮ በኩል መንገድ ፈልጎ፣ አገራዊ ጉዳይን በማያፈናፍን ማስረጃ አደራጅቶ ተቀባይነት እንዲያገኝ ማድረግ እንደሚቻል ያሳየናል፡፡ በአድር ባይነትና በቢሮክራሲ ሳይሸበቡ ለፍትሕና ለትክክለኛ ሥራ መቆም ምን እንደሆነ፣ ለፍትሕና ለሀቅ መታገል በብሔር/በአካባቢ ልጅነት እንደማይሠፈር እንቀስማለን፡፡ የማይውለሸለሽ ቁርጠኝነት፣ ብልህነት፣ ቀናነትና በመርህ መመራት እንደምን ተሣልተው በሰብዕና ላይ ሊንፀባረቁ እንደሚችሉ እንማራለን፡፡ ዝና ካተረፈ ምሁርና ከቅርብ ዘመድ የሚመጣ የአድልኦ ፍላጎትን መመከት ምን ያህል ፅናትን እንደሚጠይቅ እናስተውላለን (ሁለተኛ ዕትም፣ 317-9)፡፡ ይህ መጽሐፍ በሚተረትራቸው የሕይወት ልምዶችና ትዝታዎች አማካይነት፣ ወጣቶች ሊያገኙ የሚችሏቸውን ሰብዕናን የሚያንፁ ነገረ ሥራዎች ከራሳቸው ጋር ለማቆየት ከጣሩ፣ በእርግጥ ፍሬያማ የለውጥ ሒደት ውስጥ መሆናቸውን አይጠራጠሩ፡፡

በአንድ መጽሐፍ ምሳሌነት ያየነውን ለውጥ የመቆስቆስ ብርታት ሌሎች ምሁራንም በተለያየ መልክ ሊሠሩት ይችላሉ፡፡ እንደ ‹‹ኢቢሲ››፣ ‹‹ዋልታ›› እና ‹‹ፋና›› ያሉ ግዙፍ የመገናኛ ብዙኃንም፣ እንደ ሰውም እንደ ባለሙያም እንደ ተቋምም በለውጥ ተመንድጎ (በህዳሴ ሾሮ) የማሾር ነፍስ ካላቸው፣ በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ተሃድሶ ውስጥ ተዓምር መሥራት ይችላሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ የተያያዝነው የለውጥ ዕድል ከዚህ ቀደም ከተከሰቱት የለውጥ ዕድሎች ሁሉ በመሳካት አቅሙ የላቀ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ ይኼኛው ለውጥ መንግሥት ወደ ለውጥ እንዲመጣ እየተቁለጨለጭን ያለንበት ሳይሆን፣ ለውጡ ራሱ በመንግሥት የተጀመረና የለውጥ ጥረቱም መሰናክሎችን እያለፈና እየጨመረ፣ መሬት የመቆናጠጥ እንቅስቃሴውና የስኬት ተስፋውም እያደገ የመጣ ስለሆነ ነው፡፡ ተተናኳይና ዕይታ አዋኪ የፖለቲካ ጭጋጎች ሳያወላክፉት ሦስትና አራት ዓመታት የመራመድ ዕድሜ ካገኘም፣ ዓይን የሚወጋ የውጤታማነት ፍካቱ ራሱ በራሱ፣ ጨለምተኛ አውጋዦችን እያሟሸሸ አድናቂና ደጋፊዎቹን እያባዛ እንደሚጓዝ ጥርጥር የለውም፡፡ ከጦርነት አዙሪት ለመውጣት ጠመንጃ ተኳሾችን ወደ ሰላም የመሳብ ጥረታችን ዛሬም ነገም እስከ ቀጠለ ድረስ፣ የምክክር መድረካችንም የተሳትፎ ዕድልን በማንም ላይ እስካልጠረቀመ ድረስ፣ አሁን የደረስንበት አገራዊ ምክክር ኢትዮጵያን ዘላቂ የአገረ መንግሥታዊ ሥርዓት የማስያዝ ተልዕኮን የማሳካቱ ነገር በአያሌው ፊት ለፊት የሚታይ ነው፡፡ ጥቂት ቡድኖች ለምክክሩ ጀርባቸውን ሰጥተው መተኛትን ቢመርጡ፣ ራሳቸውን የተረት አካል ከማድረግ በቀር፣ በኢትዮጵያ መታደስ ላይ የቡጭሪያ ምልክት ያህል እንኳ ተፅዕኖ ማሳረፍ አይችሉም፡፡

ይህንን ያህል በእርግጠኛነት ልቦና ለመናገር የሚያበቃን፣ ህዳሴያችን ወሳኝ ካስማዎችን ማበጀቱ ነው፡፡ በሕዝቦች አገራዊ ተጋድሎ የታደሰና መታደስ የቀጠለ የመከላከያ የደኅንነትና የፖሊስ አውታር ተገንብቷል፡፡ ከዚህ ጋር የመሠረተ ልማትና የሶሲዮ ኢኮኖሚ ልማት በፍጥነት እየተጎዘጎዘ ነው፡፡ አገራዊ ምክክሩም የመንግሥት/የገዥ ፓርቲ ፕሮፓጋንዳዊ ውጥን ሳይሆን፣ የሕዝቦች ረዥም የለውጥና የሰላም ጥማት የተከማቸበትና የተገሸረበት ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፣ ከመላ አገሪቱ የወጡ የሕዝብ ሰዎች በቀጥታ የሚሳተፉበት ነው፡፡ የመሳተፋቸውም ትርጉም የወግ አይደለም፡፡ መላ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ስኬቱን በደም ለተዋደቁላት አገራቸው ፀንቶ መቀጠል ሲሉ በስስት የሚጠብቁትና ተመካካሪዎቹ የተፈነጋገጡባቸው ጉዳዮች ቢኖሩ በውሳኔ-ሕዝብ (በእያንዳንዳቸው ድምፅ ግዙፍ ድምር) ዕልባት ለመስጠት ኢትዮጵያውያን ከዳር ዳር አፍጠው የሚጠብቁት ነው፡፡ በዛሬ ውሳኔያቸው የወደዱት ነገ ባይጥማቸው/ ዛሬ የተውትን ነገ ቢከጅሉት የሚሠጉበት ነገር አይኖርም፣ ከዚህ በኋላ የአገራቸው አቀራረፅ በራሳቸው ድምር ፍላጎት ውስጥ እንደሆነ ስለሚያውቁት፡፡

ሌላም ነገር አለ፤ የአሁኑን አገራዊ ምክክርና የኢትዮጵያን ህዳሴ የሚያለመልሙ ምሁራዊ አዕምሮዎችም ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡ የዶክተር ደቻሳ አበበ ከ‹‹ኦሮሚያ ሪፐብሊክ›› እስከ ‹‹ኩሻዊት ኢትዮጵያ›› የዚሁ ምሁራዊ ውልደት አንድ ነፀብራቅ ነው፡፡ በምሁሩ ሥራ ውስጥ እንደታየው፣ የኢትዮጵያን አገር ግንባታና ፍቅር የጎዱ ዕሳቤዎች የሰረፁት የተሳሳተ ሥዕል የሚሰጥ ነገር በጻፉ የውጭ ሰዎች በኩል ብቻ እንዳልሆነ፣ ችግሩ የውጭ ሰዎች ተፅዕኖ ብርካቴ በነበረበት የዘመናዊ ትምህርት ታሪካችንም በኩል የመጣ ስለመሆኑና አገርን አንድ ዓይነት መልክ አስይዞ የመቅረፅ ውስጣዊ ሙከራችንም የችግሩ ተጋሪ መሆኑን ደፍረን መናገር ከጀመርን፣ መጪ ተስፋችን ብዙ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ምሁራዊ አቅም እየተበራከተ፣ ሚዛናዊ ግንዛቤ ለጨበጡ እልፍ አዕላፍ ልሂቃን መወለድ አብራክ ይሆናል፡፡

የተያያዝነው ተግባር ተጨባጭነት ያለው እንደመሆኑ፣ አርዝመን መተለማችን አስተዋይነት እንጂ ቅብጠት አይሆንብንም፡፡ ከኢንዱስትሪያዊ ግስጋሴ ጋር የአኗኗር-የአስተሳሰብ-የሥነ ምግባር ሥልጣኔን ብዙኃናዊ እውነታ ለማድረግ መሥራት ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡ የኅብረተሰባችንን ሰላም ከመንከባከብ ባሻገር ከቱሪዝም መናር ጋር ተያይዞ በሚመጣ የባህል መላሸቅ የመበከል አደጋን ለመቋቋም ያስችላል፡፡ በዚህ ረገድ የሚገኝ በጎ ውጤት ቀጣናችን ላይ ተጋቦት ስለሚኖረው ስኬታችን በቀጣናዊ ግቢም የሚታገዝ ይሆናል፡፡ ፈጠነም ዘገየም የዓለማችን የጉዞ አቅጣጫ ከእኛ የመሠልጠን ጥረት ጋር ተዛማጅ መሆኑ አይቀርምና ጊዜ በረዘመ ቁጥር ማጣፊያው የሚያጥረን አንሆንም፡፡

ቀርነቶችንና ልሽቀቶችን ሳይደልቡ ታፍ ታፉ እያራገፍን መሄድ የምንችለው (ባለን የአውታራትና የንቃተ ህሊና አቅሞች አማካይነት) የእርስ በርስ ግንኙነቶቻችንንና ከተፈጥሮ ጋር ያለንን ተራክቦ የሁለት በኩል ተጠቃሚ የማድረግ ጉዞ ከተያያዝን ነው፡፡ እዚህ የጉዞ አቅጣጫ ውስጥ እስከሆንን ድረስ በአጠቃላዩ የሰው ልጆች የሐርነት ጎዳና ውስጥ ነን ማለት እንችላለን፡፡ ይሁን እንጂ፣ ዛሬ ባለንበት የዓለማችን የዕድገት ደረጃ፣ የትኛውም የብልፅግና ቁልል የምዝበራ ገጽ አለው፡፡ የትኛውም ሥልጣኔ ያለመሠልጠን/ የዝቅጠት ፈርጅ አለው፡፡ ዓለማችን ደጋግ/አልሚ ሐሳቦችን ጥበቦችንና ተግባሮችን እንደሚያመነጭ ሁሉ፣ አያሌ ተንኮሎችንና ሸሮችን የጥፋት ሥራዎችንና ሰቆቃዎችን ያፈልቃል፡፡ አገራችንና ኅብረተሰባችን በዚህ መሰሉ ክፉ ነገር ለመፈተን እንግዳ አይደሉም፤ ዛሬም እየተፈተኑ ነው፡፡ ነገም ፈተናዎች አያጡንም፡፡ በጎ በጎውን እያጎለበተና እያለማ መሄድ የሚፈልገው ሥልጣኔያችን የህላዌውን ቀጣይነት ከጥቃቶች ለመጠበቅ እንዲችል፣ ተንኮሎችና የጥፋት ሥራዎች የትና እንዴት እንደሚወጠወጡና ለማን እንደሚታለሙ ነቅቶ የማነፍነፍ/የመከታተልና ለማክሸፍ የሚያስችል ጥበበኝነትን ማዳበርም ግዱ ነው፡፡

በአሁኑ ደረጃ፣ ኢትዮጵያ አንዱን ውጊያ ስትተናነቅ ሌላው እየተደረበ ወይም የገጠሟትን ውጊያዎች ስታስተነፍስ ሌሎች ደግሞ እየተተኩ ከውጊያ አዙሪት እንዳትወጣና ብላ ብላ አንድ ቀን ጦሽ እንድትል የሚሠሩ የደባ ጎሬዎች አሉባት፡፡ አሁን በምንገኝበት ወቅት እንኳ በአካባቢያችን ውስጥ ጢሳ ጢስ ያለው ያጎበረ ነገር አለ፡፡ ይህ ጉብርታ ከተመቸው ሦስት ማዕዘናዊ መተናኮል ሊፈጥር የሚችል፣ ከዚያ ዝቅ ካለም፣ የረገቡና እየረገቡ ያሉ የውስጥ ጠመንጃዎችን እንደገና ከማርገብገብ የማይመለስ ነው፡፡ በዚህ ሰዓት ይህንን ያጎበረ ነገር ውስጣ ውስጣዊ ፈትሉንና ደፈጣውን በደንብ ተረድቶ ኢትዮጵያን የሚያውክ ተንኮል እንዳያዳውር በብልኃት የማስተንፈስ ሁነኛ ተግባር ተደቅኗል፡፡ ለአገራችንና ለኅብረተሰባችን ሰላምና ግስጋሴ ቆመናል የምንል የልሒቅና የፖለቲካ ኃይሎችም፣ አገራዊ ምክክራችንን እያሳላን መግባባታችንን ካቃናን፣ ይህን በማሳካታችን ብቻ፣ አካባቢያችን ላይ ያረመመውን ንፍፊታም ነገር እናልፈሰፍሰዋለን፡፡ ከዚያም ወዲያ አገራዊ መግባባታችንን በንቃተ ህሊና፣ በተቋማዊ ግንባታና በግስጋሴ እስከመገብን ድረስ እንደ አገር አንድ ልብ ከመሆን የሚያቆመን ወይም የሚያደነባብረን ምንም ኃይል አይኖርም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...