Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ባለፈው ሳምንት እሑድ ለሰኔ ፆም መያዣ ጥቂት ወዳጆቼን ቤቴ ምሳ ጋብዤ ነበር፡፡ ወዳጆቼ በሰዓቱ ደርሰው የተዘጋጀውን ምሳ እየተጋበዙ ሳሉ በቅርቡ ከአሜሪካ የመጡ የድሮ ወዳጆች ሳይታሰብ ከተፍ አሉ፡፡ ዳያስፖራዎቹ በአንድ ዘመዴ መሪነት ‹‹ሰርፕራይዝ ቪዚት›› እያሉ ሲቀላቀሉን በደስታ ተቀበልናቸው፡፡ እነሱም ጊዜ ሳያጠፉ ምሳቸውን ይዘው በመመገቢያ ጠረጴዛው ዙሪያ ታደሙ፡፡ የናፍቆት ሰላምታችንን እየተለዋወጥን ምሳችንን እየበላን የባጥ የቆጡን ስናወራ ቆይተን፣ እንደ ፍላጎታችን መጠጥ መጎንጨት ጀመርን፡፡ የድሮ ወጋችንን አወራርደን ከጨረስን በኋላ የአገር ቤት ወዳጆቼና ዳያስፖራዎቹ ዘና ባለ ስሜት የተለመደውን የአገር ጉዳይ መነጋገር ጀመሩ፡፡

ቀዳሚው ጉዳይ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋለው የፀጥታ መደፍረስና የዜጎች ሥቃይ ሆኖ ብዙ ተባለ፡፡ አገር ሰላም አጥታ ከአዲስ አበባ ከተማ ወጣ ብሎ እንደ ሶደሬና ላንጋኖ የመሳሰሉ የዕረፍት ጊዜ ማሳለፊያ ሥፍራዎች መሄድ አለመቻሉን አንደኛው የዳያስፖራ ወዳጄ ሲናገር፣ ሌላው አገር በቀል ወዳጄ ደግሞ አዲስ አበባ አጠገብ ያለችው ቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ኩሪፍቱና ባቦጋያ ለመሄድ አስፈሪ መሆኑን ተናገረ፡፡ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በሌሎች ሥፍራዎች የተካሄዱ ውጊያዎች ያስከተሉት ዕልቂት፣ መፈናቀልና ውድመት በከፍተኛ ሐዘን ብዙ የሐሳብ ልውውጥ ተደረገበት፡፡ ከሐዘኑና ከቁጭቱ ወጣ ተብሎም መፍትሔው ምን ይሆን የሚለው ጭምር ሰፊ ጊዜ ይዞ ነበር፡፡

ይህ አብቅቶ ወደ አዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ተገባ፡፡ የኮሪደር ልማቱ መካሄድ አስፈላጊነትና የሚያስከትለው ችግር በየፈርጁ ተነስቶ ውይይትና ክርክሩ ጦፈ፡፡ ከዳያስፖራዎቹ አንደኛው መንግሥት ሆን ብሎ አዲስ አበባዊ ማንነትን ለማጥፋት በልማት ስም የሚያካሂደው መሰሪ ድርጊት መሆኑን ተነተነ፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ቢሆንም በአጭሩ አዲስ አበባን ለማሳመር ተብሎ ‹ሰው ተኮር ልማት›፣ ‹ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ፅዱና ውብ› ተብሎ ፊት ለፊት ቢነገርም፣ የከተማዋን ነዋሪዎች ወደ ዳር አፈናቅሎ ከተማዋን ባለቤት አልባ የማድረግ ድብቅ ዓላማ የያዘ እንቅስቃሴ ነው ሲል አብራራ፡፡ ‹‹መንግሥት ከተማዋን ለራሱ ፍላጎት ሲል ቢያለማትም ለነባር ነዋሪዎቿ የተረፋቸው እንደ ቆሻሻ ተንገዋሎ መባረር ብቻ ነው…›› ሲልም በመንገፍገፍ ተናገረ፡፡

ከወዳጆቼ አንደኛዋና ሁሌም በዝምታዋ የምናውቃት ከት ብላ እየሳቀች መድረኩን ስትይዘው፣ ምን ልትል ነው ብለን እሷን በመገረም ማየት ጀመርን፡፡ ‹‹አይ ዳያስፖራ፣ በቃ እናንተ ከአንድ ወንዝ የተቀዳችሁ አንድ ዓይነት ውኃ ነው የምትመስሉኝ…›› ብላ፣ እነሱ እጅግ በጣም የሠለጠነ አገር ውስጥ እየኖሩ አገራቸው ግን ዕድሜ ልኳን አፈር መስላ እንድትኖር እንደሚፈልጉ ስትናገር፣ ‹‹ሁሉንም ዳያስፖራ አንድ ላይ ደምረሽ እንዲህ ማለት የለብሽም…›› ብሎ አንደኛው አቋረጣት፡፡ ይህች ወዳጃችን ግን፣ ‹‹ቆይ ቆይ… ሁሉም አንድ ላይ መፈረጅ የለበትም፡፡ ነገር ግን ብዙዎቻችሁ ፕሮፌሰር መስፍን በአንድ ወቅት የወያኔ ቃፊሮችን እንዳሉት፣ ከአንድ ፋብሪካ የወጣችሁ እንደምትመስሉማ መካካድ የለብንም…›› ስትል ሁላችንም ማለት ይቻላል ሳቅን፡፡

‹‹ውጭ ያላችሁት አገር ቤት ስትመጡ አቤት አሜሪካ፣ አቤት ጀርመን፣ አቤት ፈረንሣይ፣ አቤት ሩሲያ፣ ወዘተ ትሉናላችሁ፡፡ እኛም ቻይና ወይም እዚህች ዱባይ ደረስ ብለን ስንመለስ የከተሞቹን ውበት፣ ብርሃን፣ ፅዳት፣ ሥልጣኔና ሌላውን አስጎምጂ ነገር እንተርካለን፡፡ እኛ አገራችንን አሳምረን ለምን እንደ ሌሎቹ አንኮራባትም፡፡ አዲስ አበባ ከ60 ዓመታት በላይ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ፣ ለበርካታ ዓመታት የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መናኸሪያ ሆና ከኒውዮርክና ከጄኔቭ እኩል ስሟ ይነሳል፡፡ ነገር ግን በዓለም ላይ ካሉ እጅግ አስቀያሚ ከተሞች አንዷ ሆና ነው የኖረችው፡፡ ቆሻሻ መንደሮችን ታቅፎ መቀጠል እንደማይቻል ሁሉ ተባብሮ አገርና ከተማ ማሳመር ታላቅ ሥራ ነው…›› አለች፡፡

ከዚህ ወዲያ የነበረው ሙግት ከተማም ሆነ አገር መልማቱም ሆነ ማማሩ የሁሉም ፍላጎት እንደሆነ፣ ነገር ግን ልማቱ ሰውን የሚጠቅም መሆን እንዳለበት፣ ሰው አልባ ከተማ የሚመስል ልማት ማካሄድ ከትርፉ ጉዳቱ እንደሚያመዝን፣ ለዚህም ሲባል በዘፈቀደ መሥራት ሳይሆን መመካከር እንደሚያስፈልግ በሌሎች ወዳጆቼም በሰፊው ተባለበት፡፡ በተለይ ከሲንጋፖር መልስ በተካሄደ የባለሥልጣናት ማብራሪያ ‹‹ጨከን ያለ ዕርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል›› የሚል ሐሳብ መነሳቱ ብዙዎችን እንደሚያሳስብ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ‹‹ንብረት ማስመለስ›› የሚል አዋጅ በማውጣት ድንጋጤ መፍጠርና ማስፈራሪያ መንዛት አላስፈላጊ እንደሆነ በቅብብል ተወሳ፡፡

ያቺ ወዳጃችን ግን አሁንም አልተበገረችም፡፡ አገርን የማልማት ኃላፊነት የማንኛውም መንግሥት እንደሆነ፣ አሁን ያለው መንግሥትም ጨከን ብሎ የሚፈለግበትን ኃላፊነት መወጣት አለበት ስትል ንግግሯን ጀመረች፡፡ አሜሪካም ሆነች ሌሎች የአውሮፓ አገሮች ከፍተኛው የሥልጣኔ ደረጃ ላይ የደረሱት ከባድ መስዋዕትነት የሚያስከፍሉ ተግባራት ተከናውነው ነው አለች፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥትም ሆነ ሕዝብ ወገባቸውን ታጥቀው ጨከን ብለው መሥራት እንዳለባቸው አስረግጣ ተናገረች፡፡ ሕዝብና መንግሥት ሆድና ጀርባ ሆነው እንዴት አንድ ላይ ይቆማሉ የሚል ጥያቄ ሲቀርብላት፣ ‹‹አንድ አገር ውስጥ ሕዝብና መንግሥት በሚስማሙት እየተስማሙ፣ በማያስማማቸው ደግሞ ልዩነታቸውን ይዘው አብረው መሥራት ይችላሉ፡፡ ችግሩ ያለው የት ነው ብትሉ ልዩነት ላይ ብቻ ማተኮር ነው…›› ብላ አሁንም ሳቀች፡፡

‹‹እንዴት ነው ነገሩ፣ አንቺ ብልፅግና ፓርቲን ወክለሽ ነው እንዴ የምንነጋገረው…›› እያለ አንዱ ዳያስፖራ አዲስ ቅኝት ሲያስጀምር፣ ‹‹ወንድሜ እባክህ እኔ በሕይወቴ የማንም ፓርቲ አባልም ደጋፊም ሆኜ አላውቅም፡፡ ለአገሬ ጥሩ ነገር ሲሠራ ድጋፌን እሰጣለሁ፣ የማይሆን ነገር ሲሠራም እቃወማለሁ፡፡ ብልፅግና ብዙ ጥፋቶች እንዳሉበት አውቃለሁ፣ ነገር ግን መልካም ሲሠራ ድጋፍ ባልሰጥ ደግሞ ህሊናዬ ይጠይቀኛል፡፡ ዜጎች ያለ አግባብ ሲንገላቱ፣ ሲከሰሱ፣ ሲታሰሩና ሲሳደዱ እጅግ በጣም እበሳጫለሁ፡፡ በማኅበራዊ የትስስር ገጼ ድምፄንም አሰማለሁ፡፡ አሁን በተነሳንበት ከተማ ማሳመር ደግሞ፣ እነ ሠራተኛ ሠፈርን የመሳሰሉ ቦታዎች ሲያበቃላቸውና ተቆራምደው ይኖሩባቸው የነበሩ ሰዎች የተሻለ መኖሪያ ሲያገኙ በጣም ደስ ነው ያለኝ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሥራ በዚህ ስሜት ከቀጠለ እስከ መጨረሻው ድጋፌን እሰጣለሁ፡፡ ካልሆነ ግን ግንባር ቀደም ተቃዋሚ እኔ ነኝ…›› ብላ አሳረገች፡፡ እኔም እላችኋለሁ በመኖሪያ ቤታችን፣ በሥራ ቦታችንም ሆነ በሌላው ሥፍራ እንዲህ ረጋ ብለን ስንነጋገር አገር ሰላም ትሆናለች፡፡ ይህ መልዕክቴ ለመንግሥትም ሆነ ለሌሎች ወገኖች ነው፡፡

(ታሪኩ ወሰኑ፣ ከብሥራተ ገብርኤል)  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...