Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበትግራይ ክልል አገራዊ የምክክር ሒደት እንዲጀመር ጥያቄ ቀረበ

በትግራይ ክልል አገራዊ የምክክር ሒደት እንዲጀመር ጥያቄ ቀረበ

ቀን:

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የአገራዊ ምክክር ሒደቱ በትግራይ ክልል እንዲጀመር ጥያቄ አቀረቡ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያቀረበውን የሥራ አፈጻጸምና ቀጣይ አቅጣጫ አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ ዓርብ ሰኔ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ውይይት ሲያካሂድ፣ የምክር ቤቱ አባላት በትግራይ ክልል የምክክር ሒደቱ እንዲጀመር ጠይቀዋል፡፡ 

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር)፣ ከትግራይ ክልል ውጪ የአማራ ክልልን ጨምሮ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተባባሪዎች ሥልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን የተሳታፊ ልየታና መረጣ ባሉት ነባራዊ ሁኔታዎች ምክንያት በአማራና በትግራይ ክልሎች አለመጀመሩን ገልጸዋል፡፡ 

ምንም እንኳን በአማራ ክልል አሁንም ግጭቶች ቢኖሩም 800 ያህል ለሚሆኑ ተባባሪዎች ሥልጠና ለመስጠት ታቅዶ ለ200 ያህሉ ብቻ ሥልጠናው መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡ በሌላ በኩል ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ምንም ዓይነት ሥራዎችን አለመጀሩን ኮሚሽነሩ በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡ በክልሉ 8,370 ያህል ተሳታፊዎች ለአገራዊ ምክክሩ እንደሚገኙ ይጠበቃል ብለው፣ የተሳታፊ ልየታ ባልተደረገበት የአማራ ክልልም 24 ሺሕ ተሳታፊዎች እንደሚኖሩ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡

የኮሚሽኑን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አስመልክቶ ጥያቄያቸውን ያቀረቡ የምክር ቤት አባላት፣ በትግራይ ክልል ሒደቱን ለመጀመር ከባድ የሆነበት ምክንያት ምን እንደሆነ ጠይቀዋል፡፡ 

ጥያቄያቸውን ካቀረቡ አባላት መካከል አቶ መለስ መና የትግራይ ሕዝብ በአሁኑ ሰዓት ሰላም ፈላጊ መሆኑን በመግለጽ፣ ክልሉ በምክክር ሒደቱ እንዲያልፍ ሁሉም አካላት መተባበር እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡ ኮሚሽኑም ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ያጋጠመው ችግር ምን እንደሆነ ጠይቀው፣ ‹‹ኮሚሽኑ በክልሉ ሥራዎችን ለማከናወን ምን ያህል ጥረት አድርጓል?›› ሲሉም አክለዋል፡፡ 

ሌላዋ የምክር ቤት አባል ነጃት ግርማ (ዶ/ር) በበኩላቸው በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ ከማኅበረሰቡ ጎን በመሆን መመልከት እንደሚገባ ገልጸው፣ ‹‹አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል በሒደቱ መሳተፍ ይፈልጋል›› ብለዋል፡፡ 

በአማራ ክልል ያለውን ሁኔታ አስመልክቶም ባለው ሁኔታ ምክንያት በሒደቱ ለመሳተፍ እየፈለጉ ያልቻሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንዴት ተደራሽ ለማድረግ እንደታሰበ ነጃት (ዶ/ር) ጠይቀዋል፡፡ 

‹‹አገሪቱ አሁን ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት ሁኔታው ይስተካከላል ብላችሁ ታስባላችሁ ወይ?›› በማለት ጥያቄያቸውን የሰነዘሩት ሌላኛው የምክር ቤት አባል ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች አንፃርም ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተሳተፉ አለመሆናቸው እየታወቀ፣ 50 በመቶ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኮሚሽኑ ጋር እየሠሩ ነው በማለት የቀረበው ሐሳብ ላይ ጥያቄ አንስተዋል፡፡ 

‹‹አክለውም በውጭ የሚገኙ የአማራ ማኅበረሰብ አባላት በሒደቱ እየተሳተፉ አለመሆናቸው እንዴት ይታያል?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ከምክር ቤቱ አባላት በኩል ከቀረቡት በርከት ያሉ ጥያቄዎች አንፃር አጭር ምላሽ የሰጡት ዋና ኮሚሽነር መስፍን (ፕሮፌሰር)፣ በአማራ ክልል የተሳታፊ ልየታ አለመካሄዱን ገልጸው፣ የተባባሪ አካላት ሥልጠናም ቢሆን ባለው ሁኔታ ምክንያት የዕቅዱን 50 በመቶ እንኳን ማሳካት እንዳልተቻለ ጠቁመዋል፡፡ 

ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ሥራዎችን ያልጀመረበትን ምክንያት አስመልክቶም ‹‹ሁላችሁም በምታውቁት ምክንያት ሒደቱ አልተጀመረም፤›› በማለት አጭር ምላሽ ሰጥተው አልፈዋል፡፡ አክለውም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በኩል አጀንዳዎችን ከማቅረብ ጋር በተያያዘ ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን በቅርበት በመነጋገር መፈታታቸውን አስረድተዋል፡፡ 

በተመሳሳይ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በኩል ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ኮሚሽኑ በውይይት ለመፍታት መሞከሩን፣ አሁንም ድረስ ከምክር ቤቱ ጋር ንግግሮችን እያካሄዱ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ 

ኮሚሽኑ ስምንት ያህል የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ከዳያስፖራ አባላት ጋር ውይይት መደረጉን የገለጹት መስፍን (ፕሮፌሰር)፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ውይይቱን ስናካሂድ የነበረው በአማርኛ በመሆኑ የብሔር ስብጥራቸውን ልናውቅ አንችልም፤›› በማለት የአማራ ተወላጆች አልተሳተፉም ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ነገር ግን ለሦስት ጊዜያት ያህል በውጭ አገሮች ከሚኖሩ የአማራ ምሁራን ጋር የውይይት መድረክ መካሄዱን ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡ 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው በትግራይ ክልል ሒደቱን ለመጀመር፣ ክልሉን አስመልክቶ በዋነኛነት ከሚመለከተው ሕወሓት ጋር ንግግሮች እየተደረጉ መሆናቸውንና ለመጓተትም የሰላም ስምምነቱ ሒደትም የራሱን አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡ 

ነገር ግን በክልሉ የሚገኙ ሁሉም አካላት የምክክር ሒደቱን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንና ንግግሮች እየተካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...