Wednesday, July 24, 2024

የትጥቅ ፍልሚያ አብቅቶ ሰላማዊ ፉክክር እንዲጀመር ግፊት ይደረግ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መወገድ ካለባቸው አስከፊ ነገሮች አንዱ የትጥቅ ፍልሚያ ነው፡፡ የትጥቅ ትግል ከመወገዱ በፊት ግን መንስዔ የሆኑ አላስፈላጊ ድርጊቶች መፅዳት አለባቸው፡፡ ለሕጋዊና ለሰላማዊ ፉክክር ፀር የሆኑ ድርጊቶች ሲፀዱ ማንም እየተነሳ ጠመንጃ ወልዋይና ጦር ነቅናቂ አይሆንም፡፡ ኢትዮጵያ በሕግና በሥርዓት የምትተዳደርበት ሁሉን አሳታፊ ሥርዓት ለማቆም የሚያስችሉ ተግባራት ወደ ጎን እየተገፉ፣ ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት ሲፈነጩ ከሰላማዊ ፉክክር ይልቅ የትጥቅ ፍልሚያ እየተመረጠ በርካታ ጉዳቶች ደርሰዋል፡፡ በተለይ በፖለቲካው ምኅዳር ውስጥ የሚስተዋለው መረን የተለቀቀ ሥርዓተ አልበኝነት፣ አገርን ከሥልጣንና ከጥቅም በታች በማድረግ በሕዝብ ላይ መጠነ ሰፊ ፈተና ደቅኗል፡፡ በሕግ የበላይነት ጥላ ሥር የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት በሆነው ሕዝብ ህሊና መዳኘት ሲገባ፣ የጉልበት መንገድ ብቻ እየተመረጠ አገር ምስቅልቅሏ ወጥቷል፡፡ በየቦታው የሚስተዋለው የፀጥታ ችግር አፋጣኝ መፍትሔ ይፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያና ሕዝቧ በሰላም የመኖር፣ የመልማት፣ የማደግና ብሩህ ተስፋ የማየት መብታቸው ሊከበር ይገባል፡፡ ማንኛውም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በሕዝብ ፍላጎትና ፈቃድ ላይ መመሥረት ይኖርበታል፡፡ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥትም ሆነ ነገ የሥልጣን መንበሩን ለመቆናጠጥ የሚያስቡ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ከምንም ነገር በላይ ለአገር ሰላምና ለሕዝብ ደኅንነት መጨነቅ አለባቸው፡፡ ችግሮች ሲያጋጥሙ ተንደርድሮ ወደ በረሃ የሚያስገባውን ጎዳና ሳይሆን፣ በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ሊያነጋግር የሚችል ሥርዓት መገንባት የሚያስችለው ጉዳይ ላይ ይተኮር፡፡ በሕዝብ ስም መነገድም ሆነ መቆመር የተለመደው፣ ሕዝብ ተንቆ ሥልጣንና የሚያስገኘው ጥቅም ላይ ማነጣጠር ስለበዛ ነው፡፡ አሁንም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄዱ የትጥቅ ፍልሚያዎች አብቅተው ሰላም እንዲወርድ ጥረት ይደረግ፡፡ በእልህና በግትረኝነት የሚካሄደው ግብግብ አገር ከማፍረስ የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡

ኢትዮጵያን በመሰለች በርካታ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥልቶች ባሉባት አገር በተለያዩ አካባቢዎች ጦርነት፣ ጥቃት፣ አፈና፣ ዕገታ፣ ግድያ፣ ማፈናቀል፣ ዘረፋና ውድመት በዚህ ዘመን ማየት አሰቃቂ ነው፡፡ ፖለቲከኞች ችግሮቻቸውን በሰከነ መንገድ ተቀምጠው መፍታት እስኪችሉ ድረስ የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሲቪል ማኅበራት ተወካዮች፣ ገለልተኛ ምሁራንና ልሂቃን፣ እንዲሁም የአገር ጉዳይ የሚመለከታቸው በሙሉ በባህላዊ የግጭት አፈታት ሥልቶች መፍትሔዎችን ማማተር ይኖርባቸዋል፡፡ በየቦታው እየፈሰሰ ያለው የንፁኃን ደም መቆም የሚችለው ሰላም ለማስፈን በጋራ ለመነሳት ቁርጠኝነት ሲኖር ነው፡፡ እንደ ፕሪቶሪያው ስምምነት የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትና አስገዳጅነት እስኪመጣ መጠበቅ አይገባም፡፡ ለአገራዊ ችግር አገራዊ መፍትሔ ለማስገኘት፣ በቅንነትና በንፁህ ህሊና ተፋላሚ ወገኖች ሰላም እንዲያወርዱ መጎትጎት የግድ መሆን አለበት፡፡ አገር አንዴ ካመለጠች ተመልሳ አትገኝም፡፡

ሰሞኑን በአማራ ክልል በትጥቅ የሚፋለሙ ወገኖች ወደ ሰላማዊ ውይይትና ድርድር እንዲመጡ እንደቀረበው ግብዣ፣ በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ተፋላሚዎችም ጥሪ ይደረግላቸው፡፡ ትጥቅ አንግበው የሚፋለሙ ወገኖችም የመደራደሪያ ነጥቦቻቸውን ይዘው ለሰላም መስፈን የሚፈለግባቸውን ይወጡ፡፡ ዘወትር እንደሚባለው ማንም አሸናፊ በማይሆንበት ጦርነት የሚጎዳው ምስኪኑ ሕዝብ ነው፡፡ በጦርነት ቀጣና ውስጥ መከራቸውን ከሚያዩ ወገኖች ጀምሮ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም ናፍቆታል፡፡ ሰላም በመጥፋቱ ምክንያት ተዓምር በሚባል ሁኔታ አስከፊ የድህነት ኑሮ የሚገፋው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ፖለቲከኞች በሚፈጥሩት እንካ ሰላንቲያ ምክንያት ሕይወት ሲኦል እየሆነበት ነው፡፡ በቀን አንዴ ምግብ ለማግኘት የሚያዳግታቸው በርካታ ሚሊዮኖች የሚኖሩባት አገር ውስጥ ጦርነት ማካሄድ፣ ከነውሮች ሁሉ የከፋ ኃጢያት መሆኑን ለመገንዘብ የድህነቱን አዘቅት ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡

መንግሥት በሁሉም አካባቢዎች ትጥቅ አንስተው ከሚፋለሙት ኃይሎች ጋር የሚያደርገው ውጊያ አብቅቶ፣ ሰላማዊ የድርድር ሒደት ለማስጀመር ከማንም የበለጠ ኃላፊነት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ሰላም ስትሆን ነው ታላላቅ የልማት ዕቅዶችን ወደ ተግባር ማስገባት የሚቻለው፡፡ ሁሌም የግጭትና የውድመት የስበት ማዕከል በሆነው የአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ተሁኖ የተራዘመ ጦርነት ማድረግ ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከዲፕሎማሲና ከሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች አኳያ ሲታይ ውጤቱ ኪሳራ ነው፡፡ በዓለም አደባባይ አንገትን ቀና አድርጎ በኩራት መራመድ የሚቻለው፣ ሰላሟ አስተማማኝና በዕድገት ጎዳና ላይ የምትራመድ አገር ስትኖር ነው፡፡ ጦርነት ውስጥ ተዘፍቆ ኩራትና ክብር ሳይሆን ጣት መጠቋቆሚያ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ አይኖርም፡፡ ኢትዮጵያ በጦርነትና በምፅዋት ለማኝነት የጎደፈ ስሟና ገጽታዋ የሚስተካከለው፣ ለሀቀኛ ድርድርና ለዘለቄታዊ ሰላም ከልብ የመነጨ ፍላጎት ሲኖር ብቻ እንደሆነ ነጋሪ አያስፈልግም፡፡

ለአገራችሁ የምታስቡ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ልዩነቶቻችሁን እንደያዛችሁ፣ ለአገራችሁ ስትሉ ለሰላም መስፈን የሚፈለግባችሁን ኃላፊነት ተወጡ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከአንዱ ጦርነት ወደ ሌላው እንደ ቀልድ ዘው ተብሎ እየተገባ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖች አልቀዋል፡፡ በርካታ ሚሊዮኖች ቀዬአቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡ ከደሃ ገበሬ ጎጆ ጀምሮ ትልልቅ መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፡፡ ዘጠኝ ሚሊዮን ያህል ሕፃናት በጦርነት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በርካታ ሚሊዮኖች ለአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ፈላጊነት ተጋልጠዋል፡፡ ትርፍ አምራች የነበሩ አካባቢዎች በጦርነት በመጎዳታቸው ዕርዳታ ፈላጊ ሆነዋል፡፡ የሰዎችና የምርቶች እንቅስቃሴ በመስተጓጎሉ ምክንያት ዜጎች ሊሸከሙት የማይችሉት የኑሮ ውድነት ተከስቷል፡፡ በአጠቃላይ ሕይወት ገሃነመ እሳት የሆነባቸው ኢትዮጵያውያን በሙሉ የሰላም ያለህ እያሉ ነው፡፡ የዜግነት ግዴታ ስለሆነ ይህ አሳሳቢ ጥሪ ይደመጥ፡፡ የትጥቅ ፍልሚያ አብቅቶ ሰላማዊ ፉክክር እንዲጀመርም ግፊት ይደረግ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከእንቆቅልሽ ጨዋታ ውስጥ ውጡ!

በወርኃ ሚያዝያ ተካሂዶ የነበረው ውይይት ቀጣይ ነው የተባለው መድረክ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንደገና ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. አገናኝቶ ነበር፡፡ መንግሥትን የሚመራው...

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...