Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ገለልተኛና በመሪዎች መቀያየር የማይዛነፉ ሆነው እንዲገነቡ ተጠየቀ

የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ገለልተኛና በመሪዎች መቀያየር የማይዛነፉ ሆነው እንዲገነቡ ተጠየቀ

ቀን:

ከአገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓትና ከተቋማት መሪዎች መቀያየር ጋር አብረው የማይቀያየሩና የማይፈርሱ ነፃ፣ ገለልተኛና ጠንካራ ተቋማት እንዲገነቡ ምሁራን ጠየቁ፡፡

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የቢሮክራሲ መዋቅርና የመንግሥት አስተዳደር ከተጀመረ አንድ ክፍለ ዘመን የተሻገረ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ የሚችሉ ገልለተኛ የሕዝብና የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መገንባት አለመቻላቸው በተለያየ መልኩ ይገለጻል፡፡

ከሰሞኑ ‹‹መልካም አስተዳደር ለአፍሪካ›› የተሰኘው ድርጅት በኢትዮጵያ የሚገኘው የምሥራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮው ‹‹ተቋማዊ ልማት፣ አደረጃጀትና መልካም አስተዳደር በኢትዮጵያ›› በሚል የውይይት መድረክ አካሂዶ ነበር፡፡

በውይይቱ የመነሻ ጽሑፍ ካቀረቡት መካከል ባህሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር)፣ በሰጡት ሐሳብ፣ በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው ተቋማዊ ቁመና አለመኖርና ከዜሮ የመጀመር ፍልስፍና መቀየር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ አክለውም በኢትዮጵያ ተቋማት የተረጋጉ አለመሆናቸውን ጠቅሰው፣ ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዲንቀሳቀሱና ራሳቸውን ችለው መራመድ እንዲችሉ የበቁ እንዲሆኑ የቁጥጥር ሥርዓቱ መልክ ሊያስፈልገው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በተቋማት ውስጥ የሚስተዋለው ለፓርቲ ተዓማኒነት የሚሰጠው የበለጠ ቦታ፣ ተቋማት ከብቃታቸው ይልቅ ሰዎች ላይ እንዲንጠለጠሉና የተቋማቱ ስኬት እንዲያሽቆለቁል ያደርገዋል ብለዋል፡፡

የመልካም አስተዳደር ለምሥራቅ አፍሪካ ተቋም በኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ዘሪሁን መሐመድ (ዶ/ር)፣ በሰጡት አስተያየት፣ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ራሳቸውን ያልቻሉ መሆንና አቅማቸው በበቂ አለመገንባቱን፣ እንዲሁም በሰዎች ላይ የተንጠለጠሉ አገልግሎቱን ለሕዝብ ማቅረብ የተሳናቸው የፍትሕና የመልካም አስተዳድር ዕጦት መንስዔ የሆኑ፣ በሰው፣ በፋይናንስና በባለሙያ ያልተደራጁ ሆነዋል ብለዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሲቪል ሰርቪሱ ጥራት እየወረደ፣ ሠራተኞች በሚከፈላቸው የወርሐዊ ደመወዝ ማነስ ምክንያት የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት የተቸገሩ መሆን፣ የተቋማት ተለዋዋጭ ቁመና በተለይም ለተወሰነ ጊዜ ረግተው አለመቆየትና በየጊዜው የሚቀያየሩ ለየተቋማቱ የሚሾሙ አለቆች የተሾሙበትን መሥሪያ ቤት በውል ሳይረዱት መሾምና ከሥልጣን መውረድ የሚሉትን ማነቆዎች አንስተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ አስተዳደርና ልማት መምህሩ ብርሃኑ ተመስገን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ሁሉም የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተመሳሳይ መልኩ የወረደ ቁመና እንዳላቸው፣ በኢትዮጵያ ዕሳቤ ያልተደራጁ መሥሪያ ቤቶች፣ በተገቢ ጥናት ተመሥርተው ያልተዋቀሩና ያልተደራጁ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ብቃቱ የሌላቸው የተቋማት መሪዎች እንደሚስተዋሉ ጠቅሰው፣ ይህ መስተካከል ያለበት ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ ተቋም በብቁ ባለሙያ ከተደራጀና ከማንኛውም ዓይነት ጫና በፀዳ መልኩ እንዲሠራ ከተደረገ የሚጠበቅበትን ሚና በተገቢው መንገድ ማስተናገድ የሚችል በመሆኑ፣ ዕሳቤው በዚህ መንገድ መቃኘት አለበት ብለዋል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ የሚፈልጉ የውጭ ባለሀብቶች የሚፈልጉትን አገልግሎት አንዲያገኙ የሚረዱና የሚያግዙ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተሟላ መሠረተ ልማት ተደራጅተው ነፃና ገለልተኛ የሆነ አገልግሎት ሊሰጡ ይገባል ብለዋል፡፡

የሕግ ባለሙያውና ጠበቃው አቶ ደበበ ኃይለ ገብርኤል በበኩላቸው፣ በአገር ውስጥ ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲፀና የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዋልታ በመሆናቸው ተጠያቂነት፣ የአገልግሎት ጥራትና ከምንም ዓይነት የፖለቲካ ሥርዓት ጋር ያልተወዳጀ፣ የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነት ያለበት የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት መተግበር አስፈላጊነቱ አጠያያቂ ጉዳይ አይደለም ብለዋል፡፡

የኢትጵያ ባለሥልጣናት በቅርቡ በደቡብ ምሥራቅ አስያዋ ሲንጋፖር ተገኝተው የቀሰሙትን ልምድ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣትና ለመተግበር ፍላጎት እንዳለ ከባለሥልጣናቱ መስማታቸውን አቶ ደበበ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሴንጋፖር አሁን ለደረሰችበት ደረጃ በአገሪቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ተጠያቂነትን በማስፈን ዕርምጃ በመውሰድ ከሙስና የፀዳ የፖለቲካ ሥርዓትንና ሕዝብን በታማኝነት የሚያገለግሉ የመንግሥት ተቋማት ስለመገንባታቸው፣ በተቋማት ውስጥ ያሉ ሰዎች በሙያቸውና በክህሎታቸው የተመረጡ ስለመሆናቸው፣ የአገራቸውን ፖለቲካ ለራሳቸው በሚሆን መንገድ ቀይሰው መፍጠራቸውን ጠቅሰው፣ የሲንጋፖርን ልምድ በኢትዮጵያ ለመተግበር በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ እውን አመቺ ነው ወይ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ለአብነትም ኢትዮጵያ ያለችበት አጠቃላይ ሁኔታ አሳሳቢና ጭራ ተርታ ላይ ናት ያሉት አቶ ደበበ በመልካም አስተዳደር፣ በፖለቲካ ገበያ ላይ ባለው ውድድር፣ ከአድልኦ የፀዳ የመንግሥት አገልግሎት ከዓለም አገሮች ግርጌ ላይ በወረደ ደረጃ የምትገለጽ ስለመሆኗ ተናግረዋል፡፡

የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተሰጣቸው ነፃነትና ገለልተኝነት እንዲሁም ይህን ለማድረግ የሚያስችላቸው የሕግ ማዕቀፍ፣ የፋይናንስና የሥራ ቦታ ነፃነት ከሌላቸው ምንም ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡

የሕግ ባለሙያውና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች ተቋም ዋና ዳይሬክተር አቶ አምሃ መኮንን በበኩላቸው፣ ‹‹የተቋማት ቆሞ ቀር መሆን መሻሻልና መለወጥ ያለበት ጉዳይ ነው፤›› ይላሉ፡፡ አክለውም የተቋማትን ገለልተኝነትና ነፃ የሆነ ቁመና እንዲኖራቸው አድርጎ ሊመራ የሚችል ራሱን የቻለ፣ ዛሬን ነገንና ትናንትን አይቶ ተቋማት ምን መምሰል አለባቸው የሚለውን እያጠና የሚተግብር አካል አስፈላጊ ስለመሆኑ ያስረዳሉ፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት የፖለቲካ ሥርዓት ዘመናት በተለይም በደርግ፣ በኢሕአዴግ እንዲሁም አሁን አገሪቱን እያስተዳደረ ባለው ገዥው ብልጽግና ፓርቲ ጭምር፣ የመንግሥት ተቋማትን በተለያዩ ጊዜያት መከለስና ደጋግሞ መዋቅር መለዋወጥ እየተለመደ የመጣ ባህል ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ይህ የበዛ የተቋማት ቁመና መቀያየርና የተቋማት መሪዎች መለዋወጥ የአጭር ቆይታ ታሪክ ያላቸው ተቋማት እንዲኖሩ ከማድረጉም ባሻገር፣ ሕዝብ የሚፈልገውን አገልግሎት በተገቢው ሰዓትና ቦታ እንዲያቀርቡ አለማድረጉ በተደጋጋሚ የሚነሳ የሕዝብ ቅሬታ ነው፡፡

የተቋማት መጠናከር ቁመና መሻሻል ለአንድ አገር የመልካም አስተዳደር ጥያቄ መመለስ ከፍተኛውን ሚና ይይዛል ያሉት ዘሪሁን (ዶ/ር) የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሕዝቡ ሊያውቃቸውና በደስታ ሊገለገልባቸው የሚችሉ እንጂ የምሬት ምንጭ ሊሆኑ አይገባም ብለዋል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ራሳቸውን የቻሉ ከአድልዎ የፀዱ ገለልተኛና ነፃነት ባለው መንገድ ያለ ማንም ጫና ሕዝባዊ አገልግሎትን እንዲሰጡ አድርጎ ማዋቀርና ማደራጀት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...