Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናምርጫ ቦርድ የተሰረዘው ሕወሓት እንዲመዘገብ ሚኒስቴሩ ያቀረበውን የትብብር ጥያቄ ውሳኔ እንደሚሰጥበት አስታወቀ

ምርጫ ቦርድ የተሰረዘው ሕወሓት እንዲመዘገብ ሚኒስቴሩ ያቀረበውን የትብብር ጥያቄ ውሳኔ እንደሚሰጥበት አስታወቀ

ቀን:

ሕወሓት በሰላማዊ መንገድ ለመታገል መስማማቱን በመጥቀስ፣ በቅርቡ በፀደቀው ማሻሻያ አዋጅ መሠረት እንደገና እንዲመዘገብ የፍትሕ ሚኒስቴር ትብብር እንዲደረግለት ደብዳቤ የተጻፈለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ በጉዳዩ ላይ በቅርቡ ውሳኔውን እንደሚያስታውቅ ገለጸ፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር ሰሞኑን ለምርጫ ቦርድ በላከው ደብዳቤ ሕወሓት በሰላማዊ መንገድ ለመታገል መስማማቱን ጠቅሶ እንደገና እንዲመዘገብ መጠየቁ ይታወሳል፡፡ ምርጫ ቦርድ የፍትሕ ሚኒስቴር ደብዳቤ እንደደረሰው ለሪፖርተር ያረጋገጠ ሲሆን፣ በተጠየቀው መሠረት ማሻሻያ አዋጁን አገናዝቦ ውሳኔ ለማሳለፍ ቦርዱ በቅርቡ እንደሚሰበሰብ ገልጿል።

ምርጫ ቦርድ ከዚህ ቀደም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ በጠሩትና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ፣ የሕወሓት ሊቀመንበርና የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ስብሰባ፣ ሕወሓት መልሶ ሕጋዊ ሰውነት የሚያገኝበት የሕግ አግባብ እንደሌለ ማስረዳቱን ከቦርዱ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

ሆኖም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም. የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅን ለማሻሻል በቀረበ ረቂቅ ላይ ተውያይቶ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መምራቱና ምክር ቤቱም ግንቦት 27 ቀን 2016 ዓ.ም. በሁለት ተቃውሞ፣ በአንድ ድምፀ ተዓቅቦና በአብላጫ ድምፅ ማፅደቁ ይታወሳል።

ለአዋጁ መሻሻል አስፈላጊነት በተሰጠው ማብራሪያ የተገለጸው ቀድሞ፣ በነበረው አዋጅ ከሕጋዊና ከሰላማዊ እንቅስቃሴ ውጪ የቆዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ፍላጎት ሲያሳዩ፣ እነዚህን አካላት ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ አድርጎ ለመመዝገብ የሚያስችል ሥርዓት አለመካተቱ ነው፡፡

አዲስ በፀደቀው የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ መሠረት እነዚህ ፓርቲዎች በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ፍላጎት ሲያሳዩ መልሶ መመዝገብ ይቻላል፡፡

ምርጫ ቦርድ የተሻሻለውን አዋጅ አስመልክቶ ከዚህ ቀደም በሰጠው ማብራሪያ፣ አዋጁ ከፀደቀ በኋላ እንደደረሰውና ወደፊት ተግባራዊ ለማድረግ አሠራር እንደሚዘረጋ ገልጾ ነበር።

በፍትሕ ሚኒስትሩ ተፈርሞ ለቦርዱ በተላከው ደብዳቤ፣ ሕወሓት በሰላማዊ መንገድ ለመታገል መስማማቱን ጠቅሶ እንደገና እንዲመዘገብ ለቦርዱ ትብብር የጠየቀው ሕወሓት በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል በሰላም እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ ምክንያት ነው፡፡ ቦርዱ በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ አማካይነት መደበኛ ሥራውን እያከናወነ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የተሻሻለው አዋጅ ከሕጋዊና ከሰላማዊ እንቅስቃሴ ውጪ የቆዩና ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለመመለስ ፈልገው በሕጋዊ መንገድ የተመዘግቡ ፓርቲዎችን ምርጫ ቦርድ ለሁለት ዓመታት እንደሚከታተል ይደነግጋል፡፡ ይህን ተከትሎም በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል የቀረበው የሕወሓት እንደገና ምዝገባ ጥያቄ፣ በቦርዱ ውሳኔ ከተሰጠው በኋላ፣ አዋጁን ለማስፈጸም ተግባራዊ በሚደረገው አሠራር መሠረት ተግባራዊ እንደሚያደርግ ቦርዱ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...