Tuesday, July 23, 2024

[ክቡር ሚኒስትሩ በቢሯቸው ሆነው ከአማካሪያቸው ጋር ስለወቅታዊ ጉዳዮች እየተነጋገሩ ነው]

 • ትናንት የሆነውን ሰሙ ክቡር ሚኒስትር?
 • አልሰማሁም፣ ምን ሆነ? 
 • ኬንያውያን የአገሪቱን ፓርላማ ጥሰው መግባታቸውን አልሰሙም?
 • ኧረ አልሰማሁም። 
 • የፓርላማውን በር ጥሰው ገብተው አንደኛውን ክፍል በእሳት አያያዙት፡፡ 
 • ምንድነው ምክንያቱ? 
 • የአገሪቱ መንግሥት ያቀረበው አዲስ የታክስ ሕግ እንዳይፀድቅ ነው።
 • ለምን?
 • አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት አልቻልነውም፣ በዚህ ችግር ውስጥ ሆነን የኑሮ ውድነቱን የሚያባብስ አዲስ ታክስ መጣል የለበትም ብለው ነው አሉ።
 • እና ፓርላማው ምን አደረገ?
 • መደበቅ ነዋ ሌላ ምን ማድረግ ይችላል?
 • ለምንድነው የሚደበቀው?
 • ተቃዋሚዎች በሩን ጥሰው በመግባት አንዱን ክፍል በእሳት አያያዙት እያልኩዎት እኮ?
 • ፓርላማውን?
 • አዎ፣ በዚህ ምክንያት ጥቃት እንዳይደርስባቸው የፈሩ የፓርላማ አባላት እየተሯሯጡ ሲደበቁ በአገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ታይተዋል።
 • የአገሪቱ ፓርላማ በዚህ ደረጃ ሲደፈር የፀጥታ አካላቱ ምንም አላደረጉም?
 • ከአቅማቸው በላይ ብዙ ሕዝብ ነበር የወጣው ቢሆንም…
 • ቢሆንም ምን?
 • ጥይት ተኩሰው የተወሰኑትን ገድለዋል የተወሰኑትንም አቁስለዋል።
 • የነውጠኛ ምሱ ይኼ ነው፣ ይበላቸው፡፡ 
 • ግን ክቡር ሚኒስትር …
 • ግን ምን?
 • እኛስ በኬንያ ከታየው መማርና መጠንቀቅ ያለብን አይመስልዎትም። 
 • የኬንያ ጉዳይ ከእኛ ጋር ምን አገናኘው?
 • እዚህም እኮ የኑሮ ወድነት አለ ክቡር ሚኒስትር።
 • ቢኖርም የእኛ የተጋነነ አይደለም። 
 • የእኛ ማኅበረሰብ ጨዋ ስለሆነ እንጂ በኑሮ ውድነቱማ ተጎድቷል። 
 • እንዴት?
 • ምን እንዴት አለው ክቡር ሚኒስትር? ሰሞኑን በእኛ ፓርላማ የተነገረውን አልሰሙም?
 • ምን ተባለ?
 • ሠራተኛው የቤት ኪራይ መክፈል አቅቶት ቢሮ እያደረ ነው መባሉን አልሰሙም።
 • ሰምቻለሁ ግን እሱም ቢሆን የተጋነነ ነው።
 • ግን ይህን የተናገሩት እኛው መዋቅር ውስጥ የሚገኙ የመንግሥት ኃላፊዎች ናቸው። 
 • ገብቶኛል።
 • እና?
 • አናልፋቸውም።
 • አናልፋቸውም ማለት?
 • ጀርባቸው ተጠንቶ የዲሲፕሊን ዕርምጃ መወሰዱ አይቀርም፡፡
 • እነ ማን ላይ?
 • ይህንን የተናገሩት ባለሥልጣናት፡፡ 
 • እነሱ ላይ ዕርምጃ ቢወሰድ እውነታውን ይቀይረዋል ብለው ያምናሉ?
 • የቱን እውነታ?
 • ማኅበረሰቡ በኑሮ ውድነት የመቸገሩን እውነታ ማለቴ ነው፣ በዚያ ላይ…
 • በዚያ ላይ ምን?
 • መንግሥት ምልክቶችን አይቶ የመፍትሔ ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ተቃራኒውን ነገር ነው እያደረገ ያለው።
 • ተቃራኒ ነገር ምን አደረገ?
 • ማኅበረሰቡ በኑሮ ውድነት ተቸግሯል፣ ሠራተኛው ቢሮ እያደረ ነው እየተባለ ሰሞኑን ለፓርላማ የቀረቡት አዋጆችን ማለቴ ነው።
 • ምን ቀረበ?
 • በመብራትና በውኃ ፍጆታ ላይ ቫት የሚጥለው አዋጅ አንደኛው ነው።
 • እሺ?
 • የንብረት ታክስ አዋጅ ሌላው ነው።
 • እሺ፣ ሌላስ አለ?
 • የንብረት ማስመለስ አዋጁም በማኅበረሰቡ ላይ ሥጋት ፈጥሯል። 
 • እሺ? 

 

 • በኑሮ ውድነት ለተቸገረው ሠራተኛ የደመወዝ ማሻሻያ በጀት ሳይያዝ ለአረንጓዴ ልማት በጀት ለመያዝ መታቀዱም ጉርምሩምታ ፈጥሯል።
 • ለምን?
 • በመጀመሪያ ለሰውና ለማኅበረሰብ ችግር ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል በሚል ነው።
 • አረንጓዴ ልማት የምናካሂደው እኮ ለማኅበረሰቡ ብለን ነው።
 • ይገባኛል፣ ነገር ግን ሠራተኛው ተቸግሮ ሳለ ለአረንጓዴ ልማት ቅድሚያ መስጠት ሚዛኑን የጠበቀ አይደለም እየተባለ ነው።
 • እንዴት?
 • እንዲያውም ፌዝ አዘል ቅሬታ እየቀረበበት ነው።
 • ምን የሚል?
 • ለአረንጓዴ ልማት ቅድሚያ የተሰጠው ተቸግሮ ቢሮ የሚያድረው ሠራተኛ እንትን ሥር እንዲያድር ነው እየተባለ ነው።
 • ምን ሥር?
 • ዛፍ ሥር።
 • ማነው ያለው? አንተ ነህ?
 • ኧረ እኔ አይለሁም ክቡር ሚኒስትር።
 • እና ማን ነው ያለው?
 • በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚባለውን ነው የነገርኩዎት።
 • ለማንኛውም ይጣራል።
 • ምኑ ክቡር ሚኒስትር?
 • ጀርባህ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ትርፍ ቢያገኝም የውጭ ምንዛሪ ገቢው ቅናሽ ማሳየቱ ተጠቆመ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የውጭ ምንዛሪ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ የቅርብ ወዳጃቸው ከሆነች አንድ ባለሀብት የተደወለላቸውን ስልክ አንስተው በኮሪደር ልማቱ ላይ የምታቀርበውን ቅሬታ እየሰሙ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እኔ የኮሪደር ልማቱ ላይ ተቃውሞም ሆነ ጥላቻ እንደሌለኝ የሚያውቁ ይመስለኛል? በዚህ እንኳን አትታሚም።  የእውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር። አውቃለሁ ስልሽ? ለኮሪደር ልማቱ አዋጡ ሲባልም ያለማመንታት አምስት ሚሊዮን...

[ክቡር ሚኒስትሩ በችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ ሳይገኝ ከቀረው አንድ የተቋማቸው ባልደረባ የሆነ የተቃዋሚ ፓርቲ አባልን አስጠርተው እያናገሩ ነው]

ለምንድነው በዚህ አገራዊ ፋይዳ ባለው ፕሮግራም ላይ ያልተገኘኸው? ክቡር ሚኒስትር ህሊናዬ አልፈቀደልኝም። መቃወምና መተቸት ብቻ ውጤት የሚያመጣ መስልዎህ ከሆነ ተሳስተሃል። አልተሳሳትኩም ክቡር ሚኒስትር? ቆይ የመጀመሪያ ዓመት የችግኝ ተከላ...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላነጋግርህ የፈለኩት ክቡር ሚኒስትር፡፡ እርስዎማ ቀጠሮ መያዝ አያስፈልግዎትም፣ ምን ገጠመዎት? እኔማ ምን ይገጥመኛል አንተኑ ልጠይቅህ እንጂ? ምን? እውነት ለመናገር የማየው ነገር አሳስቦኛል፡፡ ይንገሩኝ...