Monday, July 22, 2024

ቀዝቃዛው ቀሪና ድጋሚ ምርጫ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኢትዮጵያ በሕገ መንግሥቱ መሠረት አገራዊ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ ማካሄድ የነበረባት ቢሆንም፣ ምርጫው በ2012 ዓ.ም. ድንገት ከአንድ የዓለም ጥግ ተነስቶ መላ ዓለምን ባዳረሰው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ ዓመት ተራዝሞ በ2013 ዓ.ም. ለማካሄድ መገደዷ ይታወሳል።

የ2013 ዓ.ም. አገራዊና ክልላዊ ምርጫ በአብዛኞቹ አካባቢዎች ዕውን ቢሆንም የፀጥታ ሥጋት ውጥረት ተፍንጎ ይዟቸው በነበሩት እንደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባሉ አካባቢዎች የተደረገው ምርጫ ግን ዜጎች በፀጥታ ችግር ሳቢያ ምርጫ ጣቢያ በካርዳቸው ዕጣ ፈንታቸውን መወሰን እንዳይችሉ ከጣለባቸው ዕቀባ ባሻገር፣ ምርጫው በተደረገባቸው ውስን አካባቢዎች የተሰበሰበው ድምፅም ክልላዊ መንግሥት መመሥረት የማያስችል ነበር።

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ኦፕሬሽን ምክትል ኃላፊ አቶ ብሩክ ወንድወሰን ቦርዱ ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. የሚያደርገውን የስድስተኛው ዙር ቀሪና ድጋሚ ምርጫን በተመለከተ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በተነጋገሩበት ወቅት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለክልል ምክር ቤቶች በአራት ክልሎች የተደረገው ምርጫ በየክልሎቹ ሁኔታው እንደሚለያይ፣ አንዳንዶቹ ዘንድ ምርጫው ከዚህ ቀደም ተከናውኖ ነገር ግን የታዩ ችግሮች በመኖራቸው በድጋሚ እንደሚካሄድና በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ሳይካሄድ የቆየ ቀሪ ምርጫ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ብሩክ ማብራሪያ በአራት ክልሎች የተደረገው ምርጫ ከመንግሥት 320 ሚሊዮን ብር በጀት ተጠይቆ በተፈቀደው 240 ሚሊዮን ብር የተከናወነ ነው።

የድጋሚና የቀሪ ምርጫዎቹ በአጠቃላይ በ29 የምርጫ ክልሎች፣ በ1,258 ምርጫ ጣቢያዎች ከ12 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጡ 380 ዕጩዎች እንደሚሳተፉበትም የኃላፊው ገለጻ ያስረዳል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በአንድ የምርጫ ክልል ማለትም በመስቃንና ማረቆ የተካሄደው ምርጫ ለሦስተኛ ጊዜ የተካሄደ ነው። በ169 የምርጫ ጣቢያዎች የተወካዮችና የክልል ምክር ቤት ምርጫዎች ተደርገዋል።

በአፋር ክልል ዘጠኝ የምርጫ ክልሎች 388 የምርጫ ጣቢያዎች ሲገኙ፣ በሁሉም የምርጫ ክልሎች ለክልል ምክር ቤት ምርጫ ሲደረግ በሁለቱ ብቻ የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ተካሂዷል።

በሶማሌ ክልል በአንድ የምርጫ ክልል ማለትም በጅግጅጋ ከተማ ብቻ በ123 የምርጫ ጣቢያዎች ለክልል ምክር ቤት የሚሆን ብቻ ምርጫ ሲደረግ፣ ይህም ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ጋር በተመሳሳይ ለሦስተኛ ጊዜ የተደገመ ነው።

በስድስተኛው ዙር አገራዊ ምርጫ ላይ በጥቂት ምርጫ ክልሎች ብቻ ምርጫ የተከናወነበት ነገር ግን ቁጥሩ አነስተኛ በመሆኑ፣ መንግሥት ያልተመሠረተበት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተደረገው ምርጫ ከሌሎቹ በተለየ ሰፋ ያለ ነበር።

በ2013 ዓ.ም. ምርጫ በአገሪቱ ክልሎች ውስጥ በአብዛኛው አካባቢዎች ምርጫ ስለተከናወነ የክልል መንግሥታት መዋቀራቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ በቤኒሻንጉል ክልል ግን ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ማለትም በ2007 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ የተቋቋመ እንጂ፣ ከዚያ በኋላ እስካሁን ድረስ በምርጫ የተመረጠ መንግሥት የለም፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ2013 ዓ.ም. በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ በፀጥታ ችግር ምክንያት ምርጫ ካልተካሄደባቸው ዞኖች በተጨማሪ፣ በአሶሳ ዞን በድምፅ ሰጪ እጥረትና በኮድ ስህተት ምክንያቶች የምርጫው ሒደት መቋረጡ ይታወሳሉ።

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ኦፕሬሽን ምክትል ኃላፊው አቶ ብሩክ ባለፈው ሳምንት ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፣ ምርጫ ቦርድ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የእያንዳንዱን ምርጫ ጣቢያ አካባቢ የፀጥታና የደኅንነት ሁኔታ የዳሰሳ ጥናት ማከናወኑን ገልጸዋል።

የፀጥታ ዳሰሳ ጥናቱ በሁሉም ምርጫ በሚደረግባቸው ክልሎች በቦርዱ የመረጃ ግብዓት ሊሰጡ፣ የፀጥታውን ሁኔታ ሊያስረዱ የሚችሉ ተብለው ከተለዩ የየአካባቢው ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የተፈናቀሉ ሰዎች፣ የአስተዳደርና የፀጥታ አካላት ጋር ቃለ ምልልስ በማድረግ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ከስምምነት እየደረሱ በየቀበሌው ተጠንቶ የተጠናከረ መረጃ እንዳለም ተናግረዋል። በዚህ ጥናት መሠረት ምርጫ ቦርድ የምርጫ አካባቢዎችን የፀጥታ ሁኔታን በሦስት ፍረጃ ለይቶ ማስቀመጡ ታውቋል።

ተቀዳሚው ‹‹አረንጓዴ›› ሲሆን ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር የሌለበትና ምርጫ ለማከናወን ምቹ ሁኔታ ያለበት የተባለው አካባቢ ነው። በሁለተኝነት የሠፈረው ‹‹ቢጫ›› ደግሞ የፀጥታ ሥጋት አለበት፣ ወጣ ገባ የሚል የፀጥታ ችግር አለ በሚል ተፈርጆ የፀጥታ ኃይሉ ተጠናክሮ ምርጫው የሚካሄድበት ተብሎ የተለየ ሲሆን፣ በእነዚህ አካባቢዎች የፀጥታ ኃይሎች እጀባ የሚያስፈልግበት እንደሆነም ተጠቅሷል። በሌላ በኩል ‹‹በቀይ›› የተፈረጁ አካባቢዎች ምርጫ ለማከናወን አስቻይ የፀጥታ ሁኔታ የለበትም በሚል የተለየና ምርጫም ያልተከናወነበት ነው።

አቶ ብሩክ፣ ‹‹በምዝገባው ሒደት በቀይ ተፈርጀው የነበሩ አካባቢዎች ነበሩ። በሒደት ግን የፀጥታው ሁኔታ ተለዋዋጭ እንደ መሆኑ አንዳንዴ በፊት በጥናት ሒደት ላይ እያለን አረንጓዴ ያልነው ወደ ቀይ የሚቀየርበት፣ ቀይ ተብለው የነበሩ ሰላማዊ ሁኔታዎች የተፈጠሩባቸው ቦታዎች አሉ። በእንዲህ ዓይነት ሒደቶች አልፈን መጨረሻ ላይ 40 አካባቢዎች በቀይ ስለተፈረጁ ምርጫ የማናካሂድባቸው ቦታዎች ናቸው፤›› ብለዋል።

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ ቅዳሜ ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ዞን በመተከል ክልል አራት ወረዳዎች የሚገኙ 40 የምርጫ ጣቢያዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት ድምፅ የማይሰጥባቸው እንደሆኑ አሳውቀዋል።

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ወቅት ምንም ዓይነት የመራጮች ምዝገባ ካልተካሄደባቸው፣ የክልሉ አካባቢዎች አንዱ የመተከል ዞን እንደነበር ይታወሳል።

የስድስተኛው ዙር ቀሪና ድጋሚ ምርጫ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዋና ከተማ አሶሳን ጨምሮ በመተከል አብዛኛው ወረዳዎችና በካማሺ ዞንም እሑድ ሰኔ 16 እና ሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ተካሂዶ ነበር።

ሪፖርተር ተዘዋውሮ በተመለከታቸው በአሶሳ ከተማ ውስጥ ከተዘጋጁ የድምፅ ጣቢያዎች መሀል በሰባት ጣቢያዎች ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ የድምፅ አሰጣጥ የተከናወነ ሲሆን፣ ሒደቱ እስከ ምሽት ሁለት ሰዓት ድረስ እንዲቀጥል በምርጫ ቦርድ የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎም ጣቢያዎቹ በሮቻቸውን ለመራጭ ሕዝብ ክፍት አድርገው ቆይተዋል።

የድምፅ መስጫ ሰዓት መጠናቀቁን ተከትሎም የዕጩ አቅራቢ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች በታዛቢነት በተገኙበት የተደረጉ የምርጫ ድምፅ ቆጠራዎችን፣ ሪፖርተር በአራት የተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. እሑድ ዕለት ንጋት በሰማያዊና ነጭ የቀለሙ የፕላስቲክ ሸራዎች በቀጫጭን የእንጨት ማገሮች ተወጥረው፣ በየደጃፎቻቸው ላይ በነጭ ጨርቅ ላይ በጥቁር ቀለም የምርጫ ቦርድ ስምና ዓርማ የሠፈረባቸው ምልክቶችን በመራጮች መግቢያ ደጃፎች ላይ ተሰቅለው፣ የድምፅ መስጠት ሒደቱ በፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ፊት ለፊት በምርጫ አስፈጻሚዎች ለድምፅ መስጠት የሚያገለገሉ ግብዓቶች ተከፍተው ሥራ ሲጀምሩ ሪፖርተር የተገኘበት የምርጫ ጣቢያ ደጃፍ ባዶውን ያለ መራጮች ሠልፍ ነበር።

‹‹አሶሳ ሆሀ›› በተባለ የምርጫ ክልል ወረዳ ሁለት ቀበሌ 04 ውስጥ የሚገኘው ይህ ‹‹አሶሳ 04 ሀ2›› የሚል መጠሪያ ያለው የምርጫ ጣቢያ ዋና ምርጫ አስፈጻሚ፣ በጣቢያው ውስጥ ድምፅ ለመስጠት በ2013 ዓ.ም. ተመዝግበው የስም ዝርዝራቸው የሚገኝበት መዝገብ በቦርዱ ተጠብቆ ለአሁኑም የድጋሚ ምርጫ አገልግሎት ላይ የዋለ መራጮች ከእነዚህም ምን ያህሉ ለዚህ የድጋሚ ምርጫ ካርድ እንደወሰዱ፣ ምን ያህሉም መታወቂያቸውን ይዘው በመገኘት ከመዝገቡ ስማቸውን በማመሳከር ማንነታቸውን በማረጋገጥ መምረጥ እንደሚችሉ ሪፖርተር ለማሳወቅ ጥያቄ ቢያቀርብም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

የምርጫ ቦርድ የመገናኛ ብዙኃንና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ የሥነ ምግባርና አሠራር መመርያ ቁጥር 02/2013 ምዕራፍ ሦስት የመገናኛ ብዙኃንና የጋዜጠኞች መብቶች ግዴታዎችና ኃላፊነቶች ሥር አንቀጽ 14 የምርጫ ሒደትን ለመዘገብ ፈቃድ የተሰጠው ጋዜጠኛ መብት ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ በተደነገገው መሠረት፣ ማንኛውም ምርጫን ለመከታተል ፈቃድ የተሰጣቸው የመገናኛ ብዙኃን ወይም ጋዜጠኞች ማንኛውንም የምርጫ ሒደት ማለትም የመራጮች ምዝገባን፣ የዕጩ ምዝገባን፣ የምርጫ ቅስቀሳን፣ የድምፅ አሰጣጥን፣ የቆጠራ ሒደትንና የውጤት አገላለጽን የመከታተልና የመዘገብ መብት እንዳለው ይጠቅሳል።

የ‹‹አሶሳ 04 ሀ2›› የምርጫ ጣቢያ ዋና ምርጫ አስፈጻሚን የሚዲያ አካላት ቢያሳውቋቸውም፣ ‹‹ከቦርዱ በተላከ አጭር የሞባይል ስልክ መልዕክት መሠረት ጋዜጠኞችን ማነጋገር አልችልም፤›› የሚል ምላሽ በመስጠት የመራጮችን አጠቃላይ ቁጥር ከማሳወቅ ተቆጥበዋል።

ጥቂት ኪሎ ሜትሮችን ርቆ በከተማዋ ዋና የገበያ አካባቢ የሚገኘው የምርጫ ጣቢያ ጠዋት 12:00 ሰዓት ላይ ሥራውን በሚጀምርበት ወቅት መራጮች ቀድመው በሥፍራው ተገኝተው ተሠልፈው ታይተዋል።   

‹‹አሶሳ 03 03 ሀ2›› በተባለው በዚህ የምርጫ ጣቢያ ዋና የምርጫ አስፈጻሚ እንደገለጹት፣ በምርጫ ጣቢያው 1,500 የተመዘገቡ መራጮች ሲኖሩ ሁሉም ካርድ የወሰዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በምርጫ ጣቢያው የመጀመሪያ መራጮች ከነበሩት መካከል አቶ ቱሊና ቶሊ፣ ‹‹ምርጫው ጥሩ ነው፣ በነፃነት ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት መርጫለሁ። ነገር ግን እኛ 12 ሰዓት ላይ ነበር ጣቢያው የተገኘነው፡፡ እነሱ ግን አንድ ሰዓት ዘግይተው ነው ሥራ የጀመሩት፤›› ብለዋል።

አቶ ደበላ በቀለ የተባሉ ሌላ መራጭ በበኩላቸው፣ ‹‹ምርጫ ለእኔ አዲስ አይደለም። ልማትና ሰላም ያመጣልኛል ያልኩትን መርጫለሁ። ሒደቱ ግን ከሌሎች ምርጫዎች ጋር ሲነፃፀር ምንም ልዩነት አላየሁበትም፤›› ሲሉ ተናግረዋል።

ሪፖርተር በተመለከታቸው ምርጫ ጣቢያዎች ከዚህ ጣቢያ በስተቀር ሌሎች ስድስት ጣቢያዎች የመራጮች ሠልፍ ከአሥር ሰው ያልዘለለና በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች የሚታዩበት ነበር።

በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ሥራ አስፈጻሚዎች የድምፅ መሰጠት ሒደቱ መጀመሪያ ላይ የምርጫ ቦርድ ያቀረበውን የምርጫ ሰሌዳ ማሳያ በመጠቀም ለመራጮች ለክልል ምክር ቤቶች እስከ ስድስት ዕጩዎችን መምረጥ እንደሚችሉ፣ ለክልል ምክር ቤት ደግሞ ሁለት ዕጩዎችን መምረጥ እንደሚኖርባቸው ከተጠቀሰው በላይ ከመረጡ ግን ድምፃቸው እንደማይቆጠር ሲያስተምሩ ታይተዋል።

በሌላ በኩል በሌሎች ጣቢያዎች ደግሞ የምርጫ ካርዱን የቦርዱን ማኅተም በማድረግ ለመራጮች የሚያቀብለው ሥራ አስፈጻሚ፣ ለእያንዳንዱ መራጭ መከተል ያለባቸውን ይህን መመርያ ሲያስተላልፉ ሪፖርተር ተመልክቷል።

ረፋድ ሦስትና አራት ሰዓት ላይ በጣት የሚቆጠሩ መራጮች ከጣቢያቸው ደጃፍ ላይ ከታዩባቸው ጣቢያዎች መካከል፣ ‹‹አሶሳ 03 03 ለ2›› የተሰኘ የምርጫ ጣቢያና በነዋሪዎች የዓረብ ሠፈር በሚል ስያሜ በሚጠራው አካባቢ ከሚገኙት ጣቢያዎች አንዱ በሆነው በምርጫ ቦርድ ‹‹አሶሳ 02 ሀ1ኤ›› የሚል መጠሪያ የተሰጠው የምርጫ ጣቢያ ይገኝበታል።

ከእነዚህ ምርጫ ጣቢያዎች የተቀዳሚው ዋና ምርጫ ሥራ አስፈጻሚ እንደገለጹት፣ በ2013 ዓ.ም. የተመዘገቡና በድጋሚ ምርጫው ተሳታፊ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት ስማቸው በመዝገብ የሰፈረ መራጮች 822 ሲሆኑ ከእነዚህ የምርጫ ካርድ የተቀበሉት ደግሞ 253 ብቻ ናቸው።

በሌላ በኩል የሁለተኛው ምርጫ ጣቢያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ 994 መራጭ ተመዝጋቢዎች መኖራቸውን፣ ካርድ ያለቸው መራጮች ምን ያህል እንደሆኑ ግን ‹‹ምርጫው ሲጠናቀቅ የሚታወቅ ይሆናል፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የመራጭ ተመዝጋቢዎች ቁጥር ከፍ ቢልም ካርድ የተቀበሉ መራጮች ቁጥር በሌሎችም የምርጫ ጣቢያዎች የተስተዋለ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በተለምዶ ጫት ተራ በሚል ስያሜ በሚጠራ አካባቢ የሚገኝ አሶሳ 02 (1) በተባለ የምርጫ ጣቢያ 1,500 መራጮች በ2013 ዓ.ም. የተመዘገቡ ቢሆንም ለድጋሚ ምርጫው ካርድ የተቀበሉት 260 ሰዎች ብቻ መሆናቸው ተገልጿል።

‹‹አሶሳ 03 03 ለ2” ምርጫ ጣቢያ ወደ 15 የሚጠጉ መራጮች ተሠልፈው ሲጠባበቁ ሪፖርተር የተመለከተ ሲሆን፣ እንደ የምርጫ ሥራ አስፈጻሚዎቹ ገለጻ ከሚመጡት መራጮች አብዛኞቹ መራጮች የነዋሪነት መታወቂያ ይዘው ስማቸውን ከመዝገብ አስፈልገው ድምፅ ለመስጠት የተገኙ በመሆናቸው የማጣራት ሒደቱ የሚወስደው ሰፊ ጊዜ መጨናነቅ መፍጠሩን አስረድተዋል።

ከዚህ ምርጫ ጣቢያ በተቃራኒው የተቀዛቀዘ የመራጮች ብዛት በነበረበት ‹‹አሶሳ 02 ሀ1ኤ›› የምርጫ ጣቢያ ያለ ካርድ ድምፅ ለመስጠት የተገኙት መምህር ገመቺስ አብዲሳ፣ ‹‹ሊሰጡኝም ላይሰጡኝም ይችላሉ ብዬ እየተጠራጠርኩ ነበር የመጣሁት። እንደጠበኩት ሳይሆን ከመዝገቡ ስሜን አይተው ማንነቴን በመታወቂያዬ አረጋግጠው ድምፅ መስጠት ችያለሁ፤›› ብለዋል።

በአሶሳ ቀበሌ 01 ወረዳ ሁለት በሚገኝ የምርጫ ጣቢያ በ2013 ዓ.ም. ድምፅ መስጠታቸውን የገለጹት አቶ አብዱርቃድር ሹሮሙ ጀደማ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው፣ ‹‹ድምፄን እንዳልሰጥ ተደርጌያለሁ፤›› ይላሉ።

አቶ አብዱርቃድር፣ ‹‹በ2013 ዓ.ም. መርጬያለሁ። አሁን ቀበሌ የመራጭ ስም ዝርዝር ሲለጠፍ ስሜ የሰፈረበትን ቁጥር ተመልክቻለሁ። ግን ዛሬ ድምፅ ለመስጠት ወደ ምርጫ ጣቢያው ሁለት ጊዜ ብሄድም፣ ሁለት ጊዜም ስሜ በተራ ቁጥሩም ሆነ በአጠቃላይ በመዝገቡ ላይ ስላልተገኘ ድምፅ መስጠት ሳልችል ቀርቻለሁ፤›› ሲሉ ተናግረዋል።

ሪፖርተር ተዘዋውሮ በተመለከታቸው በአሶሳ ከተማ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች የብልፅግና፣ የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ)፣ የቤንሻንጉል ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ (ቤህነን)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካይ ታዛቢዎችን የተመለከተ ሲሆን፣ ከሰባት የምርጫ ጣቢያዎች በሁለቱ ብቻ ከሴቶች ፌዴሬሽን የተወከሉ ታዛቢዎችን አነጋግሯል።

ገለልተኛ ታዛቢዎች በሌሉበት አንድ የምርጫ ጣቢያ ጉዳዮን አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበላቸው የምርጫ አስፈጻሚ ገለልተኛ ታዛቢዎች አለመኖራቸውን አረጋግጠው፣ ምክንያቱን ግን እንደማያውቁ ተናግረዋል።

በሌላ የምርጫ ጣቢያ ከሴቶች ፌዴሬሽን የተወከሉ ወ/ሪት ዘምዘም ኢድሪስ የተባሉ ታዛቢ ምርጫው ገለልተኛና ነፃ መሆኑን መታዘባቸውን ሲገልጹ፣ ነገር ግን በተገኙበት ጣቢያ የምርጫ ሥራ አስፈጻሚዎች አምስት ቢሆንም አንድ ሴት ብቻ መኖሯን ከታዛቢዎች፣ እንዲሁም እሳቸው ብቻ ከሴት መወከላቸውን፣ በተጨማሪም በመራጮች ደረጃም የሴቶች አስተዋፅኦ የተቀዛቀዘ መሆኑን ገልጸዋል።

ከቤህነን ፖለቲካ ፓርቲ የተወከሉ በሌላኛው የከተማው ጫፍ በሚገኝ ምርጫ ጣቢያ ታዛቢ የነበሩ የኋላ በሲሶ የተባሉ ታዛቢ በበኩላቸው፣ ‹‹የምርጫ ካርድ የወሰደ ምን ያህል ነው? በመታወቂያ የሚመርጠውስ ምን ያህል ነው? በሚል የመራጮች መጠን ጋር ተያይዞ ምልልሶች ነበሩ። የጣቢያው ምርጫ አስፈጻሚ የመራጭ ቁጥር መጠን ካርድ በያዘና ባልያዘ መጠን ልዩነት ሳይሆን፣ ዋናው ድምፅ የሰጠው መራጭና በኮሮጆችው የገባው ድምፅ መመጣጠን መሆኑንና እሱን ደግሞ በቆጠራ ወቅት ማረጋገጥ ይቻላል በሚል ተስማምተን አልፈናል ብለዋል።

በሌሎች ሁለት ጣቢያዎች ሪፖርተር ያነጋገራቸው የቤህነንና የቦዴፓ ፓርቲ ተወካይ ታዛቢዎች ደግሞ ታዛቢ ለመሆን መመረጣቸውን ያወቁትና ማንነታቸውን የሚገልጽ የታዛቢነት መታወቂያ ከምርጫ ቦርድ የተቀበሉት ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. ቅዳሜ ዕለት ምሽት መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም ምክንያት የተመደቡበትን የምርጫ ጣቢያ በሰዓቱ ለማግኘትና በሥፍራው ተገኝተው ለመታዘብ አለመቻላቸውንና አርፍደው መድረሳቸውን ገልጸዋል።

እሑድ ዕለት የተደረገው ምርጫ ምሽት 12 ሰዓት ላይ መጠናቀቅና ወደ ቆጠራ መገባት የነበረበት ቢሆንም፣ አመሻሻ ላይ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው ማሳወቂያ መሠረት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ድምፅ የመስጠት ሒደቱ ዘግይቶ በጀመረባቸው ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ድምፅ የመስጠት ሒደቱ እስከ ምሽቱ 2:00 ሰዓት እንዲቀጥል ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት የድምፅ መስጠት ሒደቱ ሰዓቱ ተራዝሞ ተካሂዷል።

የድምፅ ቆጠራ ሒደቱ ሪፖርተር ተዘዋውሮ በተመለከተባቸው ጣቢያዎች በታዛቢዎችና በምርጫ አስፈጻሚዎች መካከል በአብዛኛው በስምምነት የተካሄደ ሲሆን፣ የሰዓቱን መራዘም የተቃወሙና ‹‹በሰዓቱ በመጀመራችን በሰዓቱ መዘጋት›› አለበት የሚል ተቃውሞዎችን ያሰሙ ታዛቢዎችንም ተመልክቷል።

መሰል ተቃውሞ ከታየባቸው ጣቢያዎች አንዱ ለመገናኛ ብዙኃን አስቀድሞ የመራጮችን ቁጥር ለማሳወቅ ፈቃደኛ ያልሆነው ‹‹አሶሳ 04 ሀ2›› የሚል መጠሪያ ያለው የምርጫ ጣቢያ ነው።

የድምፅ መስጠት ሒደቱ ምሽት ሁለት ሰዓት መጠናቀቁን ተከትሎ ታዛቢዎች በተገኙበት የድምፅ ቆጠራ ሒደቱ በተደረገበት ወቅት ዋጋ አልባ የሆኑ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ማለትም የምርጫ ቦርድ ማኅተም ያልተመታበት ድምፅ መስጫ፣ ከተፈቀደው ዕጩ በላይ የተመረጠበት ድምፅ መስጫ፣ በድምፅ መስጫው ላይ በመረጡት ዕጩ አጠገብ የኤክስ ወይም ራይት ምልክት በማኖር ፋንታ የተፈረመበት የድምፅ መስጫ ተቆጥሮ በተለየበት ወቅት ታዛቢዎች፣ ‹‹በትክክልም የድምፅ መስጫ ወረቀቶቹ ዋጋ አልባ የሚያደርግ ነገሮች እንደተገኘባቸው በቅርበት እንድንመለከት ሊፈቀድልን ይገባል፣ ካለንበት ቦታ ያንን ማረጋገጥ አንችልም። ካላረጋገጥን ደግሞ ትክክል ነው ብለን ለመፈረም እንቸገራለን፤›› የሚል ጥያቄ ሲያነሱ ነበር፡፡

የምርጫ አስፈጻሚው፣ ‹‹እኛ ሆን ብለን አንዱን ለመደገፍ አንዱን ለመርዳት የምንሠራው የለም፤›› የሚል ምላሽ ቢሰጡም ታዛቢዎቹ በበኩላቸው፣ ‹‹እኛም በዓይናችን ካላየን ተማምነን አንፈርምም፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ይህንን ተከትሎ የምርጫ አስፈጻሚው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኦፕሬሽን ክፍል ሠራተኛና የአሶሳ ሆሀ እና የአሶሳ መገሌ ምርጫ ክልሎች አስተባባሪ ወ/ሪት ሃያት መሐመድ፣ በስልክ ፈቃድ በመቀበል ታዛቢዎቹ ቀርበው እንዲመለከቱና እንዲያረጋግጡ አድርገዋል።  ከዚያም በኋላ ቀሪው የድምፅ ቆጠራ ሒደት ያለ ተጨማሪ ውዝግቦች መካሄዱን ሪፖርተር ተመልክቷል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ዳንጉር ምርጫ ጣቢያ ከነበሩ 33 ጣቢያዎች መካከል በሁለቱ የምርጫ ጣቢያዎች በቁሳቁስ መዘግየት ሳቢያ ለሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. መተላለፉን፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላተወርቅ እሑድ ምሽት ሰኔ 16 ቀን ያሳወቁ ሲሆን ምርጫው በተባለው ቀን መካሄዱን ሪፖርተር ከምንጮቹ መረዳት ችሏል።

በአሶሳ ከተማ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ጠዋት ከረፋዱ 3 ሰዓት ጀምሮ በየምርጫ ጣቢያው አካባቢ የምርጫ የውጤት ማመሳከሪያና ማሳወቂያ ፎርም፣ የክልል ምክር ቤትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየዘርፉ ተለይተው ለሕዝብ በሚታዩ ቦታዎች ላይ ተለጥፈው ታይተዋል።

ሪፖርተር ከተመለከታቸው ከእነዚህ ፎርሞች በአንድ ‹‹አሶሳ 03 03 ሀ2›› የተባለ የምርጫ ጣቢያ የቀረበው ውጤት ላይ የቁጥር መዛባቶችን ተመልክቷል።

በጣቢያው የቀረበው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጤት ማመሳከሪያና ማሳወቂያ ፎርም በምርጫ ጣቢያው የድምፅ መስጫ ሳጥኑ ውስጥና ውጭ ያሉት የድምፅ መስጫ ወረቀቶች አጠቃላይ ብዛት 280 መሆኑን ይገልጻል። ዋጋ ያላቸው የድምፅ መስጫ ወረቀቶች አጠቃላይ ብዛት ሥር ምንም ዓይነት መጠን ሳይገለጽ ባዶውን የሚታይ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ዋጋ አልባ የሆኑ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች አጠቃላይ ብዛት 243 መሆኑን እንዲሁም የጊዜያዊ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች አጠቃላይ ብዛት 36 መሆኑም ተጽፏል።

ምንም ዓይነት ዋጋ ያለው ድምፅ መሰጠቱን በማይገልጸው በዚህ ማሳወቂያ ፎርም ላይ የሰፈረው ዕጩዎች ምን ያክል ድምፅ እንዳገኙ የሚያሳየው ክፍል አንደኛ መነህል አምራን ኢድሪስ የተባሉ የብልፅግና ፓርቲ ዕጩ 193 ድምፅ ማግኘታቸውን፣ አብዮት ደረሶ ባጀቶ (ዶ/ር) የተባሉ የቦዴፓ ዕጩ 13 ድምፅ ማግኘታቸውን፣ ሰይፈዲን ኢብራሂም ሣሌ የተባሉ የቤህነን ዕጩ 14 ድምፅ ማግኘታቸውን፣ እንዲሁም ይትባረክ ደመቀ ገብረአብ የተባሉ የአብን ተወካይ ደግሞ 23 ድምፅ ማግኘታቸውን ይገልጻል።

ይህ ፎርም ሦስት የፓርቲ ወይም የዕጩ ወኪል ስምና ፊርማ፣ እንዲሁም ሦስት የምርጫ አስፈጻሚዎችና የምርጫ ጣቢያ ሰብሳቢ ስምና ፊርማ ያረፈበት ሲሆን፣ የልዩነት ሐሳብ ካለና የሐሳብ ሰጪው ስምና ፊርማ በሚለው የፎርሙ ክፍል ላይም ‹‹የለም›› የሚል መግለጫ የተጻፈበት ነው።

ሪፖርተር ጉዳዩን አስመልክቶ ሰነዱን በማሳየት ያነጋገራቸው የምርጫ ቦርድ የኦፕሬሽን ክፍል ሠራተኛና የአሶሳ ሆሀና የአሶሳ መገሌ ምርጫ ክልሎች አስተባባሪ ወ/ሪት ሃያት፣ በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት ምላሽ እንደማይሰጡ ገልጸዋል።

ወ/ሪት ሃያት በተጨማሪም፣ ‹‹ምርጫ ቦርድ አጠቃላይ ምርጫውን ውጤትና ተያያዥ ጉዳዮችን በሚያሳውቅበት ጊዜ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው ምላሽ የሚሰጥበት ይሆናል፣ አሁን ምንም ዓይነት ምላሽ አልሰጥም፤›› ብለዋል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰብሳቢዋ ወ/ሮ ሜላተወርቅ በኩል በአራት ክልሎች የተደረገው የድጋሚና ቀሪ ምርጫ ሒደት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ማስታወቃቸው ይታወሳል። የምርጫ ውጤቶች የድምፅ ቆጠራ ሒደቶች ሲጠናቀቁ በቀጣይ ቀናት ውስጥ ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -