Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ለመሆን ከአዲስ አበባና ከኦሮሚያ የተወከሉ ዕጩዎች ቀረቡ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በሰጠው አቅጣጫ መሠረት ሐምሌ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. እንደሚካሄድ፣ ለሚጠበቀው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምርጫ የፕሬዚዳንትነቱን ቦታ ለመያዝ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችን በአሁኑ ወቅት እየመሩ የሚገኙ ፕሬዚዳንቶች በዕጩነት መቅረባቸው ታወቀ፡፡   

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምርጫውን ለማካሄድ አባል ምክር ቤቶች ዕጩዎችን እንዲያሳውቁ ባቀረበው ጥሪ መሠረት እስካሁን ለፕሬዚዳንትነት እንዲወዳደሩ በየምክር ቤቶቻቸው ቦርድ ተመርጠው በዕጩነት ከቀረቡት መካከል፣ የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰብስብ አባፊራና የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ ቀዳሚ ሆነዋል፡፡ 

የዘንድሮውን ምርጫ ለማካሄድ የምርጫ ሒደቱን በተመለከተ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት፣ እያንዳንዱ አባል ምክር ቤት ሁለት ሁለት ዕጩዎችን እንዲልክ በተላለፈው ጥሪ መሠረት ቀነ ገደቡ ከመድረሱ በፊት ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩ ዕጩዎችን በየቦርዳቸው ማስወሰን የቻሉት የኦሮሚያና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤቶች ናቸው፡፡ ሌሎቹም በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ለፕሬዚዳንትነት፣ ለምክትል ፕሬዚዳንትነትና ለቦርድ አባልነት የሚወዳደሩ ዕጩዎቻቸውን ያሳውቃሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ 

እንደ ሪፖርተር ምንጮች ገለጻ ከሆነ ግን ለፕሬዚዳንትነት በዕጩነት ይቀርባሉ ከተባሉት የሁለቱ ንግድ ምክር ቤቶች ፕሬዚዳንቶች ሌላ ሊቀርብ የሚችል አንድ ወይም ሁለት ቢሆን ነው፡፡ እስካሁን ድረስ ባለው መረጃም የሁለቱ ንግድ ምክር ቤቶች ፕሬዚዳንቶች ዋነኛ ተፎካካሪ ይሆናሉ የሚል እምነት አሳድሯል፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት በበኩሉ በሐምሌ ወር ለሚካሄደው ምርጫ 42 ዕጩዎች ብሎ ታሳቢ አድርጓል። ነገር ግን የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት አባል ከሆኑት የክልልና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደር ንግድ ምክር ቤቶች መካከል ‹‹ማን ለየትኛው ቦታ ዕጩዎችን ያቀርባል ወይም አቅርቧል?›› የሚለው በተጨባጭ ሊታወቅ የሚችለው የምርጫ አስተባባሪ ኮሚቴው ሰነዱን ከከፈተ በኋላ ነው፡፡ 

ከዚህ ቀደም ከነበረው የምርጫ ሒደት ለየት ብሎ የሚካሄደው የዘንድሮ ምርጫ፣ ሁሉም አባል ምክር ቤቶች ሁለት ሁለት ዕጩዎችን እንዲያቀርቡ የሚደረግ በመሆኑ፣ አጠቃላይ 42 ዕጩዎች እንደሚቀርቡ ታውቋል፡፡ 

እስካሁን የኦሮሚያና የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንቶች፣ ለፕሬዚዳንትነት ከመወዳደራቸው ሌላ ለቦርድ አባልነት እንዲወዳደሩ አንዳንድ ዕጩዎችን ማቅረባቸውም ታውቋል፡፡ 

በዚህ ምርጫ በጠቅላላ ጉባዔው ላይ የሚወከሉ ተሳታፊዎች ድልድል የሚካሄደው በየክልልና በከተማ አስተዳደሮች ውስጥ ባለ የፀና የንግድ ፈቃድ ቁጥር መሆኑ ታውቋል፡፡ የጠቅላላ ጉባዔውን አወካከል በተለመከተ ከንግድ ምክር ቤቱ የተገኘው ተጨማሪ መረጃ እንደሚያመለክተው የጠቅላላ ጉባዔው ተሳታፊዎች የሚኖራቸው ድምፅ የሚወሰነው እያንዳንዱ ክልልና የከተማ አስተዳደር ባላቸው የፀና የንግድ ፈቃድ ቁጥር ቢሆንም፣ የጠቅላላ ጉባዔ እንደ ቀድሞ በ176 ወንበር (ድምፅ ያላቸው ተሳታፊዎች) የሚወከል ነው፡፡ ነገር ግን ተወካዮቹ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በእያንዳንዱ ክልልና ከተማ አስተዳደር የፀና የንግድ ፈቃድ ያላቸውን የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ብዛት መሠረት በማድረግ በሚያቀርበው መረጃ ላይ በመመሥረት እንደሚደለደሉ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ 

የፀና የንግድ ፈቃድ ያላቸው የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት በብዛት ደረጃ የሚገኙት በኦሮሚያ ክልል በመሆኑ የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በጠቅላላ ጉባዔው ውስጥ ትልቁን ድርሻ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ከኦሮሚያ ቀጥሎ ከፍተኛ የፀና የንግድ ፈቃድ የተመዘገበበት የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት በመሆኑ፣ በሚካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ውስጥ ሁለተኛውን ከፍተኛ ድርሻ ይይዛሉ፡፡ ይህም በምርጫው ከሁለቱ ክልሎች የሚወዳደሩ ተወዳዳሪዎች ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት የማሸነፍ ዕድላቸው ሰፊ እንደሚሆን እየተነገረ ነው፡፡ 

እስካሁን ንግድ ምክር ቤቱን በቦርድ አባልነት እያገለገሉ ያሉ አብዛኛዎቹ የቦርድ አባላት በዚህ ምክር ቤት ተሳታፊ እንደማይሆኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

እስካሁን ባለው መረጃ የኢትዮጵያን የንግድ ኅብረተሰብ በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ፕሬዚዳንትነት ለመምራት ከሚወዳደሩት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ሰብስብ፣ ይህ ምርጫ እንዲካሄና ንግድ ምክር ቤቱ ሪፎርም ማድረግ አለበት በማለት፣ በኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በኩል ግፊት ሲያደርጉ የቆዩ ናቸው፡፡ በንግድ ዓለም ረዥም ጊዜ መቆየታቸው የሚነገርላቸው አቶ ሰብስብ የፋት ትሬዲንግ ባለቤት ሲሆኑ፣ በቡና ላኪነት፣ በኮንትራክሽን፣ በሪል ስቴት፣ በምግብ ማቀነባበርና ማፋፈል፣ እንዲሁም በተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ የጅማና የኦሮሚያ ንግድ ምክር ቤቶች የቦርድ አባልና ፕሬዚዳንት በመሆንም አገልግለዋል፡፡  

ሌላዋ ዕጩ ወ/ሮ መሰንበት ዳይሜንሽን የተባለ አማካሪ ድርጅት ባለቤት ናቸው፡፡ አብዛኛው የሥራ ልምዳቸው ከባንክ ኢንዱስትሪ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ለረዥም ጊዜ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ውስጥ በከፍተኛ የአመራር ደረጃ አገልግለዋል፡፡ የዓባይ ባንክ የመጀመሪያዋ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የአማራ ባንክ የቦርድ አባል በመሆን እያገለገሉ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤትን ከሰባት ዓመታት በላይ መርተዋል፡፡ ወ/ሮ መሰንበት ብልፅግናን በመወክለ የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክር ቤት አባልም ናቸው፡፡   

በዚህ መሥፈርት መሠረት በጠቅላላ ጉባዔው ውክልና መሠረት ከፍተኛ ድምፅ የሚኖራቸው የኦሮሚያና የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ናቸው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች