Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከአበባ አምራችነት ወደ ምግብ ነክ ምርቶች የተሸጋገረው ጆይቴክ ኩባንያ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የሆልቲካልቸር ኢንቨስትመንት ውስጥ ከሃያ ዓመታት በላይ ዕድሜ ካስቆጠሩ ጥቂት ኩባንያዎች መካከል አንዱ ጆይቴክ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ነው፡፡ 

ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ቢሾፍቱ ከተማና በሆለታ አካባቢ 100 ሔክታር መሬት ተረክቦ በመሥራት ላይ የሚገኝ ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ አበባ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማኅበር ሰሞኑን በነበረው የመስክ ጉብኝት ጆይቴክ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አንዱ ነበር፡፡ በዚህ ጉብኝት ወቅት እንደተገጸለው ኩባንያው ከ20 ዓመት በፊት ሥራ የጀመረው አበባ በማምረት ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን ወደ ምግብ ነክ ምርቶች ሽግግር በማድረግ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን አምርቶ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ 

ከአበባ አምራችነት ወደ ምግብ ነክ ምርቶች የተሸጋገረው ጆይቴክ ኩባንያ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የጆይቴክ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የኦፕሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ብሥራት ኃይለሥላሴ እንደሚሉት ከአበባ ወደ ምግብ ነክ ምርቶች የተደረገው ሽግግር ስትራቴጂያዊ ነው፡፡ በየትኛውም የዓለም ክፍል የምግብ ፍላጎት እያደገ ከመምጣቱ አንፃር ወደዚህ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል። በዚህ እርሻ የተለያዩ ቅመማ ቅመም ምርቶችን ጨምሮ ቆስጣ፣ አዝማሪኖ፣ ሽንኩርት፣ በሶቢላና ሌሎች ምርቶችን በማምረት ለአውሮፓና ለተለያዩ አገሮች ገበያዎች እየቀረበ ነው፡፡ 

ዘመናዊ የሚባል የአመራረት ዘዴና ቴክኖሎጂን በመጠቀም እያመረቱ ያሉት ምርት በአሁኑ ወቅት በዓመት ከአሥር እስከ 12 ሚሊዮን ዩሮ የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ መሆኑን የገለጹት አቶ ብሥራት፣ ገበያቸው እያደገ በመምጣቱ ተጨማሪ የማስፋፊያ ሥራዎችን በማከል የመሥራት ፍላጎት እንዳላቸውም ጠቁመዋል፡፡

ከአበባ ምርት ለምግብነት ወደሚውሉ ምርቶች መሸጋገራቸው ሌላው ምክንያት ደግሞ አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን እናት ዝርያ እዚሁ አገር ውስጥ በማምረት ያለውን ፍላጎት ከማሟላት ጋር ተያያዥነት አለው፡፡ 

ለዚህም በኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለውን የአትክልትና ፍራፍሬ እናት ዝርያዎችን ለማልማት የሚችል ላቦራቶሪ ገንብተዋል፡፡ በዚህ ላቦራቶሪ እንደ ሙዝ፣ አናናስና መሰል ምርቶችን በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ እናት ዝርያዎችን ማውጣት ለገበሬዎች ማሠራጨት ጭምር ዓላማ ያለው በመሆኑ አሁን ላይ ሥራውን መጀመራቸው ተገልጿል፡፡ 

በከፍተኛ ጥንቃቄ የተገነባው ነው የተባለው ላቦራቶሪ ሥራውን የጀመረው የሙዝ እናት ዝርያዎችን በማራባት እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ብሥራት፣ ይህም የሆነበት ዋነኛ ምክንያት በኢትዮጵያ ያለውን የሙዝ ምርት ፍላጎትና ወደ ገበያ የሚቀርበው የምርት መጠን መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት በመገንዘብ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ እጥረቱ የምርቱን ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እያናረ በመሄዱ እንዲህ ያለውን ክፍተት ለመሸፈን በዚህ ላቦራቶሪ በአጭር ጊዜ ከፍተኛ የሆነ ምርት ይሰጣል የተባለው የሙዝ እናት ዝርያ በማምረት ለገበሬው ማድረስ መጀመሩንም አክለዋል፡፡ ዝርያውን የተረከቡ አርሶ አደሮችም ምርቱን አምርተው ለገበያ ማቅረብ የጀመሩ በመሆኑ በዚሁ መንገድ ሌሎች ምርቶቹንም በተመሳሳይ መንገድ በማምረት ለአርሶ አደሮችና ባለሀብቶች የማቅረብ ዕቅድ ይዟል፡፡

በዓለም ላይ በተለይ አደጉ በሚባሉ እንደኛ ያሉ አገሮች ላይ የምግብ ዋስትና ደኅንነት በጣም አስፈላጊ በሆነበት ቦታ ላይ በአውሮፓ ኤስፖርት አድርጎ መሥራት ብዙ ተግዳሮቶች  ቢኖሩትም በእነዚህ ተግዳሮቶች ላይ ቆይተን ዛሬ በተቀናጀ መልኩ ኤስፖርት ከማድረግ ባለፈ የተለያዩ ምርቶችን የእናት ዝርያ ማራቢያ እስከመገንባት መደረሱ እንደ ትልቅ ስኬት የሚታይ ነው ይላሉ፡፡ በረዥም ጊዜ በምግብ ነክ ምርቶች ላይ በመሥራት ሒደት ውስጥ ከመቆየታችን አንፃር የፋድሰክሪውቲ በጣም ይጠቅማል ተብሎ በሚታሰበው መስመር ውስጥ መገባቱ በተለይ የእናት ዝርያ ምርቶችን ማቅረብ የአገር ውስጥ ያሉ ገበሬዎችን ይደግፋል፡፡ እንዲሁም በምግብ ምርት ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ኤክስፖርት አድርገው ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ እንዲገኝ የሚያስችል እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

በላቦራቶሪ የሚመረቱ እናት ዝርያዎችን የማምረቱ ሥራ በሙዝ ተጀምሮ ውጤቱ እየታየ በመሆኑ በተከታታይ በገበያው ውስጥ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸውንና እጥረት የሚታይባቸው ምርቶችን እናት ዝርያዎችን በማምረት ዕገዛ ለማድረግ ዝግጅት ስለመደረጉ የአቶ ብሥራት ማብራሪያ ያስረዳል፡፡ 

በዚህ ላቦራቶሪ የሥራ ሒደት ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ብስራት ላቦራቶሪው የማባዛት ሥራ የሚሠራበት ነው፡፡ ችግኝ ለማዘጋጀት የተለያዩ ሜትዶች አሉ ያሉት አቶ ብስራት አንዱ ከአትክልቱ ወይም ከምርቱ ላይ ተቆርጦ የሚሠራ ነው፡፡ ሌላኛው  ዘር ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ‹‹ቲሹ ካልቸር›› ነው፡፡ ይህም ከተክሉ አካል ላይ የሚወሰድ ሴል ወስዶ የማባዛት ዘዴ ነው፡፡ በዚህ ላቦራቶሪ የሚሠራው ይህ ነው፡፡ በዚህ መሠረት እጅግ በርካታ የሆኑ ከበሽታና ከተባይ የነፁ በተመሳሳይ የማደግ ደረጃ ላይ ብዙ ችግኞችን በአንድ ጊዜ ማግኘት የሚያስችል ዘመናዊ የማባዛት ቴክኖሎጂ ነው፡፡ 

በኢትዮጵያ ደረጃ ባለፋሲሊቲ ውስጥ ለማከናወን ባለሙያዎችን ይፈልጋል፡፡ የሰው ኃይልና ቴክኖሎጂ የሚፈልግ ሥራ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ይህ ሥራ ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም በበቂ ሁኔታ የማምረት አቅም የለም፡፡ 

ስለዚህ ይህንን በመረዳት ወደዚህ ሥራ መገባቱንም አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ያለው የምግብ ፍላጎት ለማሟላት እንዲህ ዓይነት ላቦራቶሪዎች ማስፋፋት ግድ መሆኑንም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ጆይቴክ ያስገነባው ላቦራቶሪ በዓመት 12 ሚሊዮን ችግኞችን የማምረት አቅም አለው ተብሏል፡፡ በአጭር ጊዜ በከፍተኛ መጠን ተመሳሳይ ምርቶን ለመስጠት የሚችሉ እናት ዝርያዎችን ላቦራቶሪ ውስጥ አምርቶ ማሠራጨት የአገር ውስጥ ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ እስካሁን ከውጭ የሚመጡ የነበሩ እናት ዝርያዎችን በመተካት የውጭ ምንዛሪ የማዳን አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ከተሰጠው ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

በዘርፉ እንዲህ ያሉ እንቅስቃሴዎችን ቢያደርጉም ሁሉ ነገር አልጋ በልጋ አለመሆኑንና የተለያዩ ተግዳሮቶች እንዳሉባቸው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ እንደ ተግዳሮት ከገለጹት ውስጥ ከመሬት ከሊዝ ጋር የተያያዘ እያሳሰበን ነው ያሉትን ችግር አስቀድመዋል፡፡ 

በነባሩ የሊዝ ስምምነት መሠረት ብዙዎቹ  አልሚዎች የሊዝ ዘመናቸው እያለቀ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ካልተሻሻለ ለአልሚዎች አስጊ ነው፡፡ የሊዝ ዘመኑ ከአሥር ዓመት በታች የቀረው ከሆነ ደግሞ ባለሀብቶቹ ተጨማሪ ኢንቨስት ለማድረግ ያስቸግራቸዋል፡፡ 

ስለዚህ የሊዝ ስምምነቱ ዘመን ከማለቁ በፊት አዲስ ስምምነት ማድረግና ኢንቨስትመንቱ ቀጣይ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ 

በመሆኑም ከዚህ ጉዳይ ጋር የተያያዙ ሥጋቶችን በቶሎ መቅረፍ አለመቻሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ላይ  አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረባቸው መሆኑንም አክለዋል፡፡ 

ጆይቴክ የእርሻ ቦታዎችን ለ30 ዓመት የሊዝ ዘመን የወሰደ ሲሆን የቀረው አሥር ዓመት ከመሆኑ አንፃር የሊዝ ስምምነቱ በአጭር ጊዜ የማይታደስ ከሆነ ለተጨማሪ ኢንቨስትመንት አዳጋች ይሆንበታል፡፡ ተጨማሪ ሥራዎችን ለመሥራት ማስፋፊያዎችንም ለማድረግ የመሬት ሊዝ ስምምነቱ ከወዲሁ መቋጫ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ አቶ ብስራት ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ እየገጠመን ነው ያሉ ችግሮችንም ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ አቶ ብስራት የውጭ ምንዛሪ ችግር አጠቃላይ የአገሪቱ ችግር መሆኑን እንገነዘባለን ብለዋል፡፡ 

ነገር ግን ዘርፉ ከሚፈልገው የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት አንፃር እያገኘ ያለው የውጭ ምንዛሪ በቂ ያለመሆኑን ያስረዳሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መጀመርያ ላኪዎችን 20/80 በሚለው አሠራር ሲያስተናግድ የቆየ ሲሆን ይህንን ወደ 40/60 ከፍ ማድረግ ቀደም ብሎ የነበረውን ችግር ሊያቃልል ቢችልም ያለውን ችግር ግን ሊቀርፍ አልቻለም፡፡ 

በተለይ ምግብ ነክ የሆኑ ምርቶች ላይ የሚሠሩ ኩባንያዎች በተለይ ለምግብ ማሸጊያ የሚሆኑ ምርቶች ለዘርፉ የተቀመጠውን ደረጃ ማሟላት ስለሚገባቸው ለእነዚህን ምርቶች የሚሆኑ ማሸጊያዎችን ከውጭ ማስመጣት ግድ ይሆንባቸዋል፡፡ 

እነዚህን ማሸጊያዎች ደግሞ እዚህ የሚያመርቱ ብዙም ስለሌሉ የተቀመጠውን ደረጃ የሚያሟሉ ማሸጊያዎችን ለመግዛት ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቅ አስገዳጅ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡ 

በሌላ በኩል ደግሞ ኢንቨስትመንት ተብሎ እየተሠራ ከሆነ በየጊዜው ኢንቨስት እያደረጉ መሄድ ካልተቻለ ዓመታት በመጡ ቁጥር ኪሣራ ሊያጋጥም ይችላል የሚሉት አቶ ብሥራት ኢንቨስትመንት ለማደግ ደግሞ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ በመሆኑ ይህንን አጣጥሞ መሄድ እንደሚያስፈልግ በማመን መንግሥት የበኩሉን ዕገዛ ያድርግ ብለዋል፡፡ 

የብሔራዊ ባንክ ላኪዎች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ 20 በመቶውን ብቻ እንዲጠቀሙ በወሰነበት ጊዜ የነበረው ጫና ቀላል እንዳልነበር በማስታወስ፣ አሁን ግን የቀድሞው አሰራር ተሻሽሎ ላኪዎች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ መጠቀም የሚችሉት ወደ 40/60 ከፍ በማለቱ መጠነኛ እፎይታ መገኙትን ነገር ግን ይህም ቢሆንም በቂ ባለመሆኑ ሊታይ እንደሚገባ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች