Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርአታካቹ ፓስፖርት የማግኘት መብትና የአገራችን ሁኔታ!

አታካቹ ፓስፖርት የማግኘት መብትና የአገራችን ሁኔታ!

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

ይህን ጽሐፍ ለማቅረብ ያነሳሳኝ ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም. በወጣው ሪፖርተር ዕትም፣ ‹‹የኢሜግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዜጎችን የሚያስለቅስ ተቋም ሆኗል›› ሲሉ የፓርላማ አባላት የሰነዘሩትን ጠንካራ ሒስ መመልከቴ ነው፡፡ በእርግጥም ትናንትም ሆነ ዛሬ ሥርዓቱን በሚያገለግሉና በታማኝነት ስም የአንድ ብሔር፣ ፓርቲ ወይም ቡድን ሰዎች ተደራጅተው የሚገቡበት ተቋም እየመሰለ መምጣቱ ችግሩ እየተባባሰ እንደቀጠለ በርካታ ተቺዎች በምሬት ሲናገሩ ነበር የከረሙት፡፡

እንደ መረጃው ምክር ቤቱ በ29ኛ መደበኛ ስብሰባው የአገልግሎት ሰጪ ተቋሙን አሠራር ለማሻሻል የሚረዳ ረቂቅ አዋጅን ለዝርዝር ዕይታ የመራ ሲሆን፣ በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ያለው የከፋ የመልካም አስተዳዳር ክፍተትና ሕዝብ የሚያማርር አሠራር ተባብሶ የቀጠለው በሕግ ክፍተት ምክንያት ከሆነ የማሻሻያ አዋጁ ሊረዳው ይችላል፡፡

በርከት ያሉ የተቋሙ ባለጉዳዮች እንደሚያስረዱት ግን የተባባሰው ችግር የሚመነጨው ከሕግና አሠራር መመርያ ጋር ብቻ ሳይሆን፣ በርከት ካሉ ሠራተኞችና አመራሮች የሥነ ምግባር ጉድለትና ሙስና መሻት ጋር ነው (ለነገሩ ከወራት በፊት ከፍተኛ አመራሮቹ ጭምር በኔትወርክ ተሳስረው፣ ደላላና ጉዳይ ገዳይ አሠልፈው በተደራጀ ሙስናና የደኅንነት ሥነ ምግባር ጥሰት ላይ በመሰማራት ሕዝብ ሲያስለቅሱ በመቆየታቸው አይደል እንዴ ወደ ወህኒ ተወርውረው ጉዳያቸው በሕግ እየታየ ያለው)፡፡

አሁንም ቢሆን ፓስፖርት በአቋራጭና ያለወረፋ በአፋጣኝ ለማውጣት በመቶ ሺዎች ብር የሚጠየቅበት ሁኔታ እንደሚያጋጥም መነገሩ መቀጠሉ ነው ምክር ቤቱን ያሳሰበው፡፡ ሌላው ቀርቶ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሰነዱን ለማግኘት ግዴታ ተፈላጊ የሆነውን የልደት ካርድ ለማውጣት በየወረዳው ያሉ አንዳንድ ሕገወጥ የወሳኝ ኩነት ባለሙያዎች በአሥር ሺዎች እየጠየቁ መሆናቸው፣ አስደንጋጭና መፈጠርን የሚያስጠላ እየሆነ ነው የሚሉ ሰዎች ትንሽ አይደሉም፡፡

በመሠረቱ ዜጎች ፓስፖርት ለማግኘት እየደረሰባቸው ስላለው መንገላታት ሁላችንም ችግሩን በጥልቀት የምንመረምርበት፣ የመፍትሔው አካል ለመሆንም የየራሳችንን የመፍትሔ አማራጭ ለማቅረብ የበኩላችንን ሚና የምንጫወትበት ጊዜ አሁን ይመስለኛል፡፡ ፓስፖርት የባለቤቱን ማንነትና ዜግነት የሚገልጽና ለዓለም አቀፍ ድንበር ዘለል ጉዞ መተላለፊያ ይሆን ዘንድ በብሔራዊ መንግሥታት የሚሰጥ የጉዞ ሰነድ እንጂ፣ ነፍስ የሚቀጥል ሰነድ እንዳልሆነ የተወቀ በመሆኑ እንደ መብትም መቆጠር አለበት፡፡

 የመሰደድና ከአገር እንደምንም ብሎ የመውጣት ፍላጎት እየተመነደገ መምጣቱ የፓስፖርትን ተፈላጊነት እንዳባባሰው ግን ሊካድ አይችልም፡፡ ሁሉም መንግሥት የየራሱ የጉዞ ሰነድ (ፓስፖርት) ያለው እንደ መሆኑ፣ የእኛ አገር መንግሥትም ለዜጎቹ ይህንኑ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ ከአገራዊ ደኅንነትና ብሔራዊ ጥቅም ጋር አጣጥሞ በተመጣጣኝ ዋጋና በቅልጥፍና ለየራሱ ዜጎችና እንደ አስፈላጊነቱም ለሌሎች አመልካቾች መስጠት ይኖርበታል፡፡

ፓስፖርት መያዝ ብቻውን ወደ ፈለጉበት አገር ግን አያስገባም፡፡ የቆንስላ ጥበቃም (ደኅንነት) አያስገኝም፡፡ በዋናነት ግን ባለፓስፖርቱ ወደ አገሩ እንዲመለስ የሚያስችል መብት ይሰጠዋል፡፡ በልዩ ሁኔታ ካልሆነ በቀር ወደ ሌላ አገር ለመግባት የዚያን አገር ቪዛ በፓስፖርቱ ላይ ማስመታት ያስፈልጋል፡፡ የቆንስላ ጥበቃ መብት የሚገኘውም ፓስፖርት በመያዝና ባለመያዝ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሠረት ነው፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ፓስፖርት ዓይነቱ ብዙና ደረጃውም የተለያየ ነው፡፡ መደበኛ (ordinary) ፓስፖርት፣ የቱሪስት ፓስፖርት፣ ኦፌሴላዊ (official)፣ የሰርቪስ ፓስፖርት፣ ልዩ (Special) ፓስፖርት የሚባልና ለሥራ ጉዳይ ለሚሄዱ የመንግሥት ሠራተኞች የሚሰጥ የፓስፖርት ዓይነት ነው፡፡ ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት የሚባል ለዲፕሎማቶችና ለመንግሥት ባለሥልጣናት የሚሰጥም አለ፡፡

ጊዜያዊ (Temporary) ፓስፖርት የሚባልና በየአካባቢው ባሉ ባለሥልጣናት የሚሰጥና ሰውየው የሚሄድባቸውን የድንበር ጣቢያዎች የሚገልጽ ከጠረፍ ጠረፍ፣ ከወደብ ወደብ ሲሸጋገር በየሄደበት የይለፍ ወረቀት የማይጠየቅበትና ከዚያ ጣቢያ ወጥቶ ወደ መሃል ከተማ የሚንቀሳቀስ ከሆነ ብቻ የሚጠየቅበት አሠራርም አለ፡፡ የኅብረት (ቡድን) ፓስፖርት፣ የቤተሰብ ፓስፖርት፣ የስደተኛ ፓስፖርት ሊሴ-ፓሴ፣ ወዘተ ሁሉም የይለፍ ወረቀት የጉዞ ሰነድ ፓስፖርት ዓይነቶች ናቸው፡፡

የፓስፖርቱ (የደብተሩ) ቀለምና የገጹ ብዛት እንደ አገሮች ፍላጎት ይለያይ እንጂ፣ የሁሉም አገር ፓስፖርት ይዘት አንድ ነው፡፡ የፓስፖርት የጉዞ ሰነድ ዋና ዓላማ የሰውየውን ማንነትና ዜግነት መግለጽ ነው፡፡ ስለዚህ የሰውየውን ስም፣ የትውልድ ጊዜ፣ ቦታና ፆታ፣ ይጠቅሳል፡፡ የልጆች ማንነትና ፎቶም አብሮ የሚደረግበት አሠራርም አለ፡፡

ፓስፖርቱን አስመስሎ ከተሠሩት ሐሰተኛ (ፎርጅድ) ፓስፖርቶች ለመለየት የሚያስችል ረቂቅ ጥበብ በውስጡ አለው፡፡ ይህን በተሻለ የኅትመት ስልት አትሞ ለሚፈልገው ሰው መስጠት የቀበሌ መታወቂያ/ናሽናል መታወቂያ አሰናድቶ ከመስጠት የተለየ ባልሆነ ነበር፡፡

እውነተኛ የጉዞ ሰነድ (ፓስፖርት) የሚባለውና ዘመናዊ ሆኖ የተዘጋጀ ፓስፖርት የተጀመረው በእንግሊዙ ንጉሥ ሄነሪ አምስተኛ አማካይነት እንደነበር ይነገራል፡፡ ያኔ ፎቶግራፍ ስላልነበረ ፓስፖርት ፎቶ የለውም ነበር፡፡ ፓስፖርት ላይ ፎቶ መለጠፍ የተጀመረው የፎቶግራፍ ጥበብ ከተስፋፋ በኋላ ነው፡፡

ፓስፖርት አስፈላጊ ያልነበረበትም ዘመን ነበር፡፡ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ እስከ አንደኛው የዓለም ጦርነት ድረስ ለድፍን 30 ዓመታት ፓስፖርት የሚባል ሰነድ ቀርቶ ነበር፡፡ የፈጣን ባቡር አገልግሎት መቀላጠፍና የድንበር ዘለልና የረዥም ርቀት ተጓዦች መብዛት የፓስፖርትን አስፈላጊነት አስቀርተውት ነበር፡፡

ፓስፖርት ወደ ውጭ አገር ለመሄድ ብቻ ሳይሆን በራስ መንግሥት ቁጥጥር ሥር ባሉ ክልሎችም ለመንቀሳቀስ ግዴታ የነበረበት ጊዜም ነበር፡፡ በኦቶማን ኤምፓየርና በሩሲያ ኤምፓየር አገዛዞች ዘመን ያለ ፓስፖርት ከክልል ክልል መዘዋወር አይቻልም ነበር፡፡ በኋለኛው ዘመን ግን በራስ መንግሥት ግዛት ውስጥ ለመንቀሳቀስ ፓስፖርት መጠየቅ እንደ ኋላቀርነትና ብልሹ አሠራር ስለተቆጠረ እንዲቀር ተደረገ፡፡

ስለፓስፖርት የጉዞ ሰነድ አጀማመር የሚናገሩ ማገናዘቢያዎች ፓስፖርት 450 ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት (BC) የፋርስ ንጉሥ አገልጋይ ለነበረው ነህምያ የተሰጠ ስለመሆኑ ይመሰክራሉ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መጽሐፈ ነህምያ 2፡1-9 ተጽፏል፡፡ ቀድሞ ግን በቀላሉ የሚሰናዳ እንደነበር ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡

እውነት ለመናገር በእኛም አገር እንኳን በቀደመው ዘመን፣ የዛሬ ሰላሳ ዓመታት ገደማ እንዲሁ ነበር ይላሉ አስተያየት ሰጪዎች፡፡ ኢሚግሬሽን ሄዶ የጠየቀ ሰው ፓስፖርቱን በአንድ ቀን ውስጥ ማግኘት ይችል ነበር፡፡ እኔ ራሴ ወደ ሞስኮ ሄዶ በነበረው አጎቴ (አቶ ግርማ ቸሩ) ፓስፖርት አወሳሰድ ምስክር ነኝ፡፡ ‹‹እንደ ነገ ለመብረር ዛሬ ነው የተነገረኝ፡፡ ኢሚግሬሽን ፎቶ ይዤ ሄድኩ፣ ፎርም ሞላሁ፣ ከሰዓት መጥተህ ውሰድ አሉኝ፡፡ ሄጄ ወሰድኩ፡፡ አለቀ በቃ፤›› ሲል ይናገር ነበር፡፡

ሠልፍና ወረፋ የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ እንኳን ለደላላና ውስጥ አወቅ ጉዳይ ገዳይ በአሥር ሺዎች ጉቦ ሊከፍል፣ ለአገልግሎቱ ክፍያ መኖርና አለመኖርም ጭራሽ ትዝ አይለውም ነበር፡፡ ፓስፖርት ማግኘት እጅግ በጣም ቀላል ነበር፡፡ ዛሬ ግን ሁኔታው ሙሉ በሙሉ ተለውጦ ከቁጥጥር ውጪ ሆኗል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታትም ቢሆን የባሰ እንጂ የተሻለ ነገር እንዳልታየ፣ ሌላው ቀርቶ የሰሞኑ የተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ በቂ ማሳያ ነው፡፡

በግልጽ እየተመለከትን እንዳለነው የፓስፖርት ፈላጊው ብዛት ከቀን ወደ ቀን፣ ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ መጥቷል፡፡ ገጠር፣ ከተማ፣ የተማረ፣ ያልተማረ ሁሉ ለመሰደድ የሚያበቃውን ሰነድ ለመያዝ ይጣጣራል፡፡ በኢሚግሬሽንና ዜግነት መሥሪያ ቤትና ቅርንጫፎች ሠልፉ ተመልካችን ጉድ እስኪያሰኝ ድረስ በሦስትና በአራት ረድፍ እየተሸረበና እየተጠማዘዘ ከሚሄድ በቀር፣ የቀነሰበትን ዕለት ማየት አለመቻሉም የቅርብ ትውስታችን ነው፡፡ ዛሬም ነገም ሁሌም ሠልፉ እጥፍ ድርብ ነው፡፡ የሰው ልጅ እንደ ጉድ መጉላላቱና በቀጠሮ መታከቱም ተለምዷል፡፡  

ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት የቢፒአርና አዳዲስ የአሠራር ማሻሻያ ባደረገባቸው የመጀመሪያ ዓመታት በአሠራር ቅልጥፍና በአደረጃጀት የላቀ ምሥጋናና አድናቆት የተቸራቸው ሁለቱ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች፣ ኢሚግሬሽንና ውልና ማስረጃ እንደነበሩ ትዝ ይለኛል፡፡ የኢሚግሬሽን አሠራራችን ግሩም ድንቅ ነበር፡፡ አሁን ግን ሥራው ከኢሚግሬሽን አቅም በላይ ከመሆኑ ባሻገር ከፍተኛ ምሬትና የሙስና መሰናክል የሚያጋጥምበት መስክ መሆኑ በርካቶችን እያሳዘነ ይገኛል፡፡ ፈጣንና ጥብቅ እርምት ሊጎበኘውም ግድ ይላል፡፡

በደላላ ከንቱ ስብከትና ግፊት እየተታለሉ ከየክልሉ የመጡ፣ በጦርነትና ሥራ አጥነት ተማረው እንጀራ ለመፈለግ የሚንከራተቱ፣ በፖለቲካ ጥገኝነት ፍለጋ የሚሰደዱ፣ ወዘተ ፓስፖርት ፈላጊዎች አንዳንዶቹ በረሃብ እየተጠበሱ፣ የቋጠሯትን ጥቂት ብር በማደሪያ ክፍያ እየጨረሱ መንገላታታቸውን እንሰማለን፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴም የችግሩን መጠነ ሰፊነት ተገንዝቧል፡፡ የኢሚግሬሽን ኃላፊዎችም ችግር መኖሩን አልካዱም፡፡ ታዲያ ይህን ያገጠጠ ችግር ከሥሩ መንግሎ መንቀል ለምን አልተቻለም የሚለው ጥያቄ ነው መልስ ያላገኘው፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት መልካምና የተቀላጠፈ አገልግሎት ከሚሰጡ መሥሪያ ቤቶቻችን አንዱ የነበረ ኢሚግሬሽንና ዜግነት መሥሪያ ቤት በዘመድና በአቋራጭ የመሥራት ነገር እንዴት ሊተበትበው ቻለ?  ብቃትና ተወዳዳሪነትስ ለምን ሸሹት? ብሎ መፈተሸ ካልተቻለም ከውድቀት መነሳት የሚቻል አይሆንም፡፡

በእርግጥ አሁን የፓስፖርት ቀጠሮ በኦንላይን ሆኗል፡፡ ተቺዎች እንደሚሉት ግን አንዳንድ አዳዲስ የተቋሙ ሠራተኞች ፎርሙን አስተካክለው መሙላት እንኳን አይችሉም፡፡ ለሚጠየቁት ተጨማሪ ጥያቄና ማብራሪያ ፈጣንና ግልጽ ምላሽ አይሰጡም፡፡ ተገልጋዮቹም ቢሆኑ ነገረ ሥራቸው ሁሉ የሚከወነው በደላሎቻቸው አማካይነት ስለሆነ ደላሎቹ አጠገባቸው ከሌሉ ግራ ይገባቸዋል፡፡ ቀላሉ ነገር ሁሉ ያደናግራቸዋል፡፡ አብዛኞቹ የድርጅቱን የሥራ ቋንቋ አያውቁም፡፡ የተጻፈውንም አያነቡም፡፡ በእውነቱ ግራ የገባ ነገር ነው ይላሉ፡፡

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከሚስተናገደው ሕዝብ ብዛት አንፃር ሲታይ በሠራተኞቹ ላይ የሚደርሰው መጨናነቅ ተስፋ መቁረጥና መሰላቸትም ሊያስደንቀን አይገባም፡፡ መቼም ከስንዴ መሀል እንክርዳድ እንደማይጠፋ ሁሉ ጥቂት ሠራተኞች የብልሹ አሠራር ተጠቃሚዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ባይካድም፣ እነሱን ነቅሶና ነቅሎ በማውጣት እየደከመ ያለውን ታማኝና ትጉ ሠራተኛ ማበረታታትና መሸለምም ያስፈልጋል፡፡

እንደሚታወቀው አብዛኞቹ ተጓዦች ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሚሄዱትና ለዚያ ሁሉ ስቃይ የሚዳረጉት ከቤት ሠራተኝነት ላልበለጠ ሥራ ነው፡፡ ይህን የሚመጥን የሥራ ዕድል እንደ አገር መፍጠር ግን ይቻላል፡፡ መንግሥትም የውጭ ጉዞ የሥራ ፍለጋውን ሕጋዊነት እያላበሰ እንደ አንድ የሥራ ዕድል መስክ መመልከት ከጀመረ ከራርሟል፡፡ ደሃ፣ ሀብታም ሳይባል ማንኛውም ዜጋ ፓስፖርት ለማግኘት ተመጣጣኝ ክፍያና ውጣ ውረድ የሌለው አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ መትጋት ይኖርበታል፣ ግዴታውም ነው፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተጀማመረው የጉዞ ሰነድን (ፓስፖርትን) በየክልሉ እንዲሰጥ ማድረግም ሆነ፣ የፌዴራሉ ኢሚግሬሽን አሠራር በሰው ኃይልና በአደረጃጀት የማስተካከል ሒደት ጊዜያዊ መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡ ዋናው ግን በተጓዦች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በመላው ሕዝባችን አመለካከትና አስተሳሰብ ላይ በአገር ሠርቶና ተባብሮ ለመቀየር በመትጋትና ስደትን በመተው አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት መሥራት ነው፡፡ አጠቃላይ ድኅነታችንና ተደማምጠን የተቃና ሰላምና አገራዊ ደኅንነትን አለማረጋገጣችን  ዋንኛ ጠላታችን መሆኑን ተግባብቶ ለለውጥ መነሳት ያስፈልገናል፡፡

ከ200 ሺሕ እስከ 800 ሺሕ ብር ከፍሎ መሄድና አንዳንድ ጊዜ ምንም ሳይዙ ብቻ ሳይሆን፣ ጤናንም አጥቶና ተዋርዶ መመለስ ግን የግንዛቤ ችግር መሆኑን ማመንና ይህንንም ለመቅረፍ መሥራት ተቀዳሚ ኃላፊነታችን መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡ ችግሩን ለመፍታት ሲባል ዜጐች ወደ ሌላ አገር (ሥፍራ) እንዳይሄዱ ለጊዜውም ቢሆን በሚል ሰበብ ማገድ (ጉዞ መከልከል) ግን የባሰ ሌላ ችግር ያስከትላል፡፡ የውጭ ጉዞ ሰነድ እንዳያገኙ በውጣ ውረድ ማስለቀስና በብልሹ አሠራር ጥቂቶችን ማበልፀግም ፍፁም መፍትሔ ሊሆን አይችልም፡፡  

እንዲህ ያለ ኋላቀር መፍትሔ በአንድ በኩል ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚፃረር ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚያስፋፋ በመሆኑ ዜጐችን ለደላላ ሲሳይ ይዳርጋል፡፡ የጉዞ ላይ ችግሮችንም ያባብሳል (በየጊዜው እንደሚያጋጥመው በቅርቡ በቦሳሶ 200 ሕገወጥ ስደተኞች በጀልባ መገልበጥ አደጋ ማለቃቸውን በአሰቃቂ ሁኔታ መመልከታችንን ልብ ይሏል)፡፡ ሰዎች መሄድ መብታቸው መሆኑን ሳንዘነጋ፣ ላለመሄድ የሚያስችሉ የአገር ውስጥ ሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲና ተንቀሳቅሶ የመሥራትና የመኖር ዕድል መልካም አማራጮችን ለማቅረብ ቆርጦ መነሳት ያስፈልጋል፣ የመንግሥት ኃላፊነትም ነው፡፡

ሰላም!!

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው nwodaj@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...