Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሥቃይና ጥጋብ!

እነሆ ጉዞ ከቦሌ ወደ ሜክሲኮ። ታክሲ የሚባል የለም፡፡ የምፀት፣ የኃፍርትና የቁጭት ስሜት የኮሰኮሰው ሁሉ ከንፈሩን እየመጠጠ ቆሟል። የመኖር ጉጉት የቀዘቀዘበት ሆኗል ጎዳናው። የእንቅስቃሴው ልግመኝነት ይህን ያሳብቃል። በአጠቃላይ የጎዳናው ስሜት ያስፈራል። የታመቀ የሰቀቀንና የእልህ ትንፋሽ መንገደኛው ላይ ይትጎለጎላል። ዕርምጃዎች ሁሉ እንዳልተመቻቸው ያስታውቃሉ። ምቾቱ ቀርቶባቸው መወገድ ያለባቸው እንቅፋቶች ፈቀቅ ያልተደረጉላቸው እልፍ ይመስላሉ። ይኼው ነው የዚህ ጎዳና የዘመኑ ታሪክ። ሲመጣ ሲሄድ የኖረው ሁሉ አንድ ዓይነት እንቅፋት እያነቀፈው ነው የአቅሙን ያህል ሳይሮጥ የሚያልፈው። ይህ ነው የዚህች አገር ታሪክ። ላይድን ቁስሏ ጠገግ ሲል፣ ላይሽር ጠባሳዋ ሲደበቅ፣ ከፍ እንዳትል የሚኮረኩማት ችግር እየላቀ፣ ሸለቆውና ስርጓጉጡ መንገድ ባረዘመ መጠን የመጣ የሄደውን አደከመው። ትውልድ ሁሉ ራዕይ ርቆት የኑሮ ጣሪያው ‘እንተያያለን’ በሚል አጉል ጀብድ የታጠረ ሆነ። አጉል ቀልደኛው በዝቶ ቁምነገር ከሰመ!

ጎዳናው ላይ ያልተጻፈ ነገር የለም። ብሶት፣ እልህ፣ ታጋሽነት፣ አርቆ አሳቢነት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ከንቱ የመሆን ስሜት። ስሜት ነው የሰው ልጅ የአካሉ ድምፅ። ሁሉም በመሰለው ለመሮጥ አሰፍስፎ ግን የአቅሙን ያህል እንዳይሮጥ ዙሪያውን ከትራንስፖርት ችግር እስከ አስተሳሰብና አመለካከት ችግር መንገድ ተዘግቶበት ቆሟል። ከሚታየው እስከማይታየው ሁሉም የመንገድ ጋሬጣ ነው። እንደዚህ ነው የዚህ ጎዳና ህላዌ ሚስጥር። የፈቀዱትን ለመሆን ባልፈቀዱት ሥፍራና ሰርጥ ውስጥ ወድቀው የሚነሱበት። ለዚህም ብዙ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትንታኔዎች የሚቀርቡበት። ድንገት ከዚህ ሐሳባዊ ፍልስፍናና ምርምር ወጣ ሲባል፣ ታክሲ ፍለጋ የተገተርነው መሄጃ ስላጣን ሊመስል ይችላል። ቀደም ቀደም ያልነው በመጣችው ብቸኛ ታክሲ ውስጥ ገብተን ተሳፍረናል። ተጓዥ ይኑር እንጂ መንገድማ መቼ ጠፍቶ ያውቃል? የጠፋው ሰው የመሆን ክብር ነው!

ጉዟችን ተጀምሯል። አንድ ጎልማሳ በስልኩ መነጋገር ጀመረ። ‹‹እየመጣሁ ነው አልኩህ እኮ! ሃሎ? አይሰማም? አንተ ብቻ ፖሊሶች ጥራልኝ…›› ይላል። ንዴትና እልህ አወራጭቶ ስልኩን እየዘጋው። የታክሲዋ ተሳፋሪዎች በፀጥታ የሰውየውን ሁናቴ ይከታተላሉ። ‹‹ሰላም አይደለም?›› አለችው ከጎኑ የተቀመጠች የቦሌ ሽቅርቅር። ‹‹ኧረ ተይኝ፣ የዘንድሮ ነገራችን በየት በኩል ሰላም ይሰጣል?›› ብሏት ሩቅ ያውጠነጥን ጀመር። ጥያቄዋን መግታት ያልቻለችው ዘናጭ፣ ‹‹ፖሊሶች ለምን አስፈለጉህ ታዲያ?›› ብላ ስትጠይቀው፣ ‹‹ይኼውልሽ ላቤን ጠብ አድርጌ የሠራሁትን የመነገጃ ቤቴን ለማፍረስ የመጡ ሰዎች አሉ ተብዬ ነው…›› አላት በንዴት። ‹‹በአንድ በኩል አገራችንን ተባብረን እናሳድግ ይባላል፣ በሌላ በኩል ኑሮ መደጎሚያ መሥሪያችን እንደ ቀልድ ይፈርሳል…›› ብሎ እንደ መተከዝ አሰኘው። ‹‹አ…ሄ…ሄ… የዘንድሮ ነገር ምን ውል አለው ብላችሁ ነው? እኛ እንኳ በዚያ በድንቁርናው ጊዜ ኑሮ ለመደጎም ብለን የሠራናቸውና ስንቶችን በአነስተኛ ክፍያ ያስጠለሉ የጭቃ ቤቶቻችን ሳይቀሩ በደርግ ተወርሰው አልነበር?›› ብለው አንዲት እናት ትዝብታቸውን አካፈሉን። ትዝብታችን ብዙ ሆነ እኮ ጎበዝ!

‹‹ኧረ እውነትዎን እማማ፣ ያኔ አወቅን ተማርን ያሉ በስመ ሶሻሊዝም የሀብታሙንም የደሃውንም ንብረት አንድ ላይ ጨፍልቆ እንዲወረስ አድርገው እኮ ነው መሥራት ዕርም የሆነው። ከዚያ ወዲህ የሚከበረው አንገቱን ደፍቶ የሚሠራ ሳይሆን ሰርቆ የከበረ ነው፡፡ ለፍቶ የሚሠራው ምግብና ሌሎች ወጪዎቹን መቻል አቅቶት በድህነት ይቆራመዳል፡፡ በአቋራጭ እየከበረ ያለው ግን የ40 ሚሊዮን ብር መኪና የሚነዳበት ዘመን ላይ ደርሰናል…›› ብሎ ሳይጨርስ ከአጠገባቸው የተቀመጠ ወጣት፣ ‹‹ኑሮ ቀልባችንን ገፎት እንዴት ብለን እንዲህ ያለውን ጉዳይ እናስታውሰው እባካችሁ? በዚህ የሰላም ዕጦት፣ በዚህ ግድያ፣ በዚህ የቀለብና የቤት ኪራይ ወጪ፣ በዚህ የሐሰት ወሬና አሉባልታ ‹ቢዚ› አድርጎን እንዴት ብለን ነው የአገራችንን ጉዳይ በኅብረት መላ የምንፈልግለት?›› ብላ ጋቢና የተቀመጠች ወይዘሮ ብሶት መፍትሔ ይሆን ይመስል በቁጭት ተናገረች። ኧረ ይኼ ቁጭት ጥሩ አይደለም! 

ከወቅቱ ያስመረረ ሞቃት የአየር ፀባይ ይልቅ የአገር ችግር ያማረረው ነው የበዛው። ታክሲያችን ጉዞ ላይ ናት። ‹‹በቀደም ሶሻል ሚዲያ አንዱ የደላው ሮልስ ሮይስ ተደግፎ አየሁ፡፡ እሱ ሲገርመኝ በንፋስ አመጣሽ ሀብት የከበሩ የሚመስሉ አዲስ የተወለደ ልጃቸውን በሊሞዚን ተቀብለው እጅግ ውድ በሚባሉ መኪኖች አሳጅበው፣ ከሠርግ በማይተናነስ ድግስ በኦርኬስትራ ዕልልታውን ሲያቀልጡት እዚህ አገር መኖር አስጠላኝ…›› ትላለች ጠየም ያለች ቀጭን ቆንጆ። ከሁኔታዋ ነገር ዓለሙን የተፀየፈች ዓይነት ናት። ‹‹ቅንጡዎቹ አንቺን አናደው እንዲህ በንዴት ባያናግሩሽ ኖሮ በዚህ ወበቅ አንችን የመሰለችዋ መቼ ትታየን ነበር? አይደል እንዴ?›› ይላታል ከጎኗ የተቀመጠ ወጣት። እያሳሳቀ ትሆነው እንደሆነ ለመሞከር ያህል። ‹‹የእኛ ነገር ለአንዴው አበሳጭቶ ለአንዴው ደግሞ ፈገግ የሚያደርገን ነገር ነው የሚገርመኝ እኮ። አሁን የአገራችን ችግር ስሞታ ሳያልቅ ከመቼው ትስቃለች?›› ይላሉ አዛውንቷ። ‹‹አይ እማማ ታዲያ እንዲህ ካልሆነ የዘንድሮ ችግራችን ብቻውን አማሮ አይገለንም ነበር?›› ይላቸዋል ከአጠገባቸው ያለ ወጣት። አዛውንቷ ቀና ብለው ወጣቱን ደቂቃዎች ሲያስተውሉት ቆይተው፣ ‹‹ለመሆኑ እየተዘጋጀህ ነው አንተ?›› ብለው ጠየቁት። ምን ይበሉ ታዲያ!

ወጣቱ ከዕድሜያቸው አኳያ የጤንነታቸው ነገር አጠራጥሮት ጥያቄው ግራ እንዳጋባው ይንፀባረቅበታል። ‹‹ለምኑ ነው የምዘጋጀው?›› አላቸው ትኅትናው የድምፁን ክሮች ክፉኛ እያርገበገባቸው። ‹‹ለምኑ? ለገጠመን ችግር ነዋ። ዘንድሮ ለአገሩ ወኔ የሌለው መሳቂያ ሆኖ የሚቀረው ሲባል የትነው ያለኸው?›› ቢሉት የኮረኮሩትን ያህል ሳቀ። የልቡን ነው መሰል የነገሩት። ‹‹አትሳቅ ቀልዴን አይደለም የምነግርህ። በዚህ አስተዛዛቢ ጊዜ እንደ ጀግኖቹ አያት ቅድመ አያቶቻችን ለአገር ዘብ መቆም ማለፊያ ነው…›› ሲሉት ደግመው የታክሲው ተሳፋሪዎች በይሁንታ ተቀበሉ። ይኼኔ ከኋላ መቀመጫ አንዱ ተሳፋሪ፣ ‹‹እማማ አገር ሲባል የሚያንገሸግሻቸው እየበዙ ስለሆነ ምን እናድርግ?›› ሲል፣ ‹‹አገር የጋራ ርስት እንደሆነች በቃልም በተግባርም ማሳየት ነዋ…›› ብለው መለሱለት፡፡ እውነታቸውን እኮ ነው፡፡ አንዳንዱ የአገር ባለቤት ሆኖ ሌሎችን እንደ ባዕድ ማየት ሲቃጣው፣ አንዳንዱ ደግሞ በሆነ ባልሆነው እያኮረፈ ራሱን ሲያገል አስማሚ ከሌለ ሆድና ጀርባ መሆን ይከተላል፡፡ ይህ ደግሞ ማንን በጀ ቢባል ማንንም ይሆናል መልሱ፡፡ አይደለም እንዴ!

ወያላው ሒሳቡን እየተቀበለ ነው። ገንዘብና ስደት ተራቸውን የመወያያ ርዕስ ሆነዋል። ‹‹እውነት አሁን ከምናየውና ከምንሰማው ነገር ስደት ምን ይረባል? የምታገኘው በቂ ባይሆንም አገርን የመሰለ እኮ የለም…›› ሲል አንዱ ከኋላ መቀመጫ ‹‹ይህች አባባል ወደ ግጥም ብትቀየር አሪፍ ነጠላ ዜማ ይወጣታል…›› እያለ ከዚያው መቀመጫ ሌላው ያሾፋል። ‹‹እዚህ አገር ተቀምጦ ሙሰኛ ከመቁጠር፣ የፉገራ ዴሞክራሲ ከማማትና ከመፎገር፣ በሰላም ዕጦት ሌት ተቀን ከማልቀስ ሌላ ምን የተረፈን ነገር አለ? ባይሆን በሕገወጥ መንገድ የሚሰደዱትን ማስቆም እንጂ፣ በሕጋዊ መንገድማ እንኳን እኛ መንግሥትም ቢያገኝ ዓይኑን የሚያሽ አይመስለኝም…›› የምትለው ከኋላ መቀመጫ አንዲት ጠይም ቆንጆ ናት። ‹‹እንዴት ነው ነገሩ? ቁጭ ብሎ ከማላዘን የተበላሸውን በጋራ እናስተካከል ማለት ማንን ገደለ?›› ይላሉ እኚያ እናት፡፡ ግን ማን አዳምጦ!

ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው። ወጪና ወራጁ በዕለታዊ እንቅስቃሴው ተመስጦ አንዱ አንዱን የማየት ትዕግሥት አጥቶ ይራወጣል። ሁሉም የሕይወቱን አቅጣጫ ለማስተካከል ሽር ጉድ ይላል። ታክሲያችን እኛን ወደ ምታራግፍበት አካባቢ ለቁጥር የሚታክት ወረፋ ጠባቂ ለሌላ አዲስ ጉዞ አሰፍስፎ ይጠብቃል። የትራንስፖርት ችግር እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ‹‹ኧረ ጎበዝ በዚህ ዓይነት እስከ መቼ ልንዘልቅ ነው?›› ሲል አንዱ፣ ‹‹ማን አወቀ ብለህ ነው?›› ይለዋል ከወዲያ ሌላው። ‹‹አሁንማ የለም፣ አልቋል፣ ጠፍቷል፣ ጨመረ የሚሉት ቃላት ራሳቸው እንደ ሰለቹን ምንም አልሰለቸንም። ታክሲ ስትሉ የለም፣ ኔትወርክ ስትሉ የለም፣ መብራት ጠፍቷል፣ የእህል ዋጋ በእጥፍ ጨምሯል። እንዲያው ምን እንደሚሻላት ይህች አገር?›› ትላለች ሦስተኛ ወንበር ላይ ያለችው ቀዘባ። ወይ ምሬት!

‹‹ወጡ ሳይወጠወጥ ወስከንባዩ ይሮጥ›› ስለሆነ እኮ ነው የዚህ ሁሉ ችግር መንስዔ። መንግሥት ሳያስበው ዘጠኝ ድስት ጣደና አንዱን ሲለው አንዱ፣ አንዱን ሲለው ሌላው ይኼው የሚያርበት በዛ። ሌላው ቢቀር ሕግ ማስከበር፣ ጥፋተኞችን መቅጣት፣ የኑሮ ጫናን ማቃለል፣ ተዘዋውሮ የመሥራት መብትን ማስከበር፣ ልማቱን ከሕዝብ ጋር እየመከረ ማስኬድ ሲኖርበት…›› እያለ ሲናገር ጎልማሳው ሌላው ድንገት ጥልቅ ብሎ፣ ‹‹እንግዲህ መንግሥት ሥራውን መሥራት ሲያቅተው ፍርድ ቤት ማቅረብ ነው…›› ሲል ከዚህም ከዚያም ጩኸት በዛ። ወያላችን ‹‹መጨረሻ!›› ብሎ በሩን ሲከፍተው ከደጅ የነበረው ወረፋ ጠባቂ እኛ እስክንወርድለት በትዕግሥት መጠበቅ አልቻለም። እንደ ምንም ቀስ በቀስ ወርደን ስንበታተን መሀል ወንበር ላይ ተቀምጦ የነበረው ወጣት፣ ‹‹ኧረ ስቃይም ልክ አለው…›› እያለ መራመድ ሲጀምር፣ ‹‹ጥጋብም ልክ አለው…›› የሚል ድምፅ ከበስተኋላ እየተሰማን ተለያየን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት