Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

በርካታ ሐኪሞችን የሚፈልገው የጨቅላ ሕፃናት ሕክምና

በኢትዮጵያ የጨቅላ ሕፃናት ሞትን ለመቀነስ ባለፉት አሠርታት የተሠሩ ሥራዎች ለውጥ አምጥተዋል፡፡ ሆኖም በጨቅላ ሕፃናት ሕክምና ዘርፍ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ከነበረው ቢሻልም፣ የጨቅላ ሕፃናት ሐኪሞች ምጣኔም ዝቅተኛ ነው፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ የጤና ሚኒስቴር፣ የሕክምና ማኅበራትና ተቋማት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ቦጋለ ወርቁ (ፕሮፌሰር) የኢትዮጵያ ሕፃናት ሕክምና ማኅበር ዋና ዳይሬክተርና የብሔራዊ ፖሊዮ ሠርተፊኬሽን ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው፡፡ በሕክምናው፣ በክትባቱና ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮችን በተመለከተ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ መቼ እንደተቋቋመና በሕፃናት ሕክምና ዙሪያ እያበረከተ ያለውን አገልግሎት ቢያብራሩልን?

ቦጋለ (ፕሮፌሰር)፡– ማኅበሩ ከተቋቋመ 25 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ በሕፃናት ሕክምና ዙሪያ የሚሠሩ ሐኪሞችንና ነርሶችን በአባልነት አቅፏል፡፡ ማኅበሩ ሲቋቋም ዋናው ሥራ ወይም ሐሳቡ ለአባላቱ ቢሆንም፣ ትልቁን ተግባር የሚያከናውነው በሕፃናት ጤንነት ዙሪያ ነው፡፡ ሕፃናት ተገቢውን፣ ጥራቱንና ፍትሐዊነቱን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ነው፡፡ ከጤና ሚኒስቴርና ጉዳዩ በይበልጥ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋርም አብሮ ይሠራል፡፡ በዚህ መልኩ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል የፖሊሲና የምክር አገልግሎት መስጠት፣ በተለያዩ የሥራ መደቦች ውስጥ ገብቶ የክትባት አገልግሎት፣ የጨቅላ ሕፃናት ሕክምናና ኢንፌክሽንን የመከላከል ሥራ ይሠራል፡፡ አባላቱ ማኅበሩን እየወከሉ ጤና ሚኒስቴርን እያገዙ ይገኛሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የጨቅላ ሕፃናት ሕክምናን በተለያዩ ሆስፒታሎች ለማስፋፋት ምን እየተደረገ ነው?

ቦጋለ (ፕሮፌሰር)፡– ጨቅላ ሕፃናትን በተመለከተ በኅብረተሰቡም ሆነ በመንግሥት ደረጃ የነበረው ግንዛቤ ትንሽ ነው፡፡ ትኩረትም አልተሰጠውም፡፡ በኅብረተሰብ ውስጥ አንድ ጨቅላ ሕፃን እንደተወለደ ቢሞት ‹ጠፋ!! ተመለሰ› ነው የሚባለው፡፡ ይህም ሆኖ ሰው ለቅሶ አይደርስም፡፡ ይህም የሚያሳየው ጨቅላ ሕፃን ከሰው ያነሰና ምንም ትልቅ ቦታ እንዳልተሰጠው ነው፡፡ በመንግሥት ዘንድም ትኩረት አልተሰጠውም ብዬ በድፍረት የተናገርኩበት ምክንያት በጊዜው ከነበሩት ከጥቁር አንበሳና ከጦር ኃይሎች ሆስፒታሎች ውጪ ለጨቅላ ሕፃናት ሕክምና የሚሰጥ ምንም ዓይነት የጤና ተቋምም ስላልነበር ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የጨቅላ ሕፃናት ሕክምናን ወደ 300 በሚጠጉ የመንግሥት ሆስፒታሎች ተደራሽ ለማድረግ ተችሏል፡፡ ማኅበሩም ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሕክምናው እንዲስፋፋ፣ የጤና ባለሙያዎችን በማሠልጠን፣ መንግሥትን በማበረታታትና ያሉትንም ችግሮች በማሳየት ከፍተኛ ሥራ አከናውኗል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የጨቅላ ሕፃናት ሕክምና የማግኘት ችግር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ አለ፡፡

ሪፖርተር፡- የጨቅላ ሕፃናት ሕክምና በየሆስፒታሎቹ እንዲስፋፋ ሲደረግም የሕክምናው ጥራት ላይ ምን ተሠርቷል?

ቦጋለ (ፕሮፌሰር)፡– በ300 ሆስፒታሎች ውስጥ የጨቅላ ሕፃናት ሕክምና እንዲከናወን ለማድረግ የሚያስችሉ ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎች እንዲሟላላቸው አቅም በፈቀደ መጠን ጥረት ተደርጓል፡፡ መንግሥትም ለጉዳዩም ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ለመሣሪያዎቹ ግዢ ብዙ ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርጓል፡፡ ማኅበሩም የበኩሉን ተወጥቷል፡፡ ይህ ሁሉ ጥረት ቢደረግም፣ የሕክምናው ጥራት በእጅጉ የወረደ ነበር፡፡ እስካሁንም እየተሠራ ያለው ጥራቱን ለመጠበቅና ፍትሐዊም እንዲሆን ለማድረግ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የተያዘው አቅጣጫ ጥሩ ነው ብለን እናስባለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከምዕት ዓመቱ የልማት ግቦች አንፃር በኢትዮጵያ የሕፃናት ሕክምና ያስገኘው ውጤት እንዴት ይታያል?

ቦጋለ (ፕሮፌሰር)፡– የዓለም መንግሥታት እ.ኤ.አ. በ1991 ስምንት ነጥቦችን የያዙ የምዕት ዓመቱ የልማት ግቦች አውጥተው ሥራ ላይ እንዲውል አድርገው ነበር፡፡ ከነጥቦቹም መካከል በተራ ቁጥር አራት ከተቀመጡት፣ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን ሞት ከ25 ዓመታት በኋላ በሁለት ሦስተኛ መቀነስ የሚል ይገኝበታል፡፡ ኢትዮጵያ ይህንኑ ግብ ከሁሉም አገሮች ቀድማ አሳክታለች፡፡ ያሳካቸውም ለምዕት ዓመቱ የልማት ግቦች ማጠናቀቂያ ከተቀመጠው ከሁለት ዓመት አስቀድማ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰባቱም ግቦች ሲሳኩ፣ በተራ ቁጥር አራት የተቀመጠውና ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን ሞት በሁለት ሦስተኛ መቀነሱ አልተሳካም፡፡ ለምን አልተሳካም ተብሎ ሲፈተሽ፣ የጨቅላ ሕፃናት ሞት በመዘንጋቱ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በዚህም የተነሳ ዓለም በጨቅላ ሕፃናቱ ሞት ዙሪያ ትኩረት ማድረጉን ተያያዘው፡፡ ኢትዮጵያም ይህንኑ አቅጣጫ መከተል ጀመረች፡፡ ኢትዮጵያ በምዕት ዓመቱ የልማት ግቦች በተራ ቁጥር አራት የተቀመጠውን ብታሳካም፣ የጨቅላ ሕፃናት ሞት አልቀነሰም ነበር፡፡ እንደውም በዓለም ውስጥ ጨቅላ ሕፃናት በብዛት ከሚሞቱባቸው አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ስድስተኛ ነበረች፡፡

ሪፖርተር፡- ከምዕት ዓመቱ የልማት ግቦች በፊትና በአሁኑ ጊዜ ያለው የጨቅላ ሕፃናት ሞት መጠንን ቢያብራሩልን?

ቦጋለ (ፕሮፌሰር)፡– ከልማት ግቦቹ በፊት በየዓመቱ ከሚወለዱት 1000 ጨቅላ ሕፃናት መካከል 50 ያህሉ ለሕልፈተ ሕይወት ይዳረጉ ነበር፡፡ በምዕት ዓመቱ የልማት ማገባደጃ ደግሞ የሞት መጠኑ ወደ 33 ዝቅ አለ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ይኸው መጠን ወደ 27 ወርዷል፡፡ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ማለትም እ.ኤ.አ. በ2030 ከሚወለዱት 1000 ጨቅላ ሕፃናት መካከል የሞት መጠኑን ወደ 11 ዝቅ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ በስንት ክልሎች ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ነው? የሕፃናት ሕክምናን አስመልክቶ ተግባራዊ የሆነ አዲስ አሠራር ይኖር ይሆን?

ቦጋለ (ፕሮፌሰር)፡– ማኅበሩ አዲስ አበባንና ድሬዳዋ ከተሞችን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ይንቀሳቀሳል፡፡ በሕፃናት ሕክምና ዙሪያ የተቀናጀ የሕፃናት ሕክምና ተቀርጾ ተግባራዊ ከሆነ ከርሟል፡፡ ይህ ዓይነቱም ሕክምና ከቀድሞው ሕክምና የተለየና የተሻሻለ ነው፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት አንድ እናት በተቅማጥ የታመመባትን ሕፃን ልጇን ወደ ሆስፒታል ይዛ ስትመጣ ተቅማጡን የሚያስቆም መድኃኒት ተሰጥቶት ወይም ታክሞ እንዲመለስ ይደረግ ነበር፡፡ የተቀናጀ የሕፃናት ሕክምና ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ ግን፣ ሕፃኑ ተቅማጥ ይዞት ቢመጣ ለተቅማጥ መከላከያ የሚሆን መድኃኒት ብቻ ሰጥቶ መመለስ ሳይሆን ክትባት መውሰድ፣ አለመወሰዱን፣ የምግብ እጥረትና ትኩሳት፣ የሳምባ ምችን ጨምሮ በአጠቃላይ ስድስት ወይም ሰባት የሚሆኑ ገዳይ በሽታዎች እንዳሉበትና እንደሌሉበት የማጣራትና የመመርመር ሥራ ይከናወናል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ለአባላቱ ምን ዓይነት ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡ የአባላቱስ ብዛት ስንት ነው?

ቦጋለ (ፕሮፌሰር)፡– በአሁኑ ጊዜ አንድ ሐኪም ከተመረቀ በኋላ የሙያ ፈቃዱን በየአምስት ዓመት እያደሰ የሚቀጥልበት አሠራር ተቀይሯል፡፡ ለማደስ የተወሰኑ ትምህርቶችን መውሰድ አለበት፡፡ በእነዚህም ትምህርቶች 150 ነጥብ ማግኘት ይጠበቅበታል፡፡ ይህንንም ከተወጣ በኋላ ሠርተፊኬት ይሰጠዋል፡፡ የሙያ ፈቃዱም ይታደስለታል፡፡ ፈቃዱ የሚታደሰው በየሦስት ዓመቱ ነው፡፡ በዚህ በኩል ማኅበሩ ለአባላቱ በሁለት ዓይነት መንገዶች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ዕገዛና ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ዕገዛና ድጋፍ የሚያደርገው አንደኛው በቨርቹዋል ኔትወርክ ሲሆን፣ ሁለተኛው መንገድ በአካል በመገኘት ነው፡፡ በመላው ኢትዮጵያ ከ500 በላይ የሕፃናት ሐኪሞች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል 300 ያህሉ የማኅበሩ አባላት ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ሞት እንዲቀንስ ያስቻለው ምንድነው?

ቦጋለ (ፕሮፌሰር)፡– የክትባት መርሐ ግብሩ በአግባቡና የጥራት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በመከናወኑ፣ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች በመሠልጠናቸውና በየገጠሩ ያሉትን ሕፃናት ማከም በመቻላቸው፣ የኅብረተሰቡ የኑሮ ደረጃና ጤናውን ከመጠበቅ አኳያ የነበረው አመለካከትና አስተሳሰብ በማሻሻሉና ሌሎችም የጤና እንክብካቤ ሥራዎች በተቀናጀና በተደራጀ መልክ በመከናወናቸው የተፈለገው ውጤት ሊመጣ ተችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- በእርስ በርስ ግጭቶች፣ በድርቅ፣ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ ችግሮች ሳቢያ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያዎች የሚገኙ ሕፃናትን ጤና ለመታደግ ማኅበሩ ምን ያህል ቁርጠኛ ነው?

ቦጋለ (ፕሮፌሰር)፡– በዚህ ዙሪያ ትንሽ አስተዋጽኦ አድርገናል፡፡ ሆኖም ይህን ያህል የሚወራለት አይደለም፡፡ ከዚህ በተረፈ ማኅበሩ ገንዘብ የለውም፡፡ የሚንቀሳቀሰው በአባላት መዋጮ ነው፡፡ በተለያዩ መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ሕፃናትን በሽታዎች ለመታደግ የማኅበሩ አባላት ዝግጁ ናቸው፡፡ ዝግጁነታቸውንም ለሚመለከተው መንግሥታዊ አካልና ለአጋር ድርጅቶች አሳውቀዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ተመራቂ ሐኪሞች ሥራ የማግኘት ዕድላቸው የተጣበበ ነው ይባላል፡፡ በሥራ ላይ ያሉትንም ማቆየቱ ችግር እየሆነ ነው፡፡ በዚህ ላይ ያለዎትን አስተያየት ቢያካፍሉን?

ቦጋለ (ፕሮፌሰር)፡– በሕፃናት ሕክምና ዙሪያ ተመርቆ ሥራ ያጣ ምንም የለም፡፡ ምክንያቱም በጣም ተፈላጊ ናቸው፡፡ ቁጥራቸው 500 ያህል ቢሆን ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉት በእያንዳንዱ የመንግሥት ሆስፒታሎች አንድ የሕፃናት ሐኪም ብቻ ነው ያለው፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ሐኪሞች ግን በጣም በብዙ ቦታ ይመረቃሉ፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ቀደም ሲል የነበሩት ባለሥልጣናት እንደ ጎርፍ ሐኪሞችን እናመርታለን የሚል ፍላጎት፣ ምኞትና ዕቅድ ስለነበራቸው ነው፡፡ ሐሳቡ ጥሩ ቢሆንም፣ ተቋማቱ እነዚህን ሁሉ መቀበል አቃታቸው፡፡ በተረፈ አሁንም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያለው ሐኪም በቂ አይደለም፡፡ በዓለም ጤና ድርጅት ቀመር መሠረት ገና ብዙ ሐኪሞች ያስፈልጉናል፡፡ እውነታው ደሃ መሆናችን ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ለሐኪሞች የሚገባቸው የክፍያ መጠን እየተከፈለ አይደለም፡፡ ይህም በመሆኑ ሁልጊዜ ዓይናቸው የተሻለ ክፍያ ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ዕድሎች ወዳሉበት አቅጣጫ ሁሉ ይሄዳሉ፡፡ በዚህ ዙሪያ የሚያሳዝነው ነገር ቢኖር የሚሄዱት ጀማሪ ሐኪሞች ሳይሆኑ ነባርና የረዥም ዓመት የሥራ ልምድና ዕውቀት ያካበቱ ከፍተኛ ሐኪሞች መሆናቸው ነው፡፡ ጀማሪ ሐኪሞችም ቢሆኑ የሚከፈላቸው ደመወዝ አነስተኛ በመሆኑ የተነሳ ሥራቸውን እየተዉ፣ እየለቀቁና ሙያቸውንም እየቀየሩ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የብሔራዊ ፖሊዮ ሠርተፊኬሽን ኮሚቴ ሰብሳቢ ነዎት፣ ፖሊዮን በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ቦጋለ (ፕሮፌሰር)፡-ፖሊዮ የጥንት ወይም የቆየ እንጂ አዲስ በሽታ አይደለም፡፡ መምጫውም በቫይረስ ሲሆን፣ ፖሊዮ ቫይረስ ታይፕ ዋን፣ ታይፕ ቱ፣ ታይፕ ስሪ  ተብሎ በሦስት ይከፈላል፡፡ ከእነዚህም መካከል ቫይረስ ቱ ከዓለም ጠፍቷል፡፡ በአብዛኞቹ አገሮች ውስጥ ፖሊዮ የለም፡፡ ነገር ግን በምሥራቅ እስያ፣ በፓኪስታንና አፍጋኒስታን ፖሊዮ በብዛትና በስፋት ተንሰራፍቷል፡፡ በአፍሪካ አንዳንድ አገሮች ውስጥም ሄድ፣ መጣ እያለ ነው፡፡ ፖሊዮ ከሌለባቸው አገሮች መካከልም ኢትዮጵያ አንዷ ነች፡፡ ለዚህም ዕውቅና ተሰጥቷታል፡፡

ሪፖርተር፡- ፖሊዮ የሌለባቸው አገሮች ‹ከፖሊዮ ነፃ ናቸው› የሚል ዕውቅና ነው የተሰጣቸው?

ቦጋለ (ፕሮፌሰር)፡– በምንም ዓይነት ከፖሊዮ ነፃ ነው የሚል ዕውቅና አይሰጥም፡፡ ምክንያቱም ፖሊዮ ያለባቸው አገሮች ስላሉ በተለያየ ምክንያት በየአገሩ ሊዛመት ይችላል የሚል ሥጋት አሳድሯል፡፡ ስለሆነም ፖሊዮ የሌለባቸው አገሮች ይህ በሽታ እንዳይዛመትባቸው ተግተው ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተረፈ ኢትዮጵያ ፖሊዮ የለባትም የሚለውን ዕውቅና ያገኘችው መቀመጫውን ጆሃንስበርግ ደቡብ አፍሪካ ካደረገው አፍሪካ ሪጂናል ሠርተፊኬሽን ኮሚሽን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ግምገማው፣ ቁጥጥሩና ክትትሉ የትና እንዴት ነው የሚከናወነው? ይህንንስ የሚያስፈጽመው የትኛው አካል ነው?

ቦጋለ (ፕሮፌሰር)፡– ግምገማውና ክትትሉ የሚካሄደው በፀበል ቦታዎችና በየጤና ተቋማት ነው፡፡ አንድ ልጅ የልምሻ በሽታ ቢይዘው ለሕክምና ወይም ለፈውስ ወደ ጠበልና ጤና ተቋም መሄዱ አይቀሬ ነው፡፡ በተቋሙም የዓይነ ምድር ምርመራ ይደረግለታል፡፡ በምርመራውም የልምሻ በሽታው መንስዔው የፖሊዮ ቫይረስ አለመሆኑ ከተረጋገጠ፣ ለበሽታው ተስማሚ ሕክምና ይደረግለታል፡፡ መንስዔው የፖሊዮ ቫይረስ መሆኑ ከተረጋገጠ ዝርያውን ለመለየት የሚያስችል ምርመራ ለማካሄድ ዕዳሪው ወደ ደቡብ አፍሪካ ይላካል፡፡ በዚህም ልጅ በገባበት ተቋም ቆይቶ ክትባትና ሕክምና ይደረጋል፡፡ ከመጣበትም አካባቢ የሚገኙና ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ሁሉ የፖሊዮ ክትባት ቢከተቡም ባይከተቡም ክትባት እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ ክትትሉንና ግምገማውንም የሚያካሂደው የብሔራዊ ፖሊዮ ሠርተፊኬሽን ኮሚቴ ነው፡፡ የልምሻ በሽታ መንስዔው የተለያዩ ቫይረሶች ናቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱና ዋነኛው የፖሊዮ ቫይረስ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...