Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየክረምት ጉዞና ብሂሉ

የክረምት ጉዞና ብሂሉ

ቀን:

‹‹ሰኔ ደግሞ መጣ ክረምት አስከትሎ

ገበሬው ተነሳ ማረሻውን ስሎ፤

ሐምሌም ተከተለ ገባ ዝናብ ጭኖ

ቀንና ሌሊቱን በዝናብ ጨፍኖ፡፡››

ከአንድ የግጥም ገበታ የተገኘው ይህ አንጓ የኢትዮጵያን ወርኃ ክረምት የያመቱን ገጽታ የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ አርሶ አደሩ በክረምት ወቅት ከፊሎቹ አዝርዕት በሰኔ፣ ገሚሶቹን በሐምሌ እንዲሁም ሌሎቹን ደግሞ በነሐሴና በመስከረም ይዘራል፡፡ አትክልቱንም ይተክላል፡፡

የክረምት ጉዞና ብሂሉ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ከሰኔ አጋማሽ እስከ ነሐሴ በብዙ ነገሩ የክረምት ውበትና ጣዕም ይታይበታል፡፡ ክረምትን ተከትለው የሚመጡት ለመብል የሚውሉት እነ በቆሎ፣ በለስና ስኳር ድንች ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡ ክረምት ለማሰላሰያ ዕድል ይሰጣል የሚሉም አሉ፡፡ ተማሪዎችና መምህራን ሌሎችም ባመዛኙ የሚያርፉበት በመሆኑ የጽሞና ጊዜን እንዲያሳልፉ ዕድል ይሰጣል።

ለዚህም ነው በያሬዳዊ ብሂል የዝናብ ኮቴ ሲሰማ፣ ዝናብ ሲዘንብ የተቸገሩ ይደሰታሉ፣ የተጠሙ የተራቡ ይጠግባሉ የሚባለው፡፡ ፀደያዊው በልግ እንደተገባደደ ሰኔ 26 ቀን የሚገባው የዝናቡ ወራት ክረምት ነው፡፡

መዝሙረኛው እንደሚለው፣ ሰማዩ በደመናት የሚሸፈንበት ለምድርም ዝናብ የሚዘጋጅበት፣ ሣር በተራሮች ላይ የሚበቅልበት ለምለሙ ሁሉ ለሰው ልጆች ጥቅም የሚውልበት ነው ክረምት፡፡ በረዶውና ውሽንፍሩ ብርቱውም ዝናብ በምድር ላይ የሚወድቁበት ነው ክረምት፡፡

የደመናትን ንብርብር፣ ከድንኳኑም የሚሰማውን ነጎድጓድ ማን ሊያስተውል ይችላል? በረዶውን እንደ ፍርፋሪ ያወርዳል፣ በበረዶውስ ፊት ማን ይቆማል? ፀሐይና ጨረቃ ከዋክብትም እንደተዘጋጁ ክረምትና በጋ፣ መፀውና ፀደይ ለሰው ልጅ ሁሉ ተዘጋጁ፡፡

ደብተራና የሕግ ባለሙያው በአማን ነጸረ፣ ‹‹የክረምት ጓዝና ቅኔያት›› በሚለው መጣጥፉ፣ ዕፀዋትና ዝናም ያላቸውን ተዘምዶ የሚያጠቃቅስ የአንድ መምህር ቅኔን ምስጢር በአንድ ዓረፍተ ነገር ያጠቃለለው ‹‹ወዳጄ! የሰማይ ጉድለት፣ ምድርን በዕፀዋት ስትከድናት ይሞላል›› በሚል ነው፡፡ አከለበትም፡፡ ‹‹ዕፀዋት ካሉ፣ ዝናማት አሉ! የዝናም መውረድ መቆም በዕፀዋት ነው!››፡፡

የክረምት ጉዞና ብሂሉ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ነገረ ዛፍ

ዛፍ ከባህልና ከኪነ ጥበባት ጋር የተቆራኘ በተረትና ምሳሌ የመገለጽ ዕድሉም የጎላ ነው፡፡ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ዛፍ ተምሳሌታዊ ነው፡፡ የቤተሰብን መሠረት፣ የመኖሪያ አካባቢን በማጠናከር ረገድ ይጠቀሳል፡፡

ዛፍ የተለያየ ዓይነት ዝርያ እንዳለው ሁሉ አንዱ ከአንዱ ልዩነት ያለው በመሆኑም ለተለየ አገልግሎት የሚመረጥ ይሆናል፡፡ ከሰዎችም የሚለዩ በሥልጣን፣ በዕውቀት ወይም በሹመት የሚመረጡ ልሂቃንም ይኖራሉና፡፡ «ከሰው መርጦ ለሹመት ከዛፍ መርጦ ለታቦት» የተሰኘውን አነጋገር አትርፏል፡፡

በዕውቀት የጎለመሱ፣ ለአገር መልካም ትሩፋት ያተረፉ ሊቃውንት የመበርከታቸው ያህል «የአቡጊዳ ሽፍቶች»፣ ለዕውቀት የማይተጉም ያጋጥማሉ፡፡ ሊቃውንቱ በዝምታ ይሁን በቦታው ባለመኖራቸው ብልጣ ብልጦች የሚከሰቱበት አጋጣሚም አይጠፋም፡፡ በዚህም አጋጣሚ ነው የዛፍ ተምሳሌታዊነት ብቅ ያለው፡፡ «ዛፎች ቢጠፉ፣ ቁጥቋጦዎች ተሠለፉ፣ ዋርካ በሌለበት ዋጮ አድባር ይሆናል፡፡» ተብሎ የተተረተው፡፡

በየዓለሙ   የሚገኙ ኅብረተሰቦች  ለዛፎች  ልዩ  ክብር  እንደሚሰጡ  በየአገሮቻቸው ስለዛፍ  ከተነገሩ  ቁምነገሮች  መረዳት  ይቻላል፡፡ የሥነ ሕይወት  ፕሮፌሰሩ ለገሠ ነጋሽ  ካጠናቀሩት የሚከተሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡     

አንድ ጸሐፊ፣ ኤመርሰን ‹‹በዛፎች ስታጀብ  በጥበብና  በእምነት  እታጀባለሁ፤›› ብሎ የተናገረውን  ተንተርሶ፣  በጥበብና  በእምነት ለመታጀብ  ከፈለግህ ለአረንጓዴ አሻራ ቀን ስኬት ዛፍን  በተለይም አገር በቀሉን እንትከል ብሏል፡፡ የዛፍ  ምስጢሩ  ውበቱ  ብቻ ሳይሆን፣ ተስፋን  ማጫሩ ሕይወትን ማደሱ ነው፡፡ እውነትን መሻት ጥሩ ነው፣ የበለጠ  ጥሩው ግን  ስለ ዛፍ እውነቱን መናገር ነው፡፡ ‹‹ሠርግ ደግስ ደስታህ ያንድ ቀን ነው፣ ተሾም ተሸለም፣ ደስታህ  ያንድ ወር ነው፣ ዛፍ ትከል፣ ደስታህ የዕድሜ ልክ ነው፡፡››

‹‹የደን ደሴት››

‹‹የኢትዮጵያ  ቤተ ክርስቲያን  ሚና  በአየር ንብረት ለውጥ››  በሚል ርዕስ ያጠኑት የቅርስ ባለሙያው አቶ ተስፋዬ አራጌ እንደገለጹት፣ የቤተ ክርስቲያን ተፈጥሯዊ  ደኖች  አገር በቀል ዛፎች ለዘር ተርፈው የሚገኙባቸው የደን ደሴት ፈጥረዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያን የሚገኙ ደኖችን መቁረጥ በቃለ ዓዋዲ የተከለከለና የተወገዘ ነው፡፡ ምዕመኑ የቤተ ክርስቲያን አፀድን መቁረጥ የሚያስቀስፍ እንደሆነ ስለሚያምን አይደፍርም፤ እንሰሳትንም አያስገባም፡፡

‹‹አፀድ የሌለው ደብር ጽሕም  የሌለው መምህር፣ ለሰው  ጨርቅ ነው ልብሱ፣ ለቤተ ክርስቲያን ደን ነው ሞገሱ፣ ጥምጣም የሌለው ካህን፣ አፀድ የሌለው ቤተ ክርስቲያን›› የሚሉት የማኅበረሰቡ ብሂሎች የቅዱሳን መጠለያና መጠጊያ ሆኖ ለኖረው የቤተ ክርስቲያን የተፈጥሮ ደን ምዕመናን ያላቸውን አመለካከትና አክብሮት የሚያጠይቁ ናቸው፡፡

እንደ አቶ ተስፋዬ ማብራሪያ፣ ኦርቶዶክሳዊቷ ቤተ ክርስቲያን ያለውን አገር በቀል ዛፍ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን አዲስ ችግኞችን በመትከልና በመከባከብ  የተፈጥሮ አካባቢን በመጠበቅ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተች ትገኛለች፡፡ በዚህ የተነሣ ቤተ ክርስቲያኗ የራስዋን ቅጥር በደን ከመሸፈን አልፋ ዛሬ በሰሜኑ ክፍል ለሚገኙ ብሔራዊ  ፓርኮች መመሥረት ምክንያት እንደ ሆነች መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ የስሜን ብሔራዊ ፓርክ ለመመሥረቱ ከሚጠቀሱት ምክንያቶች አንዱ የቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን በቦታው መኖሩ ነው፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን የደንቆሮ ደን ብሔራዊ ፓርክ መነሻው የምስካበ ቅዱሳን ማርያም ገዳም መሆኗ፣ እንዲሁም በጣና ደሴት ለሚገኘው የተፈጥሮ ደን ጥበቃ ዋነኛው የገዳማቱ መኖር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጥናት በተደረገባቸው የደቡብ ጎንደር ሦስት ወረዳዎች  እንደታየው፣ እንደ ሊቦ ከምከም ጣራ ገዳምና በፋርጣ ወረዳ የሚገኘው የዓለም ሳጋ  የመንግሥት ደኖችና በዳራ ወረዳ የመካነ ሰማዕት ገላውዴዎስም ከገዳማት ይዞታዎች የተወሰዱና ዛሬም ከገዳማቱ ጋራ የተቆራኙ መሆናቸውን በጥናታቸው ጠቁመዋል፡፡

አረንጓዴ አሻራ

ክረምቱን ተከትሎ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በየአካባቢያቸው ከቀደመው ጊዜ ጀምሮ ችግኝ የመትከል ልማድ እንዳለ ይታወቃል፡፡  በኢትዮጵያ ሚሌኒየም ክብረ በዓል አጋጣሚ  በሦስተኛው  ሺሕ  መቀበያ  ዋዜማ ‹‹ሁለት  ዛፍ  ለሁለት  ሺሕ››  እና  ‹‹ሦስት ዛፍ ለሦስት ሺሕ›› በሚል  መሪ ቃል የችግኝ  ተከላው በወቅቱ ተከናውኗል፡፡

ልጄ ብቻ  አይደለም  ትምህርት  የሚያስፈልገው ደጄም ዛፍ  ማግኘት አለበት በሚል  መነሻም ‹‹ትምህርት ለልጄ፣ ዛፍ ለደጄ››  የሚለው  ብሂልም ተንፀባርቆ ነበር፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ  መንግሥት በተለመው መርሐ ድርጊት መሠረት ‹‹የአረንጓዴ አሻራ ቀን›› በሚል መጠሪያ አገር አቀፍ ችግኝ ተከላ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...