Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአዲስ አበባን የፈተናት ያልተናበበ አካባቢ ጥበቃ

አዲስ አበባን የፈተናት ያልተናበበ አካባቢ ጥበቃ

ቀን:

በቀንም ሆነ በማታ የሚሠሩ ወንጀሎች፣ ለአካባቢ ብክለት መንስዔ የሚሆን ቆሻሻ በዘፈቀደ ሲወገድና ሌሎችም ተመሳሳይ ችግሮች ሲፈጸሙ ከማኅበረሰቡ ዓይን የተሰወሩ አይደሉም፡፡

ሆኖም የአካባቢ ብክለትን የሚያባብሱ ሕገወጥ ድርጊቶች መልካቸውን እየቀያየሩ በየ ዕለቱ አጀንዳ ሆነው ቀጥለዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት በርካታ ሕጎችና መመርያዎች ቢፀድቁም፣ ተፈጻሚነታቸው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ሰኔ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. የከተማዋን የአየር ብክለት ለመከላከል እየገጠሙ ያሉ ችግሮችና የተሠሩ ሥራዎችን ለመገምገም ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ በውይይቱ ወቅትም ለከተማዋ ብክለት መንስዔ ናቸው የተባሉ የተለያዩ ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡

የኅብረተሰቡ የግንዛቤ ለውጥ አለመኖር፣ የባለድርሻ አባላት ተቀራርቦና የወጣውን የቅጣት ሕግ መሠረት አድርጎ አለመሥራትና መመርያውን በሚተላለፉ አካላት ላይ ዕርምጃ አለመውሰድ ዋና ዋናዎቹ ናቸው ተብሏል፡፡

አስፈጻሚ አካላት ሥራቸውን ለይተው ባለማወቃቸው የተለያዩ ጥፋቶች እየደረሱ ነውም ተብሏል፡፡

ጤናማ ከተማ ለመገንባት የወጡ አስገዳጅ ሕጎችን ለማስፈጸም የፍትሕ አካላት ድርሻ እጅግ የጎላ ነው ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋለልኝ ደሳለኝ ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት እየታዩ ላሉ ችግሮች ዋነኛ መነሻቸው ከተማዋ የመጣችበት የእድገት መንገድ ነው በማለትም፣ ቀደም ሲል በዘፈቀደ በወንዞች ዳርቻ የሰፈሩ ሰዎችን አሁን ለሚታየው የወንዞች ብክለት ተጠያቂ አድርገዋል፡፡

በወቅቱ የተቋቋሙ ኢንዱስትሪዎች ፍሳሻቸውን ለማስወገድ በሚል ወንዞችን መሠረት አድርገው መቋቋማቸው፣ በአሁኑ ወቅት በወንዞችና በከተማዋ መካከል ያለውን ዕድገት ለማስታረቅ ፈተና ነው ብለዋል፡፡

ችግሩን ለማቃለል በተለይ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ቆሻሻ አወጋገድ ሕጎች መውጣታቸውንና ሕጉን ተላልፈው በሚገኙት ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድ አክለዋል፡፡

ከመኖሪያ ቤትም ሆነ ከኢንዱስትሪ የሚወጣን ቆሻሻ ከወንዝ ጋር በሚያገናኙ ተቋማትና ግለሰቦች ቁጥጥር እየተደረገ ቢሆንም፣ የፖሊስ አካላት ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአካባቢ ብክለትን በሚጨምሩ ጉዳዮች ላይ የፍትሕ አካላት ተሳትፎም ዝቅተኛ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ዋለልኝ፣ ተቋማቸው ወንጀለኞችን ይዞ ካልሰጣቸው እንደ ሌሎች ወንጀሎች ተከታትለው የመቆጣጠርና ጥፋተኞችን በሕጉ መሠረት የመቅጣት ሁኔታ እንደማይታይ ጠቁመዋል፡፡

ቆሻሻን በየአካባቢው መጣል፣ ፍሳሽን ከወንዝ ጋር ማገናኘትና መሰል ችግሮች የሕግ ጥሰት ናቸው? ወይስ አይደሉም? የሚሉትን አለመረዳት በፖሊሶች ዘንድ የሚታዩ ውስንነቶች እንደነበሩ ተረድተናል ያሉት አቶ ዋለልኝ፣ ችግሩን ለመፍታት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ዘንድሮ በተሠሩ ሥራዎች ከአሥር ሺሕ በላይ ተቋማት ከገንዘብ ቅጣት እስከ ማሸግ የሚደርስ ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡

ወንጀሎቹ በቀንና በሌሊት የሚሠሩ መሆናቸውና የሰዎች የኃላፊነት ጉድለት ሥራቸውን ከባድ እንዳደረገው የተናገሩት ምክትል ሥራ አስኪያጁ፣ የአስፈጻሚ አባላት የግንዛቤ ጉድለትም ሌላኛው ፈተና መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሁሉም አካላት የሚታይ የግንዛቤ ማነስ፣ የቅንጅት ሥራ ጉድለት፣ ኅብረተሰብን አለማሳተፉ፣ የመረጃ ልውውጥ እጥረት፣ ባልተፈቀደ ሁኔታ የአረንጓዴ ቦታ በሚል መውረርና ግንባታ መገንባት እየታዩ ያሉ ክፍተቶች ተብለው የተጠቀሱ ናቸው፡፡

የሚወጡ ሕጎች ተፈጻሚ ካለመሆናቸው ባሻገር ቆንጠጥ የሚያደርጉና ለሌሎች ማስተማሪያ ሊሆኑ የሚችሉ አይደሉም የሚሉ አስተያየቶችም ቀርበዋል።

የምሽት ጭፈራ ቤቶችና የተሽከርካሪ ድምፆች፣ ካረጁ ተሽከርካሪዎች የሚወጣው በካይ ጋዝ፣ በመንገድ ዳር ሽንት መሽናትና ሌሎች በርካታ ቅጣት ሊያስከትሉ የሚችሉ ድርጊቶች ዛሬም በቅንጅት ከመሥራት ማነስ የተነሳ ችግር ሆነው መቀጠላቸው ተነግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...