Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የደረሰው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ

የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የደረሰው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ

ቀን:

ከተጀመረ 13 ዓመታትን ያስቆጠረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሒደት 96 በመቶ መድረሱን የፕሮጀክቱ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያውያን ተሳትፎ እየተገነባ የሚገኘው ይህ ፕሮጀክት፣ ከግብፅና ሱዳን ተቃውሞ የገጠመው ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ የሁለቱንና የሌሎችንም አገሮች ጫና ተቋቁማ ግድቡን ወደ ማጠናቀቅ ምዕራፍ ደርሳለች፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ፣ በግለሰብም ሆነ በተቋም ደረጃ በርካታ ኢትዮጵያውያን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የሲቪል ማኅበራት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት፣ ከፍተኛ የሲቪክ ማኅበራትና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ተሳትፎ አደረጃጀት ባለሙያ አቶ እንቻለው ታደሰ እንደሚናገሩት፣ እስካሁን ከተሰባሰበው የ19.5 ቢሊዮን ብር ድጋፍ 17 ቢሊዮን ብር ያህል የተሰበሰበው ከአገር ውስጥ ቦንድ ሽያጭ ነው፡፡ ይህም ሲቪክ ማኅበረሰቡ በግድቡ ግንባታ የነበረውን አስተዋጽኦ በጉልህ የሚያመላክት ነው፡፡

‹‹በኢትዮጵያ ከ500 በላይ ሲቪክ ማኅበራት በተለያዩ የልማት ዘርፎች ተሠማርተው ይገኛሉ፤›› ያሉት ባለሙያው፣ 96 በመቶ የተጠናቀቀውንና ቀሪ የአራት በመቶ ሥራ ብቻ የቀረውን ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ የሲቪል ማኅበራት ድርሻ ወሳኝ በመሆኑ ድጋፋቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

የፕሮጀክቱን ሥራ ለማጠናቀቅ ከ40 እስከ 45 ቢሊዮን ብር ያስፈለገበት ምክንያትንም ‹‹ሥራው ውስብስብና ዘመናዊ የሆነ ቴክኖሎጂ የሚጠይቅ፣ ቴክኒካል ባለሙያዎች የሚሳተፉበትና የውጭ ምንዛሪም የሚጠይቅ በመሆኑ ነው፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም የሲቪክ ማኅበራት ለፕሮጀክቱ ቀሪ ሥራዎች ሀብት በማሰባሰብና ከፕሮጀክቱ ጋር ተያያዥነት ባላቸው የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ላይ ተሳትፏቸውን እንዲያጎለብቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

እንደ አቶ እንቻለው፣ የሲቪክ ማኅበራት ባለፉት 13 ዓመታት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በዘርፉ የተለያዩ አደረጃጀቶች ላይ የሚገኙ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት አባልና መሥራች ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩና አሁንም በማገልገል ላይ ናቸው፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውኃ ሀብት ምሕንድስና መምህር አብደላ ከማል (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የዝናብ መጠን ከሚያገኙ አገሮች መካከል ትጠቀሳለች፡፡ ሆኖም ይህ ከዝናብ የሚገኘው ውኃ አብዛኛው በትነት መልክ የሚባክን ነው፡፡ አሁን ላይ ኢትዮጵያ አላት የሚባለው የውኃ ሀብት 122 ሜትሪክ ኪዩቢክ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆነው በወንዞችን አማካይነት ድንበር ተሻግሮ የሚወጣ ነው፡፡ ድንበር አቋርጠው ከሚወጡ ወንዞች መካከል ተከዜ፣ ዓባይና ባሮ አኮቦ ብቻ የአገሪቱን 70 በመቶ የውኃ ሀብት የሚይዙ ናቸው፡፡

አብደላ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ባለመሆኑ፣ የህዳሴው ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማያገኘው 50 ሚሊዮን ሕዝብ የኃይል አቅርቦት እንዲያገኝ በማድረግ በኩል ከፍ ያለ ሚና ይኖረዋል፡፡

በተጠኑ ጥናቶች መሠረት የኢትዮጵያ የኃይል ፍላጎት በየዓመቱ 30 በመቶ ዕድገት እያሳየ በመምጣቱ ፣ ይህንን የኃይል ፍላጎት በማሟላት ረገድ ግድቡ በተጨማሪ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ይሆናል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ወንዞች ከ45 እስከ 50 ሺሕ ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ቢኖራቸውም በጥቅም ላይ የዋለው አሥር በመቶ ብቻ መሆኑን፣ የህዳሴ ግድቡ መጠናቀቅ ከቻለና ሙሉ በሙሉ ኃይል ማመንጨት ሲጀምር ይህ ቁጥር ወደ 20 በመቶ ሊያድግ የሚችል ይሆናል ብለዋል፡፡

ግድቡ ከሕዝቡ የማደግና የመልማት ፍላጎት በመነጨ ካለ ማንም የውጭ ለጋሽ አገሮች ድጋፍ በኢትዮጵያውያን አቅም ብቻ እየተገነባ ይገኛል ያሉት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፣ አሁን ላይ የግድቡን 96 በመቶ ሥራ ማጠናቀቅ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

እስካሁን ሁለት ተርባይኖች ተገጥመው ሥራ መጀመራቸውን፣ በቀሪው ጊዜ 11 ተርባይኖች በግድቡ ለመግጠምና ሙሉ በሙሉ ኃይል ለማመንጨት ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡

የህዳሴው ግድብ ቀሪ ሥራዎችን ለማከናወን እንዲቻል የሲቪክ ማኅበረሰቡ፣ ዳያስፖራውና ሕዝቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ የሚሰጡትን ድጋፍ ለማሳደግ ‹‹It’s My Dam›› (ግድቡ የእኔ ነው) የሚል መተግበሪያ ሥራ ላይ መዋሉ በቅርቡ መገለጹ ይታወሳል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...