Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምበኬንያ ተቃውሞ ያስነሳው የታክስ ማሻሻያ ሕግ

በኬንያ ተቃውሞ ያስነሳው የታክስ ማሻሻያ ሕግ

ቀን:

የኬንያ ፓርላማ አገሪቷ ያለባትን ከፍተኛ የዕዳ ጫና ለማቃለል ይረዳል በተባለው የታክስ ጭማሪ ረቂቅ ሕግ ላይ ሲመክር፣ ተቃዋሚዎች ደግሞ ብሶታቸውን አደባባይ በመውጣት መግለጽ የጀመሩት ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡

በኬንያ ተቃውሞ ያስነሳው የታክስ ማሻሻያ ሕግ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ወጣቶች ስለአዲሱ የታክስ ማሻሻያ ረቂቅ መረጃ ከማግኘት ባለፈ የየአካባቢያቸውን
የፓርላማ ተወካይ እንዲያገኙ ጥሪ ቀርቧል (ኢፒኤ)

በግንቦት 2024 ይፋ ሆኖ ባለፈው ሳምንት የኬንያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተከራከረበት ሕግ፣ ሰኔ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. የፀደቀ ቢሆንም፣ ኬንያውያን ተቃውመውታል፡፡

ባለፈው ሳምንት የተጀመረውና ሕጉ የመጨረሻ ውሳኔ በሚያገኝበት ሰኔ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ዳግም የተጠራው ተቃውሞ፣ በኬንያ ናይሮቢን ጨምሮ በ19 ግዛቶች ውስጥ መካሄዱን ኔሽን ዘግቧል፡፡

የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ይፋ ያደረጉትን ‹‹የፋይናንስ ቢል›› የታክስ ማሻሻያ ረቂቅ ሕግ፣ ኬንያውያን መቃወማቸውን ተከትሎ የተወሰኑ ማሻሻያዎች የተደረገበት ቢሆንም፣ የታክስ ማሻሻያው ሙሉ ለሙሉ ውድቅ ይደረግ የሚል ውዝግብም አስነስቷል፡፡

በኬንያ ተቃውሞ ያስነሳው የታክስ ማሻሻያ ሕግ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ለሳምንት የዘለቀው የኬንያውያን ተቃውሞ

ባለፈው ማክሰኞ ተጀምሮ እስከ ትናንት የቀጠለው ተቃውሞ፣ በተጀመረበት ሳምንት ሰላማዊ የነበረ ቢሆንም፣ የፀጥታ አካላት በወሰዱት የአስለቃሽ ጭስ፣ የውኃ ርጭት በኋላም ለአንድ ሰው ሞት ምክንያት በሆነው የጥይት ተኩስ ሳቢያ፣ ተቃውሞው ወደ አመፅ ተቀይሮ ነበር፡፡

ትናንት ለተጠራው ሰልፍ፣ ኬንያውያን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተቃውሟቸውን እንዲገልጹ የኬንያ መንግሥት ጥሪ ያቀረበ ቢሆንም፣ ተቃውሞው ወደ ግጭት አምርቷል፡፡

ቢቢሲ እንደዘገበው፣ በናይሮቢ ወደ ፓርላማ በመጠጋት ፖሊስ ማለፍ ከከለከለበት መስመር ካለፉ ተቃዋሚዎች ጋር ግጭት ተፈጥሯል፡፡

ተቃዋሚዎች የፖሊስን ገደብ አልፈው ፓርላማውን የወረሩ ሲሆን፣ የፓርላማው የተወሰነ ክፍል በእሳት መያያዙም ተነግሯል፡፡ ቀጥታ ያስተላልፉ በነበሩ የአገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያዎችም፣ ከፓርላማው ሕንፃ ጭስ ሲወጣ ታይቷል፡፡  

የፓርላማ አባላት ተቃውሞ የገጠመውን የታክስ ሕግ ባፀደቁበት ቅስበት ፓርላማው በተቃዋሚዎች መወረሩን ተከትሎ፣ ፖሊስ በአራት ሰዎች ላይ ተኩሶ ጉዳት ማድረሱንም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ኮንነዋል፡፡ አምስት ሰዎች መገደላቸውም ተነግሯል፡፡

በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ከፖሊስ ጋር ግብግብ ሲገጥሙ፣ በርካታ የፖሊስ ተሽከርካሪዎችም ተቃጥለዋል፡፡ የንግድ ተቋማት ሲዘጉ፣ ትራንስፖርትም ተቋርጧል፡፡

ውዝግብ ያስነሳው የኬንያ የታክስ ማሻሻያ ሕግ ምን ይላል?

በኬንያ ተቃውሞ ያስነሳው የታክስ ማሻሻያና ጭማሪ፣ በዲጂታል መንገድ የሚተላለፉ ይዘቶች ላይ ቀረጥ መጣልን  ጨምሮ በዲጂታል መንገድ በሚፈጸሙ ክፍያዎችም የአምስት በመቶ ጭማሪን ያካትታል፡፡

የባንክ የገንዘብ ዝውውር፣ የዲጂታል ክፍያና በተለይም የሞባይል ገንዘብ ዝውውር ኬንያውያን አብዝተው የሚጠቀሙበትና የገንዘብ ዝውውራቸውንም በዚህ ያደረጉ በመሆኑ በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳል የሚል ተቃውሞ የተነሳበት ነው፡፡

ኬንያውያንን ይበልጥ ለታቃውሞ ያስወጣቸው ደግሞ በአትክልት ዘይትና በዳቦ ላይ የተጣለው ግብር ነው፡፡ አልጄዚራ እንደዘገበው፣ የታክስ ማሻሻያው በዳቦ ላይ የ16 በመቶ ተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) እንዲሁም በኬንያ በሚመረቱና ለምግብነት በሚውሉ የአትክልት ዘይት ምርቶች ላይ የ25 በመቶ የኤክሳይዝ ታክስ ጥሏል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው የደመወዝ ግብር የ2.75 በመቶ ጭማሪ እንዲሁም ለተሽከርካሪዎች የተጣለው የ2.5 በመቶ ዓመታዊ ግብር ውዝግብ ካስነሱት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

ተቃዋሚዎች እንደሚሉት፣ በተለይ በዳቦና በምግብ ዘይት የተጣለው ታክስ አጠቃላይ የግብዓቶችን ዋጋ ያንረዋል፡፡

የትኞቹ የታክስ ዓይነቶች እንዲወጡ ተደረገ?

ኬንያውያን የቀረበውን የታክስ ረቂቅ በመቃወማቸው በረቂቁ ላይ ማስተካከያ ተደርጓል፡፡ ሆኖም ኬንያውያን የታክስ ረቂቅ አዋጁ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡

ተቃውሞውን ተከትሎ በተደረገ ማሻሻያ መሠረት፣ ሕግ አውጪው ክፍል በዳቦ፣ በምግብ ዘይት፣ በተሽከርካሪዎች፣ የሞባይል የገንዘብ ዝውውርን ጨምሮ በዲጂታል የገንዘብ ዝውውሮች ላይ አስቀምጦ የነበረውን ታክስ አንስቷል፡፡

ለአየር ንብረት ተስማሚ የሚሆኑ ምርቶችን ለማበረታታት ሲባል ከውጭ በሚገቡ የፕላስቲክ ምርት የሆኑ ዳይፐር፣ ሶፍትና ስልኮች ላይ የተጣለው ታክስ ባይነሳም፣ እነዚህ ምርቶች በአገር ውስጥ የተመረቱ ከሆነ ከታክስ ነፃ ይሆናሉ፡፡

በደመወዝ ለሚተዳደሩ ዜጎች የሕክምናና የቤት ኢንሹራንስ ላይ ተጥሎ የነበረው ቀረጥ እንዲቀንስም ተደርጓል፡፡

የታክስ ጭማሪ ረቂቅ አዋጁ ለምን ፖለቲካዊ ይዘት ኖረው?

እንደ ተቃዋሚዎች፣ አዲሱ የታክስ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ኬንያውያንን ለከፋ ችግር የሚዳርግ ነው፡፡ ምክንያቱም በኬንያ የምግብና የኑሮ ወጪ በጣም ጨምሯል፡፡ በተለይ እ.ኤ.አ. በ2023 የታክስ ጭማሪ ከተደረገ በኋላ፣ የኑሮ ውድነት አይሏል፡፡

የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ፣ በ2022 ሥልጣን ከያዙ በኋላ የታክስ ጭማሪ የተደረገ ቢሆንም፣ የመንግሥት አገልግሎቶች አልተሻሻሉም፡፡

አምና 1.5 በመቶ የቤት ታክስ መደረጉ እንዲሁም በነዳጅ ላይ የነበረው የስምንት በመቶ ተጨማሪ እሴት ታክስ ወደ 16 በመቶ ማደጉ፣ በኬንያውያን ኑሮ ላይ አሉታዊ ጫና አሳድሯል፡፡ በዚህም በቀጣዩ ምርጫ ሩቶን አትምረጡ የሚል መልዕክት በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ተስተጋብቷል፡፡

የኬንያውያንን ሕይወት አሻሽላለሁ ብለው የምረጡኝ ቅስቀሳ ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሩቶ፣ ሥልጣን ከያዙበት ከ2022 ጀምሮ የተለያዩ የታክስ ጭማሪዎችን አድርገዋል፡፡

ኬንያ 11.1 ትሪሊዮን የኬንያ ሽልንግ ወይም 82 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ መክፈል አለባት የሚሉት ሩቶ፣ የታክስ ጭማሪ ማድረግ ያስፈለገው ዕዳ ለመክፈል መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ኬንያ በ2024፣ 3.3 ትሪሊዮን የኬንያ ሽልንግ ከታክስ ለመሰብሰብ ያቀደች ሲሆን፣ ሩቶም ከታክስ ተጨማሪ ገቢ ማግኘትን ዓላማ አድርገዋል፡፡

የታክስ ረቂቁን ተቃውመው ሰልፍ ለወጡ ኬንያውያንም ‹‹ዴሞክራሲን የምንተገብር አገር ነን፣ ተቃውሞ ማድረግ የሚፈልጉ መብታቸው ነው፡፡ ውሳኔ የሚተላለፈው በተቋም ደረጃ ነው፡፡ እንደ ሥራ አስፈጻሚ ነው የምንወስነው፡፡ ጉዳዩን ወደ ሕግ አውጪዎች ውሰዱት፣ ኬንያውያን በሕዝባዊ ተሳትፎ ስለጉዳዩ ያውሩ፣ ሌሎች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ይውሰዱት፡፡ ዴሞክራሲ የሚሠራው እንዲህ ነው፡፡ እኔም በዴሞክራሲ አምናለሁ፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...