Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናክልሎች ለፌዴራል ፕሮጀክቶች ካሳ እንዲከፍሉ የሚያስገድድ አዋጅ ፀደቀ

ክልሎች ለፌዴራል ፕሮጀክቶች ካሳ እንዲከፍሉ የሚያስገድድ አዋጅ ፀደቀ

ቀን:

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል መንግሥት ለሚያከናውናቸው መሠረተ ልማቶችና ማኅበራዊ አገልግሎት ማስፈጸሚያ ሥራዎች፣ ንብረት መገመትና ካሳ መክፈል ክልሎች እንዲያስፈጽሙ የሚያስገድድ አዋጅ አፀደቀ፡፡

ምክር ቤቱ ትናንት ማክሰኞ ሰኔ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፣ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትን፣ ካሳ የሚከፈልበትንና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ድንጋጌ የያዘ ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ ላይ ተወያይቶ አፅድቋል፡፡

በምክር ቤቱ የፀደቀው አዋጅ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን በተመሳሳይ ወጪና ተቀራራቢ በሆነ ጊዜ እንዲጠናቀቁ የሚያስችል አሠራር የሚደነግግ፣ በሁሉም ክልሎች ወጥ ሊባል የሚችል የካሳ ተመን ያወጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል፡፡

የመሠረተ ልማት ግንባታ ወጪ፣ ጥራትና ጊዜ ቆጣቢ ሆኖ እንዲከናወን ለማስቻል፣ ካሳ የመክፈል ኃላፊነትን ከመሠረተ ልማት ገንቢ ተቋም በማንሳት፣ ለክልልና ለከተማ አስተዳደር አካላት መስጠት አስፈላጊ መሆኑ እንደታመነበት ተገልጿል፡፡

በሥራ ላይ ባለው አዋጅ የፌዴራል ፕሮጀክቶች የፌደራል መንግሥት ባለው የጎላ ሚና ምክንያት ከፍተኛ ካሳና ወጪ እየተጠየቀባቸው፣ ነገር ግን በክልል ባለቤትነት የሚከናወኑት ደግሞ በዝቅተኛ ወጪ እየተገነቡ ስለሆነ አዲሱ ሕግ ይህን ከልክ ያለፈ የካሳ ጥያቄና የክፍያ ልዩነት ያስቀራል ተብሏል፡፡

በተጨማሪም የወሰን ማስከበር ሥራ ላይ የሚሳተፉት አካላት በርካታ በመሆናቸው፣ የንብረት ማስነሳትና ለልማት የሚፈለገውን መሬት ከንብረት ነፃ አድርጎ ለማስረከብ የሚወሰደው ጊዜ እጅግ የተራዘመ በመሆኑ፣ ተሻሽሎ በፀደቀው አዋጅ ንብረት ገማቹና ካሳ ከፋዩ አካል ወረዳና ከተማ ከሆነ ሥራውን በባለቤትነት ስሜት እንዲሠራ እንደሚያደርገው ተብራርቷል፡፡

በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ንብረቶቹ ከሚያወጡት ዋጋ በላይ የተጋነነ ዋጋ እንዲከፈል በርካታ ጥያቄ ስለሚቀርብ፣ የእርሻ ማሳዎች ከሚሰጡት ምርታማነት በላይ እጅግ የተጋነነ ምርት ከአንድ ማሳ እንደሚገኝ ተደርጎ ዋጋ የሚሰላ በመሆኑ፣ ክፍያ የተራዘመባቸው ንብረቶች ጊዜን ታሳቢ አድርጎ በቅልጥፍና ስለማይነሱ፣ ሕገወጥ ግንባታዎች እየተበራከቱ በመምጣታቸውና የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜና በጀት ስለማይጠናቀቁ፣ ባለቤትነቱን ለክልል መንግሥታት መስጠት አስፈላጊ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በመሆኑም ለመሠረተ ልማት ካሳ የሚከፈለውን ገንዘብ የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች ከሚመድበው የበጀት ድጋፍ ጋር የካሳ ክፍያ ታሳቢ ተደርጎ ገቢ እንደሚደረግ፣ በፀደቀው አዋጅ ማብራሪያ ላይ ተገልጿል፡፡

በመሠረተ ልማት ግንባታ ሒደት በአንድ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ወረዳዎችን ወይም ከተማ አስተዳደሮችን የሚመለከት ከሆነ ሥራውን የማስተባበር ኃላፊነት የክልል አስተዳደር ሲሆን፣ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ክልሎችን የሚመለከት ከሆነ ግን ጉዳዩን የፌዴራል ተቋም እንደሚመራው ተመላክቷል፡፡

በመሠረተ ልማት ግንባታ ወቅት የሚነሱ ማናቸውም ዓይነት የፍርድ ቤት ክርክሮችና በፍርድ ቤት የመሠረተ ልማት ወይም የማኅበራዊ አገልግሎት አከናዋኝ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ታስረው ውሳኔውን እንዲፈጽሙ፣ ወይም የልማት ሥራው እንዲታገድ ትዕዛዝ እንደሚሰጥ፣ የባንክ ሒሳብ የማገድ ወይም በቀጥታ ከሒሳቡ ላይ ተቀናሽ ተደርጎ እንዲፈጸም ትዕዛዝ የሚሰጠው፣ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አማካይነት ብቻ መሆኑ ተደንግጓል፡፡

ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያት የመሠረተ ልማት ገንቢው ተቋም የመንግሥት ተቋም በመሆኑ ፍርዱን ማስፈጸም አዳጋች ስለማይሆን፣ የባንክ ሒሳብ ላይ የሚሰጡ የዕግድ ትዕዛዞች የመንግሥት ገንዘብ ያለ እንቅስቃሴ ታስሮ እንዲቀመጥ ስለሚያደርግ በተመረጠና ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ለመምራት ሲባል ስለመሆኑ በማብራሪያው ተገልጿል፡፡

ለክልሎች የሚሰጠው የካሳ ክፍያ የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች ከሚመድበው በጀት ጋር ለካሳ ክፍያ ታሳቢ ተደርጎ እንደሚደለደል የቀረበውን ደንጋጌ በተመለከተ፣ የምክር ቤት አባላት የፌዴራል መንግሥት በየትኛው አሠራርና ቀመር ገንዘቡን ለክልሎች ሊልክ ይችላል የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ተጀምረው ያልተጠናቀቁ በርካታ ፕሮጀክቶች ባሉበት አዲስ አሠራር መጀመር የፍትሐዊነት ችግር አያመጣም ወይ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል የግንባታ ተቋሙና ቅሬታ አለብኝ የሚል ካሳ ጠያቂ አካል መካከል የሚፈጠረውን አለመግባባት ከአገሪቱ ጫፍ ተነስቶ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ድረስ መጥቶ የማቅረብ ዕድል አለ ወይ? አንድ አርሶ አደር ከሰሜንና ከደቡብ ጫፍ፣ ከምዕራብና ከምሥራቅ ጫፍ አዲስ አበባ ድረስ ተመላልሶ የደረሰበትን በደል ማቅረብ ይችላል ወይ? ይህ ፍትሐዊ አካሄድ ነው ወይ? ሲሉ የጠየቁት አቶ ጋሻው ዳኛው የተባሉ የምክር ቤት አባል ናቸው፡፡

አቶ አበራ አዳሙ የተባሉ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው፣ ‹‹ለፌዴራል የመጀመርያ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ብቻ ተብሎ መሰጠቱ ዓላማው አልገባኝም፣ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ ይህ የዳኝነት ሥርዓቱን የሚጋፋ ነው፡፡ የፍሬ ነገርና የሥልጣን ክፍፍል ዓይቶ መወሰን የነበረበት ምክር ቤቱ አምኖ የሾመው በየትኛው ደረጃ ያለ ዳኛ ነው እንጂ፣ እንዴት እንዲህ ዓይነት አሳሪ ሕግ ሊወጣ ቻለ?›› ብለው ጠይቀዋል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ አቶ አበባው ደሳለው፣ ክልሎች ከሚያመነጩት ገንዘብ ለካሳ ክፍያ ይጠቀማሉ ተብሎ የቀረበው ድንጋጌ ደመወዝ መክፈል ባልቻሉበት በዚህ ጊዜ እንዴት አድርገው በቂ ካሳ ሊከፍሉ ይችላሉ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ሌላው የምክር ቤት አባል ዜጎች ሳይንገላቱ ጉዳያቸው በተዘዋዋሪ ችሎት የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሚታይበት አሠራር እንዲኖር አስገዳጅ ሁኔታ መፍጠርና ውክልና ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡

ከአባላቱ ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት የሕግና የፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እፀገነት መንግሥቱ፣ በጣምራም ሆነ በተናጠል መሠረተ ልማት የሚገነባውን የፌዴራል ተቋምን እከሳለሁ ብሎ የሚፈልግ አካል፣    ከክልል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጀምሮ እስከ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድረስ አልፎ በይግባኝ እስከ ላይኛው ፍርድ ቤት ድረስ ለመምጣት በሩ አልተዘጋም ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ የመሠረተ ልማቱን ለመክሰስ ፍላጎት ያለው ከሳሽና ሀብቱን አስይዛለሁ፣ አሳግዳለሁ ለሚል ይህን የመወሰን ሥልጣኑ ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ደመወዝ መክፈል ያልቻለ ክልል እንዴት ካሳ ሊከፍል ይችላል ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሸዊት ሸንካ በበኩላቸው፣ ለካሳ የሚውለው ገንዘብ የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች በፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀመር መሠረትና ፕሮጀክት ታሳቢ በማድረግ የሚሰጠው በጀት ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም የካሳ በጀት አመዳደቡ ላይ ምንም ዓይነት የፍትሐዊነት ጥያቄ እንደማይነሳ አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...