Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአማራ ክልል ከተፈጠረው ቀውስ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞችን ጨምሮ ሁሉም እስረኞች...

በአማራ ክልል ከተፈጠረው ቀውስ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞችን ጨምሮ ሁሉም እስረኞች እንዲለቀቁ ተጠየቀ

ቀን:

በባህር ዳር ከተማ ላለፉት ሁለት ቀናት የተካሄደው የሰላም ጉባዔ ባለአሥር ነጥቦች የአቋም መግለጫ በማውጣት ትናንት ሰኔ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲጠናቀቅ፡፡ በክልሉ ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያዘ የታሰሩ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ምሁራንና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንዲፈቱ ተጠየቀ፡፡

የአቋም መግለጫው ከዚህ በተጨማሪም የፕሪቶሪያውን ስምምነት በጣሰ ሁኔታ የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄዎች ባለባቸው አካባቢዎች ሕወሓት የፈጸመውን ወረራ ያወገዘ ሲሆን፣ በአስቸኳይ ከእነዚህ ቦታዎች ለቆ እንዲወጣም ተጠይቋል፡፡

አዲስ አበባን ጨምሮ በሰባት የአማራ ክልል ከተሞች ሲካሄድ የሰነበተው የሰላም ጉባዔ በባህር ዳር ከተማ ላለፉት ሁለት ቀናት ሰኔ 17 እና 18 ቀን 2016 ዓ.ም. የመዝጊያ ጉባዔውን በባህር ዳር አድርጓል፡፡ በዚሁ ጉባዔ ማሳረጊያ ላይም ይፋ የሆነው ባለአሥር አንቀጹ የአቋም መግለጫ የክልሉን የሰላም ቀውስ መፍታት ያስችላሉ ያላቸውን ነጥቦች አስቀምጧል፡፡

ጉባዔው በሚካሄድበት ወቅት የክልሉ ፕሬዘዳንት አቶ አረጋ ከበደ “በችግሩ ላይ መግባባት፣ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚያስችሉ ዘዴዎችን መዘየድ፣ ገቢራዊ ለማድረግ የሚያስችል አደረጃጀት መፍጠር” ይኖርብናል ብለዋል፡፡

በኮንፍረንሱ ማብቂያ በወጣው የአቋም መግለጫም ከሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተወክለዋል የተባሉት የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች፣ በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና የክልሉን ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ለመቀየር በቁርጠኝነት እንደሚሰለፉ ቃል በመግባት የአቋም መግለጫ በማውጣት ኮንፍረንሱ መጠናቀቁ ተነግሯል፡፡

የክልሉን ሕዝብ ጥያቄዎችና የጥያቄዎች አመላለስ ሒደት በማስቀደም የሚጀምረው የአቋም መግለጫው፣ ለሚዲያዎች፣ ለፖለቲከኞችና ለምሁራን የሰላም አተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀርባል፡፡ በማስከተልም ታጥቀው በጫካ ለሚገኙ ኃይሎች ላላቸው ወገኖች ጥሪ የሚያቀርበው መግለጫው፣ በሰላማዊ መንገድና በድርድር ጥያቄዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ሲል ጥሪ ያብራራል፡፡

የክልሉ መንግሥት አካላትም ሆነ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፌደራል ፀጥታ አካላት ታጥቀው በጫካ የቆዩ ወገኖች ወደ ኅብረተሰቡ ለመቀላቀል የሚያደርጉትን ጥረት በሆደ ሰፊነትና በይቅርታ እንዲቀበሉትም ጥሪ ያቀርባል፡፡

ከጫካ ከተመለሱ ኃይሎች ጋር በድርድርና ውይይት ለችግሮች ዕልባት ከተሰጠ በኋላ፣ የአገሪቱን ሁለንተናዊ ችግር ይፈታል ተብሎ በታመነበት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ውይይት በንቃት ስለመሳተፍም መግለጫው ያትታል፡፡ በክልሉ ከተፈጠረው ችግር ጋር በተገናኘ በቁጥጥር ሥር የሚገኙ ሰዎች እንዲፈቱና የዘላቂ ሰላሙ ግንባታ አካል እንዲሆኑ ጥሪ ያቀረበው መግለጫው፣ ሕወሓት የያዛቸውን መሬቶች ለቆ እንዲወጣና የፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዲደረግ በመጠየቅ ሐሳቡን አጠቃሏል፡፡

ከሰሞኑ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ለሚዲያዎች ዝግ በሆነ ሁኔታ ተከታታይ የሰላም ጉባዔዎች ሲካሄዱ ሰንብተዋል፡፡ በዚህ ጉባዔም የሰላም ኮሚቴ የተባለ አንድ ግብረ ኃይል ስለመዋቀሩ የተለያዩ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ይህ ኮሚቴም ከፋኖ ኃይሎች ጋር የሚደረግ የሰላም ንግግርን የማመቻቸት ሥራ እንደሚሠራ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ሪፖርተር ከተለያዩ ምንጮች ባደረገው ማጣራት በአዲስ አበባውና በባህር ዳሩ ጉባዔ ላይ ስብሰባውን የመሩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የጦር አመራሮች፣ ከፋኖ ኃይሎች ጋር በተደራጀ መንገድ ጥያቄ እስካቀረቡ ድረስ ለመነጋገር መንግሥት ዝግጁ መሆኑን መናገራቸውን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ይሁን እንጂ ከፋኖ ጋር የሚካሄዱ ንግግሮች ወይም ድርድሮች በክልል ማዕቀፍ ብቻ የተወሰነ ይዘት እንደሚኖራቸው ነው ምንጮች የጠቆሙት፡፡

በባህር ዳሩ መድረክ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ በክልሉ የቀጠለው ግጭት የክልሉን ሕዝብ ለብዙ ችግር እንደዳረገ መናገራቸው ተዘግቧል፡፡ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ተቀንጭቦ በተደመጠው ንግግራቸው፣ “ከአማራ ክልል አዲስ አበባ በአውቶብስ መሄድ ቅንጦት ሆኗል፣ ተማሪዎች መማር አልቻሉም፣ መፈተን አልቻሉም፣ መንግሥት ልማት መሥራት አልቻለም እንዲሁም ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መሠራጨት አልቻለም” የሚል አስተያየት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም በሚል መሪ ቃል በተደረገው በዚህ ተከታታይ ጉባዔ፣ በተለይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደና የኢፌድሪ መከላከያ ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ ተደራጅቶ የሚመጣ የድርድር ሐሳብ ካለ በሩ ክፍት መሆኑን መናገራቸውን ከተለያዩ ምንጮች ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ስብሰባውን የመሩት ሁለቱ ባለሥልጣናት በመንግሥት በኩል ድርድርን በይፋ የመቀበል፣ የተደራጀ ተወካይና የተደራጀ ሐሳብ ይዞ ከቀረበ ለመደራደር ዝግጁ የመሆን አቋም እንዳለ ስለመናገራቸው ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...