Monday, July 22, 2024

የአማራ ክልል ችግር እንዲያበቃ ለሰከነ ንግግር ዕድል ይሰጥ!

ቀደም ሲል በተለያዩ ከተሞች፣ ባለፈው ሳምንት በዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም፣ በዚህ ሳምንት ደግሞ በባህር ዳር ከተማ ከአማራ ክልል ወቅታዊ አሳሳቢ ችግር ጋር የተያያዙ ስብሰባዎች ተደርገዋል፡፡ አማራ ክልል ውስጥ የሚካሄደው ውጊያ መንስዔና መፍትሔ ላይ የተለያዩ ድምፆች ተሰምተዋል፡፡ መንግሥትና የታጠቁ ኃይሎች የሚወዛገቡባቸው ደም አፋሳሽ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ ግን፣ በሁሉም ወገኖች በኩል ሰከን ያለ የንግግር ዓውድና መደላድል ማመቻቸት አስፈላጊ ነው፡፡ በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ውጊያ ከዓውደ ግንባር ተፋላሚዎች በተጨማሪ፣ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡ ዕልቂቱን፣ መፈናቀሉን፣ የንብረት መውደሙንና ሌላውን ሥቃይ ለማስቆም በተቻለ መጠን በቅንነትና በአገር ወዳድነት ስሜት የሚያነጋግር መድረክ ያስፈልጋል፡፡ ‹‹እልህ ምላጭ ያስውጣል›› በሚባለው ደምፍላትና ግንፍልተኝነት የተገባበት ውጊያና ውድመት ሊቆም የሚችለው፣ ሁሉም ያገባናል ባይ ባለድርሻ አካላት በስክነት ለመነጋገር ፈቃደኝነት ሲያሳዩ ነው፡፡

ከአንድ ዓመት በላይ ሰላም ያጣው የአማራ ክልል ሕዝብ ሥቃይ እንዲያበቃ ሥርዓት ያለው ንግግር ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት ያሉበትን ችግሮች በሚገባ አጢኖ ለመፍትሔ የሚረዱ ሐሳቦችን ይዞ ሲቀርብ፣ ከመንግሥት ጋር የሚፋለሙ ኃይሎችም በዚያው ልክ ሐሳባቸውን ቢያቀርቡ መልካም ነው፡፡ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ያለው ሕዝብ በቀጥታም ሆነ በሚወክሉት አማካይነት ፍላጎቱ መደመጥ ይኖርበታል፡፡ መንግሥት በችግሩ ላይ ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን በተደጋጋሚ መግለጹ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ረጅም ርቀት ተጉዞ ለሰላም መስፈን ያለውን ፅኑ ፍላጎት ሲያሳይ መተማመን ይፈጠራል፡፡ መሣሪያ ያነገቡ ኃይሎችም በዚያ ልክ ለሰላም መስፈን ያላቸውን ፍላጎት ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ መሀል ግን በሚደረጉ ውይይቶችም ይባሉ ምክክሮች የአማራ ክልል ሕዝብ ፍላጎት ጎልቶ መደመጥ አለበት፡፡ ከእሳቱ ራቅ ብለው ችግሩ ተባብሶ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ኃይሎች ከድርጊታቸው ቢታቀቡ የተሻለ ነው፡፡

ማንም አሸናፊ የማይሆንበት ጦርነት እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ ያገኘውን ነገር ሁሉ እንዲበላ መፍቀድ ተገቢ አይደለም፡፡ በጦርነት ወቅት ብዙኃኑ ሕዝብና አገር ለከፍተኛ ሥቃይ ሲዳረጉ፣ ከጦርነቱ አትራፊ የሚሆኑ ወገኖች እንዳሉ በተለያዩ ጊዜያት በስፋት ታይቷል፡፡ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች አማካይነት ገንዘብ የሚያሰባስቡና በበሬ ወለድ መረጃዎች መደናገር እየፈጠሩ የሚከብሩ ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች ጦርነት ሲቆም ገቢያቸው ስለሚቋረጥ ትንቅንቁ ተጧጡፎ እንዲቀጥል ማንኛውንም አስከፊ ድርጊት ከመፈጸም አይታቀቡም፡፡ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በተገታው በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትም ሆነ በአማራ ክልል ጦርነት ተመሳሳይ ድርጊቶች እየተፈጸሙ፣ አንድ ላይ የነበሩ ግለሰቦችና ቡድኖች በጥቅም ተጋጭተው እርስ በርስ ሲወነጃጀሉ በተደጋጋሚ ተስተውለዋል፡፡ በጦርነት ቀጣና ውስጥ ያሉ ንፁኃን ግን በስማቸው እየተነገደ ቁምስቅላቸውን እያዩ ነው፡፡ ለአገር እናስባለን የሚሉ ወገኖች ይህንን ድርጊት ተባብረው ያስቁሙ፡፡

የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ የውይይት መድረኩ እንዲመጡ መንግሥት ፍላጎት እንዳለው፣ በባህር ዳር የሰላም ኮንፈረንስ ማስጀመሪያ ላይ ሲነገር ተደምጧል፡፡ የማንኛውም ጦርነት መቋጫ ውይይትና ድርድር ስለሆነ በሁለቱም ወገኖች በኩል እኩል ትኩረት ቢሰጠው፣ ለሕዝብ ሰላምና ለአገር ህልውና ይበጃል፡፡ እንደተባለውም መገዳደልና መጠፋፋትን ማስቆም ካልተቻለ የትም መድረስ አይሞከርም፡፡ ስለዚህም ለአማራ ክልል ዘለቄታዊ ሰላም ሲባል ከክልሉ ባለድርሻዎች በተጨማሪ፣ በመላ አገሪቱ የሚገኙ የአገር ጉዳይ የሚያሳስባቸው ወገኖች ለመፍትሔ የሚረዳ ሐሳብ ካላቸው የሚደመጡበት ዕድል ቢገኝ ጠቃሚ ነው፡፡ ብዙዎች በፍርኃት ቆፈን ውስጥ ባሉበት በዚህ ጊዜ በእውነተኛ የአገርና የሕዝብ ፍቅር ስሜት ሰላም ለማስፈን፣ ችግሮች ሳይድበሰበሱና ከይሉኝታ አጥር ወስጥ በመውጣት መነጋገር ቢቻል መፍትሔው አያስቸግርም፡፡ ለዚህ ግን ቅንነትና ስክነት ያስፈልጋል፡፡

ስለሰላም ለመነጋገር ከአሉባልታ መፅዳት እንደሚያስፈልግ ሲነገር ተሰምቷል፡፡ አሉባልታ የበላይነቱን ይዞ ሰላም አደፍራሽነት እንዳይበዛ ግን ሀቁን ለመናገር የሚደፍሩ ወገኖች መበረታታት አለባቸው፡፡ በአድርባይነትና በአስመሳይነት ከሚቀርቡ የማይጠቅሙ ሐሳቦች ይልቅ፣ በድፍረት እውነቱን አቅርበው ለመፍትሔ የሚያግዙ ድምፆች ትኩረት ያግኙ፡፡ አሉባልታ፣ ሐሜት፣ ሐሰተኛ መረጃዎች፣ ሴረኝነት፣ ክፋት፣ ተንኮል፣ ጥቅም አሳዳጅነትና ቂመኝነት ከመጠን በላይ በበዙበት በዚህ ጊዜ ለአገርና ለወገን የሚያስቡ ድምፆች ካልተደመጡ ችግሩ ተባብሶ ይቀጥላል፡፡ ስህተቶች የሚታረሙት፣ ያጋጠሙ ችግሮች የሚቀረፉትና ብሩህ ተስፋ ማየት የሚቻለው ለትክክለኛ መፍትሔ አመልካች ሐሳቦች ዕድል ሲገኝ ነው፡፡ ‹‹ዕድል አንድን በር አንዴ እንጂ ደግሞ አያንኳኳም›› እንደሚባለው፣ ለዘለቄታዊ ሰላም የሚጠቅም ጠቃሚ ዕድል እንደ መልካም አጋጣሚ እንጂ እንደ ተራ ነገር አይታለፍ፡፡ ለሰላም የማይጠቅሙ ነገሮችም ትኩረት ይነፈጋቸው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም አካባቢዎች ግጭቶችም ይባሉ ጦርነቶች በፍጥነት መቆም አለባቸው፡፡ የዜጎች መሠረታዊ መብቶች በሙሉ ሊከበሩ የሚችሉት ጦርነት ሲቆም ነው፡፡ በጦርነት ውስጥ የዜጎች የመንቀሳቀስ መብትም ሆነ የምርትና የአገልግሎቶች ዝውውር አይታሰብም፡፡ እርሻው፣ ንግዱ፣ ኢንቨስትመንቱ፣ ትምህርቱም ሆነ ሌላው የሥራ እንቅስቃሴ የሚቀላጠፈው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ሰላም በሌለበት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማሳካት አይደለም ማሰብ አይቻልም፡፡ የትኛውም ዓይነት የልማት ዕቅድ አውዳሚ ጦርነት እየተካሄደ ሊሳካ አይችልም፡፡ በሁሉም አካባቢዎች የሚስተዋሉ አለመግባባቶችን በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት የሚያስችል ምኅዳር መፈጠር አለበት፡፡ ለቅራኔና ለግጭት ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ አላስፈላጊ ነገሮችን በማስወገድ፣ ለአገር ጉዳይ የጋራ ራዕይ የሚያስይዙ ገንቢ ውይይቶች ያስፈልጋሉ፡፡ የአማራ ክልል ችግር እንዲያበቃ ለሰከነ ንግግር ዕድል መስጠት ተገቢ ነው! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ትርፍ ቢያገኝም የውጭ ምንዛሪ ገቢው ቅናሽ ማሳየቱ ተጠቆመ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የውጭ ምንዛሪ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...